ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕይወታቸውን ለማዳን የተሰጣቸው ደም ለኤችአይቪ ያጋለጣቸው ሕጻናት
በሕንድ በዘር የሚተላለፍ የነጭ ደም ሕዋስ እክል ታላሴሚያ (thalassemia) ያለባቸው ልጆች ለኤችአይቪ መጋለጣቸው ወላጆችን ልብ በእጅጉ ሰብሯል።
ልጆቹ በሕይወት እንዲቆዩ በሚያስላቸው የደም ልገሳ ምክንያት ነው በኤችአይቪ ኤድስ የተያዙት።
የደም ማነስን ለመግታት እና ሕይወትን ለማስቀጠል ለልጆቹ ደም ሊሰጣቸው ይገባል።
የሕንድ ማዕከላዊ ግዛት ማዳያ ፕራዴሽ ባለሥልጣናት እንዳሉት፤ አምስት ህመሙ ያለባቸው እና ዕድሜያቸው ከሦስት እስከ 15 የሆኑ ልጆች ኤችአይቪ በደማቸው ተገኝቷል።
ስለ ደም ልገሳ ጥያቄ በመነሳቱም መርማሪ ኮሚቴ ተዋቅሯል።
ወላጆቹ የሚኖሩት በሳንታ ግዛት ነው። ልጆቹ በደማቸው ውስጥ ኤችአይቪ እንዳለ የታወቀው ባለፈው ዓመት ከጥር እስከ ግንቦት በተደረገላቸው መደበኛ ምርመራ ነው።
ከዚህ ቀደም በምሥራቃዊ ሕንድ ጃራካንድ ግዛትም ተመሳሳይ ነገር ተከስቷል። ዕድሜያቸው ከስምንት ዓመት በታች የሆነ አምስት ታዳጊዎች በመንግሥት ሆስፒታል ደም ተሰጥቷቸው ለቫይረሱ መጋለጣቸው ተገልጿል።
ኤችአይቪ በግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ከእናት ወደ ልጅ እንዲሁም ጥንቃቄ በጎደለው የሕክምና አሰጣጥ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል። የደም ልገሳም በዚህ ውስጥ ይካተታል።
ኤችአይቪ የዕድሜ ልክ የጤና ክትትል የሚያስፈልገው ህመም ነው። በሕንድ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ በየዓመቱ 66 ሺህ በላይ ሰዎች በህመሙ ይያዛሉ።
ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የዕድሜ ልክ ሕክምና (antiretroviral therapy ወይም ART) እየተከታተሉ እንደሆነ የመንግሥት መረጃ ያሳያል።
የሳንታ ግዛት አመራር ሳታሽ ኩማር ኤስ እንዳሉት፤ አምስት ልጆች በተለያዩ ቦታዎች እና ከተለያዩ ደም ለጋሾች ደም ተሰጥቷቸዋል።
በዚህ ውስጥ የመንግሥት ሆስፒታሎች እና የግል የሕክምና ተቋማትም ይገኙበታል። ልጆቹ አሁን ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።
የሦስት ዓመት ታዳጊ እናት እና አባት ቫይረሱ እንዳለባቸው ሲገለጽ፤ የተቀሩት ወላጆች ግን ኤችአይቪ አልተገኘባቸውም።
ይህም ከእናት ወደ ልጅ ቫይረሱ እንዳልተላለፈ ያሳያል።
የሳንታ የሕክምና ኃላፊ ዶ/ር ማኖጅ ሻኩላ እንዳሉት፤ የተለያየ የደም ልገሳ የተሰጣቸው ልጆች የበለጠ ለኤችአይቪ ተጋላጭ ሆነዋል።
"ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደተገኘ ወደ ሕክምና በአፋጣኝ እንወስዳቸዋለን" ብለዋል።
ዶክተሩ እንዳሉት የሚለገስ ደም ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ለህሙማን ይሰጣል።
"ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ሕክምናውን ወዲያውኑ እንዲጀምሩ ተደርገው እንዲቀጥሉ ይደረጋል። በአሁኑ ጊዜ የልጆቹ ጤና በደህና ሁኔታ ላይ ይገኛል።"
ሆኖም ግን ኤችአይቪ ወደ ደማቸው ከገባ ብዙም ያልቆየ ሰዎች ደም ሲመረመር የቫይረሱን መኖር የሚያሳይ ምልክት ላይስተዋል ይችላል።
በሕንድ በዘር የሚተላለፍ የነጭ ደም ሕዋስ እክል ያለባቸው ሰዎች በደም ልገሳ ምክንያት በኤችአይቪ መያዛቸው አዲስ ዜና አይደለም።
ባለፈው ጥቅምት በጃካርድ ግዛት ተመሳሳይ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በመንግሥት ሆስፒታል ውስጥ ይሠሩ የነበሩ የላብራቶሪ ባለሙያ፣ የኤችአይቪ ክፍል ኃላፊ እና ዋና የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ከሥራ ታግደዋል።
ዋና ሚኒስትር ኸርመት ሶረን ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች 200 ሺህ ሩፒ (የሕንድ ገንዘብ) ወይም 2,212 ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2011 በጉጅራት ግዛት 23 በዘር የሚተላለፍ የነጭ ደም ሕዋስ እክል ያለባቸው ልጆች በኤችአይቪ ከተያዙ በኋላ ምርመራ ተከፍቶ ነበር።
ባለፈው ሳምንት የሕንድ ምክር ቤት ብሔራዊ የደም ልገሳ ሕግ እንዲያጸድቅ ተጎጂዎች ሲጠይቁ ነበር። ይህ ግንም የደም ምርመራ እና የደም ልገሳን መቆጣጠር የሚያስችል ሕግ እንደሆነ ተገልጿል።
ኤችአይቪ የያዛቸው ታካሚዎች፣ የመብት ተሟጋቾች እና ወላጆችም ሕጉ እንዲጸድቅ ጫና ማሳደራቸውን ገልጸዋል።
ሕጉ በተደጋጋሚ ደም እየተለገሳቸው ሕይወታቸው የሚቀጥል ሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ እንደሚውልም ይታመናል።
በተለይም በገጠሪቱ ሕንድ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ ልጆቻቸው በኤችአይቪ የተያዙባቸው ወላጆች ስጋት ውስጥ ወድቀዋል።
አንድ አባት "ልጄ በዘር የሚተላለፍ የነጭ ደም ሕዋስ እክል አለባት። አሁን ደግሞ ኤችአይቪ ተጨመረባት። ለዚህ ተጠያቂዎቹ በማዳያ ፕራዴሽ ያሉ ሕክምና ተቋማት ናቸው" ብለዋል።
ሌላ ወላጅ እንዳሉት፤ ልጃቸው የኤችአይቪ መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት በሆነው ማስመለስ እየተሰቃየች ነው።
በሕንድ ኤችአይቪ ያላቸው ሰዎች አሁንም ድረስ መገለል እና መድልዎ ይደርስባቸዋል።
በጃካርድ ግዛት የሰባት ዓመት ልጅ በኤችአይቪ መያዙትን ተከትሎ ሰባት ቤተሰቦቹ ቤት አልባ ሆነዋል። አባትየው እንደገለጹት፤ ቤት አከራያቸው የልጁን መታመም እንደሰሙ ነበር ከቤት ያባረሯቸዋል።
"ላሳምናቸው ብዙ ብሞክርም ቤቱን ለቅቃችሁ ውጡ አሉን። በዚህም ምክንያት 27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው መንደሬ ከመመለስ ውጪ አማራጭ አልነበረኝም። በዚያ መንደር ውስጥ ደግሞ ለልጄ ሕክምና እና ጥሩ ትምህርት ማግኘት ቀላል አይደለም" ብለዋል።