ኢትዮጵያ ያለባት ዕዳ ስንት ነው? ዕዳዋን ባትከፍልስ ምን ይከተላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ ዕዳ ከዓመት ዓመት በፍጥነት እያደገ መምጣት ይዟል።
የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው ደርግ ከሥልጣን ሲወርድ የኢትዮጵያ ዕዳ 9 ቢሊዮን ዶላር ነበር።
ነገር ግን በ2006 የፈረንጆቹ ዓመት ይህ ዕዳ ወርዶ 2.2 ቢሊዮን ወርዶ የነበረ ቢሆንም፣ ከዚያ በኋላ ግን የኢትዮጵያ ዕዳ ከዓመት ዓመት በቢሊዮን ዶላሮች ይጨምር ያዘ።
የዓለም ባንክ በፈረንጆቹ 2020 ባወጣው መረጃ የአገሪቱ ዕዳ 30.36 ቢሊዮን ዶላር ነበረ።
እነሆ ከሁለት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ከአገር ውስጥና ከውጭ የወሰደችው ብድር 56.6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ይላል የገንዘብ ሚኒስቴር።
የኢትዮጵያ ዕዳ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት ግማሽ ያክል መሆኑን ተከትሎ ባሉ ወቅታዊ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ምክንያት አበዳሪዎች በኢትዮጵያ እና በሌሎች አገራት የብድር አከፋፈሉ ዙሪያ ውይይት ይዘዋል።
ከኢትዮጵያ የውጭ አበዳሪዎች የአንበሳውን ድርሻ የምትይዘው ቻይና እንዲሁም ፈረንሳይ ናቸው ስብሰባውን የሚመሩት።
የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ዕዳ ስለማሸጋሸግ ውይይት ማድረግ የጀመሩት ባለፈው ዓመት ነበር። ነገር ግን በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት ጉዳዩን አጓተተው።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ)፣ የዓለም ባንክ፣ ሌሎች የገንዘብ ተቋማት ቻይና እና ሌሎች አበዳሪዎች ኢትዮጵያ፣ ቻድ እና ዛምቢያ ላለባቸው ዕዳ አስተያየት እንዲያደርጉ በመወትወት ላይ ናቸው።
የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ዕዳ ኖሮባቸው ተጨማሪ ፈተና እየገጠማቸው ላሉ አገራት መፍትሔ መበጀት አለበት ሲሉ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።
ለመሆኑ ዕዳ ማሸጋሸግ ምንድን ነው? ኢትዮጵያ ዕዳዋን መክፈል ባትችል ምን ይፈጠራል?
“ብድሩ ጥቅም ላይ አልዋለም”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ኢትዮጵያ የነበረባት ዕዳ 28 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነበር ይላሉ አየለ ገላን (ዶ/ር)።
የምጣኔ ሃብት ተንታኙ እንደሚሉት በወቅቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ የተመለከቱ አበዳሪዎች ለኢትዮጵያ ልገሳና ብድር ሰጥተዋል።
“ሁኔታው የተበላሸው ከተፈጠረው ትልቅ ተስፋ አንፃር መንግሥት የተበደረውን ገንዘብ ጥቅም ላይ አለማዋሉ ነው” ይላሉ ተንታኙ።
“ብድሩን ተጠቅሞ ተጨማሪ ገቢ ማስገባት አለመቻሉ፤ በቂ ሥራ አለመፈጠሩና ገንዘቡ የውጭ ምንዛሬ አለማምጣቱ ችግር ፈጥሯል።”
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት በፊት የነበረው አስተዳደር የወሰደው ብድር ሳይመለስ እስከ 2012 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ቢያንስ ተጨማሪ 10 ቢሊዮን ዶላር ብድር መንግሥት መውሰዱ የዕዳውን መጠን እንዳሻቀበው ያምናሉ።
“ብድር መክፈል ከዚህ ቀደም ከነበረው ይልቅ አሁን አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።”
ለኢትዮጵያና ሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራት ብድር ከሚሰጡ መካከል አንዱ የሆነው አይኤምኤፍ፣ በፈረንጆቹ 2020 ለኢትዮጵያ 3 ቢሊዮን ዶላር ብድር አፅድቋል።
ሌሎች አበዳሪዎችና የዓለም ባንክም እንዲሁ ተጨማሪ 6 ቢሊዮን ዶላርመስጠታቸውን ተከትሎ አሁን ኢትዮጵያ ያለባት ዕዳ መጠን ከ38 ቢሊዮን ዶላር አያንስም ይላሉ ተንታኙ።
አይኤምኤፍ ብድሩን ከማፅደቁ በፊት በ2019 ኢትዮጵያ ብድር ለመመለስ ከሚቸገሩ አገራት መካከል እንደሆነች ገልጦ ነበር።
“ይህ ማስጠንቀቂያ የኢትዮጵያ ዕዳ መጠን በ2 ቢሊዮን ዶላር ቀንሶ በነበረ ጊዜ የወጣ ነው።”

ዕዳ ማሸጋሸግ ምንድን ነው?
የዐቢይ አሕመድ መንግሥት አበዳሪዎች ለኢትዮጵያና ለሌሎች የአፍሪካ አገራት የዕዳ ሽግሽግ [ዴት ሪስትራክቸሪንግ] እንዲያደርጉ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል።
ከሰሞኑ አበዳሪዎችና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ውይይት ጀምረዋል።
የምጣኔ ሃብት ሙያተኛው አየለ ገላን፣ መንግሥት የ2015 ዓ.ም. በጀትን አስመልክቶ ባቀረበው ሪፖርት በቀዳሚነት ያሰፈረው ጉዳይ ብድር መመለስ መሆኑን ያወሳሉ።
ኢትዮጵያ ከሰሜኑ ጦርነት በፊት ጀምሮ የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄ ስታቀርብ ብትቆይም በጦርነቱ ወቅት ከአበዳሪዎች ጋር የነበራት የሻከረ ግንኙነት ችግር እንደፈጠረ ተንታኙ ይገልጣሉ።
“መንግሥት በበጀት ድልድል ውስጥ ብድር መክፈልን ከላይ ሲያስቀምጥ አይቼ አላውቅም” የሚሉት ተንታኙ፤ ይህ የዕዳ ጫናው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያሳያል ባይ ናቸው።
“አሁን የቀረበው የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄ በአጭሩ ‘ብድሩ ከአቅም በላይ ስለሆነብኝ ማሻሻያ ይደረግልኝ’ ማለት ነው።”
እንደ ተንታኙ ገለፃ ሽግሽጉ በዋናነት ሦስት መንገዶች አሉት።
“አንደኛው ብድሩ ከአቅሜ በላይ ስለሆነ ይሰዘርልኝ ብሎ አበዳሪን ለማስማማት መሞከር ነው። ሁለተኛው፤ የብድሩ ወለድ ከፍተኛ ስለሆነብኝ ይቀነስልኝ የሚል ሊሆን ይችላል፤ ሦስተኛው ደግሞ ብድሩን ከፍዬ የምጨርስበት ጊዜ ይራዘም የሚል ነው።”
አየለ (ዶ/ር) በዓለም አቀፍ ደረጃ ብድር ወስዶ በጊዜው አለመመለስ ወንጀል ነው ይላሉ።
“ከዚህ ለመራቅ አገራት አበዳሪዎቻቸው ብድሩን እንዲሽሩላቸው የሚቻላቸውን ያደርጋሉ። ይህ ካልሆነ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ይገባሉ። ይህ ደግሞ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል።”
ከዚህ ቀደም ብዙ ጊዜ አበዳሪ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ብድር እንደ ሰረዙ የሚያስታውሱት ተንታኙ በአሁኑ ድርድር ሊሆን የሚችለው የክፍያ ጊዜን ማራዘም እንደሚሆን ግምት አላቸው።
የመሳካት ዕድል የሚያገኘው የክፍያውን ጊዜ ማርዘም ነው።
“የክፍያ ጊዜን በማራዘም የሚደረግን ሽግሽግ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ መልካም ዜና ቢያየውም አደጋ አለው። ጊዜያዊ መፍትሔ ሊሆን ቢችልም የክፍያ ጊዜው በረዘመ ቁጥር የወለድ መጠኑም እየጨመረ ይመጣል። ይህ ለበለጠ ድህነት የሚዳርግ ነው። ‘ሾርት ተርም ጌይን፤ ሎንግ ተርም ፔይን’ (አጭር ጊዜ ጥቅም፤ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጉዳት) ይሆናል።”
የዕዳ ክምችት የፈጠረው ጫና
በርካታ የልማት ተቋማት 40 በመቶ የሚሆኑ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ከባድ የብድር ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) በፈረንጆቹ 2018 ባወጣው መረጃ አፍሪካ የዕዳ ቀውስ ውስጥ እየገባች ነው ሲል አስጠንቅቆ ነበር።
ተቋሙ እንደሚለው ባለፉት አምስት ዓመታት የዕዳ ስጋት ያለባቸው የአፍሪካ አገራት ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል።
ቻይና ለአፍሪካ አገራት ብድር ከሚሰጡ መካከል ቁንጮዋ ናት። ከአፍሪካ መንግሥታት መካከል 20 በመቶው የቻይና ዕዳ አለባቸው።
35 በመቶ ብድር የሚገኘው እንደ ዓለም ባንክ ካሉ ተቋማት ሲሆን፣ 32 በመቶ ደግሞ ከግል አበዳሪዎች ነው።
ባለፉት 11 ወራት [እስከ ግንቦት ወር 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ] መንግሥት 330 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 309 ቢሊዮን ብር ብቻ መሰብሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ተናግረው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ እንደራሴዎች ፊት ቀርበው ባሰሙት ንግግር መንግሥት 500 ቢሊዮን ዶላር ወጭ አድርጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወጪ ከገቢዋ አንጻር ያለው ልዩነት እንደህ እንዲሰፋ ያደረገው አገሪቱ ያለባት ዕዳ ነው።
“በዚህ ዓመት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ከፍለናል። ይህ መቶ ቢሊዮን ብር አካባቢ ማለት ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ የ2015 በጀት እንዲሆን የመደበው ገንዘብ 786.6 ቢሊዮን ብር ነው።
በወቅቱ ከዚህ ገንዘብ መካከል አብዛኛው ለዕዳ ክፍያ፣ ለመልሶ ማቋቋምና ለመከላከያ ግንባታ የሚውል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ጠቅሶ ነበር።
የምጣኔ ሃብት ሙያተኛው አብዱልመናን አሕመድ ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ከሚጎትቱ ፈተናዎች መካከል አንደኛው አገሪቱ ያለባት ዕዳ ነው ይላሉ።
አብዱልመናን መንግሥት የግል ዘርፉን የሚያበረታታ ፖሊሲ ካልቀረፀ ምጣኔ ሃብቱን ማሳደግ ሊከብደው ይችላል ብለው ያምናሉ።
“የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ፣ የማክሮ ኢኮኖሚው ጉዳይ [ለምሳሌ የዋጋ ግሽበት] እና መንግሥት ያለበት የተጠራቀመ ዕዳ ማነቆ ሆነዋል።”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ያለበትን የዕዳ መጠን እንዲሁም ከአገሪቱ በጀት ገዘፍ የሚለው ለዕዳ ክፍያ መሆኑን ባስረዱበት ወቅት በርካታ እንደራሴዎች ጥያቄ አንስተው ነበር።
የመንግሥት የበጀት አጠቃቀም ችግርና ብክነት እንዲሁም የአገር ውስጥ ገቢ የመሰብሰብ አቅም አለመጎልበት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ እንደራሴዎቹ።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከ2011-13 ዓ.ም. ባለው ዘመን ከዕቅድ በታች የሆነ 7.1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያን ብድር የሚከፍለው ማን ነው?
ኢትዮጵያ ካለባት ዕዳ 97 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው የረጅም ጊዜ ብድርና ‘ፐብሊክና ፐብሊክሊ ጋራንቲንድ’ የተሰኘ የብድር ዓይነት እንደሆነ ኢኮኖሚስቱ አየለ ገላን ይተነትናሉ።
“የረጅም ጊዜ ብድር ማለት ክፍያው ከ30 እስከ 50 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከፈል ነው። ይህ ማለት ብድሩን መመለስ አሁን የተበደረው መንግሥት ኃላፊነት ላይሆን ይችላል ማለት ነው።”
‘ፐብሊክና ፐብሊክሊ ጋሪንቲንድ’ [በሕዝብ ንብረት ዋስትና የተገኘ ብድር] የተሰኘው ደግሞ ክፍያው መመለስ ባለበት ሰዓት የመመለስ ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲሆን፣ ብድሩን የሚመልሰው የአሁኑ ትውልድ አይሆንም ማለት ነው ይላሉ ተንታኙ።
ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ሲያበድሩ ብድሩ በጊዜው የማይመለስ ከሆነ እንደ ዋስትና የሚይዙት ሃብት አሊያም ንብረት ይኖራል።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ብድር የምትወስደው ምን አስይዛ ነው?
አገራት ብድራቸውን መከፍል ሲሳናቸው ፕሮጀክቶቻቸው እንደ መያዣ ሲያዙ መስማት የተለመደ ሆኗል።
ለምሳሌ ብቸኛው የዚምባቡዌ አየር መንገድ ለደቡብ አፍሪካ መንግሥት መክፈል የነበረበትን ዕዳ ባለመክፈሉ እስከ 2019 ተይዞ ቆይቷል።
አየር መንገዱ በ2019 በረራ ሲጀምር 2017 በተከማቸበት ከፍተኛ ውዝፍ ዕዳ ምክንያት ከግማሽ በላይ ሠራተኞቹን ለማሰናበት ተገዶ ነበር።
ይህ ሳያንሰው ኤይር ዚምባብዌ በደኅንነት ስጋት ምክንያት በአውሮፓ አገራት አየር ክልል የመብረር ፈቃዱን ተነጥቋል።
አንጎላ ደግሞ መክፈል ያለባትን 100 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ በገንዘብ መመለስ ባለመቻሏ ለቦትሰዋና ከብቶች በመስጠት ጭምር እየከፈለች መሆኑን በ2020 የአገሪቷ ጋዜጣ አስነብቦ ነበር።
የምጣኔ ሃብት ተንታኙ አየለ ገላን እንደሚሉት ኢትዮጵያ ምን አስይዛ ብድር እንደምትወስድ እስካሁን በግልፅ አይታወቅም።
የሌሎች አገራትም ልምድ ተመሳሳይ መሆኑን የሚገልጡት ባለሙያው አገራት ምን አስይዘው ብድር እንደሚወስዱ የሚታወቀው በተበዳሪውና በአበዳሪው መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ወደ ሕግ ሲያመሩ እንደሆነ ያስረዳሉ።
“መንግሥት ሲበደር በእጁ የሚገኘውን የትኛውንም ሃብት አስይዞ ነው። ምንድነው የሚለው ግን ምስጢር ነው።”
ተንታኙ በኬንያ እና ቻይና መካከል የተፈጠረውን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
“ኬንያ ከቻይና ወስዳ በነበረው ብድር ዙሪያ አለመግባባት ተፈጥሮ የሞምባሳ ወደብ እንደ ዋስትና ተይዞ እንደነበር ግልፅ የሆነው ቻይና ወደቡ የእኔ ነው ማለት ስትጀምር ነው።
“ዛምቢያም እንዲሁ ከቻይና ተበድራ ለነበረው ገንዘብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተቋሟን ማስያዣ አድርጋ እንደ ነበር አለመግባባት ሲፈጠር ነው ያወቅነው።”
ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎቿ ጋር ግልፅ የሆነ አለመግባባት ውስጥ ስላልገባች ምን እንዳስያዘች ማወቅ አዳጋች ነው ይላሉ።












