የትራምፕ አስተዳደር ሉኮቭሪን ለኦቲዝም ሕክምና መዋል ይችላል የሚለው ለምንድን ነው?

ነርስ ለአዋላጅ ነርስ ፎሊክ አሲድ ኣለበት ካርቶን ስታሳያት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ መንግሥት የሕጻናትን ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደርን (ASD) ለመከላከል እና ለማከም አወዛጋቢ መመሪያ ሰጥቷል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ለነፍሰ ጡር እናቶች የሚሰጠው የሕመም ማስታገሻ፣ታይሌኖል (ፓራሲታሞል) አጠቃቀም እና በአንዳንድ ሕጻናት ላይ የሚታይ የኦቲዝም ተጋላጭነት መካከል ግንኙነት አለ ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ መግለጫ የተሰማው የትራምፕ አስተዳደር "የኦቲዝም ወረርሽኝ" ሲል የገለፀውን ለመቅረፍ እየወሰዳቸው ካላቸው እርምጃዎች ጋር ነው።

ከተሰጡት ምክሮች አንዱ ኦቲዝም ላለባቸው ሕጻናት የንግግር ችግርን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውለው የፎሊክ አሲድ ዓይነት የሆነውን ሉኮቮሪን (leucovorin) የተባለውን መድኃኒትን መጠቀም ነበር።

የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር የኦቲዝም ምልክቶችን በመቀነስ ረገድ ሊገኙ የሚችሉትን ጥቅሞች ለማንፀባረቅ የመድኃኒቱን መለያ እንደሚቀይር ተናግሯል።

የአሜሪካ የጤና እና የሰብዓዊ አገልግሎት ቢሮ ባወጣው መግለጫ "ሉኮቮሪን ለኤኤስዲ ፈውስ እንዳልሆነ ማወቅ ጠቃሚ ነው" እንዲሁም "ከንግግር ጋር የተያያዙ ጉድለቶችን ለመሻሻል ብቻ ሊረዳ ይችላል" ብሏል።

በአሜሪካ የሚገኘው የኦቲዝም ሳይንስ ፋውንዴሽን ባወጣው መግለጫ "መደምደሚያ ላይ ከመድረሱ በፊት ተጨማሪ ጥናቶች አስፈላጊ ናቸው" ሲል ሉኮቮሪን ለኦቲዝም ሕክምና ጥቅም ላይ እንዲውል አይመከርም ብሏል።

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኦቲዝም መንስኤ ምን እንደሆነ እናውቃለን?

ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በመሆን የትራምፕ አስተዳደርን ከተቀላቀሉ በኋላ በአሜሪካ ኦቲዝምን ዋና ትኩረት አድርገው በአገሪቱ ስላለው የኦቲዝም ቁጥር መጨመር የተዛቡ ንድፈ ሃሳቦችን በማቀንቀን ላይ ናቸው።

በአምስት ወራት ውስጥ የኦቲዝምን መንስኤ ለማወቅ "ትልቅ የምርመራ እና የምርምር ጥረት" ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ቀጥተኛ የኦቲዝም መንስኤዎችን መፈለግ ውስብስብ እና አወዛጋቢ ነው። ተመራማሪዎች በሰፊው የሚያምኑት ኦቲዝም የሚያስከትለው መንስኤ ይህ ነው ተብሎ የሚታወቅ አንድም ነገር እንደሌለ ነው።

የኦቲዝም ሳይንስ ፋውንዴሽን ዋና ሳይንቲስት አሊሺያ ሃላዳይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ዘረመል አንዱ ትልቁ ምክንያት መሆኑን በእርግጠኝነት እናውቃለን" ብለዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ናሽናል ኦቲስቲክስ ሶሳይቲ ከትራምፕ ንግግር በኋላ በሰጠው መግለጫ "የኦቲዝም መንስኤዎች አሁንም ምርምር እየተካሄደባቸው ነው፤ ብዙ ባለሙያዎች አንድ የተለየ ምክንያት እንደሌለ እና የዘረመል ምክንያቶች እንዳሉ ያምናሉ" ሲል አስታውቋል።

የኦቲዝም መንስኤን ፍለጋ በተሳሳተ መረጃ የጠየመ ነው።

እአአ በ1998 አሁን ተቀባይነቱን የተነጠቀው ብሪታኒያዊው ዶክተር አንድሪው ዋክፊልድ ኩፍኝ፣ የጆሮ ደግፍ እና ሩቤላ (የጀርመን ኩፍኝ) ክትባት ከኦቲዝም ጋር ግንኙነት አለው የሚል የተሳሳተ ጥናት አሳትሟል፤ ይህ የተሳሳተ መረጃ ለረዥም ጊዜ ተቀባይነት አግኝቶ ቆይቷል።

ኬኔዲ እአአ በ2023 ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ "ኦቲዝም የሚመጣው ከክትባት ነው" በማለት ይህንኑ ሐሰተኛ መረጃ ደግመውታል።

ለኦቲዝም 'ፈውስ' አለ?

በኦቲዝም ስፔክትረም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች፣ ኦቲዝም "መስተካከል ይችላል" የሚለው እምነት ከኒውሮዳይቨርሲቲ አስተሳሰብ ጋር በተቃራኒ የቆመ ነው።

በኤድንበርግ ዩኒቨርሲቲ የእድገት ሥነ ልቡና ፕሮፌሰር የሆኑት ሱ ፍሌቸር-ዋትሰን "ኦቲዝም መሞከር ያለበት እና የተለየ ውጤት ወይም ትንበያ የሚያገኙበት ሥነ ሕይወታዊ ክስተት አይደለም" ብለዋል።

አክለውም "ይህ እንደ ካንሰር ያለ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጥፎ መሆኑ ስምምነት ላይ የተደረሰበት እና ሁሉም ሰው መድኃኒት የሚፈልግበት ነገር አይደለም። በእኔ አስተያየት በጭራሽ አይሆንም" ብለዋል።

ስቴፋኒ ሃንራሃን (በስተግራ) ከሁለት ልጆቿ (መካከል) እና ከባለቤቷ ጋር (በስተቀኝ) ተቃቅፈው

የፎቶው ባለመብት, Handout

የምስሉ መግለጫ, ስቴፋኒ ሃንራሃን (በስተግራ) በማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ ላይ ኦቲዝም ያለበት ልጅ ስለማሳደግ ታወራለች

በአሜሪካ ውስጥ ለምትኖረው በኦቲዝም ስፔክትረም ውስጥ ያለች ልጅ ላላት ስቴፋኒ ሃራሃን ኦቲዝም መዳን አያስፈልገውም ምክንያቱም በሽታ አይደለም።

"ኦቲዝም መምረጥ የሚችሉት ጉዳይ አይደለም" ትላለች። "ይህቺን ዓለም እና ያቺን ውብ ሕይወት የሚያዩበት መነፅር ነው።"

በእንግሊዝ ኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን ክሊኒካል ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ኢድ ሙሊንስ ኦቲዝም የስፔክትረም ዲስኦርደር ነው (ይህም የተለያዩ ሁኔታዎችን የሚያመለክት ነው)፤ ስለዚህ ሰዎች ለሕክምና ያላቸውን ፍላጎት ጨምሮ የተለያዩ ልምዶች ሊኖሩ ይችላሉ ብለዋል።

"ውዝግቡ በኦቲዝም የተጠቃ ልጅ ሲወልዱ ነው፤ ከዘያ በፊት መከላከል እንደሚያስፈልገው ዲዝኦርደር ስለማያዩት ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ይሁን እንጂ ብዙ ታካሚዎቼ በኦቲዝም የተጠቃ ልጅ መኖር በወላጅነት ሕይወት ውስጥ ትልቅ ነገር እንደሆነ ይናገራሉ።"

ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች የበሽታውን ምልክቶች ሊቀርፉ የሚችሉ አማራጮችን ይፈልጋሉ ሲል አክሏል።

ሉኮቮሪን ምንድን ነው? ኦቲዝምን ማከም ይችላል?

ለልጁ መድሃኒት ለመስጠት የተዘጋጀ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሉኮቮሪን (Leucovorin) ፎሊክ አሲድ ሆኖ ሰው ሠራሽ ቫይታሚን ቢ9 ነው።

የአንጎል እድገትን የሚያፋጥነው እና በተፈጥሮ የሚገኘው የቫይታሚን ቢ9 ፎሌት ሚና የሚተካ ነው።

በተገቢው ሁኔታ ይህንን ቫይታሚን አለማግኘት ደግሞ የወሊድ ጉድለት ያስከትላል።

ሰውነታችን ፎሌትን ከጥራጥሬዎች፣ ሆምጣጣ ፍራፍሬዎች እና ንጥረ ነገር ከገባባቸው በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች ያገኛል።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የኦቲዝም ሳይንስ ፋውንዴሽን በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ወራት ወቅት ዝቅተኛ የፎሌት መጠን፣ በአንዳንድ ጥናቶች ምንም እንኳን ግኝቱ ወጥነት ያለው ባይሆንም፣ በልጆች ላይ የኦቲዝም ተጋላጭነት ከመጨመር ጋር ተያይዟል።

ፋውንዴሽኑ በተጨማሪም ኦቲዝም ባለባቸው ሕጻናት ላይ ፎሊክ አሲድ አንዳንድ ምልክቶችን ሊያሻሽል ይችላል የሚለው ሀሳብ የመጣው ሉኮቮሪን ተብሎ ከሚጠራው የካንሰር መድሃኒት ሙከራ በኋላ ነው።

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከመደበኛው ፎሊክ አሲድ በተቃራኒ ሉኮቮሪን በቀላሉ የደም የአንጎልን ሽፋን በማቋረጥ የቫይታሚን ቢ9 እጥረትን ሊፈታ ይችላል።

አራት አነስተኛ እና የተለያዩ ጥናቶች ሁሉም የተለያየ የስኬት መስፈሪያዎችን አስቀምጠው ተካሂደዋል።

አንዱ በአሜሪካ ውስጥ 48 ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ላይ እአአ በ2016 የተደረገ ሲሆን ለሥነ ልቡና ድጋፍ ከሚሰጥ መድኃኒት አንጻር ሲታይ የቃል ተግባቦትን በመሻሻል ረገድ ለውጥ አሳይቷል።

ጥናቱን ያደረጉት ተመራማሪዎች ግኝቱን ለሰፊው ማኅበረሰብ ለማረጋገጥ ሰፋ ያለ ናሙና መውሰድ እና ብዙ ጥናት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ተመራማሪዎች ሳይንሱ ገና በመጀመርያ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና የትኛውም ድምዳሜ ላይ ከመደረሱ በፊት ተጨማሪ ሥራ ያስፈልጋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በተጨማሪም የመድኃኒቱ ደህንነት ላይ የመረጃ እጥረት አለ፤ የመድሃኒቱ የረጅም ጊዜ ተፅዕኖዎች ገና አልተፈተሹም ብለዋል።

ሕክምና ሳይሆን ድጋፍ?

ለሀንራሃን እና ቤተሰቧ ኦቲዝምን እንደ ወረርሽኝ መፈረጅ በኦቲዝም ምርመራ ዙሪያ ያለውን መገለል ይጨምራል።

"ወረርሽኞች ይፈራሉ፤ በአንድ አካባቢ ተከልለው ይቀመጣሉ፤ እናም ይወገዳሉ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። "ከኦቲዝም ጋር ያለን የግል የአኗኗር ልምዳችን ከዚያ ቋንቋ ወይም ንግግር ጋር አይጣጣምም።"

እናም በፈውሶች እና መንስኤዎች ላይ በማተኮር ኤኤስዲ ላለባቸው ሰዎች እና ቤተሰቦች እውነተኛ ድጋፍ ከውይይቱ እንደጠፋ ትናገራለች።

"ኦቲዝም የሚቀረፍ ችግር አይደለም፤ በቅድመ ጣልቃገብነት እና ሕክምና እንዲሁም በተንከባካቢ መደገፍ የሚያስፈገው ሕመም ነው።"