ለ‘ልጃችሁን ለልጃችን’ ጥያቄ ሴቶችን የላከው ዘማሪ አቤኔዘር ፍቅሩ

የፎቶው ባለመብት, Abenezer Fikru
ዘማሪ አቤኔዘር ፍቅሩ ወደ ፍቅረኛው ቤተሰቦች ‘ልጃችሁን ለልጃችን’ ብለው እንዲጠይቁ ሴቶች መላኩ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።
በዘልማድ ወደ ሴቷ ቤተሰብ የሚላኩት ወንዶች ናቸው። ለጋብቻ የልጃችሁን ለልጃችን ጥያቄ በወንዶች ከመዘውተሩም ባሻገር ወንዶችን ብቻ በሚወክለው ‘ሽምግልና’ በሚለው መጠሪያ ነው የሚታወቀው።
ዘማሪ አቤኔዘር ግን ዘልማዱን ‘በመስበር’ ሴቶችን ልኳል።
አባታዊ ሥርዓት በተጫናት አገር ሴቶችን ለልጃችሁን ለልጃች ጥያቄ መላካቸውን በማድነቅ አስተያየታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩም አሉ።
ወንድ የጋብቻ ‘ጠያቂ’ የሴት ቤተሰብም ‘ፈቃጅ’ ተደርጎ መወሰዱ በራሱ የማይዋጥላቸው ደግሞ፣ ለልጃሁን ለልጃችን ማንም ቢላክ እምብዛም ለውጥ እንደሌለው ተከራክረዋል።
የዘማሪ አቤኔዘር ፍቅረኛ ቤተሰቦች ቤት የተላኩት ሴቶች ጥበብ ልብስ ለብሰው የተነሱት ፎቶ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት እየተጋራ ነው።
ዘማሪ አቤኔዘር ከቢቢሲ ጋር ያደረገውን ቆይታ የጀመረው የፍቅረኛው ቤተሰቦች “. . . ተቀብለውኛል። እሺ ተብያለሁ” በማለት ነበር።
ዘማሪ አቤኔዘር እንደሚለው፣ ሴቶችን ወደ ፍቅረኛው ቤት ለመላክ እንዳሰበ መጀመሪያ የነገረው ለአባቱ ነበር።
“ወላጅ አባቴ ጋር ነው መጀመሪያ የሄድኩት። እናቶችን ልልክ አስቤያለሁና ምን ትላለህ? ስለው እጅግ በጣም ነው ደስ ያለው” ሲል ያስታውሳል።

የፎቶው ባለመብት, Abenezer Fikru
ይህንንም ሃሳቡን አባቱ ያጸኑለት “ለእናቶች ክብር እንዲኖርህ አድርገን እንዳሳደግንህ ነው ያሳየኸን ነው ያለኝ” ይላል።
አይይዞም “ቤተሰቦቼ በጣም ነው ደስ ያላቸው። በጥሩ ሁኔታ እንዳሳደግንህ፣ ለሴት ክብር እንዲኖርህ አድርገን እንዳሳደግንህ አሳይተኸናል ብለው ነው የፈቀዱልኝ” ሲል አክሏል።
የፍቅረኛውን ቤተሰቦች ሴቶች እንደሚልክ አስቀድሞ እንደነገረ ለቢቢሲ የገለጸው ዘማሪ አቤኔዜር መጀመሪያ ስላሰበው የሽምግልና ጥያቄ የእሷን ቤተሰብ ጠይቆ ነበር።
እነሱም “[ሴቶችን መላክ] ከባህልም ከሃይማኖትም አንጻር ነውር የሚያደርገው ነገር የለም። [ሴቶች] ኩራቶቻችን እንጂ የሚያሳፍሩ ስላልሆኑ አምኜበት ልኬያለሁ። ቤተሰቦቿ በጣም ነው ደስ ያላቸው” ብሏል።
አቤኔዘር ሴቶቹን ለሽምግልና ወደ ፍቅረኛው ቤት የጋብቻ ጥያቄውን አስይዞ ሲልካቸው የነበረውን ሁኔታ “ከልማዱ ወጣ ያለ ስለሆነ ማስረዳት ነበረብኝ” በማለት ነው የገለጸው።
ስለዚህም ሃሳቡን ለሽምግልና ለመረጣቸው ሴቶች “. . .ለእናንተ ፍቅር እና አክብሮት ስላለኝ እናንተን ብልክ አታሳፍሩኝም። የእሷም ቤተሰቦች ‘ደስ ነው የሚለን፣ አክብሮት ነው የሚሰማን’ ስላሉ እባካችሁ ሂዱልኝ” በማለት ነበር ጥያቄውን ያቀረበው።
እነሱም ሃሳቡን ተቀብለው ለአቤኔዘር እጮኛ ቤተሰብ ልጃችሁን ለልጃችን ስጡ የሚለውን ጥያቄ ይዘው በደስታ ነበር የሄዱት።

የፎቶው ባለመብት, Abenezer Fikru
ጥር 07/2015 ዓ.ም. ወደ ፍቅረኛው ቤተሰቦች ቤት ለሽምግልና የተላኩት እናቶችም የተደረገላቸው አቀባበል እና መስተንግዶ በጣም ደስ እንዳሰኛቸው እና “ይሁን፤ ጥያቄያችሁን ተቀብለናል” በማለት ቀልጠፍ ያለ ምላሽ ይዘው ተመልሰዋል።
የፍቅረኛው ቤት ከሄዱ እና ጥያቄውን ካቀረቡ በኋላ ደግሞ የፍቅረኛው ቤተሰቦች “እናቶችን ማስቆም በጣም ነው የሚከብደው። ቆመው እባካችሁ እያሉ፣ ልጃችሁ ለልጃችን፣ የሚሆናትን ልጅ ነው ይዘን የመጣነው ሲሉ ጥያቄ ራሱ ማብዛት ከበዳቸው” እንዳሉ አክሏል።
ሴቶችን በሽምግልና በመላኩ የጋብቻ ጥያቄው እንደሰመረለት ሲገልጽም “[ሴቶች መላክ] ቆንጆ ጥበብ ነው። እውነቱን ለመናገር እናቶች ቆመው እየጠየቁ፣ እየለመኑ እምቢ ማለትና መግፋት፣ ረዥም ሰዓት እነሱን ማጉላላት ከባድ ነው” በማለት ነው።
በፍቅረኛው በኩል ደግሞ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሴቶች እና ወንዶችም የቤተሰቧ አባላት እንደተገኙ እና በሥነ ሥርዓቱ ደስተኛ እንደነበሩ ሳይግጽ አላለፈም።
ወንዶች ቢላኩ በሴቷ ቤተሰብ ‘ተቀባይነት ያገኛሉ’ የሚለው እንዲሁም ሴቶችን መላክ ያልተለመደ እና የሴቷን ቤተሰብ ‘መናቅ ነው’ በሚለው አመለካከት ሳቢያ ወንዶችን መላክ ልምድ ዘማሪ አቤኔዘር ለውጦታል ማለት ይቻላል።
እሱም ለዘመናት ከነበረው ልማድ በተቃራኒ “የተለየ ትርጉም መስጠት ስላለብኝ እና እናቶች ክብር ስለሚገባቸው” ሴቶችን ሽምግልና መላኩ ክብር እንዲሰማውና በእጮኛው ቤተሰቦችም ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘለት ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Abenezer Fikru
የአቤኔዘር ወደ እጮኛው ቤት ለጋብቻ ጥያቄ ሴቶችን መላኩ በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ሰፊ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል።
በርካቶች ከነበረው ልማድ በተለየ ሁኔታ ወደ ሴቷ ቤት ሴቶችን መላክ መምረጡን በማድነቅ ታላቅ አርአያነት እንደሆነ በመግለጽ ሲደግፉት፣ ከተለመደው አካሄድ የወጣ ነው በሚል የተቹም ነበሩ።
ከዚህ ባሻገርም “ሽምግልና” የሚለው ስያሜ የወንዶችን ሚና ብቻ የሚያሳይ ነው በሚል በቃሉ ላይ የተለያዩ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ ጥያቄዎችም ሲነሱ ነበር።
ነገር ግን በርካቶች ከአቤኔዘር 'ደፋር' እርምጃ ባሻገር፣ ሴቶቹ ጥያቄውን በመቀበላቸው እንዲሁም የእጮኛው ቤተሰቦች እንግዶቻቸውን በወጉ ተቀብለው በማስተናገዳቸው ሁሉም አድናቆት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።












