እስካሁን የተመዘገቡ በእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያጋጠሙ የፊደላት እና የቃላት ስህተቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቲቲቪለስ በመካከለኛው ዘመን አውሮፓውያን አፈ ታሪክ ውስጥ የሚገኝ ክፉ መንፈስ ነው። ዲያቢሎስ ልንለው እንችላለን።
የዚህ ክፉ መንፈስ ሥራ ስህተቶችን ሆን ብሎ መሰብሰብ እንደሆነ ይታመናል። በተለይ ደግሞ ስህተቶቹ በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በፀሎቶች እና በመነኮሳት አንደበቶች ላይ ካገኘ ይመዘግባል።
በኋላም የፍርድ ቀን ሲመጣ ግለሰቡን በኃጢአት ለመወንጀል እንደ ማስረጃ ይጠቀምባቸዋል ተብሎ ይነገርለታል።
በእኛ አገር 'ሰይጣን አሳስቶኝ ነው' ከምንለው መለስ ያለ የአውሮፓውያኑ የስህተት ማላከኪያ ይመስላል።
ይህንን ክፉ መንፈስ "ዲያቢሎስ" አንድ መነኩሴ አግኝተው ማንነቱን ሲጠይቁት "ምስኪን ዲያቢሎስ ነኝ፤ ስሜም ቲቲቪለስ ይባላል" ብሎ መመለሱ በአፈ ታሪኮቹ ውስጥ ይነገራል።
ይህ በየዕለቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስህተቶችን በከረጢት እየሰበሰበ የሚያስቀምጠው ክፉ መንፈስ ከአፍ ድልጫ እስከ ጽሑፍ ግድፈት፣ ከሚነበነብ ፀሎት፣ ፊርማ እስከሚያርፍበት ሰነድ ስህተቶችን ሲለቅም ይውላል።
ይህንን ካላደረገ ራሱ ክፉ ቅጣት እንደሚጠብቀው ያምናል ይላሉ የአፈ ታሪኩ ባለቤቶች አውሮፓውያን።
የተሠሩ ስህተቶች በሰው ዘንድ ቢረሱ ይህ ክፉ ግን አይረሳቸውም።
አንዳንዴ እነዚህ ስህተቶች ከክፉ መንፈሱ ከረጢት አልፈው በእያንዳንዱ ሰው ትውስታ ውስጥ የመታተም አቅም ያገኛሉ።
በባሕል ውስጥ ተረት ሆነው፣ ታሪክ ሆነው እየተነገሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋሉ። በተለይ ደግሞ ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ስህተቶች የምጽአት ቀን ከመድረሱ በፊትም በሰው ፊት የፍርድ አደባባይ ያስቆማሉ።
እንግሊዛዊው ሮበርት ባርከርን እዚህ ላይ መጥቀስ ጥሩ እማኝነት ነው።
በአውሮፓውያኑ 1600 ሃብት የበዛለት፣ የቤተመንግሥት ደጃፍ ያለ ማንኳኳት የሚከፈትለት ማተሚያ ቤት የነበረው ግለሰብ ነበር።
በዘመኑ ይህንን ሃብት ያገኘው ለፍቶ ጥሮ ግሮ አልነበረም፤ ከአባቱ ወርሶ ነው።
አባቱ ይህንን የማተሚያ ቤት ንግድ ሥራ በ1589 አቋቁሞ ቤተሰቡ በእንግሊዝ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን እያተመ አንዲሸጥ የሚያስችል ፈቃድን ከንግሥት ኤልሳቤጥ ቀዳማዊ አግኝቷል።
ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ አዳዲስ የእንግሊዘኛ ዕትሞች ሲኖሩ አትሞ ለአንባቢው ማቅረብ የዚህ ቤተሰብ ኃላፊነት ነው።
ለዚያም ነው በስፋት የተሠራጨው እና በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙት የኪንግ ጀምስ ስድስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ህትመቶች በዚህ ቤተሰብ ጫንቃ ላይ የወደቁት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ ባርከር የኪንግ ጀምስ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ተቀብሎ ከአንድ ዓመት በኋላ አትሞ አስረከበ። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በተለያዩ ስህተቶች የተሞላ ነበር።
በዚህ የእንግሊዘኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ህትመት ላይ በመጽሐፈ ሩት ምዕራፍ 3፡15 ላይ በተፈጠረው ስህተት ምክንያት የተነሳ በአውሮፓውያኑ 1611 ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጎሞች በመሆን ተሠራጭቷል።
በዚህ ቦአዝን በሚጠቅሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ "በላይሽ የደረብሽውን ልብስ አቅርቢልኝ፤ ዘርግተሽም ያዢው አላት፤ ዘርግታ እንደያዘችም ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰፍሮ አሸከማት፤ ከዚያም ወደ ከተማ ተመለሰች" የሚለው ክፍል ላይ "ከዚያም ወደ ከተማው ተመለሰ" የሚል ስህተት ተሠርቷል።
በዚህም የተነሳ "ታላቁ የእርሷ መጽሐፍ ቅዱስ" እና "ታላቁ የእርሱ መጽሐፍ ቅዱስ" በሚሉ ሁለት ዕትሞች ተሠራጭተዋል።
ይሁን አንጂ ይህች ስህተት አይደለችም የዚህን ቤተሰብ የማተሚያ ቤት ሥራ ዕጣ ፈንታ ከአፈር የደባለቀችው።
ከ20 ዓመት በኋላ ማተሚያ ቤቱ ሌላ የእንግሊዘኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያትም የፈጠረው የቃላት ግድፈት፣ ዝንፈት ብቻ ሳይሆን ያስቀረው ቃል እጅግ የከፋ ሆኖ በታሪክ ሰነድ እንዲሁም ስህተቶችን በሚሰበስበው ክፉ መንፈስ ወይንም ዲያቢሎስ ረገድም ተመዝግቦለታል።
በ1631 ባርከር ከማርቲን ሉቃስ ጋር በመሆን ሌላ የኪንግ ጀምስ መጽሐፍ ቅዱስ አተመ።
ያኔ የቲቲቪለስ ስህተት መሰብሰቢያ አቁማዳ ዳግም እንዲሞላ አደረገው። ይህ ስህተት የተገኘው ደግሞ ኦሪት ዘዳግም 5፡24 ላይ ነው።
ስህተቱ በእንግሊዘኛው ቃል ላይ የተመሠረተ ነው። greatness የሚለው ቃል great-asse በሚል ተተይቧል።
ስለዚህ "እነሆ፥ አምላካችን እግዚአብሔር ክብሩንና ታላቅነቱን አሳይቶናል፥ ከእሳቱም ውስጥ ድምፁን ሰምተናል፤ እግዚአብሔርም ከሰው ጋር ሲነጋገር ሰውዮውም በሕይወት ሲኖር ዛሬ አይተናል" የሚለው ክፍል ታላቅነቱን የሚለው "his great ass" በሚል ተተርጉሟል።
የማተሚያ ቤቱ ባለንብረቶች በዘመኑ እጅጉን ዕድለኛ ነበሩ ማለት ይቻላል። asse የሚለው ቃል ትርጉም ዛሬ ያለውን ፍቺ ገና አላገኘም ነበር። ያ ባይሆን ኖሮ "እግዚአብሔር ታላቅነቱን እና . . . . አሳየ" በማለታቸው ይደርስባቸው የነበረውን መገመት ቀላል ነው።
ነገር ግን በወቅቱ ለህትመት የበቃውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ዝነኛ ያደረገው ግን ይህ የቃላት ግድፈት አይደለም።
በኦሪት ዘፀአት 20፡14 ላይ ከሰፈሩት አስርቱ ትዕዛዛት መካከል አንዲት የቃል ግድፈት ተገኝታለች። በዚህም የተነሳ ትርጉሙ ተዛብቶ "አታመንዝር" የሚለው ትዕዛዝ "አመንዝር" የሚል ነውርን የፈቀደ አስመሰለው።
ኦሪት ዘፀአት 20፡14 "አታመንዝር።"

በሺህዎች የሚቆጠር የመጽሐፍ ቅዱሱ ህትመት ከተሠራጨ ከዓመት በኋላ ስህተቱ ታየ። በካህኑ ጴጥሮስ ሄይሊን (1599-1662) እንደተመዘገበው ቅጣቱ እጅጉን ከባድ ነበር።
"የንጉሡ አታሚዎቹ ከአስርቱ ትዕዛዝ በሰባተኛው ላይ "ኖ" የሚለውን ቃል በመግደፋቸው በእንግሊዘኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳፋሪ ስህተት ሠርተዋል" ነበር ያለው።
በወቅቱ የተፈጠረው ስህተት በለንደኑ ጳጳስ በኩል ለንጉሡ የተነገረ ሲሆን፣ አታሚዎቹ ንጉሡ ፊት እንዲቀርቡ ተደርጓል።
የተሠራው ስህተት ቀርቦ በዝርዝር ከታየ በኋላ ተገቢ የተባለ ቅጣት እንደተጣለባቸው ተገልጿል።
ከቅጣቱ ባሻገርም ባርከር እና ሉቃስ የማተሚያ ቤት ፈቃዳቸው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰርዟል።
ይህም ከማተሚያ ቤት ሥራ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲሰናበቱ እና ኪሳራን እንዲከናነቡ አድርጓቸዋል።
ባርከር በ1635 ባለ ዕዳ ሆኖ ዘብጥያ የተወረወረ ሲሆን፣ ከአስርት ዓመታት በኋላ በዚያው በማረሚያ ቤት ሕይወቱ አልፏል።
የቃላት ግድፈት የተሠራባቸው መጽሐፍ ቅዱሶች በሙሉ ተሰብስበው እንዲወገዱ ተደርጓል።
አንዳንዶች ግን ምናልባትም እጅግ በጣም ጥቂቶቹ በግለሰቦች እጅ የሚገኙ ሲሆን፣ ዛሬም ድረስ "እርኩሱ መጽሐፍ ቅዱስ"፣ "ማመንዘርን የፈቀደው መጽሐፍ ቅዱስ" ወይም "የኃጥአን መጽሐፍ ቅዱስ" በመባል ይታወቃል።
ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ የተሠራው ትልቁ ስህተት ቢሆንም በተለያዩ የእንግሊዘኛ ዕትሞች ላይ የተለያዩ የቃላት ግድፈቶች ተከስተው ያውቃሉ።
ከዚህ በፊት ማቲዮስ 10፡34 ላይ ያለው ቃል "እኔ የመጣሁት ሰላምን በምድር ለማስፈን አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ. . ." የሚለው መልዕክት ከግሪኩ የተወሰደው ቃል ላይ የትርጉም ስህተት በመፈጠሩ "ሰይፍ" የሚለው በደስታ ተተክቶ ነበር።
ይህ ስህተት የተፈጠረው ሰይፍ ለሚለው የግሪክ ቃል 'gladium' ደስታ በሚለው 'Gaudium' ግድፈት በመፈጠሩ ነው። "እኔ የመጣሁት ሰላምን በምድር ለማስፈን አይምሰላችሁ፤ ደስታን እንጂ. . ." በሚል ተተካ ማለት ነው።

በእንግሊዘኛ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የታዩ የቃላት ግድፈቶች
ሌላው በህትመት ወቅት የተፈጠረ የፊደል ግድፈት የታየው በ1562 በታተመው የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ህትመት ላይ ነው።
በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ህትመት ላይ "peacemakers" የሚለው ቃል "placemakers" ተብሎ የተጻፈ ሲሆን፣ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 21፡ 3 ላይ "God commends the poor widow," (አደነቃት) የሚለው "God condemns the poor widow" (አወገዛት) በሚል ታትሟል።
ይህ ስህተት የተፈጠረው 'condemns' እና 'commends' የሚሉት ቃላት ላይ በተፈጠረ የትየባ ስህተት የተነሳ ነው።
የክፍሉ ሙሉ ቃል በአዲሱ መደበኛ ትርጉም ላይ አንዲህ ይነበባል።
"እውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት ከሁሉም የበለጠ ጨመረች። እነዚህ ሰዎች የሰጡት ከትርፋቸው ላይ ሲሆን፣ እርሷ ግን የሰጠችው ከጉድለቷ ያላትን መተዳደሪያዋን በሙሉ ነው።"
እንደገና በ1653 'ኖ' የሚለው ቃል ተገድፎ ሌላ ውዥንብር ተከስቶ ነበር።
1ቆሮንጦስ 6፡9 ላይ ሁለተኛው አፍራሽ ቃል በገደፉ የተሳ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው "አመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አንደማይወርሱ አታውቁምን?" የሚለው ቃል "እንደሚወርሱ" ተብሎ ታትሞ ነበር።
ዳግም በ1763 ሌላ 'ኖ' ተገደፈች። መዝሙረ ዳዊት 14፡1 ላይ "ሞኝ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል" የሚለው ክፍል "ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር አለ ይላል" ተብሎ ታትሟል።
ሌላኛው ስህተት ደግሞ የተፈጠረው በሉቃስ 23፡32 ላይ "ከእርሱ ጋር እንዲገደሉ ሌሎች ሁለት ወንጀለኞችን ወሰዷቸው" የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል "ሌሎች ሁለት ወንጀለኞችም አብረውት ነበሩ" ተብሎ ታትሟል።
በ1612 የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ደግሞ መዝሙረ ዳዊት 119፡161 "ገዢዎች ያለ ምክንያት አሳደዱኝ" የሚለውን "አሳታሚዎች ያለምንክንያት አሳደዱኝ" ተብሎ ታትሟል። 'ፕሪንስስ' የሚለው ቃል በፕሪንተርስ ተሳክሮ ማለት ነው።
በ1682 በታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ደግሞ ዘዳግም 24፡3 "ሁለተኛውም ባል ቢጠላት፥ የፍችዋንም ጽህፈት ጽፎ በእጅዋ ቢሰጣት፥ ከቤቱም ቢሰድዳት፥ ወይም ሚስት አድርጎ ያገባት ሁለተኛው ባልዋ ቢሞት. . ."
ሁለተኛው ባል ቢጠላት የሚለው ቢበላት በሚል ታትሟል። "hates her" የሚለው ተገድፎ "eats her" ተብሎ ታትሟል።

የፎቶው ባለመብት, Sepia Times/Universal Images Group via Getty Images
በመጽሐፍ ቅዱስ ህትመት ወቅት የሚከሰቱ የቃላት ግድፈቶች ከጥንት ጀምሮ የነበሩ እና ዲያቢሎሱ ቲቲቪለስ እየሰበሰበ እና እያሳሳተ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቀጥሏል።
በ1966 በታተመው መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክፍል ውስጥ የእንግሊዘኛዋ 'r' ተገድፋ "Pray for peace" የሚለው "Pay for peace" በሚል ታትሟል።
በዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕትመት ላይ 'no' ዳግም ተገድፋለች።
በ1970 ደግሞ ዮሐንስ 1፡5 ላይ "ከርሱ የሰማነው ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት፣ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በርሱ ዘንድ ከቶ የለም።" የሚለው ክፍል ". . . ጨለማም በርሱ ዘንድ ከቶ አለ" በሚል ታትሟል።
እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ በ1989 በነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ህትመትም ላይ የታዩ የፊደል እና የቃል ግድፈቶች አሉ።
መልካሙ ነገር የብሉይ እና አዲስ ኪዳን ታሪኮች በሚገባ የሚታወቁ በመሆናቸው የሚፈጠሩ ስህተቶች ወዲያው ተለይተው እንዲታረሙ ይደረጋሉ።
ግን በቅዱስ መጻሕፍት ላይ ከ1285 ጀምሮ ስህተት ሰርጎ እንዲገባ፣ ከመተየቢያው ላይ ቃልን የሚያስቀር፣ የሚያዛባ፣ የሚገድፍ፣ ቲቲቪለስ የተባለ እርኩስ መንፈስ ዛሬም ድረስ አብሮን ሳይኖር አይቀርም።















