ኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ አገራት መወዳጀት የሚያዋጣቸው ከቻይና ወይስ ከአሜሪካ?

የቻይና እና የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ፣ የአፍሪካ ካርታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ ካለባት 28 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ዕዳ 14 ቢሊዮን ዶላሩን ከቻይና እንተደበረች መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የቻይናን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ኃላፊነት ከያዙ ጥቂት ሳምንታት የሆናቸው ኪን ጋንግ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት 30 ሚሊዮን ዩዋን (ወደ 5 ሚሊዮን ዶላር) የኢትዮጵያን እዳ ዕዳ ቻይና እንደምትሰርዝ ተገልጿል።

ሚኒስትር ኪን ጋንግ ወደ አምስት የአፍሪካ ሃገራት ኦፊሴላዊ ጉብኝት ሲያደርጉ መነሻቸው ኢትዮጵያ ሆናለች።

ኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት ከቻይና የተበደረችው ገንዘብ ቀላል የሚባል አይደለም። ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በርካታ የአፍሪካ አገራት ቢሊዮን ዶላሮችን ከቻይና ተበድረው ዕዳ ውስጥ ናቸው።

ጋና በቅርቡ ያለባትን የውጭ ዕዳ መክፈል ባለመቻሏል በይፋ ‘ዕዳዬን ሰርዙልኝ’ የሚል ተማፅኖ ማቅረቧ አይዘነጋም።

ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋና ካለባት 13 ቢሊዮን ዶላር (የ2021 መረጃ) ዕዳ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ከቻይና እና ደቡብ ኮሪያ የወሰደችው ነው።

የአፍሪካ አገራት ከቻይና የተበደሩት የገንዘብ መጠን አሳስቦኛል ያለው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ‘ኮመን ፍሬምወርክ’ የተሰኘ አንድ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ የአገራት ዕዳን ለማቅለል እየሠራ ነው።

በዚህ ማዕቀፍ መሠረት ዕዳቸው እንዲቀንስላቸው ጥያቄ ያቀረቡት ሦስት አገራት ሲሆኑ፣ እነሱም ኢትዮጵያ፣ ቻድ እና ዛምቢያ።

ባለፉት አስርት ዓመታት ቻይና የአፍሪካ አገራት ዋነኛ ብድር አቅራቢ ከመሆኗ ባሻገር የአህጉሪቱ ቀዳሚ የግንባታ አጋር ናት።

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ግዙፍ ገበያ ባላቸው አገራት ውስጥ የቻይናን እንቅስቃሴ በተለይ በመሠረተ ልማት መስክ በጉልህ የሚታይ ነው።

ለመሆኑ የሰሞኑ የቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣን ጉብኝት አንደምታው ምንድነው? ኢትዮጵያ ያለባት የቻይና ዕዳስ ወዴት እያመራ ነው?

የዓለም አገራት መቧደን

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በየክፍለ ዓለማቱ አገራት የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ትብብር የሚያጠናክሩበት ቡድን ይመሠርታሉ። በዚህም አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ ርዕዮተ-ዓለም ያላቸው አገራት የሚሰበሰብቡበት ነው።

በሌላ በኩል በተለያዩ አህጉራት ያሉ አገራት የኢኮኖሚ አቅማቸው የሚመጣጠን የጋራ ስብስብ ሲመሰርቱ ይስተዋላል።

ኢጋድ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ (ኢኤሲ)፣ የምዕራብ አፍሪካ ኤኮዋስ እና የቡድን 20 እንዲሁም የቡድን 8 አገራት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው።

ከዚህ ባሻገር በምጣኔ ሃብት ኃያል የሚባሉ አገራት ከአህጉራት ጋር የሚያደርጉት ግንኙነትም የሚጠቀስ ነው።

ግዙፍ ገበያ እና ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ያላት አፍሪካ በዚህ ዘመን ከርዕዮተ ዓለም ይልቅ በምጣኔ ሃብት አንጻር ትኩትን እየሳበች ነው። ቻይና፣ ሩሲያ እና አሜሪካም በዋናነት ከአህጉሪቱ አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጥበቅ ደፋ ቀና እያሉ ነው።

“በኢኮኖሚ እና በወታደራዊ አቅም ቀዳሚ የሚባሉ አገራት ቡድን ሲፈጥሩ እናያለን። አሁን አሁን ፉክክሩ ያለው በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ነው” ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባሉሙያው ዋሲሁን በላይ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ተንታኙ እንደሚሉት የአፍሪካ አገራት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ እና የቻይና ፍላጎት እየተቀየረ መጥቷል።

አሁን ሥልጣን ያለው የጆ ባይደን አስተዳደር ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለው ግንኙነት ጠንካራ ነው የሚባል እንዳልሆነም ዋሲሁም ያምናሉ።

ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱ በፈረንጆቹ 2021 አሜሪካ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር የነበራት የንግድ ልልውጥ መጠን ከ60-70 ቢሊዮን ዶላር ነበር ይላል።

በተቃራኒው በተመሳሳይ ዓመት ቻይና ከአፍሪካ አገራት ጋር የነበራት የንግግድ ልውውጥ ከ260 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነበር።

በብድር እና እርዳታ መስክ ቻይና ቀዳሚ የአፍሪካ አገራት አጋር ሆና ዘልቃለች።

ቻይና እና አፍሪካ

ለመሆኑ አፍሪካውያን አገራት ከምዕራባዊያን ይልቅ ከቻይና ጋር ግንኙነት ለመመስረት የሚቀናቸው ለምን ይሆን? የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዋሲሁን ምላሽ አላቸው።

“ይህ የሆነበት ምክንያት አሜሪካ በአፍሪካ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ስለምትገባ፣ ለብድር እና ለእርዳታ ቅድመ ሁኔታ ስለምታስቀምጥ፣ ትንሽ ጉድለት ስትመለከት አሜሪካ የሰጠችውን ክብር ስለምትነሳ ነው ማለት እንችላለን።”

በዚህም ምክንያት በርካታ አገራት የጋራ ጥቅማቸው ወደሚከበርበት እና ጠንካራ የሆነ ቅድመ ሁኔታ ወደሌለበት የቻይና ግንኙነት እያመዘኑ እንደመጡ ምሑሩ ያስረዳሉ።

በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ “አፍሪካ የዓለም አቀፍ ፉክክር መድረክ መሆን የለባትም” ቢሉም ይህ በቅርቡ እውን የሚሆን አይመስልም።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አማካሪ የሆኑት ደለሳ ቡልቻ ነገሪ (ዶ/ር) አሜሪካ እና ቻይና አልፎም ሌሎች ምዕራባዊያን አገራት “አፍሪካን የሥልጣኔ እና የዕድገት ማሳያቸው እያደረጓት ነው” ብለው ያምናሉ።

ቻይና በፈረንጆቹ ከ2000 ጀምሮ በየሦስት ዓመቱ የቻይና-አፍሪካ የትብብር መድረክ አዘጋጅታ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ስታጠናክር ቆይታለች።

በሌላ በኩል የአሜሪካም ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ከ2014 (እአአ) ጀምሮ የሚያቀራርብ ጉባዔ ስታካሂድ ብትቆይም ፍሬያማ ነው ለማት እንደሚከብድ ምሑራኑ ይናገራሉ።

ባለፈው ታኅሣሥ የአፍሪካ አገራት በዩኤስ-አሜሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ዋሽንግተን ደርሰው እንደተመለሱ ይታወሳል። በዚህ ጉባዔ ላይ የ49 የአፍሪካ አገራት መሪዎች ተገኝተው ነበር።

“ነገር ግን የአፍሪካ አገራት የስብሰባውን አጀንዳ እንኳ አያውቁትም ሲባል ነበር” ይላሉ ዋሲሁን።

በተቃራኒው ቻይና ከበርካታ የአፍሪካ አገራት ቀረጥ ይጣልባቸው የነበሩ የግብርና ምርቶች በነፃ እንዲገቡ ማድረጓን አንስተው አገራት ለምን ቻይናን እንደሚመርጡ ያስረዳሉ።

“ቻይና፤ በአገራት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አትገባም። የአገራት የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አያሳስባትም። ደካማ የዴሞክራሲ ተቋማት ያላቸው አገራት ቅድመ ሁኔታ ስለሚሸሹ የቻይና ግንኙነት ይመቻቸዋል።”

አልፎም አሜሪካ ራሷ የምታቀርበው እርዳታ እና ብድር ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ላይ የምታሳድረው ተፅዕኖ ለአፍሪካ አገራት አሳሳቢ እንደሆነ ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ እና የቻይና ሰንደቅ ዓላማ በሚገጣጠም ቅርጽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከቻይና እና ከአሜሪካ ለኢትዮጵያ የሚበጃት. . . ?

ኢትዮጵያ እና ቻይና ከሰሜኑ ጦርነት በፊትም ሆነ በኋላ ያላቸው ግንኙነት ተመሳሳይ እንደሆነ የሚያነሱት ደለሳ ቡልቻ (ዶ/ር) “ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ስምምነት መሠረት በአገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም። ኢትዮጵያ ደግሞ ለማደግና ድኅነት ለማጥፋት ካላት ዓላማ አንፃር ከቻይና ጋር መወዳጀትን ቦታ ትሰጠዋለች።”

ነገር ግን አሜሪካም ሆነ ቻይና ምንም እንኳ አፍሪካ ላይ ለሚኖራቸው የበላይነት ቢሽቀዳደሙም ብሔራዊ ፍላጎታቸውን እንደማይረሱ ተንታኙ ይናገራሉ።

ደለሳ እንደሚሉት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከቻይናም ሆነ ከአሜሪካ ጋር በወዳጅነት እና አገራዊ ጥቅምን ባስከበረ መልኩ መሥራት እንዳለባት ይጠቁማል።

“እኔ ኢትዮጵያ የተነጠለ ወዳጅ ይዛ እንድትንቀሳቀስ አልፈልግም” የሚሉት ደግሞ ዋሲሁን በላይ ናቸው።

“ገና በማደግ ላይ ያለ፣ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ፣ የግብዓት እጥረት ያለበት አገር ሁሉንም ወዳጅ አመዛዝኖ እንዲቀጥል ነው እኔ የምመክረው።”

ከአንድ ወገን ብቻ ወዳጅነት የሚመሥርቱ የዓለማችን አገራት ከሌላኛው ወገን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጫና እንደሚደርስባቸው በመጠቆም ኢትዮጵያ ከኃይላን አገራት ጋር ሚዛናዊ ግንኙነት እንዲኖራት ይመክራሉ።

በዩክሬን ጦርነት ወቅት የአፍሪካ አገራት ከሩሲያ ጋር ተደራድረው የስንዴ ምርት ማስላክ እንደቻሉ በምሳሌ የሚጠቅሱት ተንታኙ፣ የአፍሪካ አገራት ግንኙነታቸው ከአሜሪካ ጋር ብቻ ቢሆን ይህ እውን ሊሆን እንደማይችል ይጠቁማሉ።

ዋሲሁን እንደሚሉት “በማደግ ላይ ካሉ አገራት እና ዕድገታቸውን ካስጠበቁ አገራት” ጋር የሚኖር ግንኙነት ተመሳሳይ ሊሆን አይችልም።

“በማደግ ላይ ያሉ አገራት ዋናው ግባቸው ሁሉን አካታች ፖሊሲ ይዞ ሰጥቶ መቀበል ነው። ያደጉ አገራት ግን ወለድ የሌለው ብድር ይሰጡና እነሱ ወደሚፈልጉት የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲመጣ ማድረግ እንጂ አበድረው ትርፍ መሰብሰብ አይደለም አላማቸው።”

ስለዚህ በማደግ ናት ላይ ናት ከምትባለው ቻይናም ሆነ አድገዋል ከሚባሉት ምዕራባውያን ጋር ኢትዮጵያ የምታደርገው ግንኙነት ሚዛናዊ እንዲሆን ያሳስባሉ።

ደለሳ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው ከትግራይ ጦርነት መቆም በኋላ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት እየተሻሻለ እንደሚመጣ ተስፋ አላቸው።

ከጦርነቱ ለማገገም እና ለመልሶ ግንባታ ድጋፍ ለማግኘት ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲ ማሻሻል እና “በአገር ውስጥ ያለውን ሰላም ማረጋገጥ” እንዳለባት ይጠቁማሉ።

የቻይና ብድር

“ከቻይናም ተበደርን ከሌላም ተበደርን የምንበደርበት ዓላማ እና ለምን ጥቅም ነው የምናውለው የሚለው በጣም መሠረታዊ ጥያቄ ነው” ይላሉ ዋሲሁን።

ኢትዮጵያን የጎበኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ሺንፒንግ ታማኝ ባለሟል እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

በቅርቡ በሚኒስትርነት ከመሾማቸው በፈት በዩናይትድ ስቴትስ የቻይና አምባሳደር የነበሩት ኪን ጋንግ ከኢትዮጵያ አቻቸው ደመቀ መኮንን ጋር መክረዋል።

በዚህ የሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ጉብኝት ወቅት ቻይና አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ዕዳን ከኢትዮጵያ የብድር መዝገብ ላይ ለመሰረዝ ቃል መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ያለባት ጠቅላላ ዕዳ በተለይ ደግሞ የውጭ ዕዳ ከዓመት ዓመት በፍጥነት እያደገ መጥቷል።

የምጣኔ ሃብት ተንታኙ ዋሲሁን እንደሚሉት “ብድሩ መጀመሪያ ሲመጣ መልሰው መክፈል የሚችሉ ዘርፎች ላይ ለማዋል ነው ወይ የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት።”

ምሑሩ እንደሚሉት የአፍሪካ አገራት ባለፉት 60 ዓመታት ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በእርዳታ እና በብድር ቢያገኙም አፍሪካ ከዛሬ 60 ዓመት ከነበረችበት የድህነት መጠን ፈቅ አላለችም።

“በእርዳታ ከሚሰጠው አንድ ዶላር ውስጥ 80 በመቶ አሊያም 80 ሳንቲም የሚሆነው የሚውለው ለታለመለት ዓላማ አይደለም” ይላሉ ዋሲሁን።

ለምሳሌም ኢትዮጵያ “የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ከሆነ የተበደረችው፤ ፓርኩ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገባ ፕሮጀክት መሆን አለበት።”

አሁን ለአፍሪካ አገራት የሚያበድሩ የእስያ አገራት ከዚህ ቀደም ብድር እና እርዳታ ይቀበሉ እንደነበር የሚያነሱት ዋሲሁን፣ የአፍሪካ አገራት ገንዘቡን በተገቢው መንገድ ካልተጠቀሙበት አደጋ ውስጥ እንደሚገቡ ይገልጻሉ።

“ለምሳሌ የግብርና ምርት እና ምርታማነት አሳድጋለሁ ብሎ 2 ቢሊዮን ዶላር በመበደር የስንዴ ምርትን አሳድጎ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ማስቀረት መቻል ማለት በሌላ መልኩ ብድርን መክፈል ማለት ነው። የእኛ ልምድ ግን ይህ አይደለም።”