በልብ ወለዶቿ የዳያስፖራውን ሕይወት እና ፍላጎት የምታስሰው ርብቃ ፍሰሃ

ርብቃ ፍሰሃ

የፎቶው ባለመብት, Tom Lai

ገና የአሥራዎቹን ዕድሜ አንድ ብላ እንደቆጠረች ነው የኢትዮጵያን ምድር ተሠናብታ ወደ አውሮፓ ከቤተሰቦቿ ጋር ለኑሮ የሄደችው።

ኑሮዋን በሰው አገር ሰማይ ሥር፣ በባዕድ ባድማ ብትቀጥልም የነፍሷ ቅኝት ዜማ ግን አገሯን፤አገሯን ይል ነበር።

ቤተሰቦቿ ገለታ ይግባቸው እና ከመጽሐፍ መደርደሪያቸው ላይ የኢትዮጵያውያን ደራሲያን መጽሐፍትን አላሳጧትም።

የሐዲስ አለማየሁ፣ የበዓሉ ግርማ፣ የብርሃኑ ዘሪሁን ሥራዎች የአማርኛ ንባቧን ያፍታታችባቸው ናቸው።

ዛሬ ወደ ምትኖርበት ካናዳ መጀመሪያ ላይ የመጣችው ለከፍተኛ ትምህርት መሆኑን ትናገራለች።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በካናዳ ኑሯዋን አድርጋለች።

ቴአትሮችን፣ የፊልም ድርሰቶችን፣ አጫጭር ልብ ወለዶችን፣ ወጎችን፣ የግል ማስታወሻዎችን እንዲሁም ረዣዥም ልብወለዶችን ትጽፋለች።

የመጀመሪያ ልብ ወለዷ "Daughters of Silence" ሲሆን፣ ሁለተኛ ሥራዋ ደግሞ 'Only Because It's You' በቅርቡ ለንባብ በቅቷል።

ርብቃ እስከ 12 ዓመቷ ድረስ ስላነበበቻቸው መጽሐፍት፣ ስለ ሰማቻቸው ታሪኮች እምብዛም ትውስታው የላትም፤ ወደ አውሮፓ ከሄደች በኋላ ግን የደራሲ ሐዲስ አለማየሁ መጻሕፍት የንባብ ሟሟሻዋ ሆኑ።

ፍቅር እስከ መቃብር እና የልምዣት አንብባለች።

"ደራሲ መሆን የቻልኩት ቤት ውስጥ ሁሌም መጽሐፍ ስለነበር ነው፣ እናቴም አባቴም በጣም አንባቢዎች ስለነበሩ ነው። እና ሁለቱም መጽሐፍቶች ቤታችን እንደነበሩ በደንብ አስታውሳለሁ።"

የደራሲ ሐዲስ ሌላኛው ሥራ የሆነውን ወንጀለኛው ዳኛ፣ የብርሃኑ ዘሪሁን የታንጉት ምሥጢር በደንብ የምታስታውሳቸው በጉርምስናዋ ወቅት ያነበበቻቸው መጽሐፍት ናቸው።

"ከአገር ስንወጣ በጣም ልጅ ስለነበርኩ ሀይስኩል ስገባ ነው ያነበብኳቸው። እና ፍቅር እስከ መቃብርን በኋላ ማስተርስ ስሠራ የመመረቂያ ጽሑፌን እዚያ ላይ ነበር የሠራሁት. . . ስለዚህ ከኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ በደንብ የማውቀው፣ያነበብኩት ፍቅር እስከ መቃብርን ነው።

በእርግጥ ርብቃ የአዳም ረታን ሥራዎችም ማንበቧን፣ 'ግራጫ ቃጭሎች' የተሰኘ ሥራውንም እንደወደደችው ትናገራለች።

'መጻፍ የጀመርኩት በተውኔት ነው'

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ርብቃ በካናዳ ዮርክ ዩኒቨርስቲ ቆይታዋ ያጠናችው ቴአትር ነው።የቴአትር ትወና፣ አዘገጃጀት እና ፕሮዳክሽን የትምህርቷ አካል ነበሩ።

ትምህርቷን ጨርሳ ሥራ ስትጀምርም ተውኔት በመጻፍ ነው የጀመረችው።

የርብቃ ተሰጥኦ በጥበብ መድረክ ላይ ሲገለጥ የተለያዩ ታሪካዊ ገፀ ባህሪያትን ወስዳ ለመድረክ ማብቃት ነበር ቀዳሚ ሥራዋ።

ንጉሥ ሠለሞን እና ንግሥት ሳባን "ዘ ዋይዝ ውመን" (wise.woman) በሚል ርዕስ ለመድረክ ስታበቃ፣ በቶሮንቶ በሚገኘው የቴአትር ማዕከል የታየ ሲሆን ያዘጋጀው ደግሞ ዝነኛው አህድሪ ዚና ማንዲዬላ ነበር።

ወደ ረዥም ልብወለድ ጽሑፍ ከመምጣቷ በፊት እጇን ያፍታታችው ተውኔት፣ ከዚያ የፊልም ጽሑፎችን በመጻፍ ነው።

"ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ልብወለድ ባነብም ከዚያ በኋላ ግን ለብዙ ዓመት ተወት አድርጌው ነበር።ከዚያ መልሼ ተውኔት፣ ፊልም መጻፍ ስተው እንደገና መጽሐፍ ማንበብ ጀመርኩኝ።"

የጻፍሻቸው ተውኔቶች ለትልቅ መድረክ ዕይታ በቅተዋል ብሎ ቢቢሲ ሲጠይቃት፣ የመጨረሻ ተውኔቷ በአውሮፓውያኑ 2009 ከታየ በኋላ የቴአትርን ዓለም ተሰናበተች።

እርሱን ደግሞ ትታ ወደ ዝርው ጽሑፍ (prose)፣ አጫጭር ልብወለድ፣መጣጥፎች፣ ወግ ገባሁ ትላለች።

በቴአትርን እና በፊልም ጽሑፏ የኢትዮጵያን ታሪክ መሥራት ያስደስታት እንደነበር አልሸሸገችም።

ርብቃ ቴአትርን ስትሰናበት ያመራቸው የእንግሊዝኛ መምህርት ሆና ወደ ቻይና ነው።

ቻይና ለአንድ ዓመት ያህል ስትኖር ከጓደኞቿ ጋር የምትኖርበት ክፍል ውስጥ ከዚህ ቀደም ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የተዋቸው የልብወለድ መጻሕፍትን አገኘች።

በቻይና ብዙ ጊዜ ከማስተማር በሚተርፋት ጊዜ ሁሉ ያገኘቻቸውን መጻሕፍት ማንበቡን ተያያዘችው።

በእጇ ላይ በሚገኘው 'ኢ ሪደርም' በርካታ መጽሐፍት ይዛ ስለነበር ከንባብ የሚያናጥባት አልተገኘም።

"የቺማማንዳ ሀፍ ኦፍ ዘ የሎ ሰንን ሳነበው (Half of the yellow sun)፣ ይመስለኛል በሕይወቴ ብዙ ጥያቄዎች ውስጥ ነበርኩኝ። እናቴ በቅርብ ሞታ ነበር። ውጭ አገር ነበር የተቀበረችው። እርሱ ብዙ ረብሾኝ ነበር። እንዴት ኢትዮጵያ ወስደን አልቀበርናትም። እነዚህ ግራ መጋባት ውስጥ ከተቱኝ። ዝም ብዬ ቁጭ ብዬ በዝርው መልክ መጻፍ ጀመርኩ።"

ከዚህ ውጪም ቻይና "ምን ልሠራ ነው የመጣሁት? ምን ጠፍቶኝ? ምን ፍለጋ መጣሁ?" የሚሉ ጥያቄዎች ውስጥ እንደነበረችም ታስታውሳለች።

"ራስን ፍለጋ ነው። ያኔ ነው በጣም 'አውቶ ባዮግራፊካል' የሆነ ነገር መጻፍ የጀምርኩት።"

መጀመሪያ በአጭር ልብወለድ መልክ፣ የግል ልምዷን፣ ጥያቄዎቿን አካትቶ የተጀመረው ልብወለድ በሂደት ረዥም ቅርጽ እየያዘ መጣ።

ከዚያ በተደጋጋሚ ሲከለስ፣ ሲታደት፣ ሲታረም ከአማካሪዎች ጋር ስትሠራ፣ ጭብጦቹን በጋራ ሲፈልጉ፣ የታሪኩን መቼት እየለዩ ሲመጡ እንደ ቀልድ በቻይና አፓርታማ ውስጥ የተጀመረው የመጀመሪያ ዝርው ጽሑፍ፣ የመጀመሪያ ልብወለዷ ሆኖ ተጠናቀቀ።

ምንም እንኳ የመጀመሪያ ረዥም ልብወለድ መጽሐፏ "Daughters of Silence" ስለ የቀብር ስፍራ ቢሆንም፣ የታሪክ ነገራው ግን የበለጠ እየተወሳሰበ የተዋጣ የረዥም ልብወለድ መጽሐፍ ሆኖ ተጠናቀቀ።

"ታሪኩ ቤተሰቡ መካከል በእናትየው የቀብር ቦታ ምክንያት ስለተፈጠረው ግጭት እና በባህል ውስጥ ስላለ ምሥጢር ጥበቃ እና ዝምታ ሆነ።"

አክላም "የሕይወት አጋጣሚ፣ አጠገቤ ብዙ መጽሐፍ መኖሩ፣ ብዙ መጽሐፎች ማንበቤ፣ እርሱ ሁሉ ተደማምሮ ነው ወደ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ ያደገው" ብላለች።

የርብቃ የመጀመርያ ልብወለድ መጽሐፍ ሽፋን እና ርብቃ

የፎቶው ባለመብት, CBC

የምስሉ መግለጫ, የርብቃ የመጀመርያ ልብወለድ መጽሐፍ ሽፋን እና ርብቃ

ርብቃ ለሁለተኛ መጽሐፏም መነሻ የሆናት በእርሷ እና በዙሪያዋ የሚገኙ ሰዎችን በማየት እና በአአምሮዋ የሚመላለሱ ጥያቄዎችን በማሰላሰል መሆኑን ትናገራለች።

የሁለተኛ መጽሐፏ ይዘት የፍቅር ግንኙነት፣ ስደት እና የጥገኝነት ጥያቄዎች እንዲሁም የቤተሰብ ጫና ላይ ያተኩራል።

"ዕድሜያችን ተቀራራቢ ስለሆነ ሰርግም ሲኖር በተከተታይ ብዙ ሰርጎች ይኖራሉ" የምትለው ርብቃ፣ አንዳንዴ ደግሞ ሦስት ጎጆ ለመቀለስ ተስማምተው ሰርግ የደገሱት ጥንዶች "የኢሚግሬሽን ግፊት ባይኖርባቸው ኖሮ ይጋቡ ይሆን? ወይስ አንዳቸው እንዲቀሩ ነው የሚጋቡት? የሚለውን ዝም ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ" ትላለች።

የስደተኝነት እና የጥገኝነት ጥያቄ ባይኖር ኖሮ ለመጠናናት ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ይጋቡ የነበሩ ሰዎች ወደመጡበት አገር ላለመመለስ በሚል ብቻ "አንዳንዴ ጊዜ ከሌላቸው ቶሎ እንዲጋቡ ይገፋፋል. . . በኋላ ላይ ግንኙነቱ ወይም ትዳሩ ችግር ይገጥመዋል።"

እንዲህ ዓይነት ነገሮች በዙሪያዋ ስትመለከት፣ እነዚህን ጥያቄዎች ትንሽ ቀለል ባለ፣ ሳቅ በሚዘራ፣ እና ደግሞ የትውልድ ክፍተትን በሚያሳይ መልኩ ጻፈችው።

በዚህኛው የፈጠራ ሥራዋ ውስጥ በትውልድ መካከል ያለን ክፍተት፣ እና እርሱን ተከትሎ የሚመጣውን ግጭት ለማሳየት መሞከሯን ትናገራለች።

በቤተሰቦች መካከል የማይታየው በግልጽ ማውራት፣ይህ እና ተያይዞ የሚመጣው ችግር፣ በብዛት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚታዩ ጉዳዮች ትኩረቷን ሳቡት።

በትውልዶች መካከል ". . . ብዙ ዝምታ አለ እና በኋላ ወጣቱ ትውልድ እዚያ ደረጃ ላይ ሲደርስ [ለትዳር] ምንም ምሳሌ የለውም፤ መመሪያ ነገር የለውም። መደነባበር ነው የሚመጣው። ይህንን በሁላችንም አይቸዋለሁ። ይህ ግራ መጋባት እስከ ትዳርም ይዘልቃል።"

ለረዥም ዓመት ትኩረቷን ስቦ የቆየው ጭብጥ በመጽሐፍ መልክ "Only Because It's You" በሚል ርዕስ ለንባብ በቃ።

"ሮም ኮም [rom-com የፍቅር ታሪክ ሆኖ አስቂኝ ዘውግ ያለው] ስለሆነ ቀለል ያለ አቀራረብን ነው የመረጥኩት። የፍቅር ታሪክ ነው፤ እና የፍቅር ታሪክ ደግሞ በተለያየ መልክ ይጻፋል።

"እና በሮም ኮም መልኩ ሲጻፍ የራሱ የሆነ የምትከተለው መንገድ አለው። እና ይህንን ማየት ፈለግኩኝ። እንደዚያ መጻፍ እችል ይሆን? የሚለውን ለመፈተሽ። በጣም ዝነኛ ዘውግ ነው። ደግሞ ሰፊ አንባቢንም ማግኘት ፈለግኩኝ።"

ርብቃ ፍሰሃ

የፎቶው ባለመብት, Tom Lai

ኢትዮጵያዊ ማንነት እና የርብቃ ድርሰቶች

በፊት መጻፍ ስጀምር ትላለች ርብቃ፣ በተለይ ቴአትር እና የፊልም ጽሑፍ ላይ "በጣም ኢትዮያዊነቴ ምን እንደሆነ ለማሳየት ነበር የምጽፈው። በመሠረታዊነት ለዚያ ነበር የምጽፈው። ታሪካችንን፣ አፈ ታሪካችንን እነርሱን ለዓለም ለማሳየት፣ ለማሳወቅ፣ እንዳሉ ቁጭ ነበር የማደርጋቸው።"

ከዚያ በኋላ ግን በካናዳ፣ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ዲያስፖራ ሕይወት ለማሳየት፣ በእነርሱ ላይ የሚከሰቱትን ነገሮች ማሳየት ፈለገች።

"ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚለው ቀርቶ አሁን የግለሰቦችን ሕይወት ወደ ማሳየቱ ወደ መንገሩ መጥቻለሁ። እዚያ ውስጥ ታሪክ፣ ምሳሌ፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ይገቡበታል። ምክንያቱም ገጸባህሪያቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው።"

ገፀባህሪያቱ ኢትዮጵያውያን ይሁኑ እንጂ አገልግሎታቸው ታሪክን ለማስተላለፍ እንደ መሳሪያ አይደለም የምትጠቀምባቸው።

"የራሳቸው የተለዩ ሰዎች ናቸው" ትላለች።

"ለምሳሌ 'ኦንሊ ቢኮዝ ኢትስ ዩ' ላይ ዋናው የፍቅር ታሪክ ነው። በሚዛን እና ቃልኪዳን መካከል። የእነርሱ ታሪክ ነው፤ የእነርሱን ማንነት ነው የምናየው። እንዴት እንደሚቀየሩ፣ እንዴት እርስ በርስ እንደሚጎዳዱ። ግን ታሪክም ይገባበታል። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ። ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ የሚለው ተረት ይገባል።"

እንደ መጀመሪያዎቹ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቿ ኢትዮጵያዊነት ፍጥጥ ብሎ አይመጣም፣ ታሪክ ነገራው ደረቅ ሆኖ አይቀርብም።

"ከታሪኩ ጋር አብሮ የሚፈስስ ነው እንጂ ለብቻው ግንጥል ብሎ ቁጭ ያለ ነገር አይደለም። ያ የታሪኩ አካል ነው" ትላለች።

አክላም ኢትዮጵያዊነት በድርሰቶቿ ውስጥ ከታሪኩ ጋር ተለውሶ ሲመጣ ያለውን ተጽዕኖ ስታብራራ "ተፈጥሯዊ ኢትዮጵያዊነቴ እዚያ ውስጥ የተቀየጠ ነው። በፊት ግን ፍጥጥ ብሎ ለብቻው ቁጭ ያለ ነገር ነበር" ትላለች።

ኢትዮጵያዊ ገጸባህሪ ስሎ በፈረንጅ አፍ ማዋራት ያለውን ፈተና ስትጠየቅም፣ "በተለይ ምልልሳቸው ላይ ትንሽ እንግሊዝኛውን ደንቀፍ አድርጌ በመጻፍ አማርኛ እንደሚናገሩ ለማሳየት እሞክራለሁ።"

ይህ ደግሞ በመጀመሪያ ሥራዋ ውስጥ በጉልህ ታይቷል።

በተለይ "ዶተርስ ኦፍ ሳይለንስ" ላይ አብዛኞቹ ገጸባህሪያት ኢትዮጵያ ናቸው።

አብዛኛው ታሪኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚከናወነው። በዚህም የተነሳ "ፍቺውን በመቀያየር ወይንም የአገሬው ተናጋሪ የሚጠቀማቸውን ቃላት ሳይሆን ለየት ያሉ ጠንከር ያሉ ቃላትን በመጠቀም፣ ትንሸ ጣዕም ለመስጠት ሞክሬያለሁ። ግን ምን ያህል ውጤታማ እንደነበር አላውቅም" ትላለች።

በሁለተኛው የረዥም ልብወለድ ሥራዋ ውስጥ ግን ይህ እንደማይታይ ስትገልጽ "አሁን ግን መጨናነቁን ትቼዋለሁ። መናገር የሚፈልጉትን ይናገራሉ። አንባቢው የሚፈልግ ከሆነ በጭንቅላቱ ወደ አማርኛ ተርጉሞ ወይንም አማርኛ ነው የሚናገሩት ብሎ ይሳለው።"

ርብቃ እና የሁለተኛ መጽሐፏ ሽፋን ገጽ

የፎቶው ባለመብት, CBC

ሥራዎቿ ለኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሥነ ጽሑፍ የሚኖራቸው ሚና

አብዛኛው ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ደራሲዎች ልብወለዶቻቸውን የጻፉት ጓዘ ብዙ በሆኑ ስደተኞች ታሪክ ላይ ነው።

የጣልያን ወረራ፣ የደርግ ዘመን ፍዳን እና እርሱን ተከትሎ የመጣው ሽሽት፣ ስደት፣ ወላጆችን ማጣት፣ በጉዲፈቻ መሰጠት ላይ ያጠነጥናሉ።

በስደት ያሉ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ፀሐፍት ሥነ ጽሑፋቸው "ትራውማ [ቁስለት] ላይ ያተኩራል" ትላለች ርብቃ።

የአንቺ ከእነርሱ በምን ይለያል ተብላ ስትጠየቅ "ትንሽ ለመረበሽ ሞክሬያለሁ" ትላለች እየሳቀች።

ከመረበሽ ይልቅ "ዳይቨርሲፋይ [ለማስፋት] ሞክሬያለሁ ብንለው ይሻላል። የሌሉ ዓይነት ጭብጦች ጨምሬበታለሁ" ካለች በኋላ "አዲሱ ልብወለዴ 'ቢኮዝ ኢትስ ዩ' አዲስ ነገር ያቀርባል።. . . ከእኛ የማይጠበቁ. . . ነገር ግን ሳቅ የሚያጭሩ. . . ቀለል ያለ የዳያስፖራው ማኅበራዊ ሕይወትን በማሳየት አዲስ አቀራረብ ያስተዋውቃል ብዬ አስባለሁ። የመጀመሪያው 'ዶተርስ ኦፍ ሳይለንስ፤ ደግሞ የማናወራቸው ጭብጦች ላይ ያተኮረ ነው። በተለይ በሥነ ጽሑፋችን ውስጥ ያልታዩ ነገሮችን አስገብቼበታለሁ።በሁለቱም የሚረብሽ [የዳያስፖራውን ሥነ ጽሑፍ] ነገር ጨምሬያለሁ ብዬ አስባለሁ።"

የትኛውም የጥበብ ሥራ በቀላሉ የሚሳካ ነገር አይደለም የሚትለው ርብቃ፣ "ብዙ ተስፋ መቁረጥ" ስላለ ትዕግሥት ያስፈልጋል ስትል ልምዷን በማጣቀስ ትናገራለች።

አዲስ ለሚጽፉ፣ ከአገር ውጪ ያሉ ጸሐፍትም "ትዕግሥተኛ ሁኑ፤ጠንካራ ሁኑ።. . .ጊዜ ስጡት" ስትል ትመክራለች።

ከራሷ ልምድ በመነሳትም መጽሐፍ መጻፍ የትርፍ ሰዓት ሥራ ሳይሆን፣ በተቻለ መጠን በሕይወታቸው ትኩረት እና ቦታ ሊሰጡት የሚገባ ነገር መሆኑን ታነሳለች።

ከዚህ በተጨማሪ ከበርካታ ሰዎች ጋር የመሥራት ልምድ እንደሚጠይቅም ስታስረዳ "መጽሐፍ መጻፍ ብዙ ሰው ይፈልጋል። መጀመሪያ አንድ ሰው ብቻውን ነው የሚጽፈው። በኋላ ግን ለሕዝብ ለማቅረብ ከብዙ ሰዎች ጋር መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ ከሰዎች ጋር የመሥራት ክህሎት፣ የመግባባት ክህሎት ያስፈልጋል።"

ወደፊት ምን እንጠብቅ?

ርብቃ የመጀመሪያ ረዥም ልብ ወለድ መጽሐፏን 'ዶተርስ ኦፍ ሳይለንስ' ወደ ፊልም ለመለወጥ እየሠራች ነው።

ወደ ፊልም ለመቀየር አብረዋት እየሠሩት ያሉት ደግሞ 'ፋይንዲንግ ሳሊ' እና 'ሂድን ኢትዮጵያ'ን የሠሩት ጎበዝ ሚዲያዎች እንደሆኑ ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ሦስተኛው መጽሐፌንም እየጻፍኩ ነው" የምትለው ርብቃ፣ "የመጀመሪያው መጽሐፌን ወደ ፊልም ለመለወጥ እየሠራሁ ነው። ሦስተኛው መጽሐፌም ቤተሰብ እና ሥራ፤ በአንድ የሙያ ዘርፍ ለመቀጠል ያለ ውሳኔ፣ ቤተሰብ እና ሴትነት ያላቸው ተግዳሮት ላይ ያተኩራል" ብላለች።

በተለይ ሴቶች በኢትዮጵያ ባህል ማግባት፣ መውለድ ይጠበቅባቸዋል የምትለው ርብቃ "አንዲት ሴት ይህንን ካልፈለገች እና በሙያዋ ሥራዋን መቀጠል ከፈለገች ምንድን ነው የሚገጥማት ስለሚለው ነው የምጽፈው" ትላለች።

ከዚህ ውጪ ወደፊት በምትጽፋቸው መጽሐፎች ውስጥ የዳያስፖራው ችግሮች የሆኑ የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደምትፈልግ ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ልጆች ወደ ውጪ ከወጡ በኋላ አንዳንዴ ወላጆች መጥተው አብረዋቸው መኖር ይጀምራሉ። ሌላው ደግሞ በዕድሜ የገፉ ቤተሰቦች አገር ቤት ሆነው ልጆች ውጪ ይሆናሉ።

"ያ ርቀት ያለው የስሜት ጫና፣ የቤተሰብ መጠበቅ፣ በዓመት እና ሁለት ዓመት ብቻ መገናኘት ያለውን ሰቀቀን የሆነ 'ድራማቲክ ሲሪስ'፣ የወላጅ እና ልጅ፣ልጆች በዕድሜ ከገፉ ወላጆቻቸው ጋር በርቀት ያላቸው ግንኙነት፣ አንዳንዴ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የሚወስኑ አሉ፤ እነርሱ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር እንደገና መማር አለባቸው" እነዚህ ላይ ለመጻፍ እንደምታስብ ተናግራለች።

ፈገግ ብላ፤ "ሃሳብ ነው፤ ምንም አይወጣው ይሆናል።"