ሉካስ ፓኬታ ለዓመታት ከእግር ኳስ ሊታገድ ይችላል

የዌስት ሃሙ አማካይ ሉካስ ፓኬታ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የዌስት ሃሙ አማካይ ሉካስ ፓኬታ “ባልተገባ ተግባር የስፖርት ውርርድ ገበያ ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል” በሚል በእንግሊዝ የእግር ኳስ ማህበር ክስ ተመስርቶበታል።

እአአ በ2022 እና 2023 ድረስ ከሌስተር ሲቲ፣ አስተን ቪላ፣ ሊድስ ዩናይትድ እና በርነመዝ ጋር በነበሩ ጨዋታዎች ምክንያት ነው ክሱ የተመሰረተበት።

ብራዚላዊው ተጫዋች ካለፈው ዓመት ጀምሮ ምርመራ ሲደረግበት መቆየቱም ታውቋል።

“እሱ (ፓኬታ) በእነዚህ ጨዋታዎች ሂደት፣ ስነ ምግባር ወይም በማንኛውም ክስተት ላይ ሆን ብሎ ካርድ ለማየት በመፈለግ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች ከውርርድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተጽዕኖ ለማሳደር በቀጥታ ጥረት አድርጓል” የሚል ክስ በማህበሩ ቀርቦበታል።

እአአ በ2022 ከሊዮን በ36.5 ሚሊዮን ፓውንድ ዌስት ሃምን የተቀላቀለው ፓኬታ በቀረበበት ክስ ዙሪያ “በጣም እንደተገረመ እና እንደተበሳጨ” ተናግሯል።

"ለዘጠኝ ወራት ያህል በእያንዳንዱ ምርመራቸው እያንዳንዱን እርምጃ ተባብሬያለሁ፤ የምችለውን መረጃ በሙሉም አቅርቤያለሁ። የቀረቡብኝን ክሶች በሙሉ አልቀበልም። ንጽህናዬን ለማረጋገጥ እታገላለሁ" ሲል አክሏል።

ፓኬታ መረጃ እና ሰነዶችን ከማቅረብ ጋር በተገናኘ ተባባሪ ባለመሆንም ሁለት ክሶች በእግር ኳስ ማህበሩ ቀርበውበታል።

ክሱ የተመሠረተው ቀድሞው አሰልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ ተነስተው ዩለን ሎፕቴጉ መሾማቸው በተገለጸበት ዕለት ነው።

ዌስትሃም ባወጣው መግለጫ "ክለቡ በተጫዋቹ የክስ ሂደት በሙሉ ከጎኑ መቆሙን እና ድጋፉን እንደሚቀጥል" አስታውቋል።

ፓኬታ በሚቀጥለው ወር በሚጀመረው የኮፓ አሜሪካ ላይ እንዲሳተፍ በብራዚል ብሔራዊ ቡድን ተመርጧል። ተጫዋቹ በቀረቡበት ክሶች ዙሪያ እስከ ሰኔ 3 ምላሽ መስጠት ይኖርበታል ተብሏል።

ተጫዋቹ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ረዘም ያለ ቅጣት ሊጣልበት ይችላል ተብሏል።

እአአ በ 2022 የስትራፎርድ ታውኑ ተከላካይ ኪናን አይዛክ በኤፍኤ ካፕ ውድድር ወቅት ለውርርድ ሲል ሆን ብሎ ቢጫ ካርድ በማየቱ 10 ዓመታት ታግዶ ነበር።