ነፍሰጡሮች ፓራሲታሞል መውሰዳቸው ችግር እንደሌለው በጥናት ተረጋገጠ

ፓራሲታሞል እና ውሃ በብርጭቆ የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው ዓመት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፓራሲታሞል በጽንስ ላይ ችግር ያስከትላል በማለት እርጉዝ ሴቶች እንዳይወስዱ የሰነዘሩትን ሃሳብ ማስረጃ የሌለው ነው ሲሉ የጤና ባለሙያዎች ውድቅ አደረጉት።

በፓራሲታሞል ዙሪያ በተደረገ ከፍተኛ ምርመራ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች እንዳሉት በእርግዝና ወቅት የሕመም ማስታገሻውን መውሰድ ችግር እንደሌለው እና ለኦቲዝም እንዲሁም ለሌሎች የዕድገት ችግሮች መጨመር ምክንያት ስለመሆኑ ማስረጃ የለም ብለዋል።

ባለሙያዎቹ ከዚህ ቀደም ነፍሰጡር ሴቶች ፓራሲታሞልን ፈጽሞ እንዳይወስዱ አጥብቀው የመከሩበትን አስተያየት ውድቅ በማድረግ በተደረገው ምርመራ የተገኘ ማረጋገጫ ስለሌለ መውሰድ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተያየት በወቅቱ በዓለም ከሚገኙ የሕክምና ተቋማት ትችት የገጠመው ሲሆን፣ በታዋቂው የሕክምና ጉዳዮች መጽሔት "ላንሴት" ላይ የወጣው የባለሙያዎቹ ጥልቅ የምርመራ ውጤት በፓራሲታሞል ደኅንነት ላይ የተነሳውን ጥያቄ እንዲያበቃ ያደርጋል ተብሏል።

ነገር ግን የአሜሪካ የጤና ባለሥልጣናት ፓራሲታሞልን በእርግዝና ወቅት መጠቀምን በተመለከተ "በርካታ ባለሙያዎች" ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል በማለት በአቋማቸው እንደጸኑ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና አስተዳደራቸው ባለፈው ዓመት ፓራሲታሞል ወይም በአሜሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለው ታይሌኖል የተባለው የሕመም ማስታገሻ በእርግዝና ወቅት ከተወሰደ ኦቲዝም እና ሌሎች የእድገት ችሮችን በጽንስ ላይ ያስከትላል ማለታቸው በዓለም ዙሪያ ዶክተሮችን አስደንግጦ ነበር።

ይህም በሴቶች ዘንድ ግራ መጋባትን እንዲሁም በጤና ባለሙያዎች በኩል ደግሞ አሳሳቢ ሁኔታን በመፍጠሩ አሁን ውጤቱ ይፋ የሆነው ጥናት እንዲካሄድ ምክንያት ሆኗል።

የተገኘው ውጤት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች የተሳተፉበት እና በእርግዝናቸው ወቅት ፓራሲታሞልን የወሰዱ እና ያልወሰዱ ሴቶችን በማነጻጸር የተካሄዱ 43 በጣም ጥልቅ ሆኑ ጥናቶችን መሠረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿ።

የጥናቱ ፀሐፊ የጽንስ ጤና ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር አስማ ኻሊል ስለውጤቱ "ትንተናውን ስንሠራ ፓራሲታሞልን በእርግዝና ወቅት መጠቀም ለኦቲዝም የመጋለጥ አጋጣሚን እንደሚጨምር የሚያመለክቱ አንድም ማስረጃ አላገኘንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጨምረውም "በሐኪም በታዘዘው መሠረት ከተወሰደ ፓራሲታሞል በእርግዝና ወቅት ቢወሰድ ችግር እንደሌለው የጥናቱ ውጤት ግልጽ መልዕክ ያስተላልፋል ብለዋል።

ይህ የጥናት ውጤት በዩናይትድ ኪግደም፣ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ያሉ ዋነኛ የጤና ድርጅቶች በሕመም ማስታገሻው ላይ ከዚህ ቀደም የሰጡትን መመሪያ የሚያጠናክር ነው።

"ፓራሲታሞል ሕመም እና ትኩሳት ላለባቸው ነፍሰጡር ሴቶች የሚታዘዝ ቀዳሚ መድኃኒት በመሆኑ የተገኘው የጥናት ውጤት ጠቃሚ ነው" ሲሉ በለንደን ዩኒቨርስቲ የእናቶች ሕክምና ለባሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ኻሊል ተናግረዋል።

ነፍሰጡር ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት የሚያጋጥማቸውን ከፍተኛ ትኩሳት ወይም ሕመምን ለመቀነስ እና ለማሰታገስ ሐኪም በሚያዘው መሠረት ፓራሲታሞል የማይወስዱ ከሆነ ጽንሱ የሚጎዳበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

በእርግዝና ወቅት ከፍተኛ ትኩሳት እና የሕመም ስሜት ቁጥጥር ካልተደረገባቸው የጽንስ መጨንገፍ፣ ካለጊዜ መወለድ ወይም የዕድገት ችግሮችን በሕጻናት ላይ ሊያስከሉ ይችላሉ።