የሲሲሊ ማፊያዎችን የሚያስንቁት የዘመኑ የማፊያ ጌቶችን የሚያሳድዱት ዐቃቤ ሕግ

የሲሲሊ ማፍያዎችን የሚያስንቁት የጣሊያን አደገኞቹ የማፊያ ጌቶች ማን ናቸው?
የምስሉ መግለጫ, የሲሲሊ ማፍያዎችን የሚያስንቁት የጣሊያን የማፊያ ጌቶች ማን ናቸው?

የጣሊያን ካርታ ሴቶች ክረምት ላይ የሚጫሙትን ቡትስ ጫማ ይመስላል። ጣሊያን ቦቲ ጫማ ናት ብንል ኃያላኑ ማፍያዎች የሚኖሩት አውራ ጣቷ ላይ ነው።

ካላብሪያ ትባላለች፤ ደቡባዊ ጣሊያን።

ከእነርሱ በታች ያሉት ሲሲሊዎች ናቸው።

ሲሲሊዎችን እንርሳቸው። በ80ዎቸ ገነዋል። የነማሪዮ ፑዞን የጡት አባት ታሪክን እንርሳ።

የአሁኖቹ የማፊያ ጌቶች ሌሎች ናቸው።

መኖርያቸው ካላብሪያ ግዛት ነው። የጣሊያን አውራጣት ያልናት ግዛት።

ስማቸው ንድራንጌታ ይባላል። እነርሱን ለሕግ ለማቅረብ ደፋ ቀና የሚለውን ዐቃቤ ሕግ አገኘነው።

ለምን እንደማይገድሉት ለራሱ ይገርመዋል።

እሱ እና ቤተሰቡ 24 ሰዓት ጥበቃ ይደረግላቸዋል። ኒኮላ ግራቴሪ ይባላል።

ማፊያዎች በተገኘበት ይገደል የሚል ውሳኔ የሰጡበት ሰው ነው።

እርሱ ግን ግዴለውም። እስኪገድሉት ድረስ ይፋለማቸዋል።

እርሱን በቀጠሮ ማግኘት ከባድ ነው። አንደኛ ቶሎ ቶሎ የቀጠሮ ቦታ ይቀያይራል። ሁለተኛ 20 ደቂቃ ሲቀር ብቻ ነው የቀጠሮውን ቦታ የሚገልጸው።

25 ዓመት ሙሉ ፀጉር ቤት ሄዶ አያውቅም። ፀጉር አስተካካዩ እርሱ ያለበት ቦታ ይመጣል።

25 ዓመት ሙሉ ሬስቶራንት ሄዶ ተመግቦ አያውቅም። ይመርዙታል።

ልጁን ከትምህርት ቤት አውጥቶ አያውቅም፤ ከቤተሰቡ ጋር ልዝናና ብሎ አያውቅም። ምክንያቱም የንድራንጌታ ማፊያዎች ይገድሉታል።

ዐቃቤ ሕጉ ኒኮላ ግራቴሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዐቃቤ ሕጉ ኒኮላ ግራቴሪ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ንድራንጌታዎች የሚኖሩት በካሊብሪያ ግዛት ውስጥ ነው ብለናል።

በዚያ ግዛት ከሲሲሊ ማፍያዎች የ1980ዎቹ የፍርድ ሂደት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የፍርድ ሂደት ተጀምሯል።

ክሳቸው እየተሰማ ካሉት 330 ተጠርጣሪዎች መካከል፤ 70ዎቹ ጥፋተኛ ተብለዋል።

በማንኛውም ቅጽበት ዐቃቤ ሕጉ ኒኮላ ግራቴሪ ሊገደል ይችላል። ዳኞቹም ሬሳቸው ትቦ ውስጥ ተጥሎ ሊገኝ ይችላል።

ይህ እንደሚሆን እያወቁ ነው ሥራቸውን እየሰሩ ያሉት።

ዐቃቢ ሕጉ ሊያዋራን ፈቀደ። አምስት የሚሆኑ ልዩ ጥበቃዎች ከበቡን።

በጥቅሻ የሆነ ምልክት ሰጣቸው። ወደእርሱ ተጠጋን። ቶሎ ጥያቄዎቻችንን እንድንጀምር ጠየቀን።

“በቅድሚያ ጥሪያችንን አክብረህ ለዚህ ቃለ መጠይቅ….” ተበሳጭቶ አቋረጠን።

“በሕይወቴ ሰከንዶንችን በከንቱን እንደሚገድል ሰው የሚያናድደኝ ፍጡር የለም” ብሎ ቀጥታ ወደ ጉዳያችን እንድንገባ ነገረን።

የዚህ ዐቃቤ ሕግ ሕይወት በየትኛውም ሰዓት ቀጥ ልትል ትችላለች። ስለዚህ ሰከንዶች ሕይወት ናቸው ለእርሱ። መፍጠን አለበት።

እያሳደዳቸው ያሉ ማፊያዎች በዓለም ቁጥር አንድ የሚባሉትን ነው።

ጥይት የማይበሳው መኪናው ውስጥ ተሳፈርን። እየነዳ ማውራት ጀመረ።

“ከ1980ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በሞት አፋር ነው የኖርኩት። ያን ጊዜ የእጮኛዬ መስኮት በጥይት ተበሳሳ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ስልኳ ጠራ። ደዋዩ አጭር መልዕክት ተናግሮ ስልኩን ዘጋው። መልዕክቱም ‘ከሬሳ ጋር ጋብቻ እንዳታስቢ። እጮኛሽ በቅርቡ ሬሳ ይሆናል’ የሚል ነበር።”

ከ30 ዓመት በፊት እንደርሱ ዐቃቤ ሕግ ሆነው የሲሲሊ ማፊያዎችን ለፍርድ ያቀረቡ ባልደረቦቹ ተገድለዋል።

ጂዮቫኒ እና ፓውሎ ይባላሉ።

መኪናቸው ላይ ቦብም አጥምደው ፓሌርሞ አካባቢ አፈነዷቸው። ጂዮቫኒ እና ሚስቱ እንዲሁም 3 ጠባቂ ፖሊሶቹ ወዲያውኑ ሞቱ።

የጂዮቫኒ ባልደረባ ፓውሎ ተረፈ። ‘አታመልጠንም’ አሉት። እንደዛቱትም ከሁለት ወር በኋላ በተመሳሳይ መንገድ እሱንም ገደሉት።

ይህን ያደረጉት የሲሲሊ ማፊያዎች ነበሩ። አሁን አብሮን ያለውን ዐቃቤ ሕግ የሚፈልጉት ግን ከሲሲሊ ማፊያዎችም በላይ ናቸው።

ንድራንጌታ (Ndrangheta) ይባላሉ።

በአጭሩ የጣሊያን ማፊያዎችን እንተዋወቃቸው?

ጂዮቫኒ እና ፓውሎ ዐቃቤ ሕግ ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, TONY GENTILE

የምስሉ መግለጫ, ጂዮቫኒ እና ፓውሎ ዐቃቤ ሕግ ነበሩ። እንደዛተው የሲሲሊ ማፍያ በተጠመደ ቦምብ ገድሏቸዋል

ከሲሲሊ በላይ ደግሞ ማፊያ አለ እንዴ?

ጣሊያን አራት አካባቢያዊ ማፊያዎች አሏት።

የመጀመሪያው ብዙ ሰው የሚያውቃቸው የሲሲሊ ማፊያዎች ናቸው። ሲሲሊ የቦታ ስም ነው። የማፊያዎቹ ትክክለኛ ስም ኮሳ ኖስትራ ነው የሚባለው።

ሁለተኛዎቹ ደግሞ የንድራንጌታ ማፊያዎች ናቸው። ከሲሲሊ ትንሽ ወደ ሰሜን ምሥራቅ ከፍ ብለው በካላብሪያ ግዛት፣ ደቡባዊ ጣሊያን ነው የሚገኙት።

ሦስተኛዎቹ ካሞራ የሚባሉት ናቸው።

እነዚህ ከበርካታ ጎሳዎች የሚሰባሰቡ የማፊያ ቡድኖች ናቸው። በተለይ በጣሊያኗ ኔፕልስ ግዛት ውስጥ ዕውቅ ናቸው።

አራተኛው አፑሊያን ማፊያ የሚባለው ሲሆን፣ ሰሜናዊ ጣሊያን አካባቢን በወንጀል ይቆጣጠራሉ።

ከእነዚህ ሁሉ እጅግ አስፈሪው እና እጅግ ሃብታሙ፣ እጅግ አደገኛው እና እጅግ ኃያሉ የማፊያ ቡድን በሲሲሊ ግዛት ተወልዶ ያደገው ኮሳ ኖስትራ ነበር።

በፊልሞች እና በልቦለድ መጻሕፍት ታሪካቸው የተተረከላቸው የሲሲሊ ኮሳ ኖስትራ ማፊዎች አሁንም አሉ። ነገር ግን ገናናነታቸው እየከሰመ ነው።

አሁን ጊዜው የንድራጌታዎች ነው። የዓለም ማፊያ ጌቶች ንድራጌቶች ናቸው።

እጅግ ሃብታሞቹ፣ ጨካኞቹና አደገኞቹ ሲሆኑ፣ ከመንግሥት ያልተናነሰ ጉልበት አላቸው ይባላሉ።

ምንጫቸው አንድ ጎሣ ሲሆን የሚገኙትም በደቡባዊ ጣሊያን ካላብሪያ ግዛት ውስጥ ነው።

የወንጀል መረባቸው ከደቡባ አሜሪካዋ ኮሎምቢያ አንስቶ እስከ አውሮፓ እና አውስትራሊያ ይዘረጋል።

ዋናው መጠለያቸው፤ ዞሮ መግቢያቸው ግን ጣሊያን ካላብሪያ ግዛት ነው።

በአንድ ወቅት ዋነኛው የጣሊያን ወደብን በከፊል ገዝተው ማስተዳደርም ጀምረው ነበር።

ይህን ካላብሪያ የጣሊያን ግዛት ቁጭ ብድግ እያደረገ የሚገዛው የጣሊያን መንግሥት ነው ቢባል ቧልት ነው።

ካላብሪያ ግዛት በእነዚህ ንድራጌታ የማፊያ ቡድን የሚዘወር አካባቢ ነው። ለምክር ቤት ምርጫ ከዚህ አካባቢ ተወዳዳሪ ጠፍቶም ያውቃል።

ስውር እጃቸው እስከ ቤተ መንግሥት ይገባል።

እጅግ የናጠጡ ሲሆኑ፣ ዋናው የገቢ ምንጫቸው የኮኬይን ንግድ ነው።

አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ ከሚሳለጠው አደገኛ ዕጽ አብዛኛው በንድራጌታ የጎሣ የማፊያ ቡድን ቁጥጥር ስር ያለ ነው።

በጦር መሣሪያ ዝውውር ውስጥም ገብተውበታል።

ከናይጄሪያ እና ከቱርክ የወሮ በላ ቡድኖች ጋር ደግሞ በመጠኑ በካናቢስ ንግድ ውስጥ ይሳተፋሉ።

እንደው ለወጉ ያህል ነው እንጂ ካናቢስን በከፍተኛ መጠን ካልሆነ አይነግዱትም። ንድራንጌታዎች በሚሊዮን ዶላሮች ካልሆነ አይጫወቱም።

በሱስ አስያዥነት የሚታወቀው ሜታአምፊታሚን የተባለውን መድኃኒት ወደ አውስትራሊያ የሚያቀባብሉት እነሱ ናቸው።

ካርታ

ንድራንጌታ ማፊያ ቡድን አንድ ጎሣ ነው?

አዎ! ይህ የማፊያ ቡድን የተሳሰረው በጎሣ፣ በቤተሰብ፣ በደም ነው።

ለዚህም ነው ምሥጢር የማይወጣው። ሁሉም በጋብቻ ተሳስረዋል። በጎሣው ውስጥ የአያት ስም ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

ከዚያ ቤተሰብ የከዳ ሕይወት ትከዳዋለች።

የእያንዳንዱ ቤተሰብ የአያት ስም ‘ንድሪና’ ነው። በአጭሩ ንድራንጌታ ማፊያ አንድ ግዙፍ ቤተሰብ ማለት ነው። ፍንክች የለም።

አንድ ልጅ ከዚያ ጎሣ ሲወለድ ዕቃ ዕቃ ተብሎ የሚሰጠው ሽጉጥ መወልወል ነው። የ9 ዓመት አዳጊዎች ክላሽ ይሸከማሉ።

አንድ አዳጊ ልጅ የሰውን አንገት እንደ ዶሮ ቀጭቶ ማሰናበትን ያውቃሉ።

ንድራንጌታ ማፊያ አንድ ሙሉ መርከብ ኮኬይን አስጭኖ ጣሊያን የሚያስገባበት ጊዜም አለ። ይህ የሚሆነው ቡድኑ እስከ ትልልቅ ባለሥልጣናት ድረስ እጁ ረዥም ስለሆነ ነው።

ይህን ሂደት ያደናቀፈ ደግሞ በአጭር ይቀጫል።

ንድራንጌታ አንድ ጎሣ ነው ቢባልም ግን በውስጡ ራሳቸውን የቻሉ ንዑስ ጎሣዎች የሉም ማለት አይደለም።

ይሁንና አንዱ በአንዱ ላይ ግን በፍጹም አይነሳም።

ካርታ

ነጫጭ ‘ጻድቃን ወንጀለኞች’

በዚህ ጎሣ ውስጥ ማዕረግ አለ። ‘ላ ሳንታ’ ይባላል። ቅዱስ እንደማለት ነው። ይህ ማዕረግ የተሰጣቸው ሰዎች በቀጥታ በወንጀሎች ውስጥ እጃቸውን አያስገቡም።

የላ ሳንታዎች ተግባር ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መደራደር እና የ‘ዲፕሎማሲ’ ሥራ መሥራት ነው።

ይህን ቅዱሳን ወንጀለኞች (White collar crime) ብለው ይጠሯቸዋል።

ላ ሳንታዎች የፖለቲካ ምርጫዎች ሲቃረቡ የሚፈልጉት ሰው ድምጽ እንዲያገኝ የማግባባት፤ በገንዘብ፣ በምሥጢር የመደገፍ ሥራዎችን ተግተው ያከናውናሉ።

ቅዱሳን ወንጀለኞች በተራ የኮኬን ማዘዋወር፤ ወይም አፍኖ የመግደል ‘ልክስክስ’ የሚባሉ ወንጀሎች ላይ ፈጽሞ አይሰማሩም።

ምናልባት በወንጀል የተገኘን ቢሊዮን ዶላር በማጠብ ሕጋዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ሥራዎችን ለማከናወን ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሊጓዙ ይችሉ ይሆናል።

የሚገርመው ደቡባዊ ጣሊያን ካላብሪያ በጣም ድሃ የሚባለው የጣሊያን ክፍል ነው።

ይህ አካባቢ የጣሊያን ጭርንቁሱ ሰፈር ነው።

ነገር ግን በዚህ ግዛት የሚገኘው ንድራንጌታ የማፊያ ቡድን በዓመት 60 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገባል።

ይህ ገንዘብ መጠን እንደ ኮሪያን የመሰሉ አገሮች ዓመታዊ ጥቅል ምርትን (GDP) ይስተካከላል።

ንድራንጌታ ማፊያው የጣሊያን ጎሣ የአውሮፓን 80 ከመቶ የኮኬይን ንግድ ይቆጣጠራል።

ይህን ግዙፍ ዓለም አቀፍ የአደገኛ ወሮበሎች ቡድን ከሚፋለመው ዐቃቤ ሕግ ኒኮላ ግራቴሪ ጋር ነው አሁን ያለነው።

ካርታ

“አንድ ቢሊዮን ዶላር ምን አላት?”

ዐቃቤ ሕግ ግራቴሪ ወደዚህ ካላብሪያ ግዛት ተራራዎች ይዞን ነጎደ።

ከፊትና ከኋላ ከፍተኛ ጥበቃ ተደርጎለት ነው የሚንቀሳቀሰው።

“በማንኛውም ሰዓት እንደምሞት ስለማውቅ ከሞት ጋር ቁጭ ብዬ አወራለሁ፤ ሞትን መለማመድ አለብኝ” አለ።

ይህ አካባቢ ድህነት ድምጽ አውጥቶ የሚጮኽበት ይመስላል። በፍጹም 60 ቢሊዮን ዶላር የሚያስገባ ጎሣ የሚኖርበት አይመስልም።

እያንዳንዱ ማፊያ በደም እና በቤተሰብ የተሳሰረ በመሆኑ ፈተና ነው።

ታማኝነቱ እስከ ጥግ ነው። በቤተሰብ ኮኬይን የማይነግድ የለም። አብዛኛው ኮኬይን በቅርብ በሚገኘው ጊዮ ታውሮ ወደብ የሚራገፍ ነው።

ዕጹ ከኮሎምቢያ ነው በብዛት የሚነሳው። ዐቃቢ ሕጉ እዚያ ወስዶ ፍተሻውን አሳየን። ከኮቪድ ያልተናነሰ ፍተሻ በእያንዳንዱ ከመርከብ በሚራገፍ ካርቶን ጥቅል ላይ ምርመራ ይደረጋል።

ምርመራው ላብራቶሪ እና አነፍናፊ ውሾችን እንዲሁም በሺህ የሚቆጠሩ ፖሊሶችን ያሳተፈ ነው።

መርፌ የምታልፍ አይመስልም ከዚህ ፍተሻ። የንግራጌታ ማፊያዎች ኮኬይን ግን ያልፋል። እንዴት ለሚለው መልስ ያለው የለም።

ኮኬይን ብቻም ሳይሆን ወደ ሩሲያ የሚሄድ እና ከሩሲያ የሚወጣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ንግድም በዚህ የማፊያ ቡድን በኩል በዚሁ ግዙፍ ወደብ ተጭኖ ያልፋል።

እንዴት ለሚለው ግን አሁንም መልስ ያለው የለም።

በቅርቡ 7 ቶን የሚመዝን ኮኬይን በዚሁ ወደብ ተይዞ ዓለም ጉድ ሲል ነበር። ሰባት ቶን ኮኬይን ምን አላት? 1 ቢሊዮን ዶላር ብታወጣ ነው። ይህ ደግሞ ለንድራንጌታ ማፊያ እዚህ ግባ የሚባል ገንዘብ ላይሆን ይችላል።

ቦናቬንቱራ ከማፊያው ቡድኑ ሾልከው ከወጡ ጥቂት ጣሊያናዊያን አንዱ ነው
የምስሉ መግለጫ, ቦናቬንቱራ ከማፊያው ቡድኑ ሾልከው ከወጡ ጥቂት ጣሊያናዊያን አንዱ ነው

‘በ9 ዓመቴ ሽጉጥ እወለውል ነበር’

ከዚህ ጎሣ ወጥተው በማፊያው ቡድን የሚመሰክሩ ከስንት አንድ ጊዜ ይገኛሉ። ይህ በምስሉ የምትመለከቱት ፊቱን የሸፈነ ሰው ቤናቬቱራ ይባላል።

ሰሜን ጣሊያን ውስጥ በድብቅ ቢቢሲን ለማግኘት ፈቅዶ ተገናኘን።

ከ16 ዓመት በፊት ጀምሮ ከፖሊስ ጋር ተባብሮ ቡድኑ ውስጥ ሳለ ያውቃቸው የነበሩ መረጃዎችን አቀብሏል።

ከዚያ ወዲህ እንዳይገደል በምሥጢራዊ ቦታ ጥበቃ እየተደረገለት ነው የሚኖረው።

“ንድራጌታ ማለት በቃ አንድ ጎሣ ነው። ከዚያ ጎሣ መወለድ በራሱ ማፊያ ሆኖ መወለድ ማለት ነው ይላል። ግደል-ግደል-ግደል የሚል ዜማ እየሰማህ ነው የምታድገው” ይላል።

በ9 እና 10 ዓመቴ ዕቃ ዕቃ እጫወት የነበረው በጦር መሣሪያዎች ነበር። ብዙ ውንብድናዎች ውስጥ ተሳትፊያለሁ፤ ገድያለሁ ይህ ምንም አስደናቂ ነገር አይደለም ይላል።

አሁን በእርሱ ምስክርነት በመቶዎች የሚቆጠሩ የማፊያው አባላት ታድነው ለፍርድ ቆመዋል።

የእርሱ ሕይወትም በሞት እና በመኖር ውስጥ ትዋልላለች። ትክክል የሆነውን ነገር አድርጌ ልሙት ብሎ ነው እዚህ አደገኛ ነገር ውስጥ የገባው።

የዐቃቤ ሕጉም ሕይወት እንዲያ ነው። መሞቴ ካልቀረ ለልጆቼ ሰላማዊ አገር ለምን አላወርስም ብሎ ነው የገባበት።

የሚጸጽትህ ነገር አለ ወይ? ብለን ዐቃቤ ሕጉ ኒኮላ ግራቴሪን ጠየቅነው።

“የሚጸጽተኝ ከዚህም በላይ ይህን ማፊያ ቡድን መታገል አለመቻሌ ነው፤ በዚህ ምድር ላይ ዋጋ የማያስከፍል ምን ነገር አለ?”

ይህን ብሎን ድንገት ስልኩ ጠራ። ድንገት ተቅበዘበዘ።

“ውጡልኝ ውጡልኝ! አሁኑኑ ከዚህ መልቀቅ አለብን፤ ከቆየን አደጋ ነው” ብሎን ተንደረደረ።

ይህ የየዕለት ሕይወቱ ነው።