ትራምፕ ኦቲዝም ያስከትላል ያሉትን መድኃኒት ነብሰ-ጡር ሴቶች እንዳይወስዱ አሳሰቡ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ዶክተሮች ለነብሰ-ጡር ሴቶች ታይሌኖል የተባለውን ማስታገሻ መድኃኒት እንዳይሰጡ አሳስበዋል።

ትራምፕ ይህን ያሉት መድኃኒቱ ከኦቲዝም ጋር ግንኙነት አለው ብለው ቢሆንም ይህ በሳይንስ የተረጋገጠ አይደለም።

ፕሬዝደንቱ ከጤና ሚኒስትራቸው ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር ጋር በመሆን ከዋይት ሐውስ በሰጡት መግለጫ ነው ይህን ያሉት።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት የታይሌኖል ዋነኛ ግብዐት የሆነውን ፓራሴታሞል መውሰድ "ጥሩ አይደለም" ብለው ነብሰ-ጡሮች እጅግ የከፋ ትኩሳት ሲኖርባቸው ብቻ እንዲወስዱት መክረዋል።

አንዳንድ ጥናቶች ታይሌኖል በሚወስዱ ነብሰ-ጡር ሴቶች እና በኦቲዝም መካከል ግንኙነት እንዳለ ቢያሳዩም ጥናቶች ያልተጠናቀቁ እና ያልተሟሉ ናቸው።

ታይሌኖል የተባለው ክኒን አምራች የሆነው ኬንቩዌ ሴቶች መድኃኒቱን እንዳይወስዱት መባሉን አጣጥሏል።

ድርጅቱ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ "ገለልተኛ እና ጠንካራ ሳይንስ ኤስታሚኖፊን በመውሰድ እና በኦቲዝም መካከል ግንኙነት እንደሌለ አሳይቷል ብለን እናምናለን። ከዚህ ውጭ የሚሰጥን አስተያየት አጥብቀን እንቃወማለን። ይህ ምክር ለነብሰ-ጡር ሴቶች የሚያስከተለው የጤና ቀውስም ያሳስበናል" ብሏል።

ኤስታሚኖፊን የተባለው ታይሌኖል ውስጥ የሚገኝ ኬሚካል ለነብሰ-ጡር ሴቶች የተሻለው የሕመም ማስታገሻ ተደርጎ ይቆጠራል ያለው ድርጅቱ እርጉዝ ሴቶች ከዚህ ውጭ ያላቸው አማራጭ ስቃይ አሊያም ሌሎች ስጋት ያለባቸው መድኃኒቶችን መጠቀም ነው።

የጤና ሚኒስትሩ ኬኔዲ የሀገሪቱ የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር ለጤና ባለሙያዎች ማስታወቂያ እንደሚለቅ አስታውቀው ታይሌኖል ነብሰ-ጡር ሴቶችን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ብለዋል።

አክለው መድኃኒቶቹ ላይ የሚፃፈው ማስጠንቀቂያ እንደሚቀየር እና ለሕዝቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

ኬኔዲ፤ የምግብና መድኃኒት አስተዳደር ከዚህ በኋላ ሌውኮቮሪን የተባለውን መድኃኒት ኦቲዝም ላለባቸው ሕፃናት እንዲሰጥ እንደሚመክር አስታውቀዋል። ይህ መድኃኒት ላለፉት አስርታት የካንሰር ታካሚዎችን ኪሞቴራፒ ከሚያስከትለው ስቃይ ለማስታገስ ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ነው።

ኬኔዲ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ነው በሚቀጥሉት አምስት ወራት የኦቲዝምን መንስኤ ለማወቅ "ሰፊ ሙከራ እና ጥናት ይካሄዳል" ሲሉ ያስታወቁት።

ትራምፕ ሰኞ በሰጡት መግለጫ በኦቲዝም የሚጠቁ ሕፃናት ቁጥር መጨመርን "ከፍተኛ ቀውስ" ሲሉ ገልፀውታል።

ነገር ግን ሙያተኞች ባለፉት አስርት ዓመታት ጥናት የተካሄደበትን ኦቲዝም መንስኤው ምንድነው የሚለውን በአጭር ጊዜ ማወቅ ቀላል አይደለም ይላሉ።

በጠቅላላው የኦቲዝም መንስኤ ተደርገው የሚወሰዱት ምክንያቶች በዘር የሚመጡ እና አካባቢያዊ አስተዋፅኦዎች ናቸው።