በውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን ጎራ ለይተው የሚፋለሙት ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, @hawelti
በተለያዩ የዓለም ማዕዘናት የሚገኙ ኤርትራውያን ዛሬ፣ ግንቦት 16 ዓመታዊ የነጻነት ቀናቸውን ያከብራሉ።
ከአገራቸው ውጪ ሆነው 33ኛ የነጻነት ቀናቸውን በሚያከብሩበት ዕለትም የበርካታ አገራት ፖሊሶችም ከፍተኛ ሁከት እና ግጭት ይፈጠራሉ በሚል በተጠንቀቅ ላይ ናቸው።
በአገራቸው ያለውን የከፋ ጭቆና በአገር ውስጥ መቃወም ላልቻሉ ኤርትራውያን እነዚህ ክብረ በዓላት የሁከት አውድማ ከሆኑ ሰነባብተዋል።
በዚህም የተነሳ አንዳንድ አገራት የኤርትራውያን ክብረ በዓላት እንዳይከበሩ ከልክለዋል። ለኤርትራውያን ይህች ዕለት ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጧት ናት።
ከኢትዮጵያ ጋር ከሦስት አስርት ዓመታት ጦርነት በኋላ የተቀዳጇት የነጻነት ዕለት ናት። ነገር ግን የበርካታ ሰዎች ሕይወት ተገብሮባት ነጻነትን ማጣጣም ላልቻሉ ደግሞ መራራ ማስታወሻም ናት።
ከነጻነት በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በፈላጭ ቆራጭ አገዛዛቸው ይታወቃሉ። ላለፉት 33 ዓመታት አገሪቷን እየመሩ ያሉትም ምርጫ ሳያካሂዱ ነው።
ኤርትራ በዓለም ላይ ያለ ሕገ መንግሥት የምትተዳደር ብቸኛዋ አገር ናት። ከአገሪቱ ገዢ ህግደፍ ፓርቲ ውጪ የትኛውም ዓይነት ፖለቲካዊም እንቅስቃሴ እንዲሁም ማኅበር አይፈቀድም።
ኤርትራ ከ23 ዓመት በፊት ነጻ ፕሬስን አግዳለች፣ አዘጋጆቹ እና ጋዜጠኞችን በእስር እያማቀቀች ትገኛለች። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶቿም አስገዳጅ የሆነውን ወታደራዊ አገልግሎትን ለመሸሽ ሕይወታቸውን አደጋ በሚጥል መልኩ ባሕር አቋርጠው ተሰደዋል።
በርካቶቹም ባሕር በልቷቸዋል። ኤርትራ አቅም ያለው በሙሉ ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት አለበት የሚለው የብሔራዊ አገልግሎት ፖሊሲዋ በዓለማችን ውስጥ ካሉ በስፋት ወታደራዊ ከሆኑ አገራት አንዷ አድርጓታል።
ይህንን ሁሉ አምልጦ የወጣው የኤርትራ ስደተኛ ነው በተለያዩ አገራት ተቃውሞውን እያሰማ ያለው። በቅርብ ዓመታት ደግሞ እንቅስቃሴው የበለጠ ጽንፈኝነት ያለው መስመር እየያዘም መጥቷል።
እነዚህ ወጣቶች ለስደት ተዳርገው በተበታተኑ ተቃዋሚዎች በያዙት የትግል መስመር ተሰላችተዋል። እንዲሁም ግራ የተጋቡ የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የህግደፍ አመራሮችን በጽኑ ይቃወማሉ። ከአገራቸው እንዲወጡ ያስገደዳቸውን አገዛዝ ለመታገል ቆርጠው የተነሱት እነዚህ ወጣቶች ከሁለት ዓመት በፊት ነው ብርጌድ ንሓመዱ የሚል ታጣቂ ቡድን ያቋቋሙት።
የብርጌድንሓመዱ ዋነኛ የትግል ሜዳ በተለያዩ አገራት በሚገኙ የኤርትራ ኤምባሲዎች እና የመንግሥት ደጋፊዎች የሚዘጋጁ ብሔራዊ በዓላት እና ፌስቲቫሎች ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን ከኤርትራ ታሪክ አንጻር ሲቃኙ በጣም የተለያዩ ሆነው ይገኛሉ። ኤርትራ ለነጻነት ታደርገው በነበረ ትግል ቀያቸውን ለቀው የወጡ እና በውጭ አገራት ሆነው ገንዘብ በመላክ ትግሉን እየደገፉ አዲስ አገር በማዋለዳቸው የሚኮሩ አሉ።
ሌሎቹ ደግሞ ለስደት ተዳርገውም የህግደፍ እጅ ረዝሞ በተጠለሉባቸው አገራት እንግልት እና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው የሚናገሩ ናቸው።
የብርጌድ ንሓመዱ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ሊቀመንበር ሮቤል አስመላሽ የእሱ ትውልድ አባላት አሁን የመታገያ ጊዜ እንደሆነ እንደሚሰማቸው ለቢቢሲ ተናግሯል።
“ሕዝቡ ተቃውሞውን በሰላማዊ መንገድ የመግለጽ መብቱ ተነፍጎታል” በማለት በአስገዳጅ የወታደራዊ አገልግሎት ምክንያት ከአገሩ ከ11 ዓመታት በፊት የተሰደደው የ27 ዓመቱ የታክሲ አሽከርካሪ ይናገራል።
ዘመቻቸውም “ሰማያዊ አብዮት” (ብሉ ሪቮሉሽን) የሚል መጠሪያ አለው። መነሻውም ኤርትራ ከብሪታንያ አገዛዝ ነጻ ስትወጣ ከአውሮፓውያኑ 1952 በኋላ የነበራት ሰንደቅ ዓላማ ነው።
ኤርትራ በ1952 ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ተቀላቅላ ለአስር ዓመት ብትቆይም ፌዴሬሽኑ እንዲፈርስ ተደርጎ ኤርትራ በኢትዮጵያ ስር እንድትጠቀለል ሆናለች።
ብርጌድ ንሓመዱ በዓለም ዙሪያ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ማንኛውም የኤርትራ መንግሥት ድጋፍ ያለው ዝግጅት በእነዚህ አገራት መፈቀድ የለበትም ሲል አጥብቆ ይቃወማል።
ባለፈው ዓመት በካናዳ፣ በጀርመን፣ በእስራኤል፣ በኔዘርላንድስ፣ በስዊድን፣ በስዊትዘርላንድ፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካ በነበሩ ዝግጅቶች ላይ የከፉ ሁከቶች ተከስተው ነበር።
አንዳንዶቹ የቡድኑ ተሟጋቾች የመንግሥት ደጋፊ የሆኑትን ለማሸነፍ ድንጋይ፣ ዱላ እና ስለታማ ነገሮች ሲጠቀሙም ታይተዋል።
በእስራኤል ቴል አቪቭ የነበረው ፍጥጫ ወደ ጥቃት ተሸጋግሮ የሰማያዊ አብዮት ተሟጋች የሆነ የአራት ልጆች አባት ተገድሏል። የመንግሥት ደጋፊ የሆነ ግለሰብ ደግሞ በዚያኑ ቀን በደረሰበት የከፋ አደጋ ሆስፒታል ገብቶ ሕይወቱን ለማዳን እየተሞከረ ነው።
ከጥቂት ወራት በፊት፣ በታኅሣሥ ወር በዩኬ ካምበርዌል ቲያትር ውስጥ የኤርትራ መንግሥት ድጋፍ ያለው ዝግጅትን ለመበተን የሄዱ ወጣቶች በርካታ ፖሊሶች የቆሰሉበት ጥቃት ፈጽመዋል በሚል የለንደን ፖሊስ ባለፈው ሳምንት የተፈላጊዎቹን ፎቶ አውጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
“በቲያትሩ የነበሩ ሰዎችን እንዲሁም የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ በተሰማሩ መኮንኖች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ካየኋቸው የከፋ ነው” ሲሉ አንደኛው መርማሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ ወንጀሎች አስካሁን 44 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውለናል አሁንም ለመያዝ ጥረት እያደረግን ሲሆን፣ የሕዝቡን እርዳታ የምንፈልግባቸው በርካታ ተጠርጣሪዎች አሉ” ብለዋል።
የሰማያዊ አብዮተኞች እርምጃዎች የተወሰነ ለውጥ እያመጣ ይመስላል፤ ለዚህም አንደኛው የስዊትዘርላንድ ባለሥልጣናት የዚህን ዓመት የነጻነት በዓል እንዳይከበር ፈቃድ መከልከላቸው ማሳያ ነው።
በስዊትዘርላንድ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ክልከላውን አስመልክቶ በጠንካራ ተቃውሞ በሰጠው ምላሽ ባለሥልጣናቱን “አመጸኛ ወሮበሎችን” ለማስደሰት ነው ሲል ከሷል።
የኔዘርላንድስ ሪጅስዊክ ከተማም እንዲሁ በነጻነት ቀን የሚደረጉ መሰባሰቦችን ከልክላለች። ሮቤል በአንዳንድ ዝግጅቶች ላይ መጀመሪያ አካባቢ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ አምኖ፤ ነገር ግን የብርጌድ ንሓመዱ አባላትም ዒላማ መደረጋቸውን ያስረዳል።
“በመጀመሪያ አካባቢ ሁኔታዎችን የሚቆጣጠር እና የደኅንነት ኃላፊነትን የሚወስድ አልነበረም። በዚህም ምክንያት በርካታ አባሎቻችን የጥቃቶች ሰለባ ሆነዋል” ሲል ለቢቢሲ አስረድቷል።
አክሎም “በአሁኑ ወቅት በሁሉም አገራት የብርጌድ ንሓመዱ መሪዎች ስለ ተቃውሞ ሕጎች ግንዛቤ እየሰጡ ነው። ከሕግ አስከባሪ ኃይሎች ጋር በመተባበር ተቃውሟችንን እንቀጥላለን” በማለት ስለ ትግሉ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሮቤል የተጠናከረው የተቃዋሚው ጎራ ብቻ ሳይሆን በሌላው ወገን ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ጽኑ ቁርኝት ካላቸው ቤተሰቦች የተወለዱ የኤርትራውያን ዲያስፖራ ትውልድም እንዲሰባሰብ አድርጓል።
ገዢው የኤርትራ ፓርቲ ህግደፍ ለዲያስፖራ የወጣቶች ክንፍ ያቋቋመ ሲሆን፣ ይህንንም ከባለሥልጣናቱ አንዱ “ታጣቂ ቡድን” ሲሉ ጠርተውታል።
በአውሮፓውያኑ 2005 የተቋቋመው ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ የወጣቶች ግንባር (YPFDJ) “የኤርትራ ጠላቶች የሚያሰራጩትን ሐሰቶች ለማጋለጥ” መመሥረቱን የኤርትራ የመንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።
ከእነዚህ ተመልማዮች መካከል አንዳንዶቹ ወደ ኤርትራ በመጓዝ በከፋ አያያዙ በሚታወቀው የሳዋ ማሠልጠኛ ካምፕ ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠናዎችን ወስደዋል። ነገር ግን የእነዚህ የሚለየው ኤርትራ ውስጥ ካሉ ወጣቶች በተለየ መልኩ ከአገር መውጣት ይችላሉ።
ከጦርነት ትርክቶች መራቅ ያልቻሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአውሮፓውያኑ 2017 ይሄው የዲያስፖራ ቡድን የተካተተበት “አራት ተቃዋሚ ግንባሮች” በመባል የሚታወቀውን አዲስ የአስተዳደር ሥርዓት አስተዋውቀዋል።
- የመጀመሪያዎቹ ምሥራቃዊ፣ ማዕከላዊ እና ምዕራባዊ የተሰኙት ሦስት ግንባሮች በሦስቱ የጦር ሠራዊት ዕዝ የተደራጁ ናቸው
- አራተኛው 4ጂ (4G) እየተባለ የሚጠራው በኤርትራ ኤምባሲዎች እና በወጣቱ የዲያስፖራ የህግደፍ ቅርንጫፎች አደራጅነት እና አንቀሳቃሽነት ስር ያለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ነዋሪ የሆነው ኤርትራዊው ዳንኤል ተክላይ ራሱን እንደ ህግደፍ ደጋፊ ሳይሆን እንደ ብሔርተኛ ይገልጻል።
የ53 ዓመቱ የባንክ ባለሙያ በአገር አርበኝነት መንፈስ ገንዘብ ወደ አገር የሚልኩ ዲያስፖራዎች ለህግደፍ ጭፍን ታማኝ ናቸው የሚለው አስተያየት ስህተት ነው ይላል።
ዳንኤል ከዚህ ቀደም የኤርትራን መንግሥት ቢቃወምም የትግራይ ጦርነት ሲጀመር የአርበኝነት ስሜቱ ተቀስቀስሶ መደገፉን ይናገራል።
የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመወገን ከትግራይ ኃይሎች ጋር ተዋግቷል።
የኤርትራ ጦር በትግራይ ጦርነት ግድያዎች፣ መድፈር፣ ሰላማዊ ዜጎችን ማሰቃየትን ጨምሮ አስከፊ መጠነ ሰፊ ጥሰቶች በመፈጸም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የጦር ወንጀሎችን በመፈጸም የአሜሪካ መንግሥትን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ቡድን ከሰውታል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ ከወራት በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ግድያዎችን መፈጸማቸውን እንዲሁም የመድፈር ወንጀል ክሶች ቀርቦባቸዋል።
ሆኖም ዳንኤል “በጦርነቱ ወቅት በውጭ የሚኖሩ አብዛኞቹ ኤርትራውያን፣ የፖለቲካ አመለካከታቸው ምንም ይሁን ምን ከኤርትራ መንግሥት፣ ከጦሩ እና ከአገሪቱ ጥቅም ጎን ተሰልፈው ነበር” ይላል።
ይህም “የአንድነት ሁኔታ የነጻነት ቀን እና ሌሎች ብሔራዊ በዓላት ተወዳጅነት እንዲጨምር እና በዓላቱም የበለጠ የደመቁ እና የአገር ፍቅር ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል” ይላል።
ነገር ግን ከአስገዳጅ ውትድርና ያመለጡት አብዛኞቹ የሰማያዊ አብዮተኞች የኤርትራ በትግራይ ጦርነት መሳተፍን ተቃውመዋል።
ዳንኤል የብርጌድ ንሓመዱን ተቃውሞም “ለነበረው የብሔራዊ አንድነት መጠናከር፣ ጽንፈኛ የሆነው ቡድን ሁከትን በመምረጥ ድንጋይ በመወርወር፣ መኪኖችን በማቃጠል፣ ንብረቶችን በማውደም እንዲሁም የፖሊስ መኮንኖችን ማጥቃት መረጠ” ይላል።
ዳንኤል ዲያስፖራው YPFDJ የተሰኘው ቡድን ጥቃቶችን ፈጽሟል ብሎ የማያምን ሲሆን፣ እያንዳንዷን ጥፋት የሚያሸክመው ለብርጌድ ንሓመዱ ነው።
በኤርትራ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚሟገተው 'ዋን ኔሽን' የተሰኘ ድርጅት አንደኛው መሥራች የሆነው ዳንኤል፣ የኤርትራ በዓላት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበሩ ቆርጦ መነሳቱን ይናገራል። እናም “በጽንፈኞቹ” እርምጃ ምክንያት እነዚህን ትልልቅ ክብረ በዓላት መሰረዝ መፍትሄ አይደለም ይላል።
“መፍትሄው ለእነዚህ ድርጊቶች እጅ መስጠት አይደለም። ሕግ እና ሥርዓት መከበር አለበት። ወንጀሎችን በመፈጸም ሕግ የተላለፉ በድርጊታቸው ሊጠየቁ ይገባል” ሲልም ያስረዳል።












