የቻይና የሕዝብ ብዛት በ60 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀነስ አሳየ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም ከፍተኛው የሕዝብ ብዛት ያላት ቻይና በስድሳ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ቁጥሯ መቀነስ ማሳየቱ ተገለጸ።
ለዚህም ምክንያቱ ቀደም ሲል ከነበረው በአንድ ሺህ ሰው 7.52 የአገሪቱ አጠቃላይ የወሊድ መጠን ወደ 6.77 መውረዱን ተከትሎ መሆኑን የቻይና ብሔራዊ የስታቲስቲክስ ቢሮ አስታውቋል።
የቻይና ሕዝብ በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት 1.4118 ቢሊየን የደረሰ ሲሆን፣ ይህ አሃዝም ቀደም ካለው 2021 (እአአ) በ850,000 መቀነስ አሳይቷል።
የቻይና የሕዝብ ብዛት ላለፉት ዓመታት እየቀነሰ በመሄዱ የተነሳ ይህንን ክስተት ለመቀልበስ አገሪቱ በነበራት ፖሊሲ ላይ ለውጥ ለማድረግ ተገዳለች።
ነገር ግን ቻይና የነበራትን የአንድ ልጅ ፖሊሲን ካስቀረች ከሰባት ዓመታት በኋላም የሕዝብ ቁጥሯ ከመጨመር ይልቅ በመቀነስ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አንድ ባለሥልጣን ተናግረዋል።
በ2021 (እአአ) ከአንድ ሺህ ሕዝብ አጠቃላይ የወሊድ መጠኗ ወደ 6.77 ያሽቆለቆለው ቻይና ከሌሎች አገራት ጋር ስትንጻጸር ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል።
ከዚህ አንጻር አሜሪካ 11.06፣ ዩናይትድ ኪንግደም 10.08 የወሊድ መጠን ሲያስመዘግቡ፣ በሕዝብ ብዛት የመሪነቱን ቦታ ከቻይና ለመረከብ የተቃበችው ሕንድ ደግሞ ከአንድ ሺህ ሕዝብ 16.42 ወሊድ አላት።
በቻይና ያለው የወሊድ መጠን ሲቀንስ የሞት መጠን ደግሞ ጭማሪ በማሳየት ከአውሮፓውያኑ 1976 (እአአ) ወዲህ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።
በአስር ዓመት አንድ ጊዜ በሚደረገው የሕዝብ ቆጠራ የቻይና ሕዝብ ብዛት በአዝጋሚ ሁኔታ እያደገ መሆኑን ተመልክቷል። ይህ ሁኔታም በምጣኔ ሀብት እና በጤናው ዘርፍ ላይ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል ተገልጿል።
የሕዝብ ቁጥር እድገት መቀነስ እና በእድሜ የገፉ ሰዎች መብዛት በቻይና ውስጥ ብቻ ያጋጠመ ሳይሆን ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያን በመሳሰሉ ሌሎች የምሥራቅ እስያ አገራትም ተከስቷል።
የኮሮናቫይረስ ክስተት እና የምጣኔ ሀብት መቀዘቀዝ በሕዝብ ቁጥር እድገት ላይ ያታየውን መቀነስ ሊያባብሰው እንደሚችልም ባለሙያዎች ይናገራሉ። በቻይና ውስጥ እየተስፋፋ ባለው ወረርሽኝ ምክንያት የሞት መጠን እንደሚጨምር ይገመታል።
የቻይና የሕዝብ ብዛት እድገት በአብዛኛው የተቀረጸው እአአ በ1979 ተግባራዊ በተደረገው እና የሕዝብ ብዛትን ለመቆጣጠር በወጣው የአንድ ልጅ ፖሊሲ ነው።
በዚህም መሠረት ቤተሰቦች አንድ ልጅ ብቻ እንዲወልዱ የሚገደቡ ሲሆን፣ ይህንን ተላልፈው የተገኙትም ከሥራ መባረርን ጨምሮ የተለያዩ ቅጣቶች ሲፈጸሙባቸው ቆይቷል።
በዚህም ሳቢያ በታሪክ እና በባህል ወላጆች ከሴት ይልቅ ወንድ ልጅ እንዲኖራቸው በነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ የግዳጅ ጽንስ ማቋረጥ ሲፈጸም ነበር። ይህ ደግሞ በጾታዎች መካከል የቁጥር ልዩነት እንዲሰፋ አድርጓል።
ነገር ግን የአንድ ልጅ ፖሊሲው በ2016 (እአአ) እንዲነሳ ተደርጎ ጥንዶች ሁለት ልጆች እንዲወልዱ ተፈቅዶላቸዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህም የቻይና መንግሥት እያሽቆለቆለ ያለውን የሕዝብ ቁጥር ለመግታት የተለያዩ የታክስ እና የጤና አገልግሎት ማበረታቻዎችን እየሰጠ ነው።
ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ባደረጉት ንግግር በእድሜ እየገፋ ያለውን ሕዝባቸውን ለመተካት የወሊድ መጠንን ከፍ ማድረግ ከቀዳሚ አጀንዳዎቻቸው መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው ነበር።












