የሥራዎቼ ማጠንጠኛ ጭብጦች ፍትሐዊነት እና ሰብዓዊነት ናቸው - የእመጌቶች ደራሲ መዓዛ ወርቁ

ፀሐፌ ተውኔት እና አዘጋጅ መዓዛ ወርቁ

የፎቶው ባለመብት, Meaza Worku

የምስሉ መግለጫ, ፀሐፌ ተውኔት እና አዘጋጅ መዓዛ ወርቁ

የኢትዮጵያ የቴአትር ሰማይ ላይ ተሰይመው ለየዘመናቸው የሚያበሩ ደማቅ ሴት ኮከብ ተዋንያንን ማግኘት ብዙ የሚቸግር አይደለም።

ከትወናው ውጪ ባሉ የዘርፉ ሙያዎች ላይ ግን ወንዶች አብላጫውን ወስደዋል ብንል ግን ዋሾ አያስብለንም።

አስተዳደሩም፣ አዘጋጅነቱም፣ ድርሰቱም ላይ በብዛት የምንጠቅሰው ስም የእነርሱን ነው።

የስንዱ ገብሩን ፈር ተከትለው ወጥ የተውኔት ጽሑፍ ያበረከቱልን ሴቶች የአንድ እጅ ጣቶችን እንኳ አይሞሉም።

በዝግጅቱ ዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ ዓለምፀሐይ በቀለ፣ ጀማነሽ ሰለሞን፣ መንበረ ታደሰን እንጠራ ይሆናል። በትርጉም ተውኔቶች ደግሞ አዜብ ወርቁ ከፊት ብቻዋን ትሰለፋለች።

በወጥ የተውኔት ጽሑፍ ስንመጣ ግን ከባዩሽ ዓለማየሁ፣ ከትዕግሥት ዓለሙ እና ከእታፈራሁ ኃይሉ ሌላ የምንጠቀውሰው የዛሬ እንግዳችንን መዓዛ ወርቁን ነው።

በዚህ ማጣት መካከል በወጥ የተውኔት ድርሰት ለዘመናችን ፀሐይ ሆና ብቅ ያለችው መዓዛ ወርቁ "እመጌቶች" የተሰኘ ተውኔቷን በሃያት ሬጀንሲ ፈንድቃ ለዕይታ አብቅታለች።

መዓዛ ወርቁ ቴአትርን ያጠናችው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል ነው።

እንደተመረቀች በሙሉ ዓለም የባህል ማዕከል ላይ ታየች። ቀጥላ በሜጋ የኪነ ጥበብ ማዕከል ሠርታለች። ከዚያ በመቀጠል ደግሞ በመኩሪያ የቴአትር ስቱዲዮ ላይ መሠረቷን በመጣል የዛሬዋ መዓዛ ተገኘች።

መዓዛ ከተውኔት ድርሰት ሌላ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ድራማዎችን ጽፋለች። የተለያዩ የኮሚክ መጻህፍት ደርሳለች።

ተውኔቶቿን በእንግሊዝኛም ሆነ በአማርኛ የምትጽፈው መዓዛ፣ 'ክሮስ ሮድስ' የተሰኘው ሥራዋ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለመድረክ በቅቷል።

"ደርሶ መልስ"፣ "አላውቅም፤ አናውቅም"፣ የቴሌቪዥን ድርሰቶቿ ሲሆኑ፣ "አልጋ በአልጋ"፣ "ወፌ ቆመች" ደግሞ ተከታተይ የሬዲዮ ድራማዎቿ ናቸው።

ከብዕሯ አብራክ የተከፈሉት እና በቋንቋዋ ጥበብ ከተከወኑት ተውኔቶቿ መካከል ደግሞ "ከሰላምታ ጋር"፣ "ሼክስፔር ኢትዮጵያዊ ነው" እንዲሁም "እመጌቶች" ይጠቀሳሉ።

በእንግሊዝ አፍ ደግሞ "Cross Roads"፣ "By The River" እና "Desperate To Fight" የተሰኙ ሥራዎቸወን አበርክታለች።

መዓዛ በደርሶ መልስ ድራማ ከለዛ አዋርድ ሽልማት ስታገኝ፣ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲም በሁለገብ የኪነጥበብ ባለሙያነቷ እውቅና ሰጥቷታል።

የመዓዛ ወርቁ ድርሰት የሆነው ቴአትር ላይ ኤልሳቤጥ መላኩ እና ዓለማየሁ ታደሰ ሲተውኑ

የፎቶው ባለመብት, Meaza worku

የምስሉ መግለጫ, የመዓዛ ወርቁ ድርሰት የሆነው ቴአትር ላይ ኤልሳቤጥ መላኩ እና ዓለማየሁ ታደሰ ሲተውኑ

መዓዛ እና ስልቹነት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፀሐፌ ተውኔት መዓዛ ከልጅነቴ ጀምሮ ተመሳሳይ ለሆነ ነገር ስልቹ ነኝ ትላለች።

ለድግግሞሽ ትዕግስቷ እንደ ሸረሪት ድር የቀጠነች ናት።

እርሷ ይህንን ስትገልጸው "ውስጤ የሚቅበጠበጠው ማንነቴ ለድግግሞሽ ታካች ነው" በማለት ነው።

በዚህም የተነሳ "ተመሳሳይ ነገር አንዴ ከሠራሁ በኋላ ደግሜ መሥራት አልፈልግም። ተመሳሳይ ነገር መስማት አልፈልግም። ተመሳሳይ ነገር መጻፍ አልፈልግም። ተመሳሳይ የሆነ ልማድ ውስጥ መኖር አልፈልግም። በጣም ይሰለቸኛል" ትላለች።

መዓዛ ወርቁ ለተደጋገመ ማንነት ውስጧ በመታከት "ኡፍ" ይላል።

ሰው ትዕግሥት የላትም ሊል ይችላል "ለእኔ ግን ለፈጠራ፣ ሁልጊዜ አዳዲስ ነገር እንድፈልግ ያስገድደኛል። ስጽፍም የግድ አዲስ ነገር መሆን አለበት" ትላለች።

ወዳጇቿ እና የሥራ ባልደረቦቿም ይህንን ይመሰክሩላታል። ለአስራ አንድ ዓመታት አብራት የሠራችው የፕሮዳክሽን ባለሙያዋ መዓዛ ደንድር ወደ እርሷ የሚጎትታት፣ ደጋግሞ የሚያመጣት ነገር ይህ አዲስ ነገር ናፋቂነቷ "ያልተለመደ አካሄድ መምረጧ ነው" ትላለች።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ትምህርት ቤት መምህር የሆነው ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ብርሃኑም፣ መዓዛ ጭብጦችን የምታይባቸው ዓይኖች ሁሌም አዲስ ናቸው ካለ በኋላ "እርሷ ባታያቸው ኖሮ የሚቀሩብን ነገሮች ብዙ ነበሩ" ይላል።

ፀሐፌ ተውኔት መዓዛ ወርቁ ደግሞ "በፊት የሄድኩበትን ዓይነት መንገድ አልሄድም። ዓመታት ያወራሁት፣ ለዓመታት የጻፍኩት፣ ለዓመታት የሠራሁበትን መንገድ መከተል አንድ ቦታ ላይ የቀረሁ እና የረጋሁ ያህል ይሰማኛል። እና ቅብጥብጥ የሚል ውስጣዊ ማንነት ያለኝ ሰው ነኝ" ትላለች።

ይህ ግን ያለ ዋጋ እንዲሁ አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ የተገኘ አይደለም።

የተለመደው መንገድ ለሚጎረብጥው፣ የኖረው እና የፀናው ይትባሀል ያልተመቸው፣ የራሱን መስመር ለማስመር መፍጨርጨር አለበት።

ያኔ ደግሞ ከኖረው ስሪት፣ ባህል፣ ወግ ጋር መጋጨት ያስከትላል።

መዓዛም ይህ ገጥሟታል። ትግሏ ከእንዲህ ዓይነት በዕድሜ ብዛት ከኖረ፣ አላላውስ፣ አላሠራ ከሚል አስተሳሰብ ጋር መሆኑን ትገልጻለች።

በተለይ በኪነጥበብ ዓለም ከተለመደው መስመር ወጣ ያለ፣ አዲስ ነገር መሞከር፣ አዲስ ነገር ይዞ መምጣት አስቸጋሪ መሆኑን መዓዛ በሚገባ ጠንቅቃ ትረዳዋለች።

አዲስ ነገር እንሞክር ለሚሉ የሚከረቸመው በር፣ የሚጠቁረው ፊት፣ የሚሻክረው ድምጽ ብዙ ነው።

"ዘልማድ ወይንም ልማድን ያፀና አስተሳሰብ በጣም ነው የሚጣላኝ። ሁልጊዜም ከእርሱ በተቃራኒው ለመሄድ በማደርገው ጥረት ላይ እጋጫለሁ። ከሰዎችም፣ ከአስተሳሰቦች ጋርም እጋጫለሁ።"

አክላም በኪነጥበብ ሥራዎቿ ውስጥ ሁሉ "በተቃራኒው የመጎተት፣ ተመሳሳይ ነገር ውስጥ ተጎትቶ ለመግባት እና ከእርሱ የማምለጥ ግብግብ ውስጥ ነኝ" ትላለች።

ከፀናው ልማድ ወይንም ዘልማድ ጋር በመታገል እና አሸናፊ ሆኖ በመውጣት ውስጥ በርካታ የፈጠራ ሥራዎቿን አቅርባለች።

ላለፉት 20 ዓመታት በወዳጅነትም ሥራዎቿን በመከታተልም የምታውቃት ደራሲ አዜብ ወርቁ "የእርሷ ሥራዎች በመደጋገም ካሰለቹን ልማዶች ያወጡናል" ስትል ትገልጻቸዋለች።

መጀመሪያ ላይ ብዙዎች ለመቀበል የቸገራቸው ነገር ግን በኋላ ላይ እየተቀበሏት የመጡትን ስትገልጽ "ከጊዜ ብዛት ደግሞ ይህንን እየለመዱ፣ እያወቁ የመጡ ሰዎች በዙሪያዬ እየበዙ የመጡ ይመስለኛል" ትላለች።

መዓዛ ወርቁ እመጌቶች የተሰኘውን ተውኔቷን እያዘጋጀች

የፎቶው ባለመብት, Meaza worku

የምስሉ መግለጫ, መዓዛ ወርቁ እመጌቶች የተሰኘውን ተውኔቷን እያዘጋጀች

መዓዛ በሥራዎቿ መልስ የምትፈልግባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

መዓዛ በሥራዎቿ ደጋግሞ የኖረውን አስተሳሰብ መጠየቅ፣ መሞገት እንደምትፈልግ ትናገራለች።

ቴአትሮቿ ወይንም ተከታታይ የቴሌቪዥን እንዲሁም የሬዲዮ ድራማዎቿ ጭብጣቸው ወይም ያነሱት ጥያቄ "ሰብዓዊነት" መሆኑን ትናገራለች።

"የእኔ ማጠንጠኛ ነገሮች ሰብዓዊነት፣ ፍትሃዊነት ናቸው ።"

አክላም "ኢፍትሀዊነትን እቃወማለሁም፤ እጠይቃለሁም" የምትለው መዓዛ የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር፣ እርስ በርስ ባለው ግንኙነት፣ እርሰ በርስ ባለው የኃይል አሰላለፍ፣ አንዱ ለአንዱ የሰጠው ወይንም የነፈገው፣ ምቹ ያልሆነው ዓለም የፈጠረባቸውን መንገዶች በማንሳት ለምን? ስትል እንደምትጠይቅ ትናገራለች።

ይህ ደግሞ በአማርኛ በጻፈቻቸው ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝኛ ጽፋቸው በተለያዩ ቋንቋዎች ለመድረክ የቀረቡ ሥራዎቿ ላይም ይታያል።

በእንግሊዝኛ የተጻፉት ሁለት ድርሰቶቿ የሚያተኩሩት የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ነው።

የዓለም አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ባደረጓቸው የኮፕ ስብሰባዎች የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ትኩረት የሚያሻው ዓለም አቀፍ አጀንዳ እንዲሆን ተስማምተዋል።

እርሷም በ'አክሽን ፎር ክላይሜት ቼንጅ' በልዩ ግብዣ ተመርጣ በአውሮፓውያኑ 2017 እና 2019 በእንግሊዝኛ የጻፈቻቸው ሁለት ተውኔቶች ለዕይታ በቅተውላታል።

'ክሮስ ሮድስ' ለኮፕ 2017 እና 'ባይ ዘሪቨር' ደግሞ ለኮፕ 2019 ተጽፈው በ2020 በመጽሐፍ መልክ ታትመው ለንባብ በቅተዋል።

"የሰው ልጅ ምቹ በሆነ አካባቢ መኖር አለበት ስንል የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው" የምትለው መዓዛ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ባመጣው ችግር የተነሳ ቢሆንም ዓለም ለሰው ልጆች ምቹ አይደለችም በማለት ይህንኑ በድርሰቷ ለዓለም አገራት መሪዎች እና ውሳኔ ሰጪዎች አሳይታለች።

ለታላላቅ የዓለም አገራት መሪዎች፣ ለተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና ውሳኔ ሰጪዎች ለማስገንዘብ፣ ድምጽ ለማሰማት የተጻፉት 'ክሮስ ሮድ' እና 'ባይ ዘ ሪቨር' የተሰኙት ተውኔቶቿ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያ እና በሌሎች አገራት ለዕይታ በቅተዋል።

አረብኛን ጨምሮ በሌሎች የዓለም ቋንቋዎችም ተተርጉመውላታል።

"በማንኛወም የኪነጥበብ ሥራ የሚቀርብ ማንኛውም ጥያቄ ፖለቲካዊ መፍትሄ ነው ያለው ብዬ ነው የማምነው" የምትለው መዓዛ፤ በዚህ መልክም ያሉ ኢፍትሐዊነት እና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን ማንሳቷን ትናገራለች።

ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን በበኩሉ ስለ መዓዛ ሥራዎች ጭብጥ ሲናገር "መዓዛ ባትጽፋቸው ኖሮ ሊቀሩብን የነበሩ ናቸው" ይላል።

"'ከሰላምታ ጋር' እና 'እመጌቶችን' ብንመለከት በወንዶች ዘንድ በተለምዶ የማይነሱ ወሳኝ ጥያቄዎችን ነው ያነሳችው።"

የ'ከሰላምታ ጋር' ቴአትር ዋና ገፀ ባህሪዋ ማርታ በትዳር ጉዳይ በራሷ የምትወስን ሴት ናት። የምትቀያይራቸውን ባሎቿን እንዴት አድርጋ እንደምትመለከታቸው እና በዚያ ውስጥ ማኅበረሰቡን፣ በተለይ ትዳራቸውን ስለፈቱ ሴቶች የምትሞግትበት መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ይጠቅሳል።

እመጌቶች ላይ ይላል ዘሪሁን፣ ከሁለት ፍቅረኛሞች ባሻገር "በተለይ የሴተኛ አዳሪዎች ሕይወትን በተመለከተ በጣም ወሳኝ ነጥብ ታነሳለች። ሴተኛ አዳሪዎችን የምናይበትን ዓይን ነው በደንብ የምትሞግተው።"

እነዚህ ሀሳቦች ወንድ ፀሐፌ ተውኔቶች በብዛት አላነሱትም የሚለው ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን፣ "እርሷ አንድም ሴት ስለሆነች፣ አንድም ያንን የሴቶች ችግር ለማውጣት 'አድቮኬት' ስለምታደርግ በጣም ወሳኝ የሆኑ ጥያቄዎችን ታነሳለች።"

ይህ በቴሌቪዥን እንዲሁም በሬዲዮ ድራማዎችም ላይ በተመሳሳይ እንደሚታይ ጨምሮ ጠቅሷል።

"ያ ደግሞ ሴት ስለሆነች እና በማኅበረሰቡ ውስጥ የኖረውን ሴቶች ላይ ያለውን አመለካከት ለመሞገት ከመፈለጓ ነው ብዬ ነው የማምነው። ወይንም ደግሞ ወንዶች ፀሐፊያን ያላደረጉትን ነገር ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት ታደርጋለች ብዬ አምናለሁ።"

ለፕሮዳክሽን ባለሙያዋ መዓዛ ደንድር ደግሞ የዚህ ማሳያዋ "አላውቅም፤ አናውቅም" የተሰኘው የቴሌቪዥን ድራማዋ ነው።

በድራማው ላይ የተነሳው አርግዞ መውለድ የሚፈጥረው ጓዘ ብዙ ምስቅልቅልን "አይተነው አናውቀም። ምናልባት ሴት በመሆኗ ይህንን በቅርበት እንድታይ ዕድል ሰጥቷት ይሆናል። ግን ጉዳዩ ከወንዶችም የተሰወረ አልነበረም። ከወንድ ደራሲዎች ግን አላገኘነውም። በሴትነቷ ብቻም አይደለም፤ በጣም አትኩሮ ተመልካች በመሆኗም ነው" ትላለች።

ስለዚህ የመዓዛን ሥራዎች የአትኩሮት ጥልቀትን ስታስረዳም አንዳንዴ በሴትነት የሚገኝ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጥልቅ አንባቢነት እና ብዙ በመኖር በመሆን በመጥቀስ "ከብዙ መኖር በላይ በደንብ በመኖር የሚገኝ ነው" ስትል ትገልጸዋለች።

'ሼክስፔር ኢትዮጵያዊ ነው' የሚለው ቴአትር ላይ ትወና ከተሳተፉት መካከል ቅድስት ብሩክ፣ ተስፋዬ ገብረሃና እና ሐረገወይን አሰፋ ይገኙበታል

የፎቶው ባለመብት, Meaza Worku

የምስሉ መግለጫ, 'ሼክስፔር ኢትዮጵያዊ ነው' የሚለው ቴአትር ላይ ትወና ከተሳተፉት መካከል ቅድስት ብሩክ፣ ተስፋዬ ገብረሃና እና ሐረገወይን አሰፋ ይገኙበታል

'የመጀመሪያ ድርሰቴን አንድም ቀን ወድጄው አላውቅም'

በተለምዶ ቴአትር የሚታየው ቴአትር ቤት ነው።

እነዚህ ቴአትር ቤቶች ሰፊ መድረክ፣ በቂ የብርሃን ሥርጭት እንዲሁም በርካታ ተመልካች ማስተናገድ የሚችሉ ናቸው።

መዓዛ ግን እነዚህን ቴአትር ቤቶች "ትፈራቸዋለች"።

ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን መዓዛ ወርቁን ሲገልጻት በጣይቱ ሆቴል በኋላም በጊዮን ሆቴል የታየውን 'ከሰላምታ ጋር' የተሰኘውን ቴአትሯን በማንሳት ነው።

መዓዛ 1,200 ሰው ከሚይዘው ብሔራዊ ቴአትር ቤት ይልቅ ከ200 እስከ 300 ሰው የሚይዙ የሆቴል አዳራሾችን የመረጠችበት ምክንያት ከተለመደው መንገድ የመውጣት "ድፍረት" ነው።

"ትንሽ ድፍረት ይጠይቃል፤ እዚያ አላሳይም ብሎ አማራጭ መድረክ ፈልጎ ማሳየት አንድም ድፍረት፣ አንድም ችሎታ ይጠይቃል።"

ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ይህንን ከተለመደው አካሄድ ወጣ ለማለት መሞከር "ዘመነኛ" የሚል ስም እንደሚያሰጣት ቢጠቅስም፣ መዓዛ ግን ከዚህ የተለየ ልምድ አላት።

መዓዛ የቴአትር ቤቶችን መድረክ የማትፈልግበትን፣ የማትመርጥበትን ምክንያት ስታስረዳ "ያስፈሩኛል፤ አላስባቸውም" በማለት ነው።

ለምን? ለሚል ደፋር ጠያቂ ደግሞ የመጀመሪያዋ ቴአትር የሆነው "ዝነኞቹ" ላይ የነበራትን ልምድ ትጠቅሳለች።

ዝነኞቹ የመጀመሪያ የድርሰት ሥራዋ ነው።

መጀመሪያ ግን ርዕሱ "አራት ኮከብ" የሚል ነበር። የተውኔት ድርሰቱ የተጻፈበት መንገድ ደግሞ "ልክ ዶሚኖ ቲዎሪ እንደሚባለው፣...የአንዱ ሰው ድርጊት ሌላ ሰው ላይ ተጽእኖ እያደረገ እየተከታተለ የሚወድቅ...ለየት ያለ ዓይነት አቀራረብ ነበር" ትላለች።

ይህንን ልሞክር ብላ የጻፈችው የመጀመሪያ ድርሰቷን ራሷ አዘጋጅታ ብሔራዊ ቴያትር ወስዳ ስታስገመግመው ወደቀ።

የሰጧት አስተያየት ቴአትሩ በርካታ ጥሩ ነገሮች እንዳሉት የሚገልጽ ነው፤ ግን አላለፈም።

"ብቁ ያላደረገውን ምክንያት በዝርዝር አልነገሩኝም። እና በጊዜው በጣም ከፋኝ። ለምን አልገባቸውም? ለምንድን ነው ይህንን ጥሩ የሆነውን ነገር ካሳዩ፣ ጥሩ ያልሆነውን ነገር ታግዞ እንዲወጣ ያላደረጉት? ለምን ቦታ አልተሰጠኝም ብዬ ተበሳጭቼ ነበር" ትላለች።

በኋላ በሰዎች ምክር ወደ ተለመደው ዓይነት የቴአትር ቅርጽ ቀይራው፣ ርዕሱ "ዝነኞቹ" ተብሎ አዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ፣ ማዘጋጃ ቤት መታየት ጀመረ።

ቴአትሩን ያዩት ሁሉ እንደሚወዱት ይናገራሉ። ደራሲ፣ አዘጋጅ እና ተዋናይት አዜብ ወርቁም ለዚህ ምስክር ናት።

መዓዛ ግን "እርሱን ቴያትር አንድም ቀን ወድጄው አላውቅም። መድረክ ላይ በታየ ጊዜ ሁሉ ማለት ነው። ልክ አይደለም። ልክ ነው ብዬ አላስብም፤ ይሰለቸኛል።"

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ባልተለመደ ቦታ ያልተለመደ ዓይነት ሥራ ለመሥራት ከራሷ ጋር ኪዳን አሰረች።

"ስጀምር...እንዲያውም ራሴ ነው የምተውነው ብዬ ነው የተነሳሁት። ራሴ አዘጋጅቼ በፈለግኩት ቦታ ላቀርበው የምችለው ሥራ እሠራለሁ" ብላ ተነሳች።

ከዚያ በኋላ ከሰላምታ ጋር የሚለው ቴአትሯ ተወለደ።

"ስለዚህ ሁልጊዜ አዳዲስ ነገር ስሠራ፣ እነዚህ የተለመዱ ቦታዎች ጋር ስወስድ ያ ተመሳሳይ ልምድ እንደሚገጥመኝ አውቃለሁ። ስለዚህ እርሱን እሸሻለሁ" ትላለች።

ደራሲ እና አዘጋጅ አዜብ ወርቁም "የመዓዛ ሥራዎች ራሷን የሚገልፁ፣ 'ኦሪጂናል' ናቸው" ካለች በኋላ "የተለመደው ዓይነት የሳሎን ሶፋ እና ግድግዳ የሚታይባቸው አይደሉም" በማለት ትገልጻለች።።

ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ደግሞ የአጻጻፍ ቴክኒኳ እንደሚለይ ይናገራል።

"...ከሰላምታ ጋር የተሰኘው ሥራዋ በአጻጻፍ ቴክኒኩ የተለመደውን የአጻጻፍ መንገድ ሳይሆን አዲስ የአጻጻፍ መንገድ ነው። ያም ማለት በገጸባህሪ አቀራረጽ፣ በሴራ አወቃቀር፣ በምታነሳው ጭብጥ እንዲሁም አመደራረኩን ጨምሮ ዘመነኛ የሚለውን መስፈርት ይገልጻል።"

ለመዓዛ ከቴአትር ቤት መድረኮች ለመሸሽ ሌላኛው ምክንያቷ አንድ ቴአትርን አጥንቶ ለመድረክ ለማቅረብ የሚወስደው ረዥም ጊዜ ነው።

"እኔ በሁለት ወር ወይንም በአንድ ወር መሥራት የምችለውን ለቴአትር ቤቶች ብሰጥ ግን ዓመታት ይወስዳል። ያ ዓመታት የሚባል ጊዜ እኔ ውስጥ ባለችው ቅብጥብጥ ማንነት ውስጥ የለም፤ ይሄ ነው ዋነኛው ምክንያቴ።"

በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ላይ የተላለፈው እና ሙሉዓለም ታደሰ እና ዓለማየሁ ታደሰ የተወኑበት የወፌ ቆመች የሬዲዮ ድራማ ቀረፃ
የምስሉ መግለጫ, በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ላይ የተላለፈው እና ሙሉዓለም ታደሰ እና ዓለማየሁ ታደሰ የተወኑበት የወፌ ቆመች የሬዲዮ ድራማ ቀረፃ

'ጋሽ አባተ መኩሪያ አርአያዬ ነው'

መዓዛ ለድርሰት አጻጻፏ አዲስ ነገር ለመሞከር እና ለመሥራት መድፈሯ መነሻ የሆናት መኩሪያ የቴአትር ስቱዲዮ ነው።

መኩሪያ የቴአትር ስቱዲዮ በአንጋፋው የቴአትር ባለሙያ፣ ጋሽ አባተ መኩሪያ ተቋቁሞ የተለያዩ ኪነጥበባዊ ሥራዎችን የሠራ ድርጅት ነው።

በመኩሪያ የቴአትር ስቱዲዮ ውስጥ ለአራት ዓመት በፕሮጀክት አስተባባሪነት የሠራችው መዓዛ በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ተዘዋውራ የሚሠሩትን የማየት ዕድል ገጥሟታል።

"እኛ ከምናውቀው በጣም የተለየ ነገር ይደፍራሉም፤ ይሰራሉም።...አዳዲስ አስተሳሰብ አላቸው።"

ይህ የሙያ ተጋልጦ የሰጣት ልምድ ለአሁን ሥራዎቿ እርሾ ሆኗታል።

"ዛሬ የሞከርኳቸው አዳዲስ የሚመስሉ ነገሮችን ከእኔ ቀድሞ የሞከረው እና የሚደፍረውም፣ ሲሠራውም የማየው ጋሽ አባተ መኩሪያ ነው።"

ስለዚህ ጋሽ አባተ መኩሪያ "በተለይ በድፍረት። የሆነ መንገድ ሲዘጋ ሌላ መንገድ ፈልጎ እዚያ ላይ ገንኖ መታየት፤ ከዚያ ደግሞ ያልተነኩ፣ ያልተሞከሩ የሚመስሉ አዳዲስ የቴአትር ቅርፆች፣ የቴያትር ግብዓቶችን፣ የቴያትር አቀራረቦችን የሚሞክር፣ አስተሳሰቡም አሠራሩም ማንነቱም ለየት ያለ ሰው ጋሽ አባተ ነው። እርሱን ነው እንደ ምሳሌ የምቆጥረው" ትላለች።

አልጋ በአልጋ የሬዲዮ ድራማ ተዋናዮች ፍቃዱ ተክለማርያም፣ ሳምሶን ወርቁ (ቤቢ)፣ መዓዛ ወርቁ፣ ፌሩዝ ጀማል፣ እማዋይሽ ወርቁ፣ ዓለምፀሐይ በቀለ

የፎቶው ባለመብት, Meaza Worku

የምስሉ መግለጫ, አልጋ በአልጋ የሬዲዮ ድራማ ተዋናዮች

የሴት ደራሲያን ያለህ

የኢትዮጵያ ቴአትር የወንዶች ዓለም ነው። ቀድመው መስመሩን ያሰመሩት፣ የነበረውን ደንብ እና ሥርዓት ያፀኑት ወንዶች ናቸው። ስለዚህ ዓለማችንን በሴቶች መነጽር ለማየት አልታደልንም።

ይህንን ሰብረው የወጡ ሴቶች ጥቂት ናቸው።

በኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ፀሐፌ ተውኔት ስንዱ ገብሩ ናቸው። ስንዱ ገብሩ ወጥ የሆነ ቴያትር ጽፈው አዘጋጅተዋል።

ከእርሳቸው በኋላ በኢትዮጵያ የቴአትር ዓለም ውስጥ ሴቶች በደራሲነት እና በአዘጋጅነት ያላቸው ተሳትፎ እጅግ አናሳ ነው።

ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁንም "ልክ እንደ ሌላው የሙያ ዘርፍ ሁሉ" ሴቶች በቴአትር ጽሑፍ ረገድ ቁጥራቸው ትንሽ ነው ይላል።

በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር - ማዘጋጃ ቤት የምትሠራው ትዕግሥት ዓለሙ፣ የሀገር ፍቅሯ ባዩሽ አለማየሁ እንዲሁም እታፈራሁ ኃይሉ በብሔራዊ ቴአትር ወጥ ድርሰቶቻቸውን ለዕይታ ያበቁ ሴቶች ናቸው።

ከዚያ ውጪ አዜብ ወርቁ በትርጉም የቴአትር ሥራዎቿ እና ዝግጅቷ ትጠቀሳለች።

ለምን እንዲህ ቁጥራችሁ አነሰ ተብላ የተጠየቀችው መዓዛ ወርቁ "ይህ ማለት እዚህ ሙያ ላይ ምቹ ያልሆነ ነገር አለ ማለት ነው" ስትል መልሳለች።

መዓዛ "ለምንድን ነው የማይመጡት? ለምንድን ነው የማይጽፉት? ለምንድን ነው የሌለው? ለምንድን ነው አለመኖራቸው የማይታወቀን?" ስትል መልሳ ትጠይቃለች።

ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቷ ሕዝብ ሴት ሆኖ "ሴቶች እየተወከሉ፣ ታሪካቸውን እየተናገሩ አይደለም ማለት ነው። ድምጽ አልባ ናቸው ማለት ነው።...የእነርሱ አስተሳሰብ፣ ሥነ ልቦና እና ችግር እየተወከለ አይደለም፤ እየተሰማም አይደለም ማለት ነው። በጣም ሊያሳፍረን የሚገባ ጉድለት እኮ ነው" ስትል ትቆጫለች።

ይህንን ለማስተካከል ግን መዓዛ ሁሌም "...እኔ በተለይ ሴቶች መጻፍ የምትፈልጉ ከሆነ 'ሜንቶራችሁ' ለመሆን በጣም ፈቃደኛ ነኝ። እባካችሁ የምትጽፉ ሴቶች ኑ እላለሁ። በአገኘሁት መድረክ ሁሉ ነው የምናገረው" ብላለች።

ግን እንዲህ እንደሚወራው እና እንደሚታሰበው ቀላል አለመሆኑን አይታዋለች።

"ብዙዎቹ ሴቶች በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ተምረው፣ ሙያው ውስጥ ከገቡ በኋላ ግን ወደ ጽሑፍ ሥራ ለመምጣት አይበረታቱም፤ ወይም በተለያየ ማኅበራዊም ሆነ ግላዊ ጉዳይ አይመጡም።"

የቴአትር ሙያ በግል የሚሠራ ባለመሆኑ፣ ሌሎች ሊያምኑባቸው እና ድጋፍ እና ሰፊ ተቀባይነት ሊሰጧቸው እንደሚገባ በማንሳትም ትሞግታለች።

መዓዛ ወርቁ እመጌቶችን በምታዘጋጅበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Meaza worku

የምስሉ መግለጫ, መዓዛ ወርቁ እመጌቶችን በምታዘጋጅበት ወቅት

'እርካታዬ ያለው ድርሰት ስሠራ ነው'

የሬዲዮ ድራማ ደራሲዋ፣ የቴሌቪዥን ድራማ ፀሐፊዋ እንዲሁም ፀሐፌ ተውኔቷ፣ የኮሚክ መጽሐፍት ደራሲዋ መዓዛ ወርቁ የትኛው የበለጠ ያስደስታታል?

"እኔ እርክት የምለው ድርሰት ስሠራ ነው። ድርሰት በጥቅሉ በየትኛውም ቅርጽ ብሠራው ያረካኛል።"

እኔ መጀመሪያ የድርሰት ሀሳብ ሲመጣልኝ፣ በምን ቅርጽ እንደማቀርበው አልጨነቅም የምትለው መዓዛ፣ ሀሳቡን ካዳበረች በኋላ በየትኛው መንገድ እና የትኛው ቦታ ብታቀርበው ሰፊ ተመልካች እንደምታገኝ እንደምትወስን ትናገራለች።

"ሀሳቡን አዳብሬው፤ ይህን ነገር ሬዲዮ ባደርገው በቀላሉ ልሠራው እችላለሁ።...ይሄ በቴሌቪዥን ነው መታየት ያለበት ካልኩ ደግሞ የቴሌቪዥን አደርገዋለሁ።"

በምትሠራባቸው የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ለማስተላለፊያ መንገዱ (ሚዲየሙ) የሚመጥን ለየት ያለ ነገር ለማምጣት ጥረት እንደምታደርግ የምትናገረው መዓዛ "የድርሰት ሀሳብ የመፍጠር፣ ታሪክ የመንገር ሂደት ነው የሚያስደስተኝ።...እርካታዬም ያለው እርሱ ጋር ነው ብዬ ነው የማስበው" ትላለች።

ነገር ግን ቴአትርን እንደመማሯ፣ ለቴአትርም ልዩ ፍላጎት ስላላት፣ ከተመልካች የሚገኘውም ግብረ መልስ በቀጥታ የሚመጣ በመሆኑ "ለቴአትር የተለየ ፍቅር አለኝ" ብላለች።

የእመጌቶች ቴያትር ፖስተር

የፎቶው ባለመብት, Meaza worku

የምስሉ መግለጫ, በአሁኑ ወቅት በዕይታ ላይ የሚገኘው እመጌቶች ቴያትር