የ81 ዓመቱ ሙሴቬኒ በምርጫ በማሸነፋቸው የ40 ዓመት ሥልጣናቸውን ሊያራዝሙ ነው

ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ሐሙስ ዕለት በኡጋንዳ በተካሄደው ምርጫ ለተጨማሪ አምስት ዓመት አገሪቱን ለመምራት መመረጣቸው ተገለጸ።

ሙሴቬኒ ለሰባተኛ ጊዜ በተሳተፉበት ምርጫ በሥልጣን ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ድምጽ በማግኘታቸው ኡጋንዳን የመሩበትን አርባ ዓመት ያራዝመዋል።

የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን እዳስታወቀው ሙሴቬኒ በምርጫው 72 በመቶ የመራጮች ድምጽን ሲያገኙ፣ የምርጫውን ውጤት "ሐሰተኛ" በማለት የተቃወመው ዋነኛው ተፎካካሪያቸው ቦቢ ዋይን የ25 በመቶ መራጮችን ድምጽ አግኝቷል።

በውጤቱ መሸነፉ የታወቀው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዋይን ኡጋዳውያን ሰላማዊ ተቃውሞ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የአማጺ ቡድን መሪ ሆነው በአውሮፓውያኑ 1986 ወደ ኡጋንዳ መሪነት የመጡት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በአሁኑ ጊዜ የ81 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ፣ አስካሁን የተሳተፉባቸውን ሰባት ምርጫዎችን በሙሉ አሸንፈዋል።

የአሁኑ የምርጫ ሂደት በግጭቶች የተከበበ የነበረ ሲሆን፣ ዋነኛው ተፎካካሪ የ43 ዓመቱ ጎልማሳ እና የቀድሞ ሙዚቀኛ ቦቢ ዋይን አስካሁን ቢያንስ 21 ሰዎች ተገድዋል ብሏል።

ነገር ግን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቁጥሩ ሰባት ብቻ ነው ይላሉ።

ከምርጫው ዕለት ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት የመረጃዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አዳጋች ሆኗል።

ለባሥልጣናት ኢንተርኔት እንዲቋረጥ የተደረገው የአሳሳች መረጃ ሥርጭትን፣ ማጭበርበር እና የግጭት ቅስቀሳን ለመከላከል ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ግን ኢንተርኔት እንዲዘጋ መደረጉ "በእጅጉ እንዳሳሰበው" ገልጿል።

የዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲው ዕጩ ቦቢ ዋይን የድምጽ መስጫ ሳጥኖች ቀድመው ተሞልተው ነበር በማለት የምርጫወን ሂደት ውድቅ ቢያድርግም፤ የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች ግን ክሱን የሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዳላዩ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድንን የመሩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን በአገሪቱ ኢንተርኔት መቋረጡን ተችተዋል።

በተጨማሪም "ማስፈራራት፣ እስር እና አፈናን" የሚያመለክቱ ሪፖርቶችን በማንሳት ድርጊቶቹ "ፍርሃት በመፍጠር ሕዝቡ በምርጫው ሂደት ላይ ያለውን እምነት ይሸረሽራል" ሲሉ መቃወማቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።

የቦቢ ፓርቲ መሪያቸው አርብ ሌሊት ካምፓላ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በፀጥታ ኃይሎች በግዳጅ መወሰዱን ቢገልጹም ፖሊስ አስተባብሎ ነበር።

ኋላ ላይ ግን ዋይን በፌስቡክ ገጹ ላይ ባሠራጨው መልዕክት የፀጥታ ኃይሎች በቤቱ ላይ ወረራ ፈጽመው ሊይዙት ያደረጉትን ሙከራ ማምለጡን እና ሚስቱ እንዲሁም ሌሎች ዘመዶቹ ግን በቁም አስር ላይ ናቸው ብሏል።

ቀደም ሲል በቁም እስር ላይ መሆኑን አሳውቆ ነበር።

ቅዳሜ ጠዋት የፖሊስ ቃል አቀባይ ለጋዜጠኞች ቦቢ ዋይን ከሚስቱ እና ከዘመዶቹ ጋር ቤቱ ውስጥ መሆኑን ገልጸው፣ ከእውነት የራቀ ክስ እያሰሙ ነው በማለት ቤቱ የደኅንነት ጥበቃ የሚደረግለት በመሆኑ እንቅስቃሴው የተገደበ ነው ብለዋል።

አብዛኛው ሕዝቧ ከ30 ዓመት ዕድሜ በታች በሆኑባት ኡጋንዳ ዋይን የሚወክለው ወጣቱን መሆኑን ይናገራል።

በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ቦቢ ዋይን በአገሪቱ ያለውን ሙስና ለመቆጣጠር እና መጠነ ሰፊ ለውጥ ለማካሄድ ቃል ገብቶ ነበር።

ሙሴቬኒ በበኩላቸው የረጅም ጊዜ የግጭት ታሪክ ባላት ኡጋንዳ ውስጥ መረጋጋትን ለማረጋገጥ ቀዳሚው ሰው መሆናቸውን ሲለግጹ ነበር።

በፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ሌሎች ስድስት ተወዳዳሪ ዕጩዎች የቀረቡ ቢሆንም አንዳቸውም ከ2 በመቶ በላይ የመራጮች ድምጽ ማግኘት አልቻሉም።

በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ የተገደበ የነበረ ሲሆን፣ የፀጥታ ኃይሎች በዋይን ደጋፊዎች ላይ ጥቃት እና እስር በመፈጸም ይከሰሳሉ።

ፖሊስ ግን ክሱን በማስተባበል የተቃዋሚው ደጋፊዎችን በችግር ፈጣሪነት ከስሷል።