በአውሮፓ መድረክ ለዋንጫ ክብር የበቁ አፍሪካውያን እና የዋንጫ ባለተስፋዎች ጉዞ

ኤል ካቢ ፣አዴሞላ ሉክማን እና ሰባስቲያን ሃለር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንድ አፍሪካዊ ተጫዋች ከወዲሁ ስሙን በአውሮፓ ትልቅ ስም ያለውን ዋንጫ በማንሳት ታሪክ ጽፏል።

ናይጄሪያዊው አዴሞላ ሉክማን በአውሮፓ መድረክ የፍጻሜ ውድድር ላይ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ሃትሪክ የሠራ አፍሪካዊ ተጫዋች ሆኗል። ጎሎቹ አታላንታ በዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ ባየር ሊቨርኩስንን በማሸነፍ ዋንጫውን እንዲያነሳ ረድቶታል።

በአውሮፓ መድረክ በሚዘጋጁ የክለብ ውድድሮች የፍጻሜ ሃትርክ የሠራ አምስተኛው ተጫዋች ሆኗል። ጎሎቹ 61 ዓመታት ያለዋንጫ የተጓዘው አታላንታ ወደ ድል የመለሱ ናቸው።

ሁለት ቀሪ አውሮፓ የፍጻሜ ጨዋታዎች ይከናዋናሉ። አፍሪካውያን ተጫዋቾችም ዋንጫ የማንሳት ተስፋ አላቸው።

ቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ለቡድኖቻቸው ትልቅ ሚና በመጫወት ዋንጫ ሊያሳኩ የሚችሉ ተጫዋቾችን ቃኝቷል።

ኤል ካቢ የግሪኩን ክለብ ለዋንጫ ክብር ያበቃው ይሆን?

ኤል ካቢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኦሊምፒያኮስ 47 ጊዜ የግሪክን ሊግ ክብር በመቀዳጀት ክበረ ወሰኑን ይዟል። በአውሮፓ መድረክ ግን አንድም ጊዜ ድል አልቀናውም።

በሚቀጥለው ሳምንት በዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ከጣሊያኑ ፊዮረንቲና ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ አዲስ ታሪክ ሊጽፉ ይችላሉ። ወደ ፍጻሜው ባደረጉት ጉዞ ደግሞ ሞሮኮው አዩብ ኤል ካቢ ትልቅ ሚና ነበረው።

በዘንድሮው ውድድር 10 ጎሎችን በማስቆጠር በውድድሩ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ይመራል። ከጎሎቹ ግማሽ ያህሉን ያስቆጠረው በግማሽ ፍጻሜው አስተን ቪላን ሲያሽንፉ ነው።

ከሜዳቸው ውጪ 4 ለ 2 ባሸነፉበት የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ኤል ካቢ ሃትሪክ ሠርቷል። ግሪክ ላይ በተደረገው የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ኦሊምፒያኮስ በአጠቃላይ ውጤት 6 ለ 2 እንዲያሽንፍ ረድቶታል።

በውድድሩ ላይ ሞሮኳዊው ዩሱፍ ኤል አረቢ እና የጊኒው አማካይ ማዲ ካማራም ተሳትፎ አድርገዋል።

በመጪው ረቡዕ የሚከናወነው የፍጻሜ ጨዋታ በተቀናቃኛቸው ኤኢኬ አቴንስ ሜዳ ይከናወናል። ይህ ደግሞ ካሸነፉ ድሉን የበለጠ ጣፋጭ እንዲሆን ያደርገዋል።

ፊዮረንቲና ደግሞ የአንጎላውን አጥቂ ምባላ ንዞላን እና ጋናዊውን አማካይ አለፍሬድ ደንካንን ይዟል።

ንዞላ በውድድሩ ላይ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ደንካን ደግሞ በአምስት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል።

የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ለማነሳት ከጫፍ ደረሰው ሃለር

ሰባስቲያን ሃለር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሰባስቲያን ሃለር

ሰባስቲያን ሃለር ቡድኑን ወክሎ በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ መጫወት ከቻለ ይህንን ዕድል ማሳካት ከቻሉ ጥቂት አፍሪካውያን ተጫዋቾች አንዱ ይሆናል።

የ29 ዓመቱ አጥቂ ካንሰርን ድል በመንሳት በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ አድርጓል። በፍጻሜው ጨዋታ ለአይቮሪ ኮስት የማሸነፊያዋን ግብ አስቆጥሮ ባለ ድል ለመሆን በቅቷል።

አፍሪካ ዋንጫን እና አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን በተመሳሳይ ዓመት ማሳካት የቻለ ሦስተኛው ተጫዋች ለመሆንም ከጫፍ ደርሷል።

አእአአ በ2000 በተከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ካሜሩን አሸናፊ ስትሆን ሳሙኤል ኤቶ እና ዤረሚ የቡድኑ አባላት ነበሩ። ሁለቱም ተጫዋቾች ከሪያል ማድሪድ ጋር የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ዋንጫ ከፍ አድርገዋል። ዤረሚ በቡድኑ ቆይቶ ከማድሪድ ጋር በ2002 ዋንጫው በድጋሚ አንስቷል።

በቅርብ ሳምንታት ከጉዳት ጋር እየታገለ የሚገኘው ሃለር፤ በዌምብሌዩ የፍጻሜ ጨዋታ ከተቀያሪ ወንበር ላይ ሆኖ ጨዋታውን ሊጀምር ይችላል። ጉዳት የገጠመው አልጄሪያዊው ተከላካይ ራሚ ቤንሴባይኒ ከጨዋታው ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል።

በአሠልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ የሚመራው ሪያል ማድሪድ ዋንጫውን ለ15 ጊዜ ለማንሳት ይጫወታል።

ብራሂም ዲያዝ ለስፔን ብሔራዊ ቡድን ከመጫወት ይልቅ ልቡ ወደ ሞሮኮ በማዘንበሉ በቅርቡ አገሩን ወክሎ መሰለፍ ጀምሯል። ማድሪድ የላሊጋውን ዋንጫ ሲያነሳ ስምንት ጎሎችን እና ሰባት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል።

የ24 ዓመቱ ተጨዋች ቡድኑ ለፍጻሜ ለመድረስ ባደረገው ጉዞ አብዛኛውን ተቀያሪ ወንበር ላይ ሆኖ ነው ጨዋታዎችን የጀመረው። በውሰት በኤሲ ሚላን ያደረገውን የሦስት ዓመታት ቆይታ አጠናቆ ከተመለሰ በኋላ የመጀመሪያ የሻምፒዮንስ ሊግ ድሉን ለማሳካት ያልማል።

የአታላንታን ድል ያበሰረው ሉክማን

አዴሞላ ሉክማን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አዴሞላ ሉክማን

አታላንታ በግማሽ ፍጻሜ ሲያሸንፍ አዴሞላ ሉክማን ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል። አየርላንድ ደብሊን ላይ በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ግን ሃትሪክ እሠራለሁ ብሎ አልገመተም።

ጨዋታው በተጀመረ በ26 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ግቦችን አስቆጠረ። ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊት ሃትሪክ መሥራቱን ያረጋገጠበትን ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ አታላንታን ለመጀመሪያው የአውሮፓ ክብር አበቃ።

በዚህም የሪያል ማድሪዶቹን ፍራንክ ፑስካሽ እና አልፍሬዶ ዲ ስቲፋኖ፣ የኤሲ ሚላኑ ፒዬሪኖ ፕራቲ እና የቦሪስያ ሞንቼግላድባሁ የፕ ሄይንክስን ታሪክ ለመጋራት ቻለ። ሁሉም ግን በአውሮፓ የፍጻሜ መድረክ ሃትሪክ የሠሩት እአአ ከ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ባሉት ጊዜያት ነው።

“ሁሌም በችሎታዬ እተማመናለሁ” ብሏል ሉክማን።

“ባለፉት ሁለት ዓመታት አጨዋወቴን ከማሳደግ ባለፈ አቋሜ ወጥ መሆኑንም አስመስክሬያለሁ። በለውጤ ደስተኛ ብሆንም ይህ ግን ገና ጅማሬ ነው። ሌሎች ተመሳሳይ ምሽቶች እንደሚኖሩኝ ተስፋ አለኝ” ብሏል።

ዋንጫውን ማሳካት የቻለው ማሊያዊው አጥቂ አል ቢላል ቱሬ ተቀይሮ ገብቶ ቡድንኑን ለመርዳትም በቅቷል።

በተሸናፊው ባየር ሊቨርኩሰን በኩል በርካታ አፍሪካውያን ተጫዋቾች ነበሩ።

የሉክማን የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አጋር የሆኑት ቪክተር ቦኒፌስ እና ናታን ቴላ ተቀይረው ገብተው ተጫውተዋል።

የቡርኪናፋሶው ተከላካይ ኤድመንድ ታፕሶባ እና የሞሮኮው አጥቂ አሚን አድሊ ጨዋታውን ለመጀመር ችለው ነበር።

የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳው የአይቮሪ ኮስቱ ተከላካይ ኦዲሎን ኮሱኑ ተቀያሪ ወንበር ላይ ሆኖ ጨዋታውን ለማጠናቀቅ ተገዷል።

ሊቨርኩሰን በጀርመን ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ካይዘርስላወተርንን በማሸነፍ ዋንጫ የሚያነሳበት ዕድል አለው።