ቻይና በታሪኳ ክብረ ወሰን የሆነ ከ1 ትሪሊየን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና በአውሮፓውያኑ 2025 በታሪኳ ክብረ ወሰን የሆነ ከፍተኛ የውጭ ንግድ ገቢ ማግኘቷን አስታወቀች። በዚህም ከአንድ ትሪሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ችላለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጣሉት ታሪፍ እና የንግድ ፖሊሲ መለወጣቸው የዓለም ንግድ ላይ ጫና ቢያሳድርም ቻይና ግን ትርፋማ መሆኗን ይፋ አድርጋለች።
ቻይና ወደ አገር ውስጥ ከምታስገባው ምርት ወደ ውጭ አገር የምትልከው የሚበልጥ ሲሆን፤ መጠኑም በዓለም ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል።
ቻይና በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዓመት ከኤክስፖርት ያገኘችው ገቢ ከ1 ትሪሊየን ዶላር በላይ ነው። በ2024 የተገኘው ገቢ 993 ቢሊየን ዶላር ነበር።
ቻይና በየወሩ ኤክስፖርት ያደረገችው መጠን (100 ቢሊየን ዶላር) አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው በሰባት እጥፍ ይበልጣል።
ቻይና ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው ግብይት መጠኑ ቢቀንስም ወደ ሌሎች አገራት ኤክስፖርት በማድረግ ማካካስ ችላለች።
ቻይና በዋነኛት ኤክስፖርት የምታደርገው ወደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ ነው።
የቻይና ጉምሩክ ምክትል ዳይሬክተር ዋንግ ጁን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የዓለም ግብይት ፈተና ውስጥ በወደቀበት ወቅት የተገኘው ትርፍ "ከፍተኛ እመርታ ነው" ብለዋል።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በሮቦቲክስ ዘርፍ ቻይና የኤክስፖርት መጠኗን አሳድጋለች።
የደቡብ እስያ አገራትን ጨምሮ በአፍሪካ እና በአውሮፓም ለቻይና ምርቶች ያለው ፍላጎት ጨምሯል። የቻይና የአገር ውስጥ ንግድም ተነቃቅቷል።
ቻይና ባለባት የዕዳ ብዛት እንዲሁም በቤት አቅርቦት ቀውስ ምክንያት ባለሃብቶች ገንዘብ ከማፍሰስ ሲቆጠቡ፤ ሸማቾችም ወጪ ቀንሰዋል።
በዚህም ምክንያት ቻይና ከውጭ አገራት የምታስገባው ምርት ቀንሶ 0.5 በመቶ መሆኑ ተገልጿል።
የቻይና መገበያያ የሆነው ዩዋን መዳከም፣ የሸቀጥ መትረፍረፍ እና የምዕራባውያን አገራት የዋጋ ንረት ለቻይና ኤክስፖርት ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።
በሂንሪሽ ፋውንዴሽን የንግድ ፖሊሲ ተንታኝ ዴቦራ ኤልምስ እንደሚሉት፤ ቻይና ከሽያጭ እና በውጭ አገራት ካሉ ንግዶች ተጠቃሚ ሆናለች።
ከቻይና ሸቀጦች ጋር ፉክክር የሚያደርጉ የውጭ ምርቶች ለቻይና ፈታኝ ሊሆኑ እንደሚችሉም ያክላሉ።
ቻይና በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመትም በስኬታማነት ልትቀጥል ትችላለች። የቻይና ምርት እና አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ገበያው ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተንታኟ ያስረዳሉ።
የቻይና ትርፍ አገሪቱ ከአሜሪካ ባሻገር ከሌሎች አገራት ጋርም የንግድ ትስስር እንዳላት ይጠቁማል።
በርካታ አገራት ገበያቸው በርካሽ በተሠሩ የቻይና ምርቶች በመጥለቅለቃቸው ያማርራሉ።
ሌላኛው ስጋት በትራምፕ አስተዳደር የሚጣል ታሪፍ ነው።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከ90 በላይ አገራት ላይ ታሪፍ መጣላቸው ይታወሳል። ጠንካራ ታሪፍ ከተጣለባቸው አገራት አንዷ ቻይና ናት።
የዓለም ሁለት ትልልቅ ምጣኔ ሃብት ያላቸው ቻይና እና አሜሪካ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው የዓለም ንግድ ላይ ጫና አሳድሯል።
ቻይና በአሜሪካ ገበያ ላይ ያላት መተማመን የሚፈተንበት እንደሆነ ተንታኞች በወቅቱ ተናግረዋል። ቻይና ግን ከአሜሪካ ውጭ ከሌሎች አገራት ጋር እንደምትገበያይ አስታውቃለች።
ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር በደቡብ ኮሪያ ከተገናኙ በኋላ የንግድ ጦርነቱ ጋብ ብሏል።















