ሁለገቡ የጥበብ ሰው ደበበ እሸቱ በጥበብ እና በፖለቲካ አጋሮቹ ሲታወስ

ደበበ እሸቱ

ሁለገቡ የጥበብ ሰው ደበበ እሸቱ እሁድ ነሐሴ 11/2017 ዓ.ም. በ83 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

በ1934 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ የተወለደው ተዋናይ፣ አዘጋጅ፣ ተርጓሚ እና ጋዜጠኛ የነበረው ደበበ እሸቱ ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ ጉልህ አሻራውን አሳርፏል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ ከ40 በላይ ተውኔቶች ላይ የተሳተፈ ሲሆን፣ በፊልም ሥራው ውስጥ በኢትዮጵያውያን የተዘጋጁትን ጨምሮ ከአገር ውጪ በሚገኙ ባለሙያዎች የተደረሱ እና ዳይሬክት በተደረጉ ፊልሞች ላይ ተሳትፏል።

ከእነዚህም መካከል "ሻፍት ኢን አፍሪካ"፣ "ዘ አፍሪካን ስፓይ"፣ "ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብላርተር" የመሳሰሉ ፊልሞች ተጠቃሾች ናቸው።

በተጨማሪም የተዋናይ ሀሁ፣ የባሩድ በርሜል፣ ድብልቅልቅ የመድረክ ተውኔት የተሰኙ እና ሌሎች ሥራዎችንም ተርጉሞ ለንባብ አብቅቷል።

ለረዥም ጊዜ በተለያዩ መድረኮች አብሮት የሠራው ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ ደበበን ሲያስታውሰው "የኪነጥበብ ሕይወታችን ለውጭው ዓለም ካስተዋወቁልን የጥበብ ሰዎች መካከል አንዱ" ይለዋል።

በምርጫ 97 ዋነኛ የፖለቲካ ተፎካካሪ የነበረው ቅንጅት ለአንድነት ለዲሞክራሲ ፓርቲ ውስጥ አባል የነበረችው እና አብራው የተለያዩ የፖለቲካ ሥራዎችን የሠራችው ብርቱካን ሚደቅሳ ደግሞ "ፖለቲካን ከተለመደው መልኩ በተለየ መንገድ መሥራት የቻለ" ስትል ያላትን አክብሮት ትገልጻለች።

ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ፤ ደበበ እሸቱ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ ስላበረከታቸው አስተወጽፆዎች ሲናገር "ደበበ በአንድ መስክ ብቻ የሚመደብ ሰው አይደለም" በማለት ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተለያዩ የኪነ ጥበብ ዘርፎች፣ በፖለቲካውም መስክ ውጤታማ እና ተጠቃሽ ሥራዎቸን መሥራቱን ያስታወሰው ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ "ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ካፈራቻቸው ዘመናዊ ተብለው ከሚነሱ የጥበብ ሰዎች መካከል የሚጠቀስ ሁለገብ ባለሙያ ነው" ይላል።

በቅንጅት ፓርቲ ውስጥ አብራው የሠራችው ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩሏ በፖለቲካ ሥራ ውስጥ "ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከወጣቶችም ጋር ተባብሮ በመሥራት ችሎታው አስታውሰዋለሁ" ትላለች።

አያልነህ፣ ደበበ በዘመናዊ ኪነ ጥበብ ውስጥ መሠረት ጥሎ ማለፉን ገልጾ "በቴአትር እና በፊልሞች ላይ በመተወን እንዲሁም ሌሎች የጥበብ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም የአገር ፍቅርን በሕዝብ ላይ በማሳረፍ ማንም የጥበብ ሰው የማይደፍረው የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ገብቶ የሠራ" ሲል ገልጾታል።

ኢትዮጵያን በፖለቲካው መስክ ለማገልገል መወሰኑን በተመለከተ ሲናገርም "ከጥበብ ጋር አቆራኝቶ" በማቅረብ እና በወሰደው ደፋር እርምጃ እንደሚያደንቀው ይናገራል።

ወደ ፖለቲካው ገብቶ የነበረው ደበበ በ1995 ዓ.ም. ቀስተ ደመና ፓርቲን ተቀላቅሎ የነበረ ሲሆን፤ በኋላም ቅንጅት ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት በመሆን አገልግሏል።

በዚህ በ1997 በተካሄደው አወዛጋቢ እና ደም አፋሳሽ ምርጫ ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ ቆይቷል። ከዚያም በኋላ ከሕገወጥ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አለው በሚል ለእስር ተዳርጎ ነበር።

የቅንጅት እና የቀስተዳመና ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ደርቦ ይሠራ እንደነበር የምታስታውሰው ብርቱካን ሚደቅሳ ከበድ ያሉ ኃላፊነቶችን ለመወጣት የተሰጠ ሰው ነበር ትላለች።

"በእንቅስቃሴዎች ሁሉ ነገሮችን ቀለል አድርጎ መያዝ፤ በጣም አስቸጋሪ እና አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ በነበርንበት ወቅት ሁሉ በሳቅ በፈገግታ፣ ከሁሉም ጋር በመጫወት፣ በመግባባት ሁሉንም ነገር በጣም ቀለል ያደርግልን ነበር።"

በኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ የኪነጥበብ ሥራዎች "የአገር ውስጥ ፍጆታ" ሆነው ይቀራሉ የሚለው አያልነህ ሙላት፣ ኢትዮጵያን ለውጭው ዓለም ካስተዋወቁ እና የጥበብ ሥራዎች በዚህ አገር እንደሚሠሩ ካሳዩ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ነበር ብሏል።

አክሎም "ብዙ ታላላቅ ደራሲያን ወጥተዋል። በጣም በርካታ የሆኑ የጥብብ ሥራዎች ተሠርተዋል። ነገር ግን የውጪውን ክፍተታችንን የሞሉት በጣም ጥቂቶች ናቸው። የኪነ ጥበብ ሕይወታችን ለቀሪው ዓለም ምን ይመስላል የሚለውን ካስተዋወቁልን የጥበብ ሰዎች አንዱ ደበበ ነው።"

ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ፣ ደበበ ሙያውን ለወጣቶች በማካፈል ረገድ ስላበረከተው አስተዋጽኦ ሲናገር "ደበበ ያለውን ጥበብ ክህሎት ማጋራት የሚችል ጥሩ ባለሙያ ነው። ለነገ ብሎ የሚቆጥበው ነገር የለም። በነበረበት ዘመን ውስጥ ሁሉ ለወጣቱ የጥበብ ቅርሱን፣ ሕይወቱን ሁሉ ቁጭ ብሎ የሚያካፍል ሰው ሆኖ ነው ያገኘሁት" ብሏል።

ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩሏ የደበበ እሸቱን ፖለቲካዊ አስተዋጽኦ ስትጠቅስ ቅንጅት በምርጫ 97 በተመደበለት የአየር ሰዓት የሚያስተላልፋቸውን መልዕክቶች ታስታውሳለች።

"መልዕክቶቹ በዋናነት የፖለቲካ ፓርቲው ቢሆንም በቋሚነት የሚያቀርበው ግን ደበበ ነበር" በማለትም አይረሴ ሆነው ለመዝለቃቸው እና ፓርቲው በወቅቱ ፈጥሮት ለነበረው የፖለቲካ ድባብ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ትጠቅሳለች።

ለእነዚህ የፓርቲው መልዕክቶች መወደድ "እርሱ በጣም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል" ስትልም ታክላለች።

የፖለቲካ ሥራ በአብዛኛው ኮስታራ ፊት የሚታይበት መሆኑን የምትገልጸው ብርቱካን "እርሱ ግን ቀለል ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ሳቅ እና ጨዋታ የሚፈጥር ነበር" ስትል ፖለቲካን ከተለመደው መንገድ ውጪ የሚሠራ ነው ስትል ታስታውሰዋለች።

"ከእርሱ ጋር በመሥራቴ እንደ ጥሩ እድል ነው የምቆጥረው" የምትለው ብርቱካን፣ ከደበበ ጋር በነበራት የፖለቲካ ሥራ ቆይታ ጠቃሚ ነገሮችን እንደተማረች ትገልጻለች።

ሁለገቡ የጥበብ ሰው ደበበ እሸቱ በሕይወት ዘመኑ ለኪነ ጥበብ ላበረከታቸው አስተዋጽኦዎች የተለያዩ ሽልማቶችን ከአገር ውስጥ እና ከውጪ ተቀብሏል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ የአራት ልጆች አባት እና የስምንት የልጅ ልጆችን አያት ለመሆን በቅቷል።

በ83 ዓመቱ ሕይወቱ ያለፈው ደበበ እሸቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ድጋፉን በይፋ ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፣ ናይሮቢ ላይ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ "ነጻነቴን የሰጠኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ነው" ሲል ተናግሮ ነበር።

"ነፃነቴን የሰጠኝ [ጠቅላይ ሚንስትር] ዐቢይ ነው። ሌላ ማን ሰጠኝ? ዶ/ር ዐቢይ ነው በነፃነት የመናገር መብቴን የመለሰልኝ። ዶ/ር ዐቢይ ነው ቤተ መንግሥት ያስገባኝ። ዶ/ር ዐቢይ ነው ፕሮግራም ምራልኝ ያለኝ። ከመሸማቀቅና ማን አየኝ ከሚል መሳቀቅና መገላመጥ ያወጣኝ ዶ/ር ዐቢይ ነው። ስለዚህ ያደላሁት ወደ መንግሥት ሳይሆን ወደ ዶ/ር ዐቢይ ነው። ለእሱ ደግሞ መልሴ ደግ አደረኩ ነው።"

የተዋናይ፣ አዘጋጅ፣ ተርጓሚ፣ ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ ደበበ እሸቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ምክሰኞ ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም. ይፈጸማል።