ቶኒ ብሌር እና ማርኮ ሩቢዮ ጋዛን በጊዜያዊነት የሚያስተዳድረው "የሰላም ቦርድ" አባል ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮን እና የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ቶኒ ብሌርን ለጋዛ "የሰላም ቦርድ" መሥራች አባላት አድርጎ ሰየመ።
የትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የፕሬዚዳንቱ አማች ጃሬድ ኩሽነር እንዲሁ "በመሥራች ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ" ውስጥ ስማቸው መካተቱን ዋይት ሐውስ አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ትራምፕ የቦርዱ ሊቀመንበር ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን፣ ይህም በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረገውን ጦርነት ለማስቆም ባዘጋጁት 20 ነጥብ ዕቅድ ውስጥ ይካተታል።
ቦርዱ የጋዛን አስተዳደር በጊዜያዊነት መቆጣጠር እና መልሶ ግንባታውን የማስተዳደር ኃላፊነት ይጠብቀዋል።
በተጨማሪም የግል ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ማርክ ሮዋን፣ የዓለም ባንክ ኃላፊ አጃይ ባንጋ እና የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ሮበርት ጋብርኤል በቦርዱ ውስጥ ተካትተዋል።
እያንዳንዱ አባል "ለጋዛ መረጋጋት እና ለረጅም ጊዜ ስኬት ወሳኝ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ሲል የዋይት ሐውስ መግለጫ አስታውቋል።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ቦርዱ መቋቋሙን በመግለጽ "በማንኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ቦታ ከተዋቀረ ሁሉ የላቀ ታላቅ እና እጅግ የተከበረ ቦርድ" ሲሉ ጠርተውታል።
ተጨማሪ የቦርድ አባላት በሚቀጥሉት ሳምንታት እንደሚሰየሙ ዋይት ሐውስ አስታውቋል።
ሰር ቶኒ ብሌር ከአውሮፓውያኑ 1997 እስከ 2007 የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ብሌር ከሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ለአሜሪካ፣ በአውሮፓ ኅብረት፣ በሩሲያ እና በተባበሩት መንግሥታት ተጠሪ የሆነው የመካከለኛው ምሥራቅ ልዑክ በመሆን አገልግለዋል።
ትራምፕ የቦርድ አባላቱን ያሳወቁት የጋዛን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው 15 አባላት ያሉት የፍልስጤም የቴክኖክራት (የባለሙያዎች) ኮሚቴ፣ የጋዛ ብሔራዊ የአስተዳደር ኮሚቴ ይፋ ከሆነ በኋላ ነው።
በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ያልሆነውን የዌስት ባንክ አካባቢዎች የሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር የቀድሞ ምክትል ሚኒስትር አሊ ሻዝ አዲሱን ኮሚቴ ይመራሉ።
መግለጫው በተጨማሪም የቡልጋሪያ ፖለቲከኛ እና የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት የመካከለኛው ምሥራቅ አምባሳደር ኒኮላይ ምላዴኖቭ በጋዛ ውስጥ ከኮሚቴው ጋር በመተባበር የቦርዱ ተወካይ ይሆናሉ ብሏል።

የትራምፕ ዕቅድ እንደሚያሳየው ዓለም አቀፍ የሚያረጋጋ ኃይል ወደ ጋዛ የሚሰማራ ሲሆን፣ የተመረጡ የፍልስጤም የፖሊስ ኃይሎችን ማሰልጠን እና መደገፍ ላይ እንደሚሠራ የዋይት ሐውስ መግለጫ ያስረዳል።
የአሜሪካ ሜጀር ጄኔራል ጃስፐር ጄፈርስ ይህንን ኃይል የሚመሩ ሲሆን "ደኅንነትን ማስፈን፣ ሰላምን መጠበቅ እና ዘላቂ የሆነ ከሽብርተኝነት የጸዳ አካባቢ የመመሥረት" ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
ዋይት ሐውስ አስተዳደሩን ለመደገፍ የሚረዳ እና ከመሥራች የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ጋር ተመሳሳይ ተጨማሪ ተሿሚዎችን የሚያካትት የተለየ "የጋዛ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ" እየተመሠረተ መሆኑን ተናግሯል።
የአሜሪካ የሰላም ዕቅድ በጥቅምት ወር ተግባራዊ መሆን የጀመረ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ገብቷል።
ነገር ግን ስለ ጋዛ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እና በውስጡ ስለሚኖሩት 2.1 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን አሁንም ግልጽ የሆነ ነገር የለም።
በመጀመሪያው ምዕራፍ፣ ሐማስ እና እስራኤል በጥቅምት ወር የተኩስ አቁም ስምምነት፣ እንዲሁም የታጋቾች እና የእስረኞች ልውውጥ፣ የእስራኤል በከፊል መውጣት እና ተጨማሪ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ስምምነት ላይ ተደርሰዋል።
ዊትኮፍ ሁለተኛው ምዕራፍ የጋዛን መልሶ ግንባታ እና ሙሉ በሙሉ ከወታደራዊ ኃይል ነፃ ማውጣትን ያካትታል ብለዋል።
ይህም የሐማስን እና የሌሎች የፍልስጤም ቡድኖችን ትጥቅ መፍታትን ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዊትኮፍ አሜሪካ ሐማስ ግዴታውን ሙሉ በሙሉ እንደሚወጣ እንደምትጠብቅ እና ይህም የመጨረሻውን የእስራኤል ታጋች አስከሬን መመለስን ያካትታል በማለት "ይህን አለማድረግ ከባድ መዘዝ ያስከትላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የጋዛን የተኩስ አቁም በተደጋጋሚ በመጣስ ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው ሌላኛውን ይካሰሳሉ።
በጋዛ የሐማስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሠረት ከተኩስ አቁሙ ወዲህ እስራኤል በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ወደ 450 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ በፍልስጤማውያን ቡድኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች ሦስት ወታደሮቿ መገደላቸውን ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጋዛ አሁንም የሰብአዊ እርዳታ ሁኔታ አስከፊ መሆኑን ጠቅሶ ወሳኝ የሆኑ አቅርቦቶች ያልተገደበ ፍሰት አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል።
የጋዛ ጦርነት የተቀሰቀሰው ሐማስ በደቡብ እስራኤል መስከረም 26/2016 ዓ.ም የፈጸመውን ድንገተኛ ትቃት ተከትሎ ነው።
በወቅቱ 1,200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎች ደግሞ ታግተዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃቶች ከ71,260 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የሐማስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።















