አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ቢሾፍቱ እንዲሆን ለምን ተመረጠ?

የፎቶው ባለመብት, PM Office
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ አቅራቢያ 'አቡሴራ' በተባለ አካባቢ የሚገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቅዳሜ ጥር 2/2018 ዓ.ም. መሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ኢትዮጵያ የያዘችው በርካታ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን የመገንባት ስትራቴጂ ወደፊት የአፍሪካ ግንባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት ማዕከል ለመኾን ያለመ መኾኑን ተናግረዋል።
12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚወጣበት የአውሮፕላን ማረፊያ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሲጠናቀቅ፣ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
አውሮፕላን ማረፊያው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ እንደሚችልም ዐቢይ ጨምረው ተናግረዋል።
በቢሾፍቱ አቅራቢያ የሚገነባው ይህ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ 3,500 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው።

የፎቶው ባለመብት, PM Office
ቢሾፍቱ የዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ለምን አሁን መገንባት አስፈለገ?
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ መዳረሻዎቹን እያሰፋ እና የአውሮፕላን ቁጥሮቹን እየጨመረ በሄደ ቁጥር በአዲስ አበባ የሚገኘው ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መንገደኞችንም ሆነ አውሮፕላኖችን ማስተናገድ ከሚችለበት ቁጥር ላይ እየደረሰ ነው።
አየር መንገዱ በዓመት 25 ሚሊዮን ተጓዦችን ማስተናገድ በሚችልበት የመጨረሻ አቅሙ ላይ መድረሱን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ከዚህ ቀደም ከቢቢሲ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።
በሁለት በሦስት ዓመታት ውስጥም በዓመት ሊያስተናግድ የሚችላቸው የመንገደኞች ቁጥር ጣሪያ ላይ ይደርሳል።
የአቪየሽን ጉዳዮች ጸሐፊ የሆኑት እና አውሮፕላን አብራሪ የሆኑት ዮናታን መንክር "ይህ ማለት ደግሞ በወቅቱ ተለዋጭ የመንገደኞች ማስተናገጃ እና የአውሮፕላን ማቆሚያ ካልተገነባ ዕድገቱ በዚያው ላይ ሊወሰን ይችላል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክለውም "መወሰን ብቻ ሳይሆን መንገደኞች በተጨናነቀ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲገለገሉ ማድረግ የአገልግሎት የገበያ ድርሻ እና ተወዳዳሪነት ላይ ተጽዕኖ ያሳርፋል" ይላሉ።
እንደ ዮናታን ከሆነ የቢሾፍቱ ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ "ምናልባትም ትንሽ ዘግይቶ ካልሆነ በስተቀር አስፈላጊነቱ የዕድገት እና የኅልውና ጉዳይ ነው።"
የአፍሪ አቪየሽን ኮንሰልተንሲ ባልደረባ የሆኑት አቶ ዳንኤል ኃይሉም የቦሌ ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ማረፊያ በየዓመቱ የሚያስተናግዳቸው መንገደኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ይስማማሉ።
አቶ ዳንኤል አውሮፕላን ማረፊያው በአሁኑ ወቅት በዓመት 30 ሚሊዮን መንገደኞች ያህል እንደሚያስተናግድ ገልጸው፣ ይህም ማለት የቦሌ ዓለም አፍ አየር ማረፊያ የማስተናገድ አቅም "የመጨረሻው ጥግ ነው" ይላሉ።
የአንድን አየር መንገድ እድገት ሊገቱ ከሚችሉ ነገሮች መካከል አንዱ አውሮፕላን ማረፊያ ነው የሚሉት አቶ ዳንኤል፣ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ይዞ በቀጣይ አምስት እና አስር ዓመታት ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ መቀጠል እንደማይቻል ያብራራሉ።
አውሮፕላን ማረፊያ ሲሰራ አጭር ጊዜን ብቻ በማየት አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ ዳንኤል፣ ቀጣይ አምስት እና አስር ዓመታትን ሲመለከቱ የመንገደኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር መተንበይ ከባድ እንደማይሆን ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines
ቢሾፍቱ ለምን?
የአቪየሽን ጉዳዮች ጸሐፊ የሆኑት ዮናታን አየር መንገዱን ከዚህ ቀደም የመሩ ሰዎች ነገሩኝ በማለት "መጀመሪያም ለአውሮፕላን ማረፊያ ይሆናሉ ተብለው ሲጠኑ ከነበሩ ቦታዎች መካከል አቡሴራ አንዱ ነበረ" ይላሉ።
አክለውም "ቀዳሚ ምርጫ የነበረ ቦታ ነው" ብለዋል።
አቶ ዳንኤል ደግሞ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ከዚህ በላይ ማስፋፋት እንደማይቻል በመግለጽ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አሁን ካለበት ቦታ ጋር የተያያዘ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ስለዚህ አማራጭ ሥፍራዎች ሲፈለጉ አሁን ካለበት "የተሻለ ቦታ" ማግኘቱ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ያነሳሉ።
አቶ ዮናታን ለአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ አንድ ቦታ ሲመረጥ በቅድሚያ ከሚታዩ ነገሮች መካከል አንዱ "ለአውሮፕላን ለመነሳት እና ለማረፍ ቀላል እንዲሆንለት አካባቢው ከመሬት ወለል በታች ዝቅተኛ ሥፍራ ላይ የሚገኝ ቢሆን ይመረጣል" ይላሉ።
ይህም ረዥም ርቀት ለመሄድ እና ከፍ ያለ ጭነት ለመጫን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ዮናታን ያብራራሉ።
"ከፍ ያለ ጭነት ማለት ከፍ ያለ ገቢ ማለት ነው" የሚሉት የአቪየሽን ጉዳዮች ጸሐፊው፣ አቡሴራ አካባቢ የሚሰራው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለዚህ ተስማሚ መሆኑን ያስረዳሉ።
አቶ ዳንኤል ከዚህ ሃሳብ ጋር በመስማማት አንድ አውሮፕላን ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መንገደኞችን እና እቃ ጭኖ ለመነሳት ከፍተኛ ነዳጅ መጠቀም እንደሚያስፈልገው ይናገራሉ።
አቶ ዳንኤል አክለውም በተለይ ወደ ሰሜን አሜሪካ የሚያደርጋቸው በረራዎች ላይ "ሮም አርፎ ነዳጅ ለመሙላት ይገደዳል" ይላሉ።
ሲመለስ ግን በተቃራኒው ከዋሺንግተን ወይንም ከካናዳ ቀጥታ በርሮ ቦሌ ማረፍ እንደሚችል በማነጻጸር ይናገራሉ። ዮናታን ቢሾፍቱ የሚገኘው ዝቅተኛ ቦታ ላይ በመሆኑ አየር መንገዱ ለመነሳት እና ለማረፍ የሚያወጣውን ነዳጅ ይቀንስለታል በማለት ሳይንሳዊ እና ቴክኒካዊ ያሉትን ምክንያት ያብራራሉ።
ከአዲስ አበባ ደቡብ ምዕራብ በ40 ኪሎሜትር ርቀት በ1910 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ቢሾፍቱ ከአዲስ አበባ አንጻር ስትታይ "400 ሜትር ከባሕር ወለል በላይ (above see level) ዝቅ ያለ ቦታ ላይ የምትገኝ በመሆኑ፣ የአየር ግፊቱ ተነባብሮ ከፍተኛ ስለሚሆን በቀላሉ ከመሬት ያስነሳዋል።"
አዲስ አበባ የምትገኘው ከፍታ ላይ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ዳንኤል፣ ይህም አየር መንገዱን ለበርካታ ወጪ መዳረጉን ያነሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali
"ይህ ደግሞ ወሳኝ ነው" የሚሉት አቶ ዳንኤል ወደ ሰሜን አሜሪካ በሚደረጉ ጉዞዎች ሮም ላይ መቆም ለመንገደኞች መጉላላት ለአየር መንገዱም ተጨማሪ ወጪ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ይህንን ሃሳብ የሚያጠናክሩት አቶ ዮናታን አየር መንገዱ የሰሜን አሜሪካ በረራዎቹን በሮም ወይም በሎሜ እና በአቢጃን በኩል በማድረግ ለተጨማሪ ወጪ ተዳርጎ መቆየቱን ያነሳሉ።
ከዚያ አንጻር ይላሉ አቶ ዳንኤል አየር መንገዱ ከቢሾፍቱ በሚነሳበት ወቅት ከፍተኛ ጭነት መጫን እንዲሁም ሮም የሚኖረውን መቆም ማስቀረት ስለሚችል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ያስረዳሉ።
ዮናታን በበኩላቸው አየር መንገዱ ሮም ነዳጅ ለመሙላት ሲቆም ምንም ዓይነት መንገደኛ እንደማይጭን እና እንደማያወርድ ጠቅሰው፣ ነዳጅ ቀድቶ ብቻ ሲነሳ የአውሮፕላን ማረፊያው የሚያርፍበት እና ተያያዥ ታክሶችን ጨምሮ ክፍያ ስላለው ከፍተኛ ወጪ መሆኑን ያብራራሉ።
ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር በምትገኘው ቢሾፍቱ የሚገነባው አዲሱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፤ የአውሮፕላን መነሻ እና ማረፊያ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተጓዳኝ የሆኑ በርካታ ነገሮችን እንደሚይዝ ተነግሯል።
እነዚህ ጉዳዮች የአየር መንገዱን ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምሩት ሁለቱም ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ከዓለም አቀፍ የአውሮፕላን መንገደኞች መካከል የአፍሪካ መንገደኞች ቁጥር ወደ 3 በመቶ እንደሚሆን የሚናገሩት አቶ ዳንኤል፣ አየር መንገዱ ያልተነካውን የአፍሪካ መንገደኞች (97 በመቶ) ታሳቢ አድርጎ እንደሚሰራም ጨምረው ገልፀዋል።
አቡሴራ ምንም ዓይነት ለመስፋፋት እክል የሚሆን ነገር አለመኖሩ፣ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ ሌላ ለመመረጡ ምክንያት እንደሚሆን የአቪየሽን ጉዳዮች ጸሐፊው ዮናታን ያስረዳሉ።
ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚገነባበት አካባቢ ሰፊ እና ሜዳማ ቦታ ነው የሚሉት የአየር መንገዱ የመሠረተ ልማት ዕቅድና ልማት ዳይሬክተር አብረሃም ተስፋዬ፣ ይህ ደግሞ አሁን ለሚሰሩም ሆነ ወደፊት ለሚመጡ መስፋፋቶች አመቺ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ኤርፖርት ጋር በተመጋጋቢነት እንደሚሰራ እና በፈጣን መንገድ እና በፈጣን ባቡር እንደሚተሳሰር ቅዳሜ ዕለት በተከናወነው የግንባታ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ ተነግሯል።
ይህም ሁለቱንም የአውሮፕላን ማረፊያዎች በተመሳሳይ ወቅት መጠቀም ስለሚያስችል የአየር መንገዱን አቅም ከፍ ያደርጋል።
አቶ ዮናታን ኢትዮጵያ ውስጥ ቆይታቸውን የሚያደርጉ መንገደኞች በፈጣን ባቡር ወይም በፈጣን መንገድ ከአዲስ አበባ ጋር ለማገናኘት በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ መሆኗ ሌላው ምክንያት ነው ይላሉ።
የአቪየሽን ጉዳይ ጸሐፊው ቦታው በራቀ ቁጥር ሌላ አዲስ ከተማ መመስረት እንደሚጠይቅ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ መንገደኞች ሌላ በረራ እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ መሆኑን በማንሳት አቡሴራ አዋጪ ስፍራ መሆኗን ይናገራሉ።
የቦሌ ዓለም አቀፍ አውረፕላን ማረፊያ እጣ ፈንታ
አቶ ዳንኤልም ሆኑ አቶ ዮናታን የአገር ውስጥ መንገደኞች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ይናገራሉ።
በአሁኑ ሰዓት የአገር ውስጥ መንገደኛ ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን በላይ መሆኑን የገለፁት አቶ ዳንኤል፤ በረራ የሚደረግባቸው ክልሎች እያደጉ እና የኢኮኖሚው አቅም እያደገ ሲመጣ የመንገደኞች ቁጥር እየጨመረ አንደሚሄድ ያላቸውን ግምት ይናገራሉ።
ስለዚህ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ክልል የሚደረጉ እና በአካባቢው ወደሚገኙ አገራት የሚኖሩ በረራዎች ከዚህ አየር መንገድ ይሆናሉ ብለው እንደሚገምቱ ተናግረዋል።
የኤርፖርቶች መሠረተ ልማት በሰፊው እየተገነባ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ዮናታን በበኩላቸው ከሕዝብ ቁጥር፣ ከኢኮኖሚ እድገት አንጻር ሰዎች የአውሮፕላን አጠቃቀማቸው እየጨመረ ስለሚመጣ ብዙ የአገር ውስጥ በረራዎች ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚሆኑ ይናገራሉ።
ከዚህም ባሻገር ወደ ቀጠናው የሚደረጉ የመካከለኛ እና የአጭር ርቀት በረራዎች ከዚሁ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚነሱ ተናግረዋል።















