በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኤርትራውያን የነጻነት በዓል እንዳያከብሩ መከልከላቸውን የኤርትራ መንግሥት ተቸ

የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኤርትራውያን በየዓመቱ ግንቦት 18 የሚከበረው የነጻነት በዓል መከልከላቸውን በመተቸት የኤርትራ መንግሥት ወቀሳ አቀረበ።

ለባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በኤርትራ እና በተለያዩ አገራት በሚኖሩ ኤርትራውያን የሚከበረው ብሔራዊ የነጻነት ቀን ሰላማዊ እና ቤተሰብን ያማከለ ነው ሲል በጄኔቫ ተቀማጭነቱን ያደረገው የኤርትራ ኤምባሲ ትናንት ግንቦት 1/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የስዊዘርላንድ መንግሥት የኤርትራን የነጻነት ቀንን አስመልክቶ እንዲሁም ዓመታዊውን ብሔራዊ በዓል አከባበር አስመልክቶ ሚያዝያ 9/ 2016 ዓ.ም የጻፈው ደብዳቤ “ተንኳሽ ይዘት በከፍተኛ ሁኔታ አስደንግጦኛል” ብሏል። የስዊዘርላንድ መንግሥት የጻፈውን ደብዳቤ ይዘት ምን እንደሆነ ኤምባሲው አልጠቀሰም።

ኤርትራን በፈላጭ ቆራጭነት እየገዙ ባሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ላይ ከዚህ ቀደም በዳያስፖራው ተቃውሞች ቢሰሙም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን መልኩን እየቀየረና የአገዛዙ ደጋፊዎች የሚያዘጋጁዋቸውን በዓላት በመቃወም በተነሱ ግጭቶች ደም መፋሰሶች እየታዩ ነው።

ባለፈው ወር በስዊዘርላንድ ጌርላንፊንገን ግዛት የኤርትራ መንግሥት ደጋፊ የሚሆኑ 350 ሰዎች በተሳሰቡበት ድግስ ላይ 180 የሚሆኑ ተቃዋሚዎች ድንጋይ፣ ፌሮ እና ዱላ ይዘው ዝግጅቱን ለማደናቀፍ መሞከራቸውን ተከትሎ ግጭት ተፈጥሯል። ፖሊስ ውሃ እና አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ግጭቱን ለመበተን የሞከረ ሲሆን አንድ ፖሊስ እና አንዲት ኤርትራዊት መቁሰላቸው ተነግሯል።

በቅርቡም የስዊዘርላንድ የተወካዮች ምክር ቤት የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙ ኤርትራውያንን በሶስተኛ አገር አድርጎ ወደ አፍሪካ የሚመለሱበትን ፕሮግራም አጽድቋል።

ለንደንን ጨምሮ በተለያዩ አገራት በሚነሱ የደጋፊ እና ተቃዋሚዎች ግጭት የተነሳ የዩናይትድ ኪንግደም ባለስልጣናት ኤርትራውያን የሚያከብሩት ፌስቲቫል መሰረዛቸውን ተከትሎ ኤርትራ ተቃውሟዋን አሰምታለች።

የነጻነት ቀኑ የበርካታ ሰዎች ህይወት የተገበረበት መሆኑን ያስታወሰው የኤርትራ ኤምባሲ መግለጫ ከዚህ ቀደም በነበረው አከባበር ሰላማዊ ቢሆንም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን ሁኔታዎች መቀየራቸውን ጠቁሟል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ካለፈው ዓመት ጀምሮ ኤርትራውያን ነን የሚሉና ለኤርትራውያን መብት የሚታገል የሁከት ቡድን ሰላማዊውን የኤርትራ የነጻነት በዓል ለማደናቀፍ እየሞከረ መሆኑ በጣም ያሳዝናል።እነዚህ ንብረትን የማውደም እና ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶች በህጉ መሰረት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል” ብሏል።

ሆኖም ይህንን መሰረት አድርጎ በዓሉን መሰረዙ ተቀባይነት እንደሌለውም አጽንኦት ሰጥቷል።

“እነዚህን ሁከት ፈጣሪ ወሮበሎችን ለማስደሰት ወይም ይህንን ህገወጥ ተግባራቸውን በመጠቀም በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ህግ አክባሪ ኤርትራውያን የነጻነት በዓላቸውን በሰላም እንዳያከብሩ መከልከል በምንም ዓይነት ሁኔታ ተገቢ ያልሆነ ነው” ብሏል።

ከኤርትራ የትጥቅ ትግል ጀምሮ በውጭ አገራት ጠንካራ የማህበረሰቦች አደረጃጀትን መፍጠር የቻለው የኤርትራ መንግሥት በሰኔ መጨረሻ የሚከበረውን የሰማዕታት እና የግንቦት የነጻነት በዓሎችን በኤምባሲው እና በደጋፊዎቹ አማካኝነት ሲያከብር ቆይቷል።

ነገር ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት አገዛዙን የሚቃወሙ እና የኤርትራ መንግሥት እነዚህ ክብረ በዓላትን ለፕሮፓጋንዳ እና ገንዘብ ለማሰባሰብ ይጠቀምበታል የሚሉ ‘ብርጌድ ን ሀመዱ’ የሚባል ቡድን ድንኳኖችን ማቃጠል ጨምሮ ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም እየተቃወሙ ይገኛሉ። በደጋፊዎች እና በተቃዋሚዎች በተነሱ ሁከቶች የተነሳ በተለያዩ አገራት የፓሊስ አባላት ጨምሮ በኤርትራውያን እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

ከቅርብ ግዜያት ወዲህ የኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅትን ምክንያት በማድረግ በኤርትራውያን መካከል በአውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞች ግጭት ሲፈጠር መመልከት የተለመደ ሆኗል።

በባለፈው ዓመት እስራኤልን ጨምሮ በጀርመን፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ እና በካናዳ ብዙዎችን ለጉዳት የዳረገ ግጭት ተከስቷል።

በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኤርትራ መንግሥት በዜጎቹ ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል ይላሉ።

በዚህም ምክንያት በኤርትራ ያለውን የፖለቲካ እና የእምነት ነጻነት ጭቆና እንዲሁም የጊዜ ገደብ የሌለውን አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት በመሸሽ በርካቶች ኤርትራውያን አገር ጥለው ይሰደዳሉ።