የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪዋ የፅጌረዳ ግድያና ተያያዥ ጉዳዮች

ፅጌረዳ ግርማይ

የፎቶው ባለመብት, Arbaminch University

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት 2ኛ ዓመት ተማሪ የነበረችው ፅጌረዳ ግርማይን በስለት ወግቶ የገደላት ግለሰብ ፍርድ ቤት መቅረቡን ቢቢሲ ከፓሊስና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ካገኘው መረጃ መረዳት ችሏል።

በዩኒቨርስቲው ተማሪ የሆነው ተጠርጣሪና ሁለት ሌሎች ተማሪዎች ከፅጌረዳ ግድያ ጋር በተያያዘ ማከሰኞ ዕለት በአርባ ምንጭ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን የ15 ቀናት ቀጠሮ ተሰጥቷቸው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ መደረጋቸውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ በድሩ ኢሪጎ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ፅጌረዳ ግርማይ በስለት በተፈጸመባት ጥቃት የተገደለችው ሰኞ ጥር 23/2014 ዓ.ም ምሽት በግቢው ቤተ መጻሕፍት አካባቢ መሆኑን በጋሞ ዞን የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር አዳነ ኦኬ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ጥቃቱ በጩቤ የተፈጸመ ሲሆን ጡቷና ጎኗ አካባቢ ላይ በተደጋጋሚ ተወግታ ሕይወቷን ለማትረፍ ወደ አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ብትወሰድም ልትተርፍ እንዳልቻለች ተናግረዋል።

ስለ ግድያው ፖሊስና ዩኒቨርስቲው የተገኘው መረጃ

ግድያው የተፈጸመው ጥር 23/2014 ዓ.ም ምሽት አምስት ሰዓት ገደማ ነው።

በስለት ወግቶ የገደላት ተጠርጣሪ በዩኒቨርስቲው የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት 2ኛ ዓመት ተማሪና ከፅጌረዳም ጋር በአንድ ዲፓርትመንት የሚማሩ ሲሆን የነበራቸውን ግንኙነት በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች እየተሰሙ እንደሆነም አቶ በድሩ ተናግረዋል።

ፅጌረዳ ከዚህ ቀደም ከተጠርጣሪው ጋር ግንኙነት እንደነበራትና ይህንንም ግንኙነት በማቋረጧ የተነሳ ነው የሚሉ እንዲሁም ተጠርታሪው ፅጌረዳን ለፍቅር ግንኙነት ፈልጓት ፈቃደኛ ባለመሆኗና ይህንንም እምቢታዋን በበጎ መልክ ባለመውሰድ በስለት ወግቷታል የሚል መረጃን ሰብስብዋል።

አብራት ዶርም የምትኖር ጓደኛዋንም ዋቢ አድርገው አቶ በድሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተጠርጣሪው ለፍቅር ግንኙነት እንደሚፈልጋት እና ፅጌረዳም እምቢተኝነቷን እንደገለጸች፣ ከዚያ በኋላም ምንም አይነት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረችም ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ቢቢሲ ከአካባቢው ፖሊስ ያገኘው መረጃ የጥቃቱ ሰለባና ተጠርጣሪው የፍቅር ግንኙነት እንደነበራቸው ያመለክታል።

ተጠርጣሪው ለፅጌረዳ በሚደውልላት ወቅት የእሱን ስልክ እንደማታነሳና ምላሽም እንደማትሰጠው አቶ በድሩ መረጃ ማግኘታቸውን ያስረዳሉ።

ግድያው በተፈፀመበት ምሽት ላይ ተጠርጣሪው የእሱን ስልክ ስለማታነሳ በሁለት በምታውቃቸው ወንድ ተማሪዎች አማካይነት ከምሽት አራት አስከ አምስት ሰዓት ባለው ፅጌረዳን ያስጠራታል።

ፅጌረዳም በግቢው ወደሚገኘው የካምፓሱ አስተዳደር ህንፃ አካባቢ ወይንም ቤተ መጻሕፍት አካባቢ እንድትመጣ አደረጋት።

ከደረሰች በኋላም ሁለቱን ተማሪዎች እንዲርቁና "ያለንን አለመግባባት በግል እንፈታለን" የሚል ምክንያት ሰጥቷቸው ትንሽ ራቅ ማለታቸውን አቶ በድሩ ይናገራሉ።

ብዙም ሳይርቁ ፅጌረዳ ጩኸት እንዳሰማችና በያዘው ስለትም እንደወጋት ገልጸዋል። ተማሪዎቹ ተሯሩጠው እንደመጡና ጩኸቱንም ሰምተው የካምፓስ ፖሊስና የደኅንነት አባላት በአካባቢው ደርሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ ተጠርጣሪው እና ስልክ ደውለዋል የተባሉት ሁለት ተማሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋለ ቢቢሲ ከአቶ በድሩ ተረድቷል።

በወቅቱም ፅጌረዳ ወደ አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በአስቸኳይ እንድትደርስ ቢደረግም ህክምና እየተደረገላት ህይወቷ አልፏል። በነገታው ጥር 24/2014 ዓ.ም አስከሬኗ ወደ ትውልድ ቦታዋ ወልቃይት አዲ ረመፅ ተሸኝቷል።

ፅጌረዳ ግርማይ

የፎቶው ባለመብት, Arbaminch University

ስለ ተጠርጣሪው በጥቂቱ

ከደብረ ብርሃን የመጣው በግድያው የተጠረጠረው ተማሪ ከዚህ በፊት የዲሲፒሊን ችግሮች እንደነበሩበት ቢቢሲ ከዩኒቨርስቲው ያገኘው መረጃ ያስረዳል።

ከዚህ ቀደም ሴት ተማሪዎች ዛቻና ማስፈራሪያ ያደርስብናል ብለው ለዩኒቨርስቲው መናገራቸውንና "አስቸጋሪ" የሚባል ባህርይ እንደነበረውም አቶ በድሩ የዩኒቨርስቲውን መረጃ ጠቅሰው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ሴት ጓደኛው የነበረችው ተማሪ ከእሱ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርስቲውን እንደለቀቀችና ሌሎች ሁለት ሴት ተማሪዎችም እንዲሁ ለዩኒቨርስቲው አመልክተው ጉዳዩ በዲሲፒሊን እንደታየና ማስጠንቀቂያዎችም ተሰጥተውት ነበር።

"ኃላፊዎቹ ተጠርጣሪውን በተመለከተ ለተግባቦት ምቹ አልነበረም እንዲሁም ማስጠንቀቂያዎችና ምክርም ተሰጥቶት" እንደነበር አውስተዋል።

አመልክተው የነበሩት ሁለቱ ተማሪዎች ተመርቀው እንደወጡም አቶ በድሩ ይናገራሉ። ተጠርጣሪው ከዚህ ተግባሩ እንዲታቀብ ምክርና ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ሲሆን ዛቻና ማስፈራሪያ ያደርስ እንደነበር ገልጸዋል።

ተደጋጋሚ የዲሲፒሊን ችግር ከነበረበት ለምን ዩኒቨርስቲው እርምጃ አልወሰደበትም? የሚል ጥያቄ ቢቢሲ አቅርቦላቸው ነበር "ተደጋጋሚ አይደለም። አንድ ጊዜ ነው ቅሬታ ለዩኒቨርስቲው የቀረበበት። ሟች ተማሪ ፅጌረዳም ያስፈራራኛል የሚል እንዲሁም ጥበቃ ይደረግልኝ የሚል ክስም አላቀረበችም" ይላሉ።

እንዲህ አይነት የሴት ተማሪዎችን ዛቻና ማስፈራሪያዎች ዩኒቨርስቲው እንደማይታገስና የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ይህንን ጉዳይ እንደሚከታተልም አስረድተዋል። "በሕይወቷ ላይ ስጋት ቢኖራት ለዩኒቨርስቲው ታሳውቅ ነበር" ይላሉ።

በዚህ ዓመት ተጠርጣሪው ከነበረው ባህሪይ አንጻር ከፅጌረዳም ሆነ ከሌሎች ሴት ተማሪዎች ጋር ምን አይነት ግንኙነት እንዳለው እንደማይታወቅም አቶ በድሩ ገልጸዋል።

ግድያዋ ከብር ጋር የተያያዘ ነው?

የፅጌረዳ ግድያ ከብሔሯ/ከማንነቷ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በተለያዩ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ መነሳቱን ጠቅሰን አቶ በድሩን ይህንኑ ጠይቀናቸው ነበር።

"ጉዳዩ የፖለቲካ ባይሆንም እንኳን ፖለቲካዊ ትርጉም እንዲሰጠው የሚሞክሩ ይኖራሉ" የሚሉት አቶ በድሩ ለዚህ ትርጓሜ መስረት የለውም ይላሉ።

ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ወይም ጥላቻ አድርሶ ቢሆን ኖሮ መነሻ ሊሆን ይችል ነበር የሚሉት አቶ በድሩ፣ ነገር ግን የተጠርጣሪው ባህርይ ከዚያ ሩቅ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ይህ ሁኔታ በፅጌረዳ ቦታ ማንኛዋም ሴት ብትሆን ሊደርስ የሚደርስ ጥቃት ነው በማለት "ከብሔር ጋር የተያያዘ ነው የሚያስብል ምንም አይነት ጠንካራ ምክንያት የለም። ያለውን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ብንገነዘበውና ይህንን ጉዳይ የፖለቲካዊ ይዘት ለመስጠት የሚሞከረው ነገር ተገቢ አይደለም" ይላሉ።

አክለውም አሁን ባለንበት ሁኔታ እንዲህ አይነት ትርጓሜ መስጠት ስህተት ነው የሚሉት አቶ በድሩ "የትግራይ ማኅበረሰብ አባላት በዩኒቨርስቲውም ሆነ በከተማው ይኖራሉ። ያሉት የፖለቲካ አለመግባባቶች እንዳሉ ሆነው ማኅበረሰቡን ለማጋጨት የሚሰሩ ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸው ቢቆጠቡ" በማለት ምክራቸውን ያስተላልፋሉ።

የፅጌረዳ ጓደኛና ወልቃይት ውስጥ አንድ አካባቢ ማደጋቸውን የሚናገረው ስሜ አይጠቀስ ያለ ተማሪ ግድያው በተመለከተ ከብሔር ጋር የተያያዘ ነው ስለመባሉ ለቢቢሲ የሚከተለውን ተናግሯል።

"አንድ ዲፓርትመንት አብሯት የሚማር እወድሻለሁ፣ አፈቅርሻለሁ እያለ የሚያስቸግራት የደብረ ብርሃን ልጅ ነው። እሷ ግን አትቀበለውም ነበር። ጉዳዩም የብሔር አይደለም። ጥቃቱ ሲፈጸም ማታ አራት ሰዓት አስጠርቷት ላይብረሪ ላይ ነው የተገናኙት" ብሏል።

ተማሪዋ በሞተችበት ወቅት ዩኒቨርስቲው በፌስቡክ ባወጣው መግለጫ "ድንገተኛ ሞት" ማለቱንም ቢቢሲ ጠቅሶ ግድያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ድንገተኛ መባሉን ተገቢነት አቶ በድሩ ተጠይቀው ነበር።

"ድንገት ነው የሞተችው፤ አደጋም ሆነ ግድያም ያልታሰበ ስለሆነ ነው ድንገተኛ ያልነው። በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንደተሰራጨው አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ለክስተቱ ትኩረት ከመንሳት ወይንም የእርሷን ፍትህ ለማጓደል ወይም ወንጀለኛን ለማገዝ አይደለም። ወንጀለኛውን በቁጥጥር ስር ያዋለው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ደኅንነት ነው።"

አቶ በድሩ አክለውም "ተማሪያችን የእኛ ናት። ሁሉንም በተመሳሳይ መልክ ነው የምናያቸው። በሞቷ ዩኒቨርስቲው በጥልቁ ነው ያዘነው በጣም ነው የደነገጥነው" በማለት እንዲህ አይነት ግድያ በዩኒቨርስቲው ደርሶ አያውቅም ብለዋል።

ዩኒቨርስቲው የተማሪዋን ሞት አስመልክቶ ባወጣው የሃዘን መግለጫ ተማሪ ፅጌረዳ በወልቃይት ጌታቸው አዘናው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰናዶ ትምህርቷን ከተከታተለች በኋላ፣ በመስከረም 2012 ወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ እንደተመደበችና በሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት የ2ኛ ዓመት ተማሪ ነበረች።

ተማሪ ጽጌረዳ ከአባቷ አቶ ግርማይ ገብረመድኅን እና ከእናቷ ወ/ሮ ያበሻ ያዘዘው በወልቃይት ወረዳ በአድ ረመጽ ከተማ በ1993 ዓ.ም መወለዷን የሕይወት ታሪኳ አመልክቷል።