ለብዙዎች የሳቅ ምንጭ የነበረው ነጻነት ወርቅነህ ሲታወስ

ነጻነት ወርቅነህ

የፎቶው ባለመብት, sm

ነጻነት ወርቅነህ በተለይም በአስቂኝ ፊልም እና ቴአትር ዘርፍ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ ተዋንያን አንዱ ነበር።

'ጥርስ አያስከድኑም' ከሚባሉ ጨዋታ አዋቂ የቴሌቪዥን መሰናዶ አቅራቢዎች መካከልም ይጠቀሳል።

'ኤፍቢአይ'፣ 'ባለቀለም ሕልሞች' እና 'ያንቺው ሌባ'ን ጨምሮ በሌሎችም አስቂኝ ፊልሞች እንዲሁም እንደ 'ፍሬሽማን' ባሉ አዝናኝ ተውኔቶች የሚታወቀው ነጻነት ባደረበት ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ነጻነት ተወዳጅ የሆነው እና በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው 'የቤተሰብ ጨዋታ' አዘጋጅ እና አቅራቢ ነበር።

ተወዳዳሪዎችን በሚጠይቀው አስቂኝ ጥያቄ እንዲሁም ጣል በሚያደርጋቸው አዝናኝ የስላቅ አስተያየቶች ይታወሳል።

ነጻነት በቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችም ዝነኛ ነበር።

'ፈጣኑ' ነጻነት

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የቴአትር ባለሙያው ተባባሪ ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ነጻነትን የሚያውቁት ከ1990ዎቹ አንስቶ ነው። ያኔ 20 ዓመት ቢሆነው ነው።

የ1980ዎቹ መጨረሻ እና 1990ዎቹ አዲስ አበባ ውስጥ የአማተር እንቅስቃሴ በጣም የተስፋፋበት እንደነበር ያስታውሳሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቄራ አካባቢ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ) እና ሰለሞን ቦጋለ፤ መርካቶ አካባቢ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና አብነት አጎናፍር. . . በኪነ ጥበብ እንቅስቃሴ ይታወቃሉ።

ወደ አገር ፍቅር እና ገዳም ሰፈር አካባቢ ስማቸው ከሚጠራው መካከል ደግሞ ነብዩ እና ነጻነት ይገኙበታል።

በዘመኑ በጣም ብዙ ወጣቶች ወደ ቴአትር ይገቡ ነበር። የኪነ ጥበብ ክበባትም ብዙ ነበሩ።

በትወና፣ በጽሑፍ እና በዝግጅት ስመ ጥር ባለሙያዎች መነሻቸውም ይሄ ነው።

ከእነዚያ ወጣቶች ውስጥ "በጣም ፈጣን" እና በተለይ ለኮሜድ ሥራዎች "እጅግ ከፍ ያለ ስጦታ ያለው" ነጻነት እንደነበር ያስታውሳሉ።

በ1993 ዓ. ም. እሳቸው የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳሉ ነጻነት 'ማክሲ ሚዲያ ኢንተርፕራይዝ' በሚባል ክበብ ቴአትር ሲሠለጥን አግኝተውታል። የያኔው የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነብዩ አሠልጣኝ ሆነው ነበር የሄዱት።

"የበለጠ ሙያውን እያዳበረ፣ ብዙ እየታተረ ነበር ያገኘሁት" ይላሉ።

ከዚያ በኋላም በሥራ አልፎ አልፎ ይገናኛሉ። ነጻነትን የሚገልጹት "ፈጣን አእምሮ ያለው" ብለው ነው።

ይህ ፈጣንነት ደግሞ ለኮሜዲ ሥራ አንዱ መሠረታዊ ነገር ነው።

"የኮሜዲ ሥራ ፈጣን አእምሮ እና የፈጠራ ችሎታ ይፈልጋል" ይላሉ የቴአትር ባለሙያው።

ድንገቴ ፈጠራ ኮሜዲ (Improvisation) ከሚሠሩ ባለሙያዎች መካከል ነጥረው የሚወጡት ፈጣን አእምሮ ያላቸው ናቸው።

ነጻነት ወርቅነህን ለረጅም ጊዜ ከሚያውቁት እና አብረውት ከሠሩት መካከል አንዷ የሆነችው ደራሲ እና አዘጋጅ መዓዛ ወርቁ በተለያዩ የመድረክ፣ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ሥራዎች ላይ በሚያሳየው "ተፈጥሯዊ የትወና ብቃት" ከፍ ያለ አድናቆት እንዳላት ትገናራለች።

"ኪነ ጥበብን በማንኛውም መንገድ ቢሠራ አሳምሮ እና አሳድጎ የሚሠራ ለየት ያለ ተሰጥኦ ያለው ተዋናይ እንደነበር የሚያውቀው ሁሉ የሚመሰክርለት ነው።"

ነጻነት በሥራው ላይ በምንም ዓይነት የዲስፕሊን ችግርየማይታማ፣ ለቡድን ሥራ የተመቸ ስኬታማ ባለሙያ ነው ትላለች መዓዛ።

አክላም "ሥራ ቀለል ብሎ እንዲሠራ የሚያግዝ፤ በዕድል ወይም በአጋጣሚ ስም ያገኘ ሳይሆን ለፍቶ ጥሮ ወድቆ ተነስቶ ትልቅ ስም እና ማንነትን የተከለ ታታሪ ሙያተኛ ነው" ስትል የነጻነት ስኬት ምን ያህል በጥረት መጣ እንደሆነ ተናግራለች።

ነጻነት ወርቅነህ

የፎቶው ባለመብት, sm

ድንገቴ ፈጠራ የኮሜዲያንን የአእምሮ ፍጥነት እና ስል መሆን ያሳያል። ለዚህም እንደ ምሳሌ ኮሜዲያኖቹን ትሬቨር ኖዋ እና ማክስ ሀሚኒ ይጠቅሳሉ።

ፍጥነት ብቻ ሳይሆን በፍጥነት መናገር የሚፈልጉትን ወይም ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልዕክት ማድረስ ይጠይቃል።

በዚህም ነጻነት የተካነ ሙያተኛ ነበር።

"በጣም ለዛ ያለው፣ በጣም ወዝ ያለው ሲሆን ያ ሰው ከሁሉም መጥቆ ይወጣል" የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ለዚህ ማሳያ ነጻነትን ይጠቅሳሉ።

ነጻነት መድረክ ሲመራም ይሁን ፊልም ወይም ቴአትር ላይ ሲተውን ችሎታው ጎልቶ ይታያል።

ብዙዎች 'ስንመለከተው ደስ ይለናል' በማለት አስቂኝነቱ ብቻ ቢታያቸውም "የአእምሮው ስለት እና ብስለት" ብዙ ሊባልለት እንደሚገባ ባለሙያው ያስረዳሉ።

". . . ትልቁ ችሎታው የአእምሮ ፍጥነት ነው። አእምሮ ሲፈጥን አንደበት አብሮ ከተሰናኘ፣ የቋንቋ ችሎታ አብሮ ከተቀናጀ፣ ለዛ እና ወዝ አብሮ የሚሄድ ከሆነ ያ ሰው የተዋጣላት ኮሜዲያን ነው።"

ነጻነትን የሚገልጹት ሐሳቦች የማያልቁበት፣ ቃላት የሚታዘዝለት፣ አእምሮው በፍጥነት ሁሉም የሚገዛለት ብለው ነው።

በተለይ ደግሞ ነጻነት ስታንድ አፕ ኮሜዲ እና ቴአትርን የማዋሀድ ቅርጽ እንዳመጣ ይናገራሉ።

"መድረክን መግዛት የሚችል፣ ተመልካቾች ፊት ወጥቶ አሸንፎ የሚፈልገውን አሳክቶ የሚወርድ ሰው ነበር" ሲሉም ያሞካሹታል።

አንድ ባለሙያ ለብቻው በይዘት ስብጥር እና ተለዋዋጭነት እንዲሁም በማሳቅ መድረክ በመያዝ ረገድም ነጻነት ታሪክ ለዋጭ እንደሆነ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ነጻነት ለብቻው መድረክን እያዝናና በመቆጣጠር ያለው ችሎታ 'ፍሬሽ ማን' ቴአትር ላይ ጎልቶ እንደወጣ እና በስታንድ አፕ ኮሜዲ ያመጣው ለውጥ እንደ እሸቱ መለሰ ያሉ ኮሜዲያኖችን እንዳፈራ ረዳት ፕሮፌሰሩ ያክላሉ።

እነ አውላቸው ደጀኔ፣ ተስፋዬ ሳህሉ እና አበራ ደስታ በተውኔት ውስጥ የኮሜዲ ሥራቸው እንደታወቀ በመጥቀስ፤ ነጻነት ግን ብቻውን መድረክ በመቆጣጠር 'የታሪክ እጥፋት' እንዳመጣ ይገልጻሉ።

ትሁቱ ነጻነት

"በጣም ትሁት ሰው ነው" በማለት ረዳት ፕሮፌሰሩ የነጻነትን ስብእና ይገልጹታል።

መድረክ ላይ ፈጠራ የተሞላቸው ባለሙያዎች ከመድረክ በታች አስተዋይ፣ አዳማጭ፣ ሰው አክባሪ እንደሚሆኑ ማሳያው ነጻነት ነው ብለው ያምናሉ።

"ሰው ካለፈ. . . እንደሚባለው ሳይሆን እውነቱን ነው የምናገረው፤ በጣም ሰው አክባሪ፣ በጣም ትሁት፣ አስተዋይ ነው። መድረክ ላይ የሚጠቅመውን ነገር የሚያገኘው በማስተዋል፣ በማዳመጥ እና በመጠየቅ ነው።"

ባህሪው፤ ታዋቂ ስለሆነ ሰዎች 'እንዲሸሹት' የሚያደርግ ሳይሆን ወደ እሱ የሚያቀርብ እንደሆነ ይመሰክራሉ።

"ሰፈር ውስጥም ሰፊ መድረክ ላይም፤ አንድ ሰውም ቢያገኝ ሺህ ሰው ቢኖርም፤ ትሁት ነው። መተናነስ፣ ሰው ማክበር፣ አዳዲስ ነገር መማር አይበት ነበር" ይላሉ።

"ለልጆቻችን እንደ አጎታቸው ዓይነት ሆኖ በቴቭዥን የምናየው ሰው ነበር። በኢትዮጵያውያን የጋራ እዝነ ልቦና፣ በጋራ ዕሳቤ ውስጥ ቦታ ያለው ሰው ነው" ሲሉም አክለዋል።

ነጻነት ለሙያው ታታሪ እንደነበር ሳይጠቅሱ አያልፉም። ፈጣሪ የሰጠውን ዕድሜ በአግባቡ እንደተጠቀመበት ያምናሉ።

"ብዙ ትዝታ፣ ብዙ የጥበብ ውጤት በአጭር ጊዜ ሰጥቶ የሄደ ሰው ነው" ይላሉ።

ነጻነት ለሙያው የነበረውን ተቆርቋሪነት በተመለከተ መዓዛ ወርቁ በ2004 ዓ.ም. የግል የቲያትር ሠሪዎች በቲያትር መግቢያ ዋጋ ላይ ባካሄዱት ትግል ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ "የሙያው ተቆርቋሪ ነው" ስትል ገልጻዋለች።

ከነጻነት ተወዳጀ ሥራዎች መካከል አንዱ የሆነው እና በ2000 ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ ወደ መድረክ ያመጣው "ፍሬሽማን" ቲያትሩ ረጅም ጊዜ በሙሉ አዳራሽ ከመታየቱ በተጨማሪ መነጋገሪያ የነበረ ነው።

ፍሬሽማን ቲያትር የነጻነት ድርሰት እና ዝግጅት ሲሆን በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከመታየቱ በተጨማሪ "እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እያረፈ ወደ መድረክ የሚመለስ ተመልካችን ወደ ቲያትር ቤት የሚመልስ ተወዳጅ ሥራው ነው" ስትል ደራሲ እና አዘጋጀ መዓዛ ያላትን አድናቆት ትገልለጻች።

ለነጻነት በሙያው ስኬት እንዲያገኝ ካደረጉት ነገሮች መካከል ለሁሉም ነገሮች እራሱን ቅርብ ለማድረግ ያለው ፍላጎት እና ጥረት መሆኑን የምትናገረው መዓዛ፤ የነጻነት ህልፈት በእጅጉ አሳዝኗታል።

"እኔ ሳውቀው ነጻነት ለሕዝብ፣ ለሚዲያ፣ ለዓለም አቀፍ መረጃ እና ለንባብ የቀረበ ነበር። ይሄ ደግሞ ካለው የተፈጥሮ ፈጣን አሳቢነት ላይ የተሟላ ሰብእና እና በማንኛውም ጉዳይ ላይ የተሻለ መረዳት እንዲኖረው አድርጓል። ለሥራውም የማይነጥፍ ግብአት እንዲኖረው አግዞታል።"

ነጻነት ወርቅነህ

የፎቶው ባለመብት, SM

በወጣትነት ወደ ጥበብ የተሳበው ነጻነት

አዲስ አበባ፣ ኡራኤል አከባቢ በ1975 ዓ.ም. የተወለደው ነጻነት ወደ ቴአትር የገባው በለጋ ዕድሜው ነበር።

ተዋናይ፣ ኮሜዲያን፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢ ነጻነት በኢትዮጵያ የፊልም፣ ቴአትር እና የቴሌቭዥን መሰናዶ ታሪክ ጉልህ ሚና አለው።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ የራሱን ቴአትር በመጻፍ እና ሴት ገጸ ባህሪ ወከሎ በመተወን የመምህራኑን ትኩረት እንዳገኘ ይነገርለታል። በተለይ የአማርኛ አስተማሪው ያበረታቱት እንደነበር በሰጣቸው ቃለ ምልልሶች ተናግሯል።

በኢቢኤስ ቴሌቭዥን ላይ "የቤተሰብ ጨዋታ" አቅራቢ ሳለ መሰናዶው ከፍተኛ አድናቆት ያለው እና ተወዳጅ እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል።

ኢቢኤስ ቴሌቭዥንም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አርቲስቱ ባደረበት ሕመም በድንገት ሕይወቱ ማለፉን ገልጾ ኅልፈት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በኅልፈቱ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው "ነጻነት በተለይም በሕዳሴ ግድብ በተዘጋጀው የ2016 አዲስ ዓመት የመቀበያ ፕሮግራም የነበረውን አስተዋጽዖ ሁሌም አስታውሰዋለሁ" በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም ነጻነት የመራው እና እሳቸውም የታደሙበትን የአዲስ ዓመት ዝግጅትን በማስታወስ "ሁላችንም አዲሱን ዓመት በደስታ እንድንቀበል አድርጎን ነበር። ለቤተሰቦቹ እና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን እመኛለሁ" ብለዋል።

የነጻነት ዜና እረፍት መሰማቱን ተከትሎ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ የሙያ ባልደረቦቹ እንዲሁም አድናቂዎቹ ከምሥሉ ጋር የሐዘን መግለጫዎችን እያጋሩ ነው።

ነጻነት ባለ ትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነው።

አስከ ሐሙስ ጥር 7/2018 ዓ.ም. ድረስ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ባልደረቦቹ የተናገሩ ሲሆን፣ ነገር ግን አርብ ጠዋት ድንገተኛ ሕመም ተሰምቶት ወደ ሆስፒታል ከሄደ በኋላ ዕኩለ ቀን አካባቢ ማረፉን ጓደኞቹ ተናግረዋል።

የነጻነት ወርቅነህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ቤተሰቦቹ፣ የሙያ ባልደረቦቹ እና አድናቂዎቹ በሚገኙበት በአዲስ አበባው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም እየተነገረ ነው።