የአዲስ አበባ የጥበብ መልኮች

የአዲስ አበባ የጥበብ ገፅታዎች የሚያሳይ ፎቶ

የአዲስ አበባ የመዝናኛ፣ የኪነ ጥበብ እና ሥነ ጥበብ ትዕይንት እንደ ከተማዋ ሁሉ በየጊዜው ይቀያየራል።

በ1950ዎቹ ደጃች ውቤ ሰፈር (ውቤ በረሃ) የአዲስ አበባ የመዝናኛ ገጽ ነበር።

የወቅቱ ዘመነኞች፤ ወንዶቹ አፍሯቸውን ከፍክፈው፤ ሴቶቹም በጊዜው ገትር በሚባለው ጉርድ ቀሚስ ሸሚዛቸውን ሻጥ አድርገው፣ ታኮ ጫማቸውን ተጫምተው፣ አፍሯቸውን አበጥረው ወደ ደጃች ውቤ (ውቤ በረሃ) አሰገደች አላምረው ቤት ጎራ ይላሉ።

ፓትሪስ ሉሙምባ ሆቴል፣ ቡፌ ዳላ ጋርም ከከተማይቱ የጭፈራ እና የዳንስ ድግስ ጋር ስማቸው ይጠቀሳል።

ከቡጊ ቡጊው ከጭፍራው ባለፈ የሩስያ ባህል ማዕከል፣ የአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ፣ የጣሊያን ባህል ማዕከል እና ብሪቲሽ ካውንስል በከተማዋ የጥበብ ትዕይንት ውስጥ ይነሳሉ።

ከ16 ዓመታት በፊት በ11 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ምሩቃን የተቋቋመው ነጻ አርት ቪሌጅ በሥነ ስዕል ዘርፍ ተጠቃሽ ነው።

ነጻ አርት መንደር የዘመናዊ ጥበብ ሙዚየም ለመፍጠር ባሰቡ ልሂቃን የስነ ጥበብ አካሄድን በመሻገር ህብረተሰቡን ጨምሮ የተለያዩ ጥበባዊ ዝግጅቶችን ኮንሰርቶች፣ የግጥም ዝግጅቶች፣ የጥበብ ንግግሮች እና አውደ ጥናቶች እንዲሁም አውደ ርዕዮችን አዘጋጅቷል።

ከነጻ የአርት መንደር በተጨማሪ ማኩሽ አርት ጋለሪ፣ አስኒ አርት ጋለሪ እና ሌላ ኮንቴምፖራሪ አርት ጋለሪም ይጠቀሳሉ። በቀጥታ የሙዚቃ ክዋኔ (Live music performance) ደግሞ ፈንድቃ፣ አፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ ማንሳት ይቻላል።

ከአስር ዓመታት ገደማ በፊት በራስ ሆቴል ይዘጋጅ የነበረው ግጥምን በጃዝ የሥነ ጽሁፍ መድረክም ሌላኛው የመዲናዋ ክስተት ነው።

ወዲህ ደግሞ በዘመነ ማህበራዊ ሚዲያ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማህበራዊ ሚዲያን እና ጥበብን አስተሳስረው የከተዋማ የስነ ጥበብ እና ኪነ ጥበብ መልክ የሆኑ ቦታዎች እና ሁነቶች አሉ።

እነዚህ ሁነቶች እና ስፍራዎች የሚያመሳስሏቸው ጥቂት ነገሮች አሉ። ሁሉም በሚባል መልኩ አዲስ አይነት የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እና ዘመቻን የሚከተሉ ናቸው። አብዛኛው ታዳሚዎቻቸውም ወጣት ከተሜዎች ናቸው።

Studio 11:- ሴቶች አርቲስቶች ሃሳባቸውን የሚገልጹበት ቦታ

የStudio 11 መስራቾች ናፍቆት ገበየሁ እና ፅዮን ያይኑ

የፎቶው ባለመብት, Nafkot Gebeyehu

የምስሉ መግለጫ, የStudio 11 መስራቾች ናፍቆት ገበየሁ እና ፅዮን ያይኑ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ “Modernist Art in Ethiopia” በሚለው መጽሃፏ፤ በኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ሙያ ላይ መሳተፍ እንደመሳቂያ ይቆጠር እንደነበር ታነሳለች። የስነ ጥበብ ታሪክ ተመራማሪዋ ዶ/ር ኤልሳቤጥ፤ የሴቶች ስነ ጥበብ ግንዛቤ በወንዶች የበላይነት ዕይታ የተቃኘ መሆኑን ትተቻለች።

ስቱዲዮ 11 አርት ጋለሪን የመሰረቱት ሁለት ሴት አርቲስቶች የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ዘርፍ ለሴቶች ምቹ አለመሆኑን ያነሳሉ።

ሶስት ዓመታትን ያስቆጠረውን ጋለሪ ያቋቋሙት አርቲስቶች ናፍቆት ገበየሁ እና ፅዮን ያይኑ ናቸው። ሁለቱ ሴቶች የሚተዋወቁት አንድ መስሪያ ቤት ሲሰሩ ነው። ናፍቆት የፎቶግራፍ ባለሙያ፥ ፅዮን ደግሞ ሰዓሊ ሆነው።

“ወጣት እና ሴት አርቲስቶችን የሚያበረታታ” ጋለሪ ቢኖር የሚል ምኞት ነበራቸው። ከሶስት ዓመታት በፊት ምኞታቸውን ወደ መሬት አወረዱት። ስቱዲዮ 11 ዕውን ሆነ።

“የስዕል አውደ ርዕይ የሚታዩባቸው ቦታዎች እጥረት ነበር፤ አርቲስቶች ሆቴዎች ውስጥ ነበር አውደ ርዕይ የሚያዘጋጁት” የምትለው ናፍቆት፤ “የሥነ ጥበብ ከባቢው ወጣቶችን ብዙ የሚጋብዝ አልነበረም” ስተል ያዩትን ክፍተት ታስታውሳለች።

ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ግን ሌላ ክፍተት ተመለከቱ። የስነ ጥበብ ዘርፉ ለሴቶች ምቹ አልነበረም።

ናፍቆት ይህን ስታስታውስ “ሥራው ውስጥ ከገባን በኋላ ለአርቲስቶች ጥሪ እያደረገን ስራችሁን አሳዩን እያልን ጥሪ ማድረግ ስንጀምር ብዙ ሰዎች አመለከቱ። ያን ጊዜ በወንድ እና በሴቶች አርቲስቶች መካከል ክፍተት ማየት ጀመርን” ትላለች።

ስራቸውን ለማሳየት ያመለከቱት ወንድ አርቲስቶች “ሥራቸው መጥፎም ሆነ ጥሩ” በልብ ሙሉነት ስለ ስራቸው ይናገራሉ።

የሴቶች ተሞክሮ ግን ከዚህ የተለየ ነበር።

“ሴቶቹ ደግሞ እጅግ በጣም ቆንጆ እና አስፈላጊ ሥራ ሰርተው ሥለ ስራቸው የመናገሩ ድፍረት ግን የላቸውም። እኛም አርቲስቶች ስለሆንን እናውቀዋለን ያ ስሜት እኛ ውስጥ ስላለ። ሄደን ደፍረን መናገር እንፈራለን” ትላለች ናፍቆት።

በዚህ መነሻነት ናፍቆት እና ፅዮን ሴት አርቲስቶች ስራዎቻቸውን እና ራሳቸውን እንዲገልጹ ለማድረግ ስቱዲዮ 11ን ለሴቶች ምቹ ቦታ የሆነ ቦታ ለማድረግ ወሰኑ።

ናፍቆት “ገበያው ላይ ያለው ነገር እስኪመጣጠን ድረስ ብዙ ሴት አርቲስቶች ዘርፉ ውስጥ ገብተው መወዳደር እስኪችሉ ድረስ ይህንን ስራ መስራት እንቀጥላለን” ትላለች።

ስቱዲዮ 11 እስካሁን ያዘጋጃቸው የስዕል አውደ ርዕዮች ሁሉም በሴቶች የተዘጋጁ ናቸው።

ናፍቆት ገበየሁ እና ፅዮን ያይኑ

የፎቶው ባለመብት, Nafkot Gebeyehu

የምስሉ መግለጫ, ናፍቆት ገበየሁ እና ፅዮን ያይኑ

ናፍቆት እና ፅዮን ሌላው ትኩረት ለስነ ጥበብ ያለውን ግንዛቤ መቀየር ነው። ፅዮን ያይኑ “በማህበረሰቡ ዘንድ ሥነ ጥበብን በመረዳት ረገድ ትልቅ ክፍተት አለ” ትላለች።

ናፍቆት በበኩሏ “ስዕል እንደ ቆንጆ የምናንጠለጥለው ነገር አድርገን ነው እንጂ የምናስበው የማህበራዊ ጉዳዮችን የምንወያይበት መድረክ እንደሆነ ስለ ሥነ ልቡና ጤና የምንወያይበት ነገር እንደሆነ ሰው ያንን አያይም። ስዕል ማለት ጌጥ ነው ብሎ ነው የሚያስበው” ትላለች።

አብዛኛው ሰው ሥዕልን “እንደ ጊዜ ማሳለፊያ እና ጌጥ ነው የሚመለከተው” የምትለው ፅዮን፤ “ስዕል ጊዜ ማሳለፊያ ብቻ አይደለም ታሪክን ለመተረክ እና ነገሮን መሰነጃ መሳሪያ” መሆኑን ታነሳለች።

ሰዓሊ ጥበበ ተርፋ ከ15 ዓመታት በፊት ከሸገር ራዲዮ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “ኢትዮጵያውያን ቪዥዋል አይደለንም” ሲል ኢትዮጵያውያን ለስዕል ያላቸውን ግንዛቤ ገልጾታል።

ጥበበ በዚሁ ቃለ ምልልሱ፤ “ኢትዮጵያውያኖች ካለ ስዕል ቤታቸው ውስጥ ምንም አይነት ስዕል ሳይኖር ተደስተው ፈንጥዘው መኖር ይችላሉ። ኢትዮጵያዊ ስዕል ሳይሆን በአራቱም [የቤታቸው] መዓዘን የራሳቸውን ፎቶ ግራፍ ሰቅለው ሲደሰቱ ነው የምናያቸው” ብሎ ነበር።

ሁለቱ አርቲስቶች ይህን ግንዛቤ ለመቀየር ማህበራዊ ሚዲያን ይጠቀማሉ። በሚያዘጋጇቸው አውደ ርዕዮች ላይ የሚታደሙ ሰዎችን ስለ ጥበብ እና ስዕል የሚያስቡትን እና መረዳታቸውን ይጠይቃሉ።

እነዚሀን ቃለ ምልልሶችም በተንቀሳቃሽ ምስል አድርገው በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ይለጥፋሉ።

ፅዮን “ለብዙ ሰዎች የማይከብዱ እና ከሁሉም ሰው የእለት ተእለት ህይወት ጋር የሚዛመዱ ቪዲዮዎችን የምንሰራ ከሆነ ሰዎች የጥበብ አለም ስለ ምን እንደሆነ እና አስፈላጊነቱን ለመረዳት እንደሚሞክሩ ተገንዝበናል” ትላለች።

“ቪዲዮዎቹን መስራታችን ሰዎች እንዲሳተፉ፤ ስዕልን እንዲረዱ እና የበለጠ ለጥበብ ቀና እንዲሆኑ አስችሎናል” ስትል ታክላለች።

ከአውደ ርዕዮች እና የማህበራዊ ቪዲዮዎች በተጨማሪ ስቱዲዮ 11 የስነ ጥበብ ስልጠናዎች እና የ'ሬዚደንሲ' (ሰዓሊዎች ስራቸውን የሚያከናውኑበት እና የሚቆዩበት) ፕሮግራሞችን ይሰጣል።

የ'ሬዚደንሲ' ፕሮግራሙ ለአርቲስቶች ከቴክኒካል ክህሎት ባሻገር ያሉ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ለመስጠት ያለመ መሆኑን ፅዮን ለቢቢሲ አማርኛ ተናግራለች።

በኢትዮጵያ ያሉ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች “አርቲስት ለመሆን የሚያስችለውን ቴክኒካል ክህሎት ነው የሚሰጡት” የምትለው ፅዮን፤ የ'ሬዚደንሲ ፕሮግራሙ' ከዛ ከትምህርት ባሻገር ስላለው የስዕል ዘርፍ እንደሚያተኩር ትናገራለች።

ስራን በማህበራዊ ሚዲያ ማስተዋወቅ፣ ዋጋ ማውጣት አውደ ርዕይ ማሳየት የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ሥልጠናዎችን ይሰጣል።

ባለ ‘ኩሽኔታዎቹ’ ሴቶች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች

ታዳጊ ሴት ስኬተሮች በአዲስ ዓመት

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Girls Skaters/Instagram

የምስሉ መግለጫ, ታዳጊ ሴት ስኬተሮች በአዲስ ዓመት

በኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚዲያ አዲስ ክስተቶች መካከል ናቸው። የአገር ባህል ቀሚሳቸውን ለብሰው ስኬት ቦርዳቸውን እየነዱ እንቁጣጣሽ ሲጨፍሩ የሚያሳይ ምስል በስፋት ተሰራጭቷል።

“Ethiopian Girls Skaters” (ኢትዮጵያዊ ሴት ታዳጊዎች ስኬተሮች) ይሰኛሉ።

ከአምስት ዓመታት ገደማ በፊት ነው የተመሰረተው። በአንድ የማህበራዊ ሚዲያ ልጥፍ የተመሰረተው ቡድኑ አሁን የተመዘገበ የአገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሆኗል።

ግብሩም ከፍ ብሏል። የድርጅቱ አባላት በሳምንት አንድ ጊዜ እየተገናኙ ስኬት ቦርድ ከመንዳት አንገብጋቢ የሚሏቸው ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ይሰራሉ። የአዕምሮ ጤና፣ የህጻናት መብት እና ሴቶችን ማብቃት የሴት ታዳጊዎቹ ቡድን ኩረት የሚያደርግባቸው ጉዳዮች ናቸው።

የቡድኑ መስራች ሶስና ጫላ፤ የስኬተሮቹን ቡድን ምስረታን እንዲህ በአንደበቷ ታስታውሰዋለች።

“2010 አካባቢ ከጓደኞቼ ጋር ስኬት ቦርድ ይዘን ከከተማ ወጣ እያልን እንነዳለን። ሲኤምሲ አካባቢ።

ከወንድ ጓደኞቼ ጋር ነበር የምንሄደው፤ [እዛ የሚመጡት ሴቶች] ወንዶቹ ከሚያስሞክሯቸው ይልቅ እኔ ሳስሞክራቸው ቀለል ብሏቸው ይነዳሉ።

ስኬት ቦርድ ለአደጋ የሚያጋልጥ ስፖርት ስለሆነ ሴቶችን ሲሳተፉበት ሰዎች በተለየ መልኩ ያዩዋቸዋል። ምክንያቱም ለአካልም ለሰውነትም ብትወድቅም የሆነ አይነት ጉዳት የሚያደርስብህ ስፖርት ነው።

በተደጋጋሚ እየሄድን ስኬት የምናደርግበት አካባቢ እሁድ፣ እሁድ ነበር። ሴቶቹ ይመጣሉ እኛን ይጠብቃሉ ስንጨርስ የእኛን ስኬት ቦርድ ለመንዳት። የሆነ ፍላጎት እንዳለ እና ያንን ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል አለመኖሩን ተገነዘብኩ።

እዛ አካባቢ ስሄድ ተጨማሪ ስኬት ቦርድ ይዤ መሄድ ጀመርኩ፤ የሴቶችም ቁጥር እየጨመረ ነበር።

2011 ስኬት ቦርዲንግ ስልጠና ለመስጠት እኔም ጓደኞቼም አሰብን። የተወሰኑ ጓደኞቼ ማሰልጠን እናግዝሻለን አሉኝ እና እንየው ብለን አወራን።

ራሴ አንድ ኢንስታግራም አካውንት ከፍቼ እኔ በቀሚስ ስኬት ቦርድ እየነዳሁ ያለሁበትን ፎቶ አድርጌ ነጻ የስኬት ቦርድ ስልጠና ብዬ ለጠፍኩኝ። ብዙ ሰው ይመጣል ብዬ አልጠበኩም።

ግን ከጠበቅነው በላይ ብዙ ሰው መጣ ስልጠናውን ሰጠን በጣም ደስ ይል ነበር የመጀመሪያው ቀን። ከዛ በኋላ ነው ስኬት ቦርድ ስልጠና መስጠት የጀመርነው”

ሶስና በማህበራዊ ሚዲያ ቀጠሮ ያስያዘችው ለቅዳሜ ከሰዓት 9 ሰዓት ነበር። ስልጠናውን መውሰድ የሚፈልጉ ሴቶች በሰዓቱ አልተገኙም። “ትንሽዬ 'nervous' ሁኜ [ግራ ተጋብቼ] ነበር” ትላለች ሶስና።

ሶስና ቢበዛ ሶስት ወይም አራት ሴቶች ይመጣሉ ብላ ነበር ያሰበችው ግን ሰላሳ ገደማ ሴቶች ተገኝተዋል።

ከዛን ቀን በኋላ አዲስ አበባ ባለ ኩሽኔታዎቹ ሴቶች አዲስ አበባ ከተማ ላፍቶ አካባቢ የሚገኘው የ“አዲስ ስኬት ፓርክ” ጌጦች ሆኑ። በየሳምንቱ ቅዳሜ ረፋድ ስኬት ቦርዳቸውን ይዘው ፓርክ ይገናኛሉ።

ሶስና ጫላ “ቅዳሜ በሄድን ቁጥር ሁሌ የምንሰራቸው እና የሚመጡት ሰዎች በጣም የተለያዩ ናቸው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ትንንሽ ልጆች፣ ትልልቅ ሴቶች ይመጣሉ። ሁሉም የራሳቸው ችሎታ አላቸው” ትላለች።

እነዚህ ሴቶች ግን በስኬት ፓርክ ብቻ አልተወሰኑም። እንደ እንቁጣጣሽ እና የአድዋ ድል የመሳሰሉ የህዝብ በዓላት ላይ ስኬት ቦርዳቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ጎዳናዎች ይወጣሉ። የአገር ባህል ልብስ ለብሰው የከተማይቱ ውበት ይሆናሉ።

“አሁን ስኬት ቦርድ ከመንዳት ይልቅ እህትማማች መሆናችን አመዘነ። እርስ በእርስ መተሳሰባችን መደጋገፋችን በለጠ” ትላለች ሶስና።

The Lab፦ “የሙዚቃ ቤተ ሙከራ”

የዘ ላብ ሁነት

የፎቶው ባለመብት, Yohannes Hadish

የምስሉ መግለጫ, የዘ ላብ ሁነት

ዮሐንስ ሀዲሽ የሙዚቃ ፕሮዲውሰር እና ዲጄ ነው። 'The Lab' (ዘ ላብ) ሲል የሰየመውን የሙዚቃ ድግስ የሚያዘጋጅ ድርጅት የመሰረተው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር።

ለዚህ መነሻ የሆነው በከተማይቱ የሙዚቃ እና የመዝናኛ ትዕይንት ውስጥ የተመለከተው ክፍተት ነው።

“አዲስ አበባ ውስጥ የነበረው የሁነት ትዕይንቶች በጣም ተመሳሳይ እና ተደጋጋሚ ነበሩ። በነበሩት ሁነቶች፣ በሚደረጉት ማስታወቂያዎች በሚደረጉት ፖስተር ዲዛይኖች ደስተኛ አልነበርኩም” ይላል።

“አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ ማድረግ እችላለሁ ብዬ በማሰብ ነው ዘ ላብ የተመሰረተው” ሲል ያክላል።

ከማስታወቂያው በተጨማሪ በአዲስ አበባ የሙዚቃ ሁነቶች የሚቻወቱት የሙዚቃ ስልቶችም አያስደስትቱም ነበር።

“ውስን የሆኑ የሙዚቃ ስልቶች ነበሩ ከተማው ላይ የሚጫወቱት። አዳዲስ የሆኑ ድምጾችን ለማስተዋወቅ አዳዲስ የሆኑ ሙዚቃ ስልቶችን ማጫወት እንችላለን መሞከር እንችለለን” በሚል መነሳሳት ዘ ላብ ተመሰረተ።

ዘ ላብ እንደ ስሙ ቤተ ሙከራ ነው። ዘ ላብ ውስጥ ያሉት ሰዎች ነጭ ጋዎን ለብሰው ኬሚካል አያዋህዱም። ድምጾችን ተጠቅመው ግን ህብረ ዝማሬ ይፈጥራሉ። የዚህ ሁሉ ራስ ደግሞ ዮሐንስ ሀዲሽ ነው።

ዮሐንስ ስሙ የተመረጠበትን ምክንያት እንዲህ ሲል ያስረዳል፤ “መሞከር ነበር ፍለጎታችን። ከነበረው የተለየ ነገር ይዘን እንውጣ የሚል ነው የነበረው አላማ። ላብ መባሉ ትርጉም ይሰጣል። ላብራቶሪ ውስጥ ሙከራዎችን ነው የምትሰራው ትመራመራለህ ከሰራ ይሰራል ካልሰራ ደግሞ ወደ ሌላኛው ነገር ትሄዳለህ ስለዚህ እንደዛ ነው የምናስበው። ሁል ጊዜ ኹነት ስናዘጋጅ እየሞከርን አዳዲስ ነገሮችን ማግኘት ነው የምንፈልገው”

ዮሐንስ ሙዚቃ የጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ነው። “ይበልጥ [ሙዚቃ] መስራት የቀጠልኩት ኮሌጅ ነው” ይላል።

መጀመሪያ ሙዚቃ ማቀናበር ነበር የጀመረው። ከዛ በኋላ ለጓደኞቹ ሙዚቃን ማጫወት ቀጠለ። “አምስትም አስርም ልንሆን እንችላለን ዝም ብዬ ማጫወት ጀመርኩ” የሚለው ዮሐንስ በጊዜ ሂደት የተለያዩ ቦታዎች ሙዚቃ እንዲያጫውት ግብዣ ይቀርብለት ጀመር።

እነዚህ ተሞክሮዎች ናቸው የአዲስ አበባ የሙዚቃ መዝናኛ ዝግጅቶች ላይ ያሉ ክፍተቶችን እንዲረዳ ብሎም ዘ ላብን እንዲመሰረት ያገዙት።

ዘ ላብ ይዟቸው ከመጣቸው አዳዲስ ነገሮች መካከል የማርኬቲንግ እና የማስታወቂያ ስልት አንዱ ነው። ዘ ላብ የሚያዘጋጃቸው ሁነቶች የሚተዋወቁት በቸኩት እና በተለመዱት አይነት ፖስተሮች አይደለም።

ዮሐንስ እነዚህ የተለመዱት የማስታወቂያ ስልቶች “ሳቢ አልነበሩም” ይላል። “አንድ ሁነት አንድ ወር ከቀረው ይተዋወቅ የነበረው በፖስተሮች ነው። ተደጋጋሚ ነገሮች ይኖሩት ነበር። የሚያጓጓ ነገር የለውም” ሲል ያክላል።

“እኔ የፈለኩት ታዳሚው ጊዜው እስከሚደርስ ጓጉቶ እንዲጠብቅ ማድረግ ነበር” የሚለው ዮሐንስ ይህን ለማድረግ የሚያዘጋጃቸውን ሁነቶች በአጫጭር ቪዲዮዎች ማስተዋወቅን ነበር የመረጠው።

“ደረጃቸውን የጠበቁ ሰውን ሊስቡ የሚችሉ አይነት ቪዲዮዎች መሆን አለባቸው” የሚል ውሳኔ ላይ ደረሰ።

እነዚህ የማስታወቂያ ቪዲዮዎች ግን ለሁሉም የሚገቡ አልነበሩም።

“መጀመሪያ አካባቢ ሁነቱ ላይ ያሉም ሰዎች እየተረዱት አልነበረም” የሚለው ዮሐንስ፤ “አስቸጋሪ ነበር ወደ ገበያው እስከማስገባው ድረስ። ነገር ግን እሱም ነው ሰዉ መነጋገር መቻሉ ስለ ሁነቱ ማውራት መቻሉ ጉጉቱ መኖሩ እንዲሰራ አድርጎታል” ይላል።

የተለያዩ የሙዚቃ ስልቶችን ማጫወት ሌላው ዘ ላበ ያስተዋወቀው አዲስ ነገር ነው።

“በተለምዶ ትንሽ ስልት ነው በተደጋጋሚ የሚጫወቱት ዘ ላብ ጋር እያደረግን ያለነው የተለያየ አይነት የሙዚቃ ሥልቶችን ሰዎች እንዲያዳምጡ ነው” ሲል ዮሐንስ ይናገራል።

ሴሎ፦ ጠላ በመሃል አዲስ አበባ

'ሴሎ' ጠላ ቤት መግቢያ

የፎቶው ባለመብት, Yohannes Ayichew

የምስሉ መግለጫ, 'ሴሎ' ጠላ ቤት መግቢያ

በድሮ ጊዜ በድሮ ጊዜ ጠላ የታችኛው መደብ፤ ማዕረግ የሌላቸው ሰዎች የሚጠጡት መጠጥ ነበር። የገዢው መደብ አባል የሆኑት ባላባቶች እና ባለማዕረጎች ጠጅ ተራው ባላገር ደግሞ ጠላ ይጠጣሉ።

ኧረ ጠጅ ጥሎ የተገኘ ይቀጣ ነበር ሁሉ። አጼ ዮሐንስ ናቸው አሉ ይህን ልማድ ያስቀሩት።

በጠጅ እና ጠላ መካከል ያለው የመደብ ልዩነት እንዲቀር ቢደረግም፣ ከኢትዮጵያ ባህላዊ መጠጥ ሲባል ስሙ የሚጠራው ግን ጠጅ ነው።

ይህን ጉዳይ ከታዘቡት ሰዎች መካከል አንዱ ዮሐንስ አይቼው አንዱ ነው። ዮሐንስ ለአስር ዓመታት ገደማ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ሰርቷል። ከውጭ አገር ጎብኚዎች ጋር በቅርበት የሰራው ዮሐንስ እነዚህ ጎብኚዎች፤ “ብዙ ጊዜ የሚያገኙት የነበረው እንጀራ የተለመደ ነው ከዛ ጠጅ ነው። ጠላ ደግሞ ብዙ ጊዜ አይገኝም” ይላል።

ጠላን የማሳደግ ሃሳብ የነበረው ዮሐንስ ይህ ጉዳይ ብዙ ያሳስበው ነበር። በኮሮናቫይረስ ወረርሽ ምክንያት የዓለም እንቅስቃሴ ሲቆም ዮሐንስም በቱሪዝም ዘርፉ መቀጠል አልቻለም።

“ይህን ጊዜ በኮሮናቫይረስ ሰዓት ቱሪዝሙ ሲቆይ በሃሳቤ የነበረውን ወደ ተግባር ላምጣው ብዬ ወደ ጠላ ጠመቃ ገባሁ” ይላል።

ከዚህ ሃሳብ ነው ሴሎ ጠላ ቤት የተወለደው።

“ጠላ መጥመቅ እናቶች በእጃቸው ያለ ሙያ በእጃቸው ያለ እውቀት ነው ግን ወደ ገበያ መውጣት እንደሚችል አልገባቸውም አልተረዱትም ነበር” የሚለው ዮሀንስ ያንን ጠላ በትልቁ ገበያ ላይ መዋል እንሚችል ለማሳየት ‘ሴሎ’ን እንደከፈተ ይገልጻል።

‘ሴሎ’ እስከ ስምንት የጠላ አይነቶች አሉት። እያንዳንዱ የጠላ አይነት በሚጠመቅበት ግብዓት ይለያል። ከስንዴ የሚዘጋጀው እና መብረቅ የተሰኘው ጠላ ትንሽ ጠንከር ይላል።

ከማር፣ ከዳጉሳ እና ከገብስ የሚጠመቁ የጠላ አይነቶችም አሉ።

የ‘ሴሎ’ ጠላ በግብዓቱ ብቻ ሳይሆን በአቀራረቡም ይለያል። ጠላው የሚቀዳው በታጠነ ገንቦ ነው።

‘ሴሎ’ እና ‘ሶሻል አዲስ’ ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ የመጀመሪያውን የጠላ ድግስ አዘጋጅተዋል። የጠላ ማኅበር ልንለው እንችላለን። በዚህ የጠላ ድግስ ሁሉም የጠላ አይነቶ፣ የክራር ሙዚቃ፣ እና ሌሎች ጨዋታዎች ነበሩ።

መጀመሪያ ሴሎ ጠላ ቤት የተከፈተው በመሃል ቦሌ ነበር። ከቦሌ መድኃኔዓለም ጀርባ።

ከ‘ሴሎ’ ጠላ ቤት ጋር አንድ ላይ “ያላ ሑሙስ ባር”ን ከሌሎች ሁለት ጓደኞቹ ጋር ከፈተ። ያላ በመካከለኛው ምስራቅ የሚዘወተሩትን ከሽምብራ የሚሰራውን ሑሙስ፣ ፉል እንዲሁም ከደበርጃን የሚዘጋጀውን ባባ ገኑሽ የመሳሰሉ ምግቦችን ያቀርባል።

እነዚህን ሁለት ቦታዎች በአንድ ላይ የሚያቅፍ The Social Addis (ዘ ሶሻል አዲስ) የተባለ ቦታ ደግሞ በቅርቡ ከፍተዋል። ሴሎ እና ‘ያላ’ ከቦሌ መድኃኔዓለም ወደ አትላስ አካባቢ ቦታ ቀይረዋል።

‘ሶሻል አዲስ’ አዳዲስ አርቲስቶችን የሚወጡበት፥ ሰዎች የሚገናኙበት የመዝናኛ ቦታ ነው።

ዮሐንስ ከጓደኞቹ ጋር እነዚህ ቦታዎች የከፈታቸው “አዳዲስ መድረክ ለማያገኙ አርቲስቶችን ዕድል ለመስጠት” መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

‘ሶሻል አዲስ’ የሙዚቃ አልበም ያወጡ አርቲስቶች ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት፣ እንዲሁም የሙዚቃ ዝግጅቶች የሚቀረጹበት ቦታ ሆኗል።

ማክሰኞ እና ረቡዕ ደግሞ ፊልሞችን ያሳያሉ። በ‘ሶሻል አዲስ’ የሚታዩት፤ “community based (ኮሚዩኒቲ ቤዝድ) የሆኑ ፊልሞችን ነው የምናሳየው” የሚለው ዮሐንስ፤ “ከማህበረሰብ ጋር ግንኙነት ያላቸው ፊልሞችን ነው ለማቅርብ የምንፈልገው” ይላል።

በ‘ሶሻል አዲስ’ የስዕል አውደ ርዕዮችም ይካሄዳሉ። እስካሁን ከአምስት በላይ ርቲስቶች አውደ ርዕያቸውን በ‘ሶሻል አዲስ’ አሳይተዋል።