የደም ግፊት ታካሚዎች ፓራሲታሞል አዘውትረው ከዋጡ ለልብ ድካም ሊዳርጋቸው ይችላል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች በሐኪም ትዕዛዝ አዘውትረው ፓራሲታሞል መጠቀማቸው ለልብ ድካም ሊያጋልጣቸው እንደሚችል አንድ ጥናት ጠቆመ።
የኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ አጥኚዎች እንዳሉት ዶክተሮች ለታካሚዎቻቸው ለብዙ ወራት የሚወጣ ክኒና ሲያዙ ጥቅምና ጉዳቱን ከግምት ማስገባት አለባቸው።
ሕመም ማስታገሻውን መድኃኒት ለራስ ምታትና ለትኩሳት መውሰድ ችግር እንደሌለው አጥኚዎቹ ይናገራሉ።
አንዳንድ ሙያተኞች ደግሞ በርከት ባሉ ሰዎች ላይ ጥናት ተሰርቶ ውጤቱን ማረጋገጥ ተገቢ ነው ይላሉ።
ፓራሲታሞል በመላው ዓለም የሚታወቅ ሕመም ለማስታገስ የሚዋጥ ሲሆን አንዳንዴ ጥልቅ ሕመም ለሚያስከትሉ በሽታዎችም ይመከራል። ነገር ግን ክኒናው ለረዥም ጊዜ መፍትሔ አይሰጥም።
በፈረንጆቹ 2018 ግማሽ ሚሊዮን ስኮትላንዳዊያን ይህንን ማስታገሻ እንዲውጡ በሐኪም ታዘው ነበር። ይህም ከ10 ስኮትላንዳዊ አንዱ ፓራሲታሞል ይውጥ ነበር ማለት ነው።
በዩናይት ኪንግደም ከፍተኛ የደም ግፊት ከሶስት ሰው አንድ ሰውን ያጠቃል።
ጥናቱ 110 ፈቃደኛ ሰዎችን አካቶ የተሰራ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሁለት ሶስተኛው የደም ግፊት መድኃኒቶች ይውጡ የነበሩ ናቸው።
የጥናቱ ተሳታፊዎች አንድ ግራም ፓራሲታሞል በቀን አራት ጊዜ ለሁለት ሳምንታት እንዲወስዱ ሆነ። ቀጥሎ ደግሞ ለሁለት ሳምንታት ክኒና የሚመስል ጥቅምም ጉዳትም የሌለው ቁስ እንዲውጡ ተደረጉ።
ሙከራው እንዳሳየው ፓራሲታሞል የወሰዱት የደም ግፊታቸው ጨመረ። ይህም ማለት ለልብ ድካምና ስትሮክ የመጋለጣቸው ዕድል ከፍ አለ ማለት ነው ይላሉ የኤደንብራ ፕሮፌሰር ጄምስ ዲር።
ዶክተሮች እንደ ደም ግፊት ዓይነት በሽታ ላለባቸው ታካሚዎች መጠኑ ያነሰ ፓራሲታሞል እንዲሰጧቸው አጥኚዎቹ ይመክራሉ።
የጥናቱ መሪ የሆኑት ዶክተር ኢያን ማካንታዬር ይህ ጥናት ለአጭር ጊዜ ሕመምን ለማስታገስ የሚወሰድ ፓራሲታሞልን አይመለከትም ይላሉ።
የለንደን ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ዲፔንደር ጊል፤ አሁን በሰሩት ጥናት መሠረት ክኒናው በነጭ ስከትላንዳዊያን ላይ ለደም ግፊት መባባስ ምክንያት ሆኖ ቢታይም ብዙ የማይታወቁ ጉዳዮች እንዳሉ ያስረዳሉ።
አንድ ከዚህ በፊት አሜሪካ ውስጥ የተሠራ ጥናት ለረዥም ጊዜ ፓራሲታሞል መጠቀም ለልብ ድካም ሊያጋልጥ እንደሚችል ጠቁሞ ነበር።
ሌሎች አነስ ያሉ ጥናቶች ደግሞ በክኒናውና በልብ ድካም መካከል ያለውን ግንኙነት መለየት አልቻሉም።
የኤንድብራ አጥኚዎች በፓራሲታሞልና ልብ ድካም መካከል ያለውን ግንኙነት ይህ ነው ብለው ባያስረዱም የጥናታቸው ውጤት ለሌላ ሰፋ ላለ ጥናት እንደሚጠቀም ተገልጧል።
ነገር ግን የብሪታኒያው ኸርት ፋውንዴሽን ዶክተሮችና ታካሚዎቻቸው የትኛው መድኃኒት አስፈላጊ ካልሆነ መዋጡ ያለውን ጥቅምና ጉዳት እንዲያገናዝቡ አደራ ብሏል።
ወደፊት የደም ግፊት ባለባቸው ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሌለባቸው ሰዎች ላይም ፓራሲታሞል አዘውትሮ መጠቀም ያለውን ጉዳት መቃኘት አስፈላጊ እንደሆነ የዘርፉ ሙያተኞች እየተናገሩ ነው።












