ቻይና የሕዝብ ቁጥሯን ለማሳደግ በኮንዶም ላይ የጣለችው አነጋጋሪው ግብር

ቻይናዊ ጨቅላ ባሕላዊ ልብስ ለብሶ አልጋ ላይ ተኝቶ አንጋጦ ካሜራ ሲመለከት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአዲሱ የአውሮፓውያኑ ዓመት 2026 መባቻ ጀምሮ ቻይናዊያን የእርግዝና መቆጣጠሪያ እንክብሎች ላይ 13 በመቶ ተጨማሪ ግብር ይከፍላሉ። በተቃራኒው የሕፃናት መንከባከቢያ ማዕከሎች ከግብር ነፃ ይሆናሉ።

በዓለማችን ሁለተኛ ግዙፍ ምጣኔ ሀብት ያላት ሀገር ቻይና የውልደት መጠኗን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሏታን እርምጃዎች ሁሉ እየወሰደች ነው።

ቻይና በአውሮፓውያኑ 1994 ነበር በእንግሊዝኛው 'ዋን ቻይልድ ፖሊሲ' የተባለ እና ጥንዶች አንድ ልጅ ብቻ እንዲኖራቸው የሚያስገድደውን ሕግ ተግባራዊ ያደረገችው።

ሕጉ ቤተሰቦች የሚወልዱትን ልጆች ቁጥር መጠን በአንድ በመገደብ እያደገ የነበረውን የሕዝብ ቁጥሯን ለመቆጣጠር እርምጃ የወሰደችው።

በወቅቱ በርካታ ከውልደት ጋር የተያያዙ ግብሮች ተጥለው ነበር። አሁን ይህን ቀልብሳ የጋብቻ እና የአረጋውያን እንክብካቤን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶች ከቫት ነፃ እንዲሆኑ አድርጋለች።

አልፎም ቻይና የወሊድ ፈቃድ እንዲራዘም እንዲሁም ልጅ ለሚወልዱ ቤተሰቦች የጥሬ ገንዘብ ሥጦታ እንዲደረግላቸው ልታደርግ ነው።

በመጪዎቹ ዓመታት የሕዝብ ብዛት ቁጥር ማሽቆልቆል በቻይና ምጣኔ ሀብት ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ለመከላከል ቻይና ከወዲሁ እርምጃ መውድ ጀምራለች።

ባለፉት አስርት ዓመታት የወሊድ ቁጥር በማሽቆልቆሉ ወጣቶች ወደ ጎልማሳነት እየተሻገረ ክፍተት እየተፈጠረ ይገኛል።

ስለዚህም ቤይጂንግ ወጣቶቿ እንዲያገቡ እና ልጅ እንዲወልዱ እያበረታታች ነው።

ይፋዊ ቁጥሮች እንደሚያሳዩ የቻይና ሕዝብ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ቀንሷል። በ2024 (እአአ) አገሪቱ ውስጥ 9.54 ሚሊዮን ሕፃናት ብቻ ነው የተወለዱት። ይህም ከ10 ዓመት በፊት ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በግማሽ ያነሰ ነው።

ኮንዶም እና ሌሎች የእርግዝና መቆጣጠሪያዎች ላይ የተጣለው ግብር ያልተፈለገ እርግዝና እና ኤችአይቪ እንዳይሠራጭ የሚል ስጋት ፈጥሯል። አንዳንዶች እንደሚሉት ኮንዶም ላይ የተጣለ ግብር ልጅ እንዲወልዱ አያበረታታቸውም።

አንድ ባለሱቅ ግብሩ መተግበር ከመጀመሩ በፊት ሰዎች በርካታ ኮንዶም ገዝተው እንዲያስቀምጡ ይመክራል። አንድ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ "ለሕይወት ዘመኔ የሚበቃኝን እሸምታለሁ" ሲሉ ቀልዷል።

ሰዎች በኮንዶም ዋጋ እና ልጅን በማሳደግ መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቀው ያውቃሉ ይላል ሌላ አስተያየት ሰጭ።

ቻይናዊያን ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቻይናውያን በኑሮ ውድነት የተነሳ ከጋብቻ እና ልጅ ከመውለድ እየሸሹ ነው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቤይጂንግ የሚገኘው ዩዋ ፖፑሌሽን ሴንተር የተባለው ተቋም ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ቻይና ልጅ ለማሳደግ እጅግ ከባድ ከሆነባቸው ሀገራት መካከል ናት።

ጥናቱ እንደሚያሳየው ውድ ከሆነው የትምህርት ክፍያ እንዲሁም እናቶች ሥራ እየሠሩ ልጅ ለማሳደግ ካለባቸው ኃላፊነት ጋር ተዳምሮ ለሕፃናት ማሳደጊያ የሚወጣው ወጪ ከፍ እንዲል አድርጎታል።

የቤት ዋጋ መናርን ተከትሎ በርካቶች ቁጠባቸው መቀንሱን ተከትሎ የቻይና ምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ አሳይቷል። በዚህ ምክንያትም በተለይ ወጣቶች ወደፊት ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ያሰጋቸው ይመስላል።

"አንድ ልጅ አለኝ። ሌላ ልጅ አልፈልግም" ይላል በምሥራቅ ሄናን ግዛት የሚኖረው የ36 ዓመቱ ዳንኤል ሉዎ።

"የባቡር ትራንስፖርት ዋጋ እንደጨመረ ቁጠረው። ዋጋው በአንድ ወይም ሁለት ዩዋን [የቻይና ገንዘብ] ሲጨምር ባቡር መጠቀም እናቆማለን? አናቆምም።"

"የኮንዶም ዋጋ በአምስት አሊያም በ10 ቢበዛ በ20 ዩዋን ቢጨምር ነው። በዓመት ብታሰላው ጥቂት መቶዎች ቢሆን ነው። ይህንን መቋቋም እንችላለን።"

ነገር ግን በማዕከላዊ ቻይና ዢያን ከተማ የምትኖረው ሮዚ ዣዎ ይህ ዋጋ ለሌሎች ላይቀመስ ይችላል ትላለች።

አስፈላጊ የሚባለውን የእርግዝና መቆጣጠሪያን ውድ ማድረግ ተማሪዎች አሊያም አቅሙ የሌላቸው "አደጋ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ" ማለት፤ ይህም "የዚህ ፖሊሲ አደገኛ ውጤት ይህ ነው" ትላለች።

ታዛቢዎች አዲሱ ግብር ሐሳባቸውን የከፋፈለው ይመስላል። በአሜሪካው ዊስኮንሲን-ማዲሰን ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ቁጥር ባለሙያ ይ ፉቺያን ኮንዶም ላይ ግብር ጥሎ የሕዝብ ቁጥር ይጨምራል ብሎ ማሰብ "ትክክለኛ ስሌት አይደለም" ይላሉ።

ምሑሩ እንደሚያምኑት የቤይጂንግ ዓላማ "በተቻለው መንገድ ሁሉ" ግብር ሰብስቦ የቤት ዋጋ ንረቱን መቆጣጠር እና ብሔራዊ ዕዳ መክፈል ነው።

ባለፈው ዓመት ቻይና ከተጨማሪ እሴት ታክስ 1 ትሪሊዮን ዶላር ሰብስባለች። ይህም ከጠቅላላው የግብር ገቢ 40 በመቶ ይሆናል።

ቻይናዊያን ሕፃናት ትምህርት ቤት ሲማሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቻይና በዓለማችን የልጅ ማሳደግ ወጭ ከፍተኛ ከሆነባቸው ሀገራት ተርታ ትመደባለች

ሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ኤንድ ኢንተርናሽናል ስተዲስ የተሰኘው ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሄንሪየታ ሌቪን ደግሞ ቻይና ኮንዶም ላይ የጣለችው ግብር "በአስደናጋጭ" ሁኔታ እየቀነሰ የመጣውን የውልደት መጠን ለመቀልበስ ያላትን ሙከራ " የሚያሳይ" ነው።

ሌቪን እንደሚሉት ልጅ መውለድ ግላዊ ምርጫ እንደመሆኑ አዲሱን ፖሊሲ ተከትሎ መንግሥት "ጓዳችን ገብቷል" የሚሉ ድምፆች እንዳይመጡ ያሰጋል።

በቅርቡ የወጡ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት በአንዳንድ ግዛቶች ሴቶች ስልክ እየተደወለላቸው ስለወር አበባ ዑደታቸው እና ልጅ ስለመውለድ ዕቅዳቸው እየተጠየቁ ነው።

የዩዋናን ግዛት ጤና ቢሮ እንደሚለው መሰል ቁጥሮች ምን ያክል እናቶች ሊወልዱ እንዳሰቡ ለማወቅ አስፈላጊ ነው።

"[ኮሚኒስት] ፓርቲው ያሳስበኛል ያላቸው ውሳኔዎች ውስጥ እጁን እየከተተ የራሱ ጠላት ራሱ ሆኖ ያርፈዋል" ይላሉ ሌቪን።

ታዛቢዎች እና ሴቶች እንደሚሉት በወንዶች የተሞላው የቻይና ገዢው ፓርቲ አመራሮች መሰል ፖሊሲዎች ይዘው የሚመጡትን ማኅበረሰባዊ ለውጥ መረዳት ተስኗቸዋል ይላሉ።

ምዕራባዊያን ሀገራትን ጨምሮ እንደ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ የእስያ ሀገራት የውልደት መጠናቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ እንደመጣ መረጃዎች ያሳያሉ።

ለዚህ እንደ አንድ ምክንያት የሚቆጠረው በአብዛኛው የሴቶች ጫንቃ ላይ የሚወድቀው ልጅ የመንከባከብ እና የማሳደግ ኃላፊነት ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የሚጋቡ ሰዎች ቁጥር መቀነስ ነው።

ሉዎ የቻይና አዲሱ መመሪያ ትክክለኛውን ችግር የረሳ ይመስላል ይላል። ወጣቶች ዘንድሮ እርስ በርስ የሚገናኙበት መንገድ ሀቀኛ ሰዋዊነት የጎደለው ነው ብሎ ያምናል።

በቻይና ለግለ ወሲብ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች (ሴክስ ቶይስ) ሽያጭ መጨመር "ሰዎች ራሳቸውን ብቻ ማስደሰት ነው የሚፈልጉት" እንዲል አድርጎታል። "ከሌላ ሰው ጋር ግንኙነት መመሥረት ዕዳ እየሆነ መጥቷል።"

"የዘንድሮ ወጣቶች ከማኅበረሰቡ የሚደርስባቸው ጫና ከ20 ዓመት በፊት ከነበረው በእጅጉ የላቀ ነው። እርግጥ ነው በሀብት የተሻሉ ናቸው። ነገር ግን የሚጠበቅባቸው ነገር ብዙ ነው። ብቻ ሁሉም ሰው ተዳክሟል።"