ለሰላሳ ዓመታት ሲፈለግ የነበረው የጣሊያን ማፊያ ቡድን መሪ ክሊኒክ ውስጥ ተያዘ

ማቴዎ ማሲኒ ዲናሮ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ማቴዎ ማሲኒ ዲናሮ በተያዘበት ጊዜ

ለሦስት አስርት ዓመታት ሲታደን የቆየው የጣሊያን ተፈላጊ የማፊያዎች አለቃ ማቴዎ ማሲኒ ዲናሮ ሲሲሊ ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ።

በጣም የሚፈራው ኮሳ ኖስትራ የማፊያ ቡድን አለቃ እንደሆነ የሚታመነው ማቴዎ ማሲኒ ዲናሮ የተያዘው በጣሊያኗ ግዛት ሲሲሊ ዋና ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የግል ክሊኒክ ውስጥ እንደሆነ ተዘግቧል።

የጣሊያን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ለሰላሳ ዓመታት ሲፈለግ የነበረው ግለሰብ በክሊኒኩ ውስጥ ህክምና ሲደረግለት በነበረበት ጊዜ በፖሊስ ተይዞ ወደ አንድ ምስጢራዊ ስፍራ ተወስዷል።

ማቴዎ ማሲኒ ዲናሮ ቀደም ሲል ከበርካታ የግድያ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ በሌለበት ክስ ተመስርቶበት የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

ከተከሰሰባቸው ወንጀሎች መካከልም በ1992 (እአአ) ፀረ ማፊያ ዐቃቢያነ ሕግ የነበሩትን የጂዮቫኒ ፋልኮኔ እና የፓውሎ ቦርሴሊኖ ግድያዎች ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም በ1993 ሚላን፣ ፍሎረንስ እና ሮም ውስጥ የሰው ነፍስ ባጠፉ የቦምብ ጥቃቶች እና ከማፊያ ቡድን አፈንግጦ ምስክር የሆነ ግለሰብ 11 ዓመት ልጅ ላይ ለተፈጸመ አፈና፣ ማሰቃየት እና ግድያ ይገኙበታል።

ማቴዎ ማሲኒ ዲናሮ በኮሳ ኖስትራ ቡድኑ አማካይነት ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ ማድረግ እና የዕጽ ዝውውርን ጨምሮ በርካታ ከባድ ወንጀሎችን በበላይነት በመምራት አስፈጽሟል ተብሎ ይታመናል።

ምንም እንኳን ማቴዎ ማሲኒ ዲናሮ ከ1993 (እአአ) ጀምሮ ከፖሊስ ተደብቆ የቆየ ቢሆንም፣ ካልታወቀ ቦታ ሆኖ ትዕዛዝ በመስጠት እስካሁንም ድረስ ተከታዮቹ ሲመራ እንደቆየ ይታመናል።

የግለሰቡን መያዝ ተከትሎ የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ “የማፊያ የወንጀል ቡድን ዋነኛ አባል” የሆነውን በቁጥጥር ስር በማዋላቸው የአገሪቱን ጦር ሠራዊት አመስግነው “ይህም ለአገሪቱ ታላቅ ድል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።