የወደፊቷ ጋዛ ላይ ሚና እንዲኖራቸው የሚፈልጉት የሐማስ ተቃዋሚ ታጣቂ ቡድኖች

ግዙፍ ከሆኑ ታጣቂ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ፖፑላር ፎርስ፣ በደቡባዊ ራፋህ አካባቢ ይንቀሳቀሳል

የፎቶው ባለመብት, Yasser Abu Shabab/Facebook

የምስሉ መግለጫ, ግዙፍ ከሆኑ ታጣቂ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ፖፑላር ፎርስ፣ በደቡባዊ ራፋህ አካባቢ ይንቀሳቀሳል

ከቅርብ ወራት ወዲህ በጋዛ ሐማስን ለመውጋት በተነሱት የታጠቁ ኃይሎች ላይ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።

እነዚህ ኃይሎች በቤተሰብ ጎሳዎች ዙሪያ የተመሰረቱ፣ የወንጀል ቡድኖችን እና አዳዲስ ሚሊሻዎችን የያዙ ናቸው።

አንዳንዶቹ በቅርቡ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ እንደተናገሩት ድጋፋቸውን የሚያገኙት ከቴላቪቭ ነው።

በእስራኤል በወረራ የተያዘውን ዌስት ባንክን በከፊል የሚያስተዳድረው እና የሐማስ የፖለቲካ ተቀናቃኝ የሆነው የፍልስጤም አስተዳደር ውስጥ ያሉ አካላት በድብቅ ድጋፍ እንደሚልኩም ይታመናል።

ነገር ግን እነዚህ ሚሊሻዎች በእስራኤል ጦር ቁጥጥር ሥር በሚገኘው፣ 53 በመቶ የጋዛ ግዛት ውስጥ በየአካባቢያቸው የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

በዶናልድ ትራምፕ የሰላም ዕቅድ ላይ ዓለም አቀፍ አረጋጊ ኃይል እንዲሰማራ እና አዲስ የሚሰለጥኑ የፍልስጤም ፖሊስ ኃይል እንዲደራጁ የሚለው በሚቀጥለው የሰላም ስምምነት ውይይት ላይ ይነሳሉ ተብሎ ቢጠበቅም እነዚህ ቡድኖች ግን አልተካተቱም።

ግዙፍ ከሆኑ የታጣቂ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው በያሲር አቡ ሻባብ የሚመራ ሲሆን በደቡብ ራፋህ ከተማ አቅራቢያ ይንቀሳቀሳል።

በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተለቀቀ ቪዲዮ ላይ ምክትሉ፣ በትራምፕ የሰላም ዕቅድ መሠረት ጋዛን እንዲያስተዳድር ኃላፊነት ከሚወስደው ዓለም አቀፍ አካል፣ ከሰላም ቦርድ ጋር ተቀናጅቶ ስለመሥራት ያወራ ነበር።

ሆሳም አል አስታል በኻን ዩኒስ አቅራቢያ የሚገኘውን የፀረ-ሽብር ጥቃት ኃይል ሚሊሻዎችን ይመራል

የፎቶው ባለመብት, Hossam al-Astal/Facebook

የምስሉ መግለጫ, ሆሳም አል አስታል በኻን ዩኒስ አቅራቢያ የሚገኘውን የፀረ-ሽብር ጥቃት ኃይል ሚሊሻዎችን ይመራል

በደቡባዊዋ ኻን ዩኒስ ከተማ አቅራቢያ የፀረ-ሽብር ጥቃት ኃይል የተሰኘውን ሚሊሻ የሚመራው ሆሳም አል አስታል ለእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደተናገረው "የአሜሪካ ተወካዮች" ቡድኑ በወደፊቷ የጋዛ የፖሊስ ኃይል ውስጥ ሚና እንደሚኖረው አረጋግጠውለታል።

አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ግን በአሁኑ ሰዓት ምንም የሚገልጹት ነገር እንደሌላቸው ተናግረዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አስታል አሜሪካውያንን በወደፊቷ ጋዛ ውስጥ ስለሚኖራቸው ተሳትፎ አናግሮ እንደሆነ ቢቢሲ ሲጠይቀው ፈገግ ብሎ ዝርዝሩን በቅርቡ እናገራለሁ ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ባደረጓቸው ውይይቶች ደስተኛ መሆናቸውን ሲጠየቅ በደማቅ ፈገግታ "አዎ" ሲል መልሷል።

አትክልቶች

የፎቶው ባለመብት, Hossam al-Astal

የምስሉ መግለጫ, በሆሳም አል አስታል የተጋራ አንድ ቪዲዮ የእርሱ ሚሊሻዎቹ በሚያስተዳድሯቸው ድንኳኖች ትኩስ ምግቦች ሲያከፋፈሉ ይታያል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሆሳም አል አስታል በአንድ ወቅት ለፍልስጤም አስተዳደር ሰርቷል። የእርሱ ቡድን ትንሽ ሲሆን ምናልባት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች ብቻ ይሆናል ያሉት።

ነገር ግን በራስ የመተማመን ስሜቱ እየጨመረ ሲሆን በኻን ዩኒስ አቅራቢያ ጥሩ የእርዳታ አቅርቦት የሚያገኝ የመጠለያ ድንኳን መገኛን ያስተዳድራል።

እርዳታውን የምትሰጠው እስራኤል መሆኗን ሲጠየቅ "ይህን ጥያቄ የምመልስበት ትክክለኛው ጊዜ አይደለም እንበል" ሲል ፈገግ ብሎ መልሷል።

ነገር ግን ምግብ፣ መሣሪያ፣ ሁሉንም ነገር ለማስገባት ከእስራኤል ጋር እንደሚተባበር ጨምሮ ተናግሯል።

ለታጣቂዎቹ ክፍያ ከየት እንደሚያገኝ ሲጠየቅም "በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች እየደገፉን ነው" ሲል መልሷል።

"ሁሉም ነገር ከእስራኤል የሚገኝ አይደለም፤ እስራኤል ብቻ የምትደግፈን እና እኛ የእስራኤል ወኪሎች እንደሆንን ይናገራሉ። እኛ የእስራኤል ወኪሎች አይደለንም" ብሏል።

በተኩስ አቁም ስምምነቱ በአሁኑ ጊዜ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ባለው አካባቢ፣ በቢጫው መስመር ውስጥ፣ አዲስ ወደ ተቋቋመው መጠለያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ለመኖር እየመጡ ነው እናም በየሳምንቱ ብዙ ሰዎች መምጣታቸውን ቀጥለዋል ሲል ያስረዳል።

"የአዲሲቷ ጋዛ ቀጣይ ቀኖች ነን፤ ከፍልስጤም አስተዳደር፣ ከአሜሪካኖች፣ ከእኛ ጋር ከሚስማማ ማንኛውም አካል ጋር ለመተባበር ምንም ችግር የለብንም። እኛ ከሐማስ የተሻለ አማራጭ ነን።"

ነገር ግን ብዙ በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን፣ በሐማስ ተስፋ የቆረጡትን ጨምሮ፣ ለእነዚህ አነስተኛ እና የተበታተኑ ታጣቂ ቡድኖች በተሰጠው አዲስ ኃይል ደስተኛ አይደሉም።

በአሁኑ ጊዜ በጋዛ ከተማ የሚኖሩት ሳሌህ ስዊዳን "ሃይማኖት፣ እምነት እና ሥነምግባር የሌላቸው ጥቂት ሰዎች ብቻ ወደ እነዚህ ወንጀለኞች ተቀላቅለዋል" ብለዋል።

"የጋዛ መንግሥት እያስተዳደረን ነበር፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ብዙ ጫናዎች ቢኖሩም የትኛውም መንግሥት ከወንበዴዎች ይሻላል።"

ሌላዋ የጋዛ ከተማ ነዋሪ ዛህር ዱላህ በበኩላቸው "እነዚህ ከእስራኤል ወረራ ጋር የሚተባበሩ ቡድኖች ጦርነቱ ያስከተለው እጅግ የከፋ ውጤት ናቸው" ብለዋል።

አክለውም "እነርሱን መቀላቀል አደገኛ ብቻ ሳይሆን ትልቅ ክህደት ነው።"

የፒፕልስ አርሚ መሪ የሆነው አሽራፍ ማንሲ በጥቅምት ወር ሐማስ ሚሊሻዎቹ ወደሚንቀሳቀሱበት ሰሜናዊ የጋዛ አካባቢዎች እንዳይጠጋ ባስተላለፈው የቪዲዮ መልዕከት ላይ አስጠንቅቋል

የፎቶው ባለመብት, Ashraf al-Mansi

የምስሉ መግለጫ, የፒፕልስ አርሚ መሪ የሆነው አሽራፍ ማንሲ በጥቅምት ወር ሐማስ ሚሊሻዎቹ ወደሚንቀሳቀሱበት ሰሜናዊ የጋዛ አካባቢዎች እንዳይጠጋ ባስተላለፈው የቪዲዮ መልዕከት ላይ አስጠንቅቋል

የሠላሳ አንድ ዓመቱ ሞንታሰር ማሱድ ከሁለት ወራት በፊት ከሚስቱና ከአራት ልጆቹ ጋር በመሆን ወደ አል-አስታል አዲስ የድንኳን ከተማ መምጣቱን ይናገራል።

ከሐማስ ለመሸሽ በለሊት መጓዙን የሚናገረው ማሱድ ቢጫውን መስመር አልፎ በሚገኘው የድንኳን ከተማ እየኖረ ነው።

ነገር ግን በሐማስ ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ዘመዶቹ እርምጃውን መተቸታቸውን ይናገራል።

"የሰራነው ስህተት መሆኑን፣ ምንም ተስፋ እንደሌለው በመናገር ያንጓጥጡን ነበር" ብሏል።

"ከቢጫው መስመር ውጭ ስለሚኖሩ እና ማንኛውም የሐማስ ሰው ከጎናቸው ሊደበቅ ስለሚችል የምንጨነቀው ለእነሱ መሆኑን እንነግራቸዋለን።"

ከቢቢሲ ጋር በስልክ ሲያወራ በአካባቢው ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ በተደጋጋሚ ይሰማ ነበር።

"በአቅራቢያው የሚገኝ [የእስራኤል] ጦር ነው" ሲል ገልጾ "ነገር ግን እኛ ዒላማ እንዳልሆንን ስለምናውቅ ችግር የለውም።"

ያስር አቡ ሸባብ በራፋህ የሚገኘውን የፖፑላር ፎርስ ሚሊሻዎችን ይመራል

የፎቶው ባለመብት, Yasser Abu Shabab/Facebook

የምስሉ መግለጫ, ያስር አቡ ሸባብ በራፋህ የሚገኘውን የፖፑላር ፎርስ ሚሊሻዎችን ይመራል

በአሁኑ ጊዜ በርካታ የታጠቁ ቡድኖች ውስብስብ እና እርስ በእርሱ የተጠላለፈ ግንኙነት ቢኖራቸውም ሐማስ ላይ በጋራ ዘምተዋል።

የአቡ ሸባብ ቡድን በጦርነቱ ወቅት ወደ ጋዛ የተላኩ የእርዳታ መኪኖችን ዘርፏል ተብሎ የተከሰሰ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገባ መሠረት ሁለቱ አባላቱ ከዚህ ቀደም ከእስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ጋር ግንኙነት ነበራቸው።

ባለፈው ወር የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው የሚሊሺያ ቡድኖችን በድብቅ ትደግፋለች ለሚለው ጥያቄ "ምን ችግር አለው?" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

"ጥሩ ነገር ነው፤ የወታደሮችን ሕይወት ይታደጋል" ካሉ በኋላ መረጃውን ይፋ ማድረግ "ሐማስን ብቻ ነው የሚረዳው" ብለዋል።

የፍልስጤም አስተዳደር ሜጀር ጄኔራል አንዋር ራጃብ የታጠቁት ቡድኖች በጋዛ የሚቋቋመው አዲስ የፖሊስ ኃይል ውስጥ በጅምላ ይዋሃዳሉ የሚል ነገር የለም ይላሉ
የምስሉ መግለጫ, የፍልስጤም አስተዳደር ሜጀር ጄኔራል አንዋር ራጃብ የታጠቁት ቡድኖች በጋዛ የሚቋቋመው አዲስ የፖሊስ ኃይል ውስጥ በጅምላ ይዋሃዳሉ የሚል ነገር የለም ይላሉ

ኔታንያሁ ጋዛ በሐማስም ሆነ በተቀናቃኙ የፍልስጤም አስተዳደር አትመራም ሲሉ አሳስበዋል።

በአሜሪካ የሰላም ዕቅድ መሠረት የፍልሥጤም አስተዳደር የተሃድሶ ሥራዎቹን እስኪያጠናቅቅ ድረስ፣ ከፓለቲካዊ ገለልተኛ የሆነ ከፍልስጤም ምሁራን የሚውጣጣ ኮሚቴ በዓለም አቀፍ ዕይታ ስር ሆኖ ለአጭር ጊዜ ያስተዳድራል።

ነገር ግን አንድ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለሥልጣን የአስታል ተዋጊዎች የመጪው ጋዛ የፖሊስ ኃይል አካል ይሆናሉ የሚለውን ውድቅ አድርገውታል።

የፍልስጤም አስተዳደር የጸጥታ ኃይሎች ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል አንዋር ራጃብ ለቢቢሲ በእስራኤል የሚደገፉ ከጋዛ ታጣቂ ቡድኖች የተውጣጡ ሰዎች በሙሉ በጅምላ የውህደቱ አካል ይሆናሉ የሚል ንግግር የለም ብለዋል።

በዌስት ባንክ ራማላህ ከተማ በመሆን በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ "እስራኤል የእነዚህን ሚሊሻዎች ውህደት ለራሷ ደህንነት እና የፖለቲካ ጥቅም ስትል ልትጠይቅ ትችላለች። ነገር ግን የእስራኤል ጥያቄ ፍልስጤማውያንን የሚጠቅም አይደለም፤ እስራኤል በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በጋዛ ሰርጥ ቁጥጥርዋን መቀጠል ትፈልጋለች።"

የፒፕልስ አርሚ አባላት በሰሜናዊ ጋዛ ውስጥ ቅኝት እያደረጉ

የፎቶው ባለመብት, ab.kaser/TikTok

የምስሉ መግለጫ, የፒፕልስ አርሚ አባላት በሰሜናዊ ጋዛ ውስጥ ቅኝት እያደረጉ

ዘላቂ ሰላም በሚሰፍንበት ወቅት አዲሶቹ የጋዛ ታጣቂዎች ምን ይሆናሉ የሚለው ጥያቄ አሁንም ምላሽ አላገኘም።

እስራኤል በጋዛ የጠላቷን ጠላቶች ለመደገፍ መወሰኗ ከታሪክ ያለመማሯ ምልክት ነው ሲሉ የቀድሞ የፍልስጤም ወታደራዊ መረጃ ኃላፊ ማይክል ሚልሽታይን ተናግረዋል።

"ይህ ከ30 ዓመታት በፊት አሜሪካኖች በአፍጋኒስታን ከወሰዱት እርምጃ ጋር ተመሳሳይ ነው።"

"ሶቪየቶችን ለመጣል ታሊባንን ደግፈዋል፤ ከዚያም ታሊባን ከአሜሪካ ያገኙትን መሣሪያ ተጠቅመው በአሜሪካውያን ላይ ጥቃት ከፍተዋል።"

እስራኤል አሁን ከሐማስ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ርዕዮተ ዓለም የተለየ አማራጭ እንደሚሰጡ በማሰብ አጠራጣሪ ታሪክ ባላቸው ቡድኖች ላይ ትተማመናለች ብለዋል።

"ከእስራኤል ያገኙትን መሣሪያ አፈ ሙዝ ወደ እስራኤል ጦር የሚያዞሩበት ጊዜ ይመጣል" ብለዋል።

ጡረታ የወጡት የእስራኤል ወታደራዊ መረጃ መኮንን ሚካኤል ሚልሽታይን እስራኤል የፍልስጤም ሚሊሻዎችን በመደገፍ አደገኛ መንገድ ተከትላለች ብለዋል
የምስሉ መግለጫ, ጡረታ የወጡት የእስራኤል ወታደራዊ መረጃ መኮንን ሚካኤል ሚልሽታይን እስራኤል የፍልስጤም ሚሊሻዎችን በመደገፍ አደገኛ መንገድ ተከትላለች ብለዋል

እስራኤል ሐማስን ለማዳከም ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ለታጣቂ ቡድኖች የምትሰጠው እገዛ የፍልስጤም ተቃዋሚዎችን ለመከፋፈል ቀላል ያደርግላታል።

ይህም ጦሯ ጋዛን ለቅቆ ከወጣ በኋላ ተፅዕኖዋን ማስቀጠል ያስችላታል።

አንዳንድ ተቺዎች የተለያዩ የአገር ውስጥ ቡድኖችን ማስታጠቅ ሐማስ ትጥቁን እንዲፈታ ለማግባባት ከባድ ያደርገዋል እንዲሁም የዓለም አቀፍ ኃይሎች የጋዛን ደህንነት ለማረጋገጥ እርምጃ ለመውሰድ ይቸገራሉ ይላሉ።

ነገር ግን ለእስራኤል አደጋው እየረዳቻቸው ያለቻቸው እነዚሁ ቡድኖች አንድ ቀን የምትገጥማቸው አዲስ ጠላት መሆናቸው ላይ ነው።

ከአርባ ዓመታት በፊት ተቀባይነታቸው እያደገ የመጣውን የፍልስጤሙን መሪ ያሲር አራፋትን ለመገዳደር የተመሠረተው ኃይል በጋዛ የሚገኘውን ጠንካራ እስላማዊ ድርጅት ፈጥሯል።

ያ ድርጅትም የዛሬው ሐማስ ሆኗል።