የ81 ዓመቱ ሙሴቬኒ በምርጫ በማሸነፋቸው የ40 ዓመት ሥልጣናቸውን ሊያራዝሙ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ሐሙስ ዕለት በኡጋንዳ በተካሄደው ምርጫ ለተጨማሪ አምስት ዓመት አገሪቱን ለመምራት መመረጣቸው ተገለጸ።
ሙሴቬኒ ለሰባተኛ ጊዜ በተሳተፉበት ምርጫ በሥልጣን ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ድምጽ በማግኘታቸው ኡጋንዳን የመሩበትን አርባ ዓመት ያራዝመዋል።
የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን እዳስታወቀው ሙሴቬኒ በምርጫው 72 በመቶ የመራጮች ድምጽን ሲያገኙ፣ የምርጫውን ውጤት "ሐሰተኛ" በማለት የተቃወመው ዋነኛው ተፎካካሪያቸው ቦቢ ዋይን የ25 በመቶ መራጮችን ድምጽ አግኝቷል።
በውጤቱ መሸነፉ የታወቀው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዋይን ኡጋዳውያን ሰላማዊ ተቃውሞ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
የአማጺ ቡድን መሪ ሆነው በአውሮፓውያኑ 1986 ወደ ኡጋንዳ መሪነት የመጡት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በአሁኑ ጊዜ የ81 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ፣ አስካሁን የተሳተፉባቸውን ሰባት ምርጫዎችን በሙሉ አሸንፈዋል።
የአሁኑ የምርጫ ሂደት በግጭቶች የተከበበ የነበረ ሲሆን፣ ዋነኛው ተፎካካሪ የ43 ዓመቱ ጎልማሳ እና የቀድሞ ሙዚቀኛ ቦቢ ዋይን አስካሁን ቢያንስ 21 ሰዎች ተገድዋል ብሏል።
ነገር ግን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቁጥሩ ሰባት ብቻ ነው ይላሉ።
ከምርጫው ዕለት ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት የመረጃዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አዳጋች ሆኗል።
ለባሥልጣናት ኢንተርኔት እንዲቋረጥ የተደረገው የአሳሳች መረጃ ሥርጭትን፣ ማጭበርበር እና የግጭት ቅስቀሳን ለመከላከል ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ግን ኢንተርኔት እንዲዘጋ መደረጉ "በእጅጉ እንዳሳሰበው" ገልጿል።















