እየፈረሰች ያለችውን አዲስ አበባ በመሰንቆ 'እየገነባት' ያለው ሀዲስ ዓለማየሁ

ሀዲስ ዓለማየሁ

የፎቶው ባለመብት, One String One World

የምስሉ መግለጫ, ሀዲስ ዓለማየሁ ስለ መሰንቆ አውርቶ አይጠግብም

"መሰንቆ ሕይወቴን ሠርታልኛለች።

መሰንቆ የራሴን ዓለም ፈጥራልኛለች።

መሰንቆ ባለ ራዕይ አድርጋኛለች።

እኔን አይታችሁ መሰንቆን አለማየት ከባድ ነው።"

ሀዲስ ዓለማየሁ መሰንቆ ተጫዋች ነው። ስለ መሰንቆ አውርቶ አይጠግብም።

ዓለም ሙሉ በአንዱ የመሰንቆ ገመድ ቢተሳሰርለት ምኞቱ ነው።

ሀዲስ እና መሰንቆን መለያየት አይቻልም ይላል። ስሙንና የሚወደውን መሰንቆ ገምዶ ራሱን ሀዲንቆ ሲል ይጠራል።

"ሀዲስ እና መሰንቆ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው። እኔን አይታችሁ መሰንቆን አለማየት ከባድ ነው። አንድ ነን።"

ሀዲስ የሚል ስም የተሰጠው ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁን በሚያደንቁ የወላጆቹ ጎረቤት ነው።

"የትልቅ ሰው ስም ነው የያዝኩት። እንደ ዘመኑ ሀዲስ ዓለማየሁ ትልቅ አሻራ ብተው ብዬ አስባለሁ። ሰው ሲተዋወቀኝ፣ ደራሲው ሳይሆን ባለ መሰንቆው ሀዲስ ዓለማየሁ እያልኩ እቀልዳለሁ።"

ሀዲንቆ 'Streets of Haddis' የተባለውን የመጀመሪያ አልበሙን በቅርቡ ለቋል።

የመሰንቆ አልበም ነው። በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ትዝታ የተሞላ የመሰንቆ አልበም።

ቦሌ ጃፓን፣ ትዝታ ዘ ቀበና፣ አራት ኪሎ፣ ጃን ሜዳ፣ ፒያሳ፣ መርካቶ፣ መስቀል ፍላወር፣ ካዛንችስ፣ መገናኛ፣ ሳሊተ ምሕረት እና ዓድዋ ድልድይ. . . ለአዲስ አበባ የተጻፉ የፍቅር ደብዳቤዎች ይመስላሉ።

የማንነቷ መገለጫ የሚባሉ ቀደምት ሰፈሮቿን እያጣች ላለችው አዲስ አበባ እንደ ሙገሳ፣ እንደ ስንብት፣ እንደ ማስታወሻም ልንለው እንችላለን።

ሀዲስ አገርኛ ሙዚቃን ከባሕር ማዶው ባስተሳሰረባት መሰንቆው፣ ሰፈሮቹ ሲፈርሱ ይዘው የፈረሱትን ትውስታ ቀድቶ ለታሪክ እያስቀመጠ ነው።

ሀዲስ ዓለማየሁ

የፎቶው ባለመብት, One String One World

የምስሉ መግለጫ, ሙዚቀኛው ድሮ አራት ኪሎ ሊስትሮ ሆኖ ሠርቷል

የቀበና ልጅ. . .

ሀዲስ የቀበና ልጅ ነው። 'ትዝታ ዘ ቀበና' ሙዚቃ ወደ ልጅነት ትውስታው ይወስደናል።

ልጅ ሳለ ወንድሙ ከክፍለ አገር መሰንቆ ገዛላቸው። መሰንቆው የተገዛው ለቤት ጌጥ ነበር።

"ወንድማችን ክፍለ አገር ሄዶ ሲመለስ ጌጥ እንድትሆን መሰንቆዋን አመጣትና ግድግዳ ላይ ተሰቀለች። እንዳናበላሽ እንዳትነኳት እያለ ያስፈራራን ነበር" ይላል ሀዲስ በትውስታ።

መሰንቆዋ ከግድግዳ ሳትወርድ ሁለት ዓመት ሞላት። ሀዲስም ያያታል፣ እሷም ታየዋለች።

ዛሬ "ሕይወቴን የሠራችልኝ" የሚላትን መሰንቆ አንድ ቀን ከግድግዳ አወረዳት።

ይኸው እስከዛሬ አብረው ከቀበና እስከ ጎንደር፣ ከአዲስ አበባ እስከ ጃፓን . . . ዓለምን ይዞራሉ።

ቀበና "ብዙ ትዝታ አለኝ" ይላል ሀዲንቆ።

"የቀበና ወንዟ የማንጎራጉርባት ቦታ ነበረች። ማኅበራዊ ሕይወቴን፣ ጓደኞቼን አስታውሳለሁ። አሁን አብዛኛው ነገር ፈርሷል። 'ትዝታ ዘ ቀበና' ሙዚቃ የተሠራው ቀበናን ሳስብ የሚሰማኝ ትዝታዬን በሚገልጽ መንገድ ነው። በመፈራረሱም የድሮውን ማስታወስ እፈልጋለሁ።"

'ትዝታ ዘ ቀበና' ላይ ሮክ ኤንድ ሮል ከ'ትዝታሽ ዘወትር ወደ እኔ እየመጣ. . .' እንጉርጉሮ ጋር ይሰማል።

ከቀበና ወደ አራት ኪሎ የሚወስደው ጎዳና የሀዲስ ሌላ የሕይወት ምዕራፍ ነው።

'አራት ኪሎ ሊስትሮ ነበርኩ'

ሙዚቀኛው ድሮ አራት ኪሎ ሊስትሮ ሆኖ ሠርቷል።

"ቤተሰቤን ለመርዳት፣ ደብተርና እስኪርብቶ ለመግዛት ክረምት ላይ ግንፍሌ፣ አራት ኪሎ አካባቢ ሊስትሮ ሆኜ እሠራ ነበር። ዝቅ ብሎ መሥራትን፣ ሥራ አለመናቅን፣ ጠንክሮ መሥራትን፣ ራስን ማሸነፍን፣ ራስን መቻልን ያስተማረኝ ሰፈር ነው" ይላል።

ጫማ ሲጠርግ ታዲያ እያንጎራጎረ ነበር። ድምጹን የሰሙ ደንበኞቹ እዚያው ግንፍሌ አካባቢ ያለ የፀረ ኤድስ ማኅበር እንዲገባ መከሩት።

ያንን ጊዜ የአገረ ሰብ ሙዚቃና ውዝዋዜ የተማርኩበት ሲል ያስታውሰዋል።

ብዙም ሳይቆይ የሕጻናትና ወጣቶች ቴአትር ገባ። በድምጻዊነት፣ በግጥም እና ዜማ ደራሲነት ሠርቷል።

ሀዲስ ዓለማየሁ

የፎቶው ባለመብት, One String One World

የምስሉ መግለጫ, ሀዲንቆ ጃን ሜዳ እየሄደ መሰንቆ ተጫዋቾችን ያደምጥ ነበር

የጃን ሜዳ ሀርሞኒካ እና 'ካንትሪ' ሙዚቃ

'ጃን ሜዳ' የብዙ ሙዚቃ ስልቶች ድብልቅ ነው። በተለምዶ ለጥምቀት በዓል በጃን ሜዳ የሚሰማው ሀርሞኒካ ከአገረ ሰብ ሙዚቃ ጋር ተዋህዶ ይሰማል።

ለእስክስታ የሚጋብዘውን የከበሮ ምት ከካንትሪ የጊታር ድርደራ ጋር መሰንቆዋ ታስታርቃለች። በአንድ ገመዷ እልልታውን ከፐርከሽን ታስራለች።

ሀዲንቆ ጃን ሜዳ እየሄደ መሰንቆ ተጫዋቾችን ያደምጥ ነበር። ያን የልጅነት ትውስታ በሙዚቃው ያስቃኘናል።

"ጃን ሜዳ ለጥምቀት የሀርሞኒካ ጨዋታ አዝማሪዎች ሲመጡ እየተከተልኳቸው አይ ነበር። ትውስታዬን እንዲገልጽልኝ የሃርሞኒካ ጨዋታን ከብሉዝ እና ካንትሪ ጋር አዋህጃለሁ።"

ጃን ሜዳን የሠራው ከክሮሽያዊው የሀርሞኒካ ተጫዋች ቶሚስላቭ ጎሉባን ጋር ነው።

ከጃን ሜዳ ወደ 'አዝማሪ ሰፈሩ' ካዛንችስ ሙዚቃ ስንሻገር አዝማሪት አዜብ ዳኘውን እንሰማለን።

ሀዲስ ዓለማየሁ

የፎቶው ባለመብት, One String One World

የምስሉ መግለጫ, በአልበሙ በሩቅ ምሥራቅ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በአሜሪካ ያገኛቸውን ሙዚቀኞች አሳትፏል

'የአዝማሪ ሰፈር'

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አዝማሪቷ አዜብ እና የጃፓን ሙዚቀኞች በ'ካዛንችስ' ሙዚቃ ተጣምረዋል።

ሀዲስ ሙዚቃውን ሲገልጸው በካዛንችስ መፍረስ "ያለኝን ብሶት" ለመግለጽ ነው ይላል።

መሰንቆን ከአዝማሪዎች የተማረበት ሰፈር ነው።

አልበሙ መገናኛን ከነግርግሩ፣ መርካቶን ከነቅልጥፍናው፣ ፒያሳን ከነትውስታው፣ ዓድዋ ድልድይን ከነጀግንነቱ. . . እያጣመረ ይቀጥላል።

"ዓድዋ ድልድይ ሙዚቃን ስሠራ የአፍሪካ ትልቅ አርማ የሆነውን ዓድዋ ለማስታወስ ነው። ለዓድዋ በዓል ከፒያሳ ጀምሮ እስከ ዓድዋ ድልድይ በእግር ስንሄድ የምናሳልፈውን ጊዜ የሚገልጽ ነው። ሽለላ እና ፉከራ ከኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ጋር በመሰንቆ አብረው ተሠርተዋል።"

መስቀል ፍላወር "ቤተሰብ የመሠረትኩበት ሰፈር ነው" ይላል ሀዲስ።

ለሰባት ዓመት ገደማ የኖረበትን ሰፈር በሙዚቃው ያወድሳል።

"የያሬድ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ እና የያሬድ የሙዚቃ ምልክቶችን እንዲገልጽልኝ ነው። ቅኝቶቹ ሰፈሩን እንዲቃኙ ለማድረግም ነው" ይላል ሙዚቀኛው።

"ከሥራዬ ጋር በተያያዘ ወጣ ገባ የምልበት ኮሪደር" የሚለውን ቦሌ በ'ቦሌ ጃፓን' ሙዚቃ ያስቃኘናል።

ሙዚቃውን የሠራው ከጃፓን ሙዚቀኞች ጋር ነው። ሸምሲን የተባለው የጃፓን ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ እና መሰንቆ እየተናበቡ ከቦሌ እስከ ጃፓን ያደርሳሉ።

ባለ ሦስት ገመዷ ሸምሲን ከመሰንቆ ጋር የሚመሳሰል ገጽታ አላት።

በሳሊተ ምሕረት ሙዚቃ ላይ የጃፓን ዋሽንት ይንቆረቆራል።

"የጃፓን እረኛ የሚጫወተው ዋሽንት አለ። የኢትዮጵያ እረኛም የሚጫወተው ዋሽንት አለ። ሁለቱን ለማስተሳሰር ነው።"

ሳሊተ ምሕረት የያምሉ ሞላ ስቱዲዮ የሚገኝበት፣ አልበሙ የተቀረጸበት እና የተቀናበረበት ቦታ ነው።

"ላለፈው ሦስት ዓመት እዚያ ነው የሠራነው። ሙዚቃውን ስንሠራ ዝናቡን ስንሰማ ያለውን ስሜት የሚገልጽ ነው" ሲል ስለ ሙዚቃው ይናገራል።

በአልበሙ በሩቅ ምሥራቅ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በአሜሪካ ያገኛቸውን ሙዚቀኞች አሳትፏል።

አብሮ አደግ ጓደኞቹ እና አብረውት የሠሩ ሙዚቀኞችንም እንዳካተተ ይናገራል።

"የአዲስ አበባን ጎዳና እና የኔን የሕይወት ጎዳና በከፊል የሚያሳይ" ሲል አልበሙን ይገልጻል።

ሀዲስ ዓለማየሁ

የፎቶው ባለመብት, One String One World

የምስሉ መግለጫ, ሀዲንቆ 'Streets of Haddis' የተባለውን የመጀመሪያ አልበሙን በቅርቡ ለቋል

'የአዲስ አበባ ልጅ መሰንቆ አይጫወትም'

ሀዲስ፣ ወንድሙ የገዛውን መሰንቆ ከግድግዳ ካወረደ ዓመታት ተቆጥረዋል። ሙዚቃ የሚወድ ቤተሰብ ውስጥ እንዳደገ ይናገራል።

"እናቴ የወሎ ሰው ነች። ማሪቱ ለገሰን በጣም ትወዳታለች። የዚነት ሙሀባን ካሴት ስትከፍት እሰማ ነበር። የቤተሰቤ የሙዚቃ ፍቅር በእኔ ላይ ተጽዕኖ አለው።"

ሙዚቃን ሲጀምር አጠገቡ የነበረችው መሣሪያ መሰንቆ ነበረች።

"ስለ ሙዚቃ ማወቅ ስጀምር አጠገቤ መሰንቆ ስለነበረች እሷን አንስቼ መነካካትና መተዋወቅ ጀመርኩ" ይላል።

በሸገር መሰንቆ አስተማሪ ማግኘት ግን ቀላል አልሆነም።

ራድዮ ላይ 'የአዝማሪ ምሽት' የሚባል መሰናዶ ሲቀርብ ያስታውሳል። የመሰንቆ ሙዚቃን ለማጣጣም መሰናዶውን ይከታተል ጀመር።

"አዲስ ካሴት እየገዛሁ፣ እየደመሰስኩ የድሮዎቹን ሙዚቃዎች መቅዳት ጀመርኩ። እሱን እየሰማሁ እለማመድ ነበር። ሠርግ ላይ መሰንቆ ተጫዋች ሲመጣ በደንብ እከታተልም ነበር። ጃን ሜዳም እየሄድኩ እሰማ ነበር።"

ባህላዊ ሙዚቃን አዲስ አበባ ውስጥ ለመማር ያለው ፈተና እንዳለ ሆኖ 'የአዲስ አበባ ልጅ መሰንቆ አይጫወትም' ብለው የተሳለቁበት አልጠፉም።

ሀዲስ ዓለማየሁ

የፎቶው ባለመብት, One String One World

የምስሉ መግለጫ, አልበሙ ለአዲስ አበባ እንደ ሙገሳ፣ እንደ ስንብት፣ እንደ ማስታወሻም ነው

ያኔ 'የአዲስ አበባ ልጅ መሰንቆ አይጫወትም' ቢሉትም፣ ዛሬ በአልበሙ የአዲስ አበባን ጎዳናዎች በመሰንቆው ያንቆለጳጵሳል።

"የአዲስ አበባ ልጅ ብዙ ጊዜ የባህል ሙዚቃ መሣሪያ ሲጫወት አይታወቅም። ጊታር እና ኪቦርድ በብዛት የሚማረው የባህላዊ ሙዘቃ አቅርቦትም ስለሌለ መሰለኝ" ይላል።

ሀዲንቆ ግን የባህላዊ ሙዚቃ መምህራን ወይም መሰንቆን 'የሚያከብሩ ከተሜዎች' አለመኖር ብዙም አላሰናከለውም።

ወደ መሰንቆ 'መዲና' አቀና።

"መሰንቆ መጫወት ከጀመርኩ ከአምስት ዓመት በኋላ፣ ወደ 2006 ዓ.ም. አካባቢ ስለ መሰንቆ ለማወቅ እና ከአዝማሪዎች ለመማር ወደ ጎንደር ሄድኩ። እዛ ማንንም ባላውቅም ለመማር ስል ሄድኩ። ከእነሱ ጋር አዝማሪ ቤት እና ምሽት ክበብ መሰንቆ እየተጫወትኩ፣ ያገኘነውን እየተካፈልን እየበላን እየጠጣን ቆየሁ። ከዚያ ደግሞ ወደ ባሕር ዳር ሄድኩ።"

'አስተማሪ ልሁን ወይስ መሰንቆ ተጫዋች?'

ወደ ጎንደር ሳይሄድ በፊት "መንታ መንገድ" ላይ ነበርኩኝ ይላል።

ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ተመርቆ ለሁለት ዓመት አስተማሪ ነበር። በአስተማሪነት ልቀጥል ወይስ መሰንቆ ልጫወት? በሚለው መካከል ሆኖ ብዙ አሰበ።

መሰንቆን መረጠ።

ለምን መሰንቆ? በሚል ሲጠየቅ "ለእኔም ጥያቄ ነው" ብሎ ይመልሳል። "በሕይወት ፈተና ሲበዛብኝ የኔም ጥያቄ ያ ነበር" ይላል ሀዲስ።

"አውጥቼ፣ አውርጄ የተማረ ሙዚቀኛ አገራችን ያስፈልጋታል ወደሚለው አዘነበልኩና ወደ ጎንደር ሄድኩ፤ መሰንቆን መረጥኩ።"

መንገዱ ቀላል አልነበረም። "ያበረታቱኝና ያገዙኝ እንዳሉ ሁሉ የሳቁብኝም አሉ። ከሰፈሬ ጀምሮ" ይላል ሙዚቀኛው።

የበርካቶች ሙያውን መናቅ አንዱ ፈተና ነበር። ሀዲንቆ ግን ፈተናው ብርታቴ ነው ይላል።

"ሁሉንም አሸንፎ ወደ ብርሃኑ መሄድ ይሻላል። እንዲያውም ፈተናውን መወጣጫ ድንጋይ ማድረግ ነው።"

በቀዳሚነት ደጋፊዎቹ የሆኑት ቤተሰቦቹ ናቸው። "በተለይ እናቴ ትደግፈኝ ነበር" ይላል።

ልጅ ሳለ ሁሌም ከትምህርት ቤት ሲመለስ ቤት መሰንቆው ትጠብቀዋለች። አሁንም ድረስ በቀን ከሰባት ሰዓት በላይ መሰንቆ ይጫወታል።

ስለ መሰንቆ ብዙ እየተረዳ ሲመጣ ሥነ ምግባር እና ረዥም ጊዜ መስጠት የሚፈልግ እንደሆነ ገብቶታል።

"ከደባል ነገሮች መራቅንም ይፈልጋል" ሲል ይገልጻል።

እንደ ዛሬው በየአገራቱ እየዞረ መሰንቆን መጫወት ከመጀመሩ በፊት ፈተናዎች ሲበረቱበት ጥንካሬ የሆነው ቤተሰቡ እና የሙዚቃ ፍቅር እንደሆነ ይናገራል።

"ያበረታቱኝን ሰዎች እንደካስኳቸው ይሰማኛል. . . ያኔ ያበረታኝ ነገር ይሄ ነው ለማለት ይከብደኛል። ምናልባት መልካም ነገሮች ስላመዘኑ ይሆናል። ቤት ውስጥ አይዞህ የሚል መኖሩ ከውጪው ጫጫታ ይልቅ ስለበረታ ይሆናል። የሙዚቃው ፍቅርም ነው። ፍቅር ካለ በማናውቀው ኃይል ያሸንፋል። ለምንወደው ነገር መስዋዕትነት ስንከፍል ደስ እያለን ነው። ፈጣሪም ያግዛል።"

ሀዲስ ዓለማየሁ

የፎቶው ባለመብት, One String One World

የምስሉ መግለጫ, በ2050 "ዓለም ሁሉ መሰንቆ ሲጫወት ባይ ደስ ይለኛል" ይላል ሀዲስ

'አብዮተኛ ነኝ'

ሀዲንቆ አብዝቶ የሚያደምጠው የመሰንቆ፣ የክራር እና የዋሽንት ባህላዊ ሙዚቃ ነው።

ሲምፎኒ፣ የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃ. . . እያለ በሚሰማቸው ዘመነኛ ሙዚቃዎች መሰንቆን በመጨመር እንዴት ዓለም ሊያጣጥማቸው እንደሚችል ያስባል።

"አብዮተኛ ነኝ" ሲል ራሱን የሚገልጸውም ለዚህ ነው።

በሸክላ የፈረደ ጎላ፣ የተሰማ እሸቴ፣ የእንድሪስ ሐሰን፣ የብርሃኑ ሞላ፣ የባሕሩ ቃኜ፣ የይርጋ ዱባለ፣ የዓለማየሁ ፈንታ፣ የአንሙት ክንዴ . . . ሙዚቃዎችን ይሰማል።

የብሔራዊ ቴአትር፣ የራስ ቴአትር እና የሀገር ፍቅር ሙዚቀኞችን ያደንቃል።

አልበሙን መሥራት የጀመረው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ነበር።

"በእኔ የሕይወት ጎዳና ትልቅ አሻራ" አላቸው የሚላቸውን የአዲስ አበባ ጎዳናዎች መግለጽ ነው ሐሳቡ።

"የአዲስ አበባን ስሜት ለማነሳሳትና ሰፈሮቹ በእኔ ሕይወት ያላቸውን ተጽዕኖ ለመግለጽ ነው። እነዛን የሰፈር ስሞች በማንሳት በሙዚቃው ስሜቱን ለመግለጽ ሞክረናል። የሕይወት ጎዳና እና የስኬት መንገድን ብዙ ውጣ ውረድ፣ ትዝታ እና መልካም አጋጣሚዎችን እንዲሁም አሁን እስከደረስንበት ደረጃ ድረስ ያለንን የጉዞ ታሪክ በ50 ደቂቃ አልበሙ ያሳያል።"

መሰንቆ በብዛት ድምጻውያንን አልያም ሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎችን አጃቢ ትሆናለች።

ሀዲስ ግን ይሄንን ለውጦ መሰንቆን ዋነኛው የሙዚቃው ማጠንጠኛ አድርጎ ሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎችን እንደ አጃቢ ያስገባል።

"ይሄ አልበም ማሲንቆን ከፍ አድርጎ ሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎችን እንደ አጃቢ ያደረገ ነው። ይህን አንደ አብዮት ነው የማየው" ይላል።

የአልበሙን መግቢያ የሠራው ጃማይካዊ-አሜሪካዊው ሙዚቀኛ ቲሞቲ ግሪን "የጥንታዊው እና የዘመናዊው የሙዚቃ ጋብቻ" ሲል ይደመጣል።

ሀዲንቆ እንደሚለው፣ ብዙ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በማዋሀድ የኦርኬስራ ስሜት ለመፍጠር ሞክሯል።

"ሙዚቃው መድረክ ላይ በሚስብ ሁኔታ መቅረብ የሚችል ነው። አልበሙ በደንብ የታሰበበት ነው። በጊዜም በገንዘብም ብዙ አውጥቼበታለሁ።"

'መሰንቆ ሕይወቴን ሠርታልኛለች'

በቀን ውስጥ ከሰባት ሰዓት በላይ መሰንቆ ሲጫወት "ምግብ የማልበላበት ጊዜም አለ" ይላል ሀዲስ።

መሰንቆን "ሕይወቴን ሠርታልኛለች፤ ለወደፊትም እየሠራችልኝ ነው" ሲል ያሞግሳታል።

"መሰንቆን ለመንፈሳዊ ሕይወቴ፣ ለጤናዬ፣ ለማኅበራዊ ሕይወቴም እጠቀማታለሁ። የገቢ ምንጭ ነች። ቤተሰቤን ሠርታልኛለች።"

ከባለቤቱ ጋር የተዋወቀውም በመሰንቆ አማካይነት ነው።

መሰንቆ "ስለ አገሬ፣ ስለ ባህል፣ ስለ ታሪክ፣ ስለ ዓለም እንዳውቅ አድርጋኛለች" ይላል።

ባለ ራዕይ ለመሆን እና በዕቅድ ለመመራት ምክንያቴ መሰንቆ ናት ሲል ሙዚቀኛው ይናገራል።

"ሕልም እንዲኖረኝ፣ ለአገሬ እና ለወገኔ የሆነ ነገር እንዳበረክት አድርጋኛለች።"

"የራሴን ዓለም ፈጥራልኛለች" የሚላትን መሰንቆ ሁሉም ሰው ቢጋራው ደስተኛ ነው። ከየትኛውም የሙዚቃ ስልት ጋር መሰንቆ መግባት እንደምትችል ይናገራል።

መሰንቆ እንደ ኪቦርድ እና ጊታር በየሙዚቃው ብትገባ ይመኛል።

በ2050 "ዓለም ሁሉ መሰንቆ ሲጫወት ባይ ደስ ይለኛል" ይላል ሀዲንቆ።

"አልበሜ ለዛ መነሳሻ እንዲሆን፣ መሰንቆን ወንዝ የሚያሻግር ገጸ በረከት ነው" ሲልም ይናገራል።

'One String – One World' የሚለው የሙዚቀኛው ሐሳብ መነሻውም ይህ ነው።

ሀዲስ ዓለማየሁ

የፎቶው ባለመብት, One String One World

የምስሉ መግለጫ, የሀዲንቆ 'አንድ ገመድ - አንድ ዓለም' ፕሮጀክት መሰንቆን 'ወንዝ የማሻገር' ነው

'አንድ ገመድ - አንድ ዓለም'

አንድ ገመድ - አንድ ዓለም መሰንቆን 'ወንዝ የማሻገር' ፕሮጀክት ልንለው እንችላለን።

አልበሙ በይዘት እና በሙዚቃ ስብጥርም "አዲስ ድምጽ" እንደሆነ የሚገልጸው ሙዚቀኛው፣ "ከተለመደው የመሰንቆ አጨዋወት ወጣ ያለና መሰንቆን ወንዝ ያሻገረ ነው" ይላል።

አድማጮቹ አንዷን የመሰንቆ ገመድ ከአንድ ዓለም ጋር አስተሳስረው ሙዚቃውን እንዲሰሙለት ይፈልጋል።

የአልበሙ ዓላማ የሙዚቃ መነሻውን መዘከር፣ መሰንቆን ከፍ ማድረግ፣ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወንዝ ማሻገርና የባህል ሙዚቀኞችን ማነሳሳት መሆኑን ይናገራል።