"የገና ዕለት በራችን ላይ ያገኘነው እንግዳ ለ45 ዓመታት አብሮን ኖረ"

ገና የደግነት ዐውደ ዓመት ተደርጎ ይወሰዳል። በዩናይትድ ኪንግደም የሚኖሩ ጥንዶች ከ50 ዓመት በፊት ለገና በጎ ድርጊት ለመፈጸም ሲወስኑ ሕይወታቸውን እስከወዲያኛው እንደሚለውጠው አላወቁም።

በአውሮፓውያኑ 1975 ሮብ ፓርሰንስ እና ዳያን ፓርሰን ለገና እየተሰናዱ ሳለ በራቸው ተንኳኳ። እቃዎቹን በአንድ እጁ፣ በሌላ እጁ ደግሞ ዶሮ የያዘ ሰው ደጃፋቸው ላይ አገኙ።

ሮብ ሰውየውን በትንሹ አስታወሰው። ሮኒ ሎክውድ ይባላል። ሮብ እና ሮኒ ታዳጊ ሳሉ የሰንበት ትምህርት አብረው ይማሩ ነበር። ሮኒ መልኩ ተለውጧል።

"ሮኒ ዶሮው ምን ያደርግለሀል?" ሲል ሮብ ጠየቀ።

"ሰው ሰጥቶኝ ነው" ብሎ ሮኒ መለሰ።

"ጎራ በል" ብሎ ሮብ ጋበዘው።

ያ ቅጽበት የሁለቱንም ሕይወት ቀየረ።

ሮብ እና ባለቤቱ ያኔ 27 እና 26 ዓመታቸው ነበር። ኦቲዝም ያለበት ሮኒን ወደ ቤታቸው ጋበዙት።

የያዘውን ዶሮ ተቀብለው አበሰሉት። ሰውነቱን ታጠበ። ገናን አብሯቸው አከበረ።

ያ የገና ደግነት 45 ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነት ፈጥሯል።

አሁን ሮብ እና ዳያን 77 እና 76 ዓመታቸው ነው።

ሮኒ ከ15 ዓመቱ ጀምሮ ጎዳና ነው የኖረው። ሮብ የወጣቶች ማዕከል ውስጥ ሲሠራ ያየው ነበር።

ሮኒ ገናን ደስ ብሎት እንዲያሳልፍ የጥንዶቹ ቤተሰቦች ስጦታ ይወስዱለት ነበር።

"የገና ዛፉ ጋር ቁጭ ብሎ ስጦታዎቹን እያየ አለቀሰ። ከዚያ በፊት ፍቅር ምን እንደሚመስል አይቶ አያውቅም ነበር" ትላለች ዳያን።

ሮኒን የጋበዙት ገናን አብሯቸው እንዲያከብር ቢሆንም ከቤታቸው እንዲወጣ አልፈለጉም።

ሮኒ ሥራ ለመቀጠር ቋሚ አድራሻ ያስፈልገዋል። የጎዳና ተዳዳሪዎች ሥራ አጥ እንዲሆኑ ያደረገ አካሄድ መሆኑ ይገለጻል።

ሮኒ ከስምንት ዓመቱ ጀምሮ ለታዳጊዎች እንክብካቤ በሚሰጥበት ማዕከል ኖኗል። 11 ዓመት ሲሆነው ግን ጥሎት ወጣ።

ሮብ 'A Knock on the Door' የሚል መጽሐፍ ሲያዘጋጅ ባደገው ጥናት ስለ ሮኒ ልጅነት ለማወቅ ችሏል።

በዚያን ዘመን 'ጤናማ ያልሆኑ ታዳጊ ወንዶች ትምህርት ቤት' ወደሚባል ተቋም ተልኮ ነበር። ሮኒ በትምህርት ቤቱ ጓደኛ እንዳልነበረው ሮብ ይናገራል።

"የሚያውቀው የማኅበራዊ አገልግሎት ባለሙያ የለም። የሚያውቁት መምህራንም አልነበሩም።"

ትምህር ቤት ሳለ ካሳለፈው ጊዜ ተነስቶ ሁሌም 'ስህተት ሠራሁ እንዴ?' ብሎ አዘውትሮ እንደሚጠይቅ ሮብ እና ሮኒ ይናገራሉ።

ሮኒ 15 ዓመት ሲሞላው ማንም የሚደግፈው ሰው ባይኖርም ወደ ትውልድ መንደሩ ተላከ።

ዐይን አፋሩ ሮኒ ብዙ አያወራም። ጥንዶቹ ሲቀርቡት ግን "በጣም እንደወደዱት" ይናገራሉ።

ሮኒ ቆሻሻ የመሰብሰብ ሥራ እንዲያገኝ ጥንዶቹ ረዱት። ከትምህርት ቤት ከወጣ ጀምሮ ልብሱን ቀይሮ አያውቅም ነበርና አዳዲስ ልብሶች ገዙለች።

"ልጆች ስለሌሉን እሱን ስናለብሰው ደስ ይለን ነበር" ይላል ሮብ።

ያኔ ጠበቃ የነበረው ሮብ ጠዋት እየተነሳ ሮኒን ሥራ ያደርሰዋል። አንድ ቀን ሮብ ቤት ሲገባ ሮኒ እየሳቀ አገኘው።

"ምንድን ነው እንዲህ የሚያስቅህ?" ብሎ ጠየቀው።

"ሥራ ቦታ ስታደርሰኝ 'ማን ነው?' ብለው ጠየቁኝ እና 'ጠበቃዬ ነው' አልኳቸው" ብሎ መሳቅ ቀጠለ።

ወደ ሥራ የሚያደርሰው ጠበቃ መሆኑ ያኮራው ነበር።

ሮኒ ብዙ ልማዶች አሉት። ሁሌም ጠዋት እቃዎችን ከእቃ ማጠቢያ ማሽን ያወጣል። ሮብ ሁሌም መደነቁን ለሮኒ ያሳያየዋል።

"ሮኒ ተመሳሳይ ጥያቄ ሰኞም ማክሰኞም ሊጠይቅ ይችላል። ማንበብ እና መጻፍ ቢከብደውም በየቀኑ 'ሳውዝ ዌልስ ኤኮ' ጋዜጣ ይገዛል።"

በየዓመቱ ለገና የሚገዛላቸው ፖስት ካርድ ተመሳሳይ ነው። ጥንዶቹ በየዓመቱ እንደ አዲስ ይደሰታሉ።

ሮኒ አብዛኛውን ትርፍ ጊዜውን የሚያሳልፈው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጎዳና ተዳዳሪዎች እርዳታ በመሰብሰብ ነው። ያለ ምንም መዛነፍ ወንበሮችን ይደረድራል።

ዳያን ስለ ሮኒ ደግነት እንዲህ ትገልጻለች።

"አንድ ቀን የማላውቀው ጫማ አድረጎ መጣ። የእሱ ጫማ የት እንደሄደ ስጠይቀው 'ለጎዳና ተዳዳሪ ሰጠሁት' አለኝ። ሮኒ እንደዚህ ያለ ሰው ነው። ድንቅ ሰው ነው።"

ዳያን ከፍተኛ ድካም ውስጥ የሚከተው ህመም ሲይዛት ከአልጋ መውጣት የሚሳናት ቀናት ነበሩ።

"የሦስት ዓመት ልጅ አለን። ሮብ ደግሞ ሥራ ላይ ነው" ትላለች።

በዚያን ወቅት የረዳት ኖኒ ነው። ለልጇ ሎይድ ወተት የሚያፈላው እሱ ነበር። ሌላዋ ልጃቸው ኬቲን ያጫውታል። በቤት ውስጥ ሥራ ያግዛታል።

ከሮኒ ጋር መኖር ከባድ የሆነበት ጊዜም ነበር። ሮኒ ለ20 ዓመት በቁማር ሱስ ተሰቃይቷል። ሆኖም ግን ጥንዶቹ ያለ ሮኒ መኖር አይሹም።

"ሮኒ በብዙ መንገድ ሕይወታችንን ለውጦታል" ይላል ሮብ።

ዳያን ደግሞ "ሮኒ ልበ-መልካም ነው። ደግ ነው። አንዳንዴ እንደ እናቱ አንዳንዴ እንደ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ሌላ ጊዜም እንደ ተንከባካቢው ነበርኩ" ስትል ትናገራለች።

ጥንዶቹ ጓደኞቻቸው ቤት ሲመጡም ሮኒ ሁሌም አለ።

ልጆቻቸው "እንዴት ነው በዚህ መንገድ የምትቀጥሉት?" ብለው ጠይቀዋቸዋል። ጥንዶቹም "ሮኒ፤ ሮኒ ነው" ሲሉ ይመልሳሉ።

ልጆቻቸው ያለ ሮኒ ሕይወትን አያውቁም።

"ከእሱ ውጪ ሕይወት ምን እንደሚመስል አያውቁም። እነሱ ከመወለዳቸው በፊት ሮኒ ነበር። ልጆቻችን አድገው ልጆች ካፈሩ በኋላም ሮኒ አለ" ይላል ሮብ።

ሮኒ ብቻውን ቤት እንዲከራይ ለማድረግ ጥንዶቹ በአንድ ወቅት ሞክረዋል።

ነገሩን ሊያዋዩት መኝታ ክፍሉ ሲገቡ እንደተለመደው "ስህተት ሠራሁ እንዴ?" ብሎ ጠየቀ።

ዳያን እያለቀሰች ክፍሉን ጥላ ወጣች። ሮብ እና ዳያን ጨክነው ከቤት ሊያስወጡት አልቻሉም።

ከቀናት በኋላ "እኛ ሦስታችን ጠንካራ ጓደኛሞች ነን አይደል?" ብሎ ጠየቃቸው። ትክክል እንደሆነ ነገሩት።

"ሁሌም አብረን እንኖራለን አይደል?" ብሎ ሌላ ጥያቄ አስከተለ።

ሮኒ ወደ ባለቤቱ ተመለከተ እና "አዎን፤ ሁሌም አብረን እንኖራለን" ሲል መለሰ።

ቃል እንደተገባቡትም አብረው ኖሩ።

በ2020 ሮኒ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። በስትሮክ ለዓመታት የተሰቃየው ሮኒ ሲሞት 75 ዓመቱ ነበር።

ጥንዶቹ ሮኒ እንደሚናፍቃቸው ይናገራሉ። የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሲፈጸም በኮቪድ ክልከላ ምክንያት ከ50 ሰዎች በላይ መታደም አልቻሉም።

ሮኒ ከሞተ በኋላ በካርዲፍ የሚገኘው ግሌንውድ ቤተ ክርስቲያን የከፈተው የእርደታ ማዕከል በስሙ ተሰይሞለታል።

በ1.6 ሚሊዮን ፓውንድ የተመሠረተው ማዕከል 'ሎክውድ ሐውስ' ተብሏል።

የማዕከሉን ግንባታ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልግ ነበር።

"የሚገርመው ነገር የሚያስፈልጋቸው የገንዘብ መጠን ሮብ በኑዛዜው ያስቀመጠው ያህል ነበር። ቤት ያልነበረው ሮኒ ለሁላችንም የሚሆን ቤት የሚገነባ ሰው ሆነ" ሲል ሮብ ይገልጻል።

ዳያንም "አይገርምም የዕጣ ፈንታ ነገር። እንዴት 45 ዓመት ኖራችሁ? ብለው የሚጠይቁን አሉ። አንድ ቀን ከዚያም ሌላ ቀን እያልን ነው የኖርነው። ሮኒ ሕይወታችንን ውብ አድርጎታል" ትላለች።