ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ሩሲያና ቻይና ግሪንላንድን እንዳይወስዱ ለመከላከል አሜሪካ 'ባለቤት' መሆን አለባት አሉ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ እና ቻይና ግሪንላንድን እንዳይጠቀልሉ ለመከላከል አሜሪካ "ባለቤት" መሆን ይኖርባታል ሲሉ ተናገሩ።
ትራምፕ አርብ ዕለት ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ "አገሮች የባለቤትነት መብት ሊኖራቸው ይገባል፤ የባለቤትነት መብት ያለህን ነገር ትከላከላለህ፤ የሊዝ ውሎችን አትከላከልም። እናም ግሪንላንድን መከላከል አለብን" ብለዋል።
"በቀላሉ" ወይም "በከባድ መንገድ" እናደርገዋለን ሲሉ አክለዋል።
ዋይት ሐውስ በቅርቡ አስተዳደሩ የኔቶ አባል የሆነችውን የዴንማርክን ከፊል ራስ ገዝ ግዛት ለመግዛት እያሰበ መሆኑን ቢገልጽም፣ በኃይል የመጠቅለል አማራጭን ከጨዋታ ውጭ መሆኑን ግልጽ አላደረገም።
ዴንማርክ እና ግሪንላንድ ግዛቱ ለሽያጭ እንደማይቀርብ ተናግረዋል። ዴንማርክ ወታደራዊ እርምጃ የትራንስ-አትላንቲክ የመከላከያ ጥምረትን እንዲያበቃለት እንደሚያደርግ አስጠንቅቃለች።
በሰሜን አሜሪካ እና በአርክቲክ መካከል የምትገኘው ግሪንላንድ ምንም እንኳን በጣም ብዙ ሕዝብ የማይኖርባት ግዛት ብትሆንም፣ አቀማመጧ የሚሳኤል ጥቃቶች ሲከሰቱ ለቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶች እና በክልሉ ውስጥ መርከቦችን ለመቆጣጠር ምቹ ቦታ ያደርጋታል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ግሪንላንድ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ወሳኝ እንደሆነች በተደጋጋሚ ሲናገሩ፣ ያለምንም ማስረጃ "የሩሲያ እና የቻይና መርከቦች በየስፍራው ይገኛሉ" ብለዋል።
አሜሪካ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ በግሪንላንድ ሰሜን ምዕራብ ጫፍ በሚገኘው የፒቱፊክ የጦር ሠፈሯ ከ100 በላይ ወታደሮች በቋሚነት አስፍራለች።
ከዴንማርክ ጋር በተደረጉ ስምምነቶች መሠረት፣ አሜሪካ የፈለገችውን ያህል ወታደሮችን ወደ ግሪንላንድ የማምጣት ሥልጣን አላት።
ነገር ግን ትራምፕ በዋሽንግተን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሊዝ ስምምነት በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
"አገሮች የዘጠኝ ዓመት ወይም የ100 ዓመት ስምምነቶችን ማድረግ አይችሉም" ሲሉ የባለቤትነት መብት ሊኖራቸው እንደሚገባም አክለዋል።
"የቻይናን ሕዝብ እወዳለሁ። የሩሲያን ሕዝብ እወዳለሁ" ያሉት ትራምፕ "ግን በግሪንላንድ ጎረቤቴ እንዲሆኑ አልፈልግም" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት "በነገራችን ላይ ኔቶ ይህንን መረዳት አለበት" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ማክሰኞ ዕለት ስድስት የአውሮፓ አገራት ለዴንማርክ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ፖላንድ፣ ስፔን እና የዴንማርክ መሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ "ግሪንላንድ የሕዝቧ ነች፣ ግንኙነታቸውን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ መወሰን የሚችሉትም ዴንማርክ እና ግሪንላንድ ብቻ ናቸው" ብለዋል።
እንደ አሜሪካ በአርክቲክ ደህንነት ላይ ቁርጠኛ መሆናቸውን አፅንዖት የሰጡት እነዚህ አገራት፣ ይህ ሊሳካ የሚችለው አሜሪካን ጨምሮ አጋሮች "በጋራ" በመሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
በተጨማሪም "የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መርሆዎችን ማለትም ሉዓላዊነትን፣ የግዛት አንድነትን እና የማይጣስ ድንበርን ጨምሮ" እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።
ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ፕሬዝዳንቱን ኒኮላስ ማዱሮን ለመያዝ በቬንዙዌላ ላይ ወታደራዊ ኃይል ከተጠቀሙ በኋላ የግዛቲቱ የወደፊት ሁኔታ ላይ ዳግም ስጋት ተፈጥሯል።
ትራምፕ ቀደም ሲል እአአ በ2019 በመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው ደሴቲቱን ለመግዛት ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ደሴቲቱ ለሽያጭ እንደማትቀርብ ተነግሯቸዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በሚቀጥለው ሳምንት ከዴንማርክ ጋር ይወያያሉ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግሪንላንድ ብርቅዬ ማዕድናት፣ ዩራኒየም እና ብረትን ጨምሮ ያለው ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል።
እነዚህ ማዕድናት በረዶው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሲቀልጥ በቀላሉ ማግኘት የሚቻሉ ናቸው።
ሳይንቲስቶች ከፍተኛ የነዳጅ እና የጋዝ ክምችት ሊኖር እንደሚችል ይገምታሉ።
አርብ ምሽት የግሪንላንድ ፓርቲ አመራሮች፣ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ "አሜሪካ አገራችንን መናቅ ማቆም አለባት" ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።
"አሜሪካውያን መሆን አንፈልግም፣ ዴንማርካውያን መሆን አንፈልግም፣ ግሪንላንዳውያን መሆን እንፈልጋለን" ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው "የግሪንላንድ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በግሪንላንድ ሕዝብ መወሰን አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።