ጉራጊኛን ለጃፓኖች የምታስተምረው ጁንኮ ያማማቶ

የፎቶው ባለመብት, ጁንኮ ያማማቶ
ጁንኮ ያማማቶ የቶኪዮ ልጅ ናት።
ቶኪዮ ግዙፍ ናት፤ ሕዝቡም ቀልብ የለውም። ሽው-እልም ነው።
14 ሚሊዮን ሕዝብ ይርመሰመሳል። ይወጣል ይወርዳል። ጁንኮ ተረጋግታ እስክስታ ትወርዳለች።
ሙዚቃ ትወዳለች። ቢከፋት ቢከፋት “ጃፓኗን ወድጄን” ታዜማለች።
ብቻዋን አይደለችም። መአት ተማሪዎች አሏት። አድናቂዎችም እንዲሁ፤ በቶኪዮም- በኪዮቶም፣ በኦሳካም።
ጁንካ ያማማቶ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ፍቅር ከወደቀች ዐሥርታት ተቆጥረዋል። አሁን ጉራጊኛ ውዝዋዜን ለጃፓናዊያን ታስተምራለች።
ጉራጊኛ ብቻ አይደለም ታዲያ። ወላይትኛም፣ ምንጃርኛም፣ የጎጃም እንቅጥቅጥም አይቀራትም።
በባሕል ልብስ ደምቃ፣ የመቀነቷን ጫፎች ይዛ የጎንደር ‘ጉች ጉች’ እና ‘ሰክስክ’ ስታስነካው የደባርቅ እንጂ የሩቅ ምሥራቅ ሴት አትመስልም።
ከአንገቷ ሰበር፣ ከወገቧ ዘንበል እያለች ድስቅ፣ እንዝርት፣ ዋንጫ ለቅልቅ ትሞክራለች።
ይልቅ ጃፓናዊያን የእስክስታ ተማሪዎቿ ያስቃሉ። ክብ መስመር ሠርተው ‘ዋንጫ ለቅልቅ’ ሲሞክሩ እንደማየት አዝናኝ ነገር የለም።
ጁንኮ ያማማቶ በፊት በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ሳይቀር እየገባች በሳምንት ቅዳሜ የብሔር ብሔረሰቦችን ውዝዋዜ ታስተምር ነበር፤ ለአገሯ ሰዎች። ለጃፓኖች። እንዲሁም ለአንዳንድ ሐበሾች።
ኮቪድ ይህን ሳምንታዊ መርሐ ግብር ገታው።
የጁንኮ ያማማቶ እስክስታ ግን ተገታ እንዴ? አልተገታም።
ጃፓን በቀላሉ እጅ አይሰጥም። ትምህርቱን በርቀት ቀጠለችው። ዳንስን በርቀት ደግሞ እንዴት ያለ ጉድ ነው?
ጉራጊኛን በርቀት

የፎቶው ባለመብት, ጁንኮ ያማማቶ
በ’’ዙም’’ (zoom) ውዝዋዜን መማር ፣ ዉሃ ሳይነኩ ዋናን እንደመማር ያለ ከንቱ ትግል ይመስላል። ይመስላል እንጂ አይደለም።
የርቀት ተማሪዎቿ በንቃት ይሳተፋሉ። ገለጻዋን በጥሞና ይሰማሉ።
የትከሻቸው ሎሚ እንኪወልቅ ይንቆራጠጣሉ። ክፋቱ እስክስታው አልታዘዝ ይላቸዋል።
አንዳንዶቹ ልብ ብሎ ለተመለከተ፣ የኬጂ ተማሪዎች በግድ ጨፍሩ ሲባሉ የሚያሳዩት ዐይነት አስቂኝ ትዕይንትን ያስታውሳሉ።
ጃፓኖች ጉራጊኛን ለመማር የሚያዩት ፍዳ! በሌላ ሥራ ላይ ቢያውሉት ብዙ ሮቦት ያመርቱበት ነበር ተብሎ ቢቀለድ ልፋታቸውን ይገልጸዋል።
ቢቢሲ የተመለከተው የዙም እስክስታ ትምህርት ፈገግ የሚያሰኝ ነው።
ለምሳሌ ተማሪዎቿ የርሷን “ከትከሻ ነቀል-ከወገብ ዘንበል-ከተረከዝ ፈንጠር” ገለጻ እየሰሙ ድንገት ይነሽጣቸውና ከወንበራቸው ተስፈንጥረው ጉራጊኛን ያስነኩታል።
እስክስታውን ይወርዱታል። ሳሎናቸው ውስጥ። በረንዳቸው ላይ። ወይም የትም። ብዙዎቹ ትምህርቱን ከቤታቸው ሆነው እንደሚከታተሉ ከምሥሉ ማየት ይቻላል።
እንጃ ብቻ የዙም ዳንስ ያስቃል።
ጃፓናዊ ተማሪዎቿ በተለይ ‘’ቅቤ መናጥ’’ የሚባለውን የእስክስታ ዓይነት ሲሞክሩ መሬት ላይ የኤሌክትሮኒክስ ብሎን ወድቃባቸው እየፈለጉ ነው የሚመስሉት።
ቢሆንም ገና ተማሪዎች ናቸው። ጉጉትና ደስታ ከፊታቸው አይጠፋም።
ክድን ያሉት ዐይኖቻቸው ይስቃሉ። ጃፓናዊያን በዐይን መሳቅን ያውቁበታል።
ደግሞ ጃፓናዊያን ብቻ አይደሉም የዙም ተማሪዎቿ። ከጃፓን ብቻም አይደሉም እንግዶቿ። አንዳንዴ ኢትዮጵያዊያንን ትጋብዛለች።
“ከዲሲ ባለማሲንቆ ዘፋኞችን ፕሮፌሽናል ተወዛዋዦችንም ከዲሲ እንጋብዛለን” ትላለች፣ ጁንኮ ያማማቶ።
ደግሞ የዙም ትምህርቱ ላይ አንዳንድ ጃፓናዊያን የጎንደርን ‘ጉች ጉች’ ተንበርክከው ሲደንሱ በንሸጣ ከዙም ካሜራ ዕይታ መውጣታቸውን ይረሱታል። ከቀልባቸው አይደሉማ።
በዚህ ጊዜ የዙም ዳንስ ጉባኤው ድብልቅልቁ ይወጣል። እሷም ከተማሪዎቿ የምትፈልገው ይህንኑ ነው። እንዲደበላለቁ፤ ልባቸው እስኪጠፋ እንዲጨፍሩ።
የጁንኮ ያማማቶ ጌጣ ጌጦች

የፎቶው ባለመብት, ጁንኮ ያማማቶ
ጁንኮ ደረቷ ላይ በርካታ ጌጣ ጌጥ ደርድራለች። ‘ድስቅ’ ለተሰኘው እስክስታ እንዲሆናት ነው።
በዚህ የውዝዋዜ ወቅት አንገት ላይ ያለ ጌጥ ከደረት ጋር እየተላተመ ሲንሳፈፍ ልዩ ዉበት ያጎናጽፋል። እሷም አውቃበታለች።
የጌጣጌጥ ሱቅ-በደረቴ መስላ ነው ሁልጊዜ መድረክ የምትይዝ።
ሙዚቃው ሲለኮስ የትም ትሁን እምር ብላ ትነሳለች። ልቧ እስኪቀልጥ ትጨፍራለች።
ጁንኮን የሚያስጌጣት የአንገት-ጌጥ፣ የእጅ አንባርና የጆሮ ጉትቻ ብቻ መቼ ሆነና። የቤቷ ቁምሳጥን በሐበሻ ቀሚስ ተጣቦ የለም እንዴ።
ቢቆጠር ከ20 አይበልጥም?
የትግሬ ሽፎን፣ የጉራጌ ሸማ፣ የዶርዜ ጥበብ፣ የኦሮሞ፣ የወሎ ባሕላዊ አልባሳት ታጭቀዋል።
‘ኪሞኖ’ የሚሉት የጃፓን ባሕላዊ ቀሚስ አለ። ጁንኮ ግን ከኪሞኖ በላይ ሐበሻ ቀሚስ ታዘወትራለች።
በጀፓን ደንብ እጅ ነስተን ወደ ማድቤቷ እንዝለቅ?
ሙቀጫና ዘነዘና፣ ሲኒና ጀበና በቶኪዮ ኩሽናዋ ተሰድረዋል።
ጀበናዎቿ ቀለማቸው አንድ ይሁን እንጂ ቅርጻቸው ለየቅል ነው። ቅል ያለው አለ፣ ጥምዝ እጀታ ያለው አለ፣ ግማሽ ክብ አለ።
አንድ ወሳኝ ጀበና ነው አሁን ከቤቷ የጎደላት።
“የጉራጌ ጀበና ፈልጌ አስፈልጌ አጣሁ” እያለች ታማርራለች።
ልቧ እስኪጠፋ ጉራጊኛ እየጨፈረች የጉራጌ ጀበና እንዴት እንዳጣች ለሷም እንቆቅልሽ ነው።
ከጥሬ ስጋና ከሽሮ ለጃፓን የቱ ይቀርባል?

የፎቶው ባለመብት, ጁንኮ ያማማቶ
ጁንካ ያማማቶ ውዝዋዜን ብቻ አይደለም ከኢትዮጵያ የወረሰችው። ምግቡም ይስማማታል። እንጀራው፣ ወጡ፣ ጥሬ ሥጋውም አይቀራት። ቢጠፋ ቢጠፋ ምጥን ሽሮ ከቤቷ አይጠፋም።
ከሽሮና ከጥሬ ሥጋ የቱ ይስማማሻል ስትባል አታቅማማም። ‘’ጥሬ ሥጋ ነዋ!’’
ጥሬ ሥጋ ብዙ ፈረንጆችን ያስበረግጋል። ለሷ ግን በጭራሽ። ጁንኮ ያማማቶ-እጅ አትሰጥም ከቶ። በመልክ በመልኩ እየቆረጠች ታጣጥመዋለች።
“ጥሬ መብላት እኮ የኢትዮጵያ ባሕል ብቻ አይደለም፤ እኛ ጃፓኖች ለምሳሌ ሳሺሚ የሚባል ጥሬ ዐሣ የመብላት ባሕል አለን።"
ጁንኮ ያማማቶ ከጃፓን ወደ አዲስ አበባ ስትገባ ተስገብግባ ሥጋ ቤት ነው የምታቀናው። “እስኪ ማነህ ጮማ ያልበዛበት...” ትል ይሆናል እኮ ይሄኔ። አማርኛ ትሞካክራለች።
‘’በሽታ ምናምን አትፈሪም ግን?’’ ስትባል ከጃፓን Bullet train የፈጠነ ምክር ትለግሳለች።
“when indulging in raw meat, don’t forget to have some ARAKE alongside!’’ (ጥሬ ከበላህ አረቄ ስለመከተሉ እርግጠኛ ሁን።”
‘’ኢትዮጵያን ያወቅኳት ባጋጣሚ ነው’’

የፎቶው ባለመብት, ጁንኮ
ጃፓናዊቷ ጁንኮ ኢትዮጵያን እንዴት አወቀች?
ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያን ሙዚቃ የሰማችበት ዕለት እንደ ትናንት ታስታውሰዋለች። ነገሩ የሆነው ግን ከ21 ዓመታት በፊት ነው።
አንድ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ውስጥ ቁጭ ብላ እራት እየተመገበች ነበር። ምሽቱ የፈረንጆች አዲስ ዓመት ዋዜማ ነው።
በጃፓን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድንገት እልልታውን አቀለጡት። ድብልቅልቅ ያለ ሙዚቃ መሰማት ጀመረ። ጭፈራው ደራ። ቤቱ በአንድ እግሩ ቆመ።
በጭራሽ እንዲህ ዓይነት ሙዚቃ ሰምቼ አላውቅም ነበር ትላለች ጁንኮ ያማማቶ።
“ጃፓናዊት እንደመሆኔ ለዚህ የሙዚቃ ምት ጆሮዬ ፍጹም ባዳ ነበር። ይሄ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ግን ተለየብኝ። ያን ቀን በኢትዮጵያ ሙዚቃ ፍቅር ወደቅኩ።”
ኢትዮጵያና ጃፓንን የሚያመሳስላቸው ምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, ጁንኮ
እንደ ሕዝብ ምስስሎች አለ ትላለች። ለምሳሌ ሙዚቃቸው።
አንደኛ ሁለቱም ፔንታቶኒክ ስኬል አላቸው። ሁለተኛ የትንፋሽ መሣሪያዎቻቸው ይመሳሰላል።
“ለዚያ ይመስለኛል ጃፓናዊያን የኢትዮጵያ ሙዚቃን ስንሰማ ቶሎ ጆሮ ገብ የሚሆንልን”
እንደ ሕዝብስ ምን ያመሳስለን ይሆን? ጁንኮ ምላሽ አላት።
ሁለቱም ሕዝቦች ቁጥብ ናቸው። ጃፓኖችም ሐበሾችም የበዛ ትሁትነት አላቸው።
ለምሳሌ በርከክ ብሎ እጅ መንሳት የጋራ ነው።
“እናንተም ጋ ታላላቆችን ጎንበስ ብሎ ሰላም ሲሉ አይቻለሁ” ትላለች።
ሌላስ? ሁለቱም ሕዝቦች እንግዳ ተቀባይ መሆናቸው?
አዎ! በእርግጥም ይህም ያመሳስላቸው ይሆናል። ጆንኮ አንድ አባባል ታነሳለች። “ጉዞ አዲስና አስደናቂ ነገሮችን የምናይበት አጋጣሚ ነው”
ለርሷ ግን ይሄ ጥቅስ አልሠራም።
“እኔ ግን ልንገርህና ኢትዮጵያ ስሄድ በቃ ጃፓን ያለሁ ያህል ነው የሚሰማኝ። እንዲያውም ጃፓን ስመለስ ለምን ሐበሻ ጓደኞቼ አብረውኝ እንደሌሉ እገረማለሁ። ይህን ያህል ተመሳሳይ ስሜት አስተናግዳለሁ። “ትላለች።
በሥራ አጋጣሚ ቶኪዮና አዲስ አበባ ትመላለሳለች። ሩቅ ምሥራቅና ምሥራቅ አፍሪካ በስሜትም በባሕልም ይምታቱባታል።
“በጃፓንና በኢትዮጵያ መካከል 10ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት አለ። እኔ ልብ ውስጥ ግን ርቀቱ 1 ኪሎ ሜትር አይሞላም። ትላለች።
ጃፓኖች ኢትዮጵያን ያውቃሉ?

የፎቶው ባለመብት, ጁንኮ
በጁንኮ አመለካከት ጃፓናዊያን ኢትዮጵያን የሚመለከቱበት መነጽር በትውልድ ይለያያል።
የቀድሞው ትውልድ ኢትዮጵያን ያውቃል። የአሁኑ ግን አምብዛምም ነው።
ለምሳሌ የጃፓን ንጉሣዊ ቤተሰብ ከንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ጋር መልካም ግንኙነት ነበረው።
እንዲያውም ትላለች ጁንኮ፤ እንዲያውም አንድ የኢትዮጵያዊ ልዑል ጃፓናዊ ማግባት እንደሚፈልግ ተናግሮ ይህ በጃፓን ጋዜጣ ታትሞ ነበር፤ድሮ።
ማን ይሆን ይሄ የኢትዮጵያ ልዑል?
አበበ ቢቂላም ሌላው ጃፓንና ኢትዮጵያን ያዋደደ ሰው ነው። የቶኪዮ ኦሎምፒክን ማሸነፉ በጃፓናዊያን ዘንድ የሚዘነጋ አይደለም።
በዕድሜ ገፋ ባሉ ጃፓናዊያን ዘንድ ይህ የአቤ ትዝታ አለ። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ራሱ ስለኛው አቤ ጠንቅቀው ያውቁ እንደነበር ተናግረዋል።
የ2000 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ጊዜ የአበበ ቢቂላ ልጅ ጃፓንን በተደጋጋሚ ጎብኝቷል። ግንኙነቱ በትውልድ ቀጥሏል።
በዚህ ዘመን ግን ትላለች ጁንኮ፤ አዲሱ የጃፓን ትውልድ ስለ ኢትዮጵያ ብዙ አያውቁም። “የኢትዮጵያን ውብ ባሕል ማስተዋወቅ የያዝኩትም አንድም ለዚሁ ነው። ”
''ለመስቀል ጉራጌ አገር ገባሁ''

የፎቶው ባለመብት, ጁንኮ ያማማቶ
ጁንኮ የማሲንቆ አድናቂ ናት።
ጎንደር፣ ላሊበላ፣ ባሕር ዳር ማሲንቆ ቤት የቀራት የለም።
ጁንኮ የእማሆይ ጽጌ ማሪያም፣ የማሕሙድ አሕመድና የሙላቱ አስታጥቄም ወዳጅ ናት።
በጣም የምትወጂው አንድ ብቻ ሙዚቃ ምረጪ ከተባለች ግን “ወሎ! ወሎ!’’ ትላለች፤ የደርብ ዘነበን።
ከዳንስ ደግሞ የእስክስታና የጉራጊኛ አድናቂ ናት።
“አማራ ክልል ብወለድ እስክስታ የሚያህለኝ አልነበረም፤ ጉራጌ አገር ብወለድ ጉራግኛ የሚችለኝ አይኖርም ነበር። ምን ዋጋ አለው ጃፓን ተወለድኩ” እያለች ትቀልዳለች።
በነገራችሁ ላይ ጁንኮ ያማማቶ ለመስቀል ጉራጌ አገር ገብታ ታውቃለች። ገርሟታል ብዙ ነገር። አንዱ የገረማት እዚያ ሕዝቡ ጉራጊኛ ብቻ መጨፈሩ ነው። እንደ ከተማ ሰው ሙዚቃ አይቀላቅልም።
"ጉራጌዎች የኢትዮጵያ ጃፓኖች ናቸው፤ ሥራ ይወዳሉ" ሲባል ሰምታ ነው ጉጉቷ የጨመረው። ስለ መስቀል የሰማችው ደግሞ አንድ ወዳጇ በሰጣት የሕጻናት መጽሐፍ ላይ ስለ ጉራጌ መስቀል አንብባ ነው
እሷ ጭፈራውን ስትቀላቀል የገጠሩ ሕዝብ ጉድ አለ!
የአቦነሽን ጉራግኛ-ዝነኛውን ኦሴ ባሳን- በሎሚ ቤና-ከረሜላ የሚባሉ ሙዚቃዎች ተከተሉ። ደግሞ የመስቀል ለታ የማትረሳው ነገር አለ።
ስፒከር አለ- ሙዚቃ ለማጫወት ግን ቴክኒክ ችግር ተፈጠረ።
ጃፓናዊት በመሆኗ ነው መሰለኝ ኤሌክትሮኒክስ አያቅታትም በሚል አንድ ተአምር እንድትፈጥር ተጠየቀች።
“...ስልኬን ከብሉቱዝ ጋር አገናኝቼ የጉራጌ ዲጄ ሆኜ ያሳለፍኩት ቀን መቼም አይረሳኝም። " ትላለች።
የጥላሁን ገሠሠ “ጃፓኗን ወድጄን” ጃፓኖች ያውቁታል?

የፎቶው ባለመብት, ጁንኮ ያማማቶ
“ጃፓኗን ወድጄ” የሚለውን ዝነኛ ሙዚቃ፣ ብዙም ባይሆን ለሙዚቃ ቅርብ የሆኑ ጃፓናዊያን ያውቁታል።
ጁንኮ ያማማቶ አንድ ምስክር ትሆነናለች። በቃለ ምልልሳችን ይህን ብላናለች።
“...ደግሞ ልንገርህ። ይህ ዘፈን በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አታውቅም? በዚህ ላይ ጥናት ያደረገች ጃፓናዊት አግኝቼ ከሷ ነው የሰማሁት። ዋናውን ሰው አቶ ሸዋንዳኝ ወልደየስን አግኝታ ነው ያነጋገረችው። እውነተኛውን ታሪክና የሱንም ፎቶ እና ደግሞ በፍቅሯ የወደቀላትን ጃፓናዊቷን ሴት ፎቶ አሳይታኛለች። “
''ከኢትዮጵያ ባሕል የሚገርመኝ...''

የፎቶው ባለመብት, ጁንኮ ያማማቶ
ለጃፓናዊያን አስገራሚ ከሆኑ የኢትዮጵያ ነገሮች አንዱ ጉርሻ ነው።
የቡና ሥነ ሥርዓቱም እንዲሁ ያስደንቃቸዋል።
በእርግጥ የኢትዮጵያ የቡና ሥነ ሥርዓት ከጃፓን የሻይ ሥነ ሥርዓት ጋር የሆነ የሚያመሳስለው ነገር አለው።
ጁንኮን ግን ሌላ ሁለት ነገሮች ያስደንቋታል።
አንዱ የአርሲ ኦሮሞ ዳንስ ነው። አንገታቸውን የሚያሾሩበት መንገድ ሁልጊዜ ይደንቃታል።
ከሚያስፈሯት ነገሮች ደግሞ የእርኩስ መንፈስና የደብተራ ነገር ነው።
ጃፓንን ከደብተራ ጋር ምን አገናኘው ደግሞ? ጁንኮ የማትረሳው ገጠመኝ አላት።
“...አዲስ አበባ ለፋሲካ አንድ ቤተ ክርስቲያን ወሰዱኝ። ከዚያ ድንገት አንዲት ሴትዮ በጣም ጮኸች-ተንዘፍዝፋ ወደቀች። ደነገጥኩ። ምንድነው እየሆነ ያለው ብዬ ቤተ ክርስቲያን የወሰድችንን ልጅ ጠየቅኳት። ሴትዮዋን እርኩስ መንፈስ ይዟት እንደሆነ አስረዳችኝ። ያን ቀን በጣም ነበር የተደነቅኩት። ለኔ አዲስ ክስተት ነበር።“












