ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ከሾሙ በኋላ አሜሪካ ግሪንላንድን "ማግኘት አለባት" አሉ
ዶናልድ ትራምፕ ለግሪንላንድ ልዩ መልዕክተኛ ከሾሙ በኋላ ግዛቲቱን ለመጠቅለል እንደሚፈልጉ በመናገራቸው ከዴንማርክ ጋር አዲስ ውዝግብ ውስጥ ገቡ።
ትራምፕ ለግሪንላንድ ልዩ መልዕክተኛ መሾማቸውን ተከትሎ ከቢቢሲ የተሿሚው የሥራ ኃላፊነት ምን እንደሚሆን ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ግዛቲቱን "ለብሔራዊ ጥበቃ" እንደሚፈልጓት ተናግረው "የእኛ ልትሆን ይገባል" ብለዋል።
አዲሱ ተሿሚ የሉዊዚያና አስተዳዳሪ ጄፍ ላንድሪ የዴንማርክ መንግሥት ከፊል ራስ ገዝ ግዛት በሆነችው በግሪንላንድ ልዩ መልዕክተኛነት "የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ" ተናግረዋል።
ይህ እርምጃ ዴንማርክን ክፉኛ ያስቆጣ ሲሆን የአሜሪካን አምባሳደር "ማብራሪያ" እንደምትጠይቅ ገልጻለች።
የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው የደሴቷ ነዋሪዎች "የራሳችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መወሰን አለባቸው" እንዲሁም "የግዛት አንድነቷ መከበር አለበት" ብለዋል።
ላንድሪ በኤክስ ገጻቸው ላይ በተሰጣቸው ኃላፊነት የተሰማቸውን ክብር ገልጸው "ግሪንላንድን የአሜሪካ አካል ለማድረግ በፈቃደኝነት ማገልገል ክብር ነው" ብለዋል።
ትራምፕ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ በኋላ ግሪንላንድ ያላትን ስትራቴጂካዊ ጥቅም እና የማዕድን ሀብቷን በመጥቀስ የአሜሪካ አካል ለማድረግ ያላቸውን የረዥም ጊዜ ፍላጎት ዳግም ተናግረዋል።
ደሴቲቱን ለመቆጣጠር ኃይል መጠቀም ያስቡ እንደሆን የተጠየቁት ፕሬዚዳንቱ ከመመለስ ተቆጥበዋል።
ይህ አቋም የኔቶ አባል እና የአሜሪካ የቅርብ አጋር የሆነችውን ዴንማርክን አስደንግጧል።
ትራምፕ "ይህንን መፍታት አለብን" ሲያሉ ሲሆን "ግሪንላንድ ለብሔራዊ ደህንነታችን ታስፈልገናለች፣ ለማዕድን ሃብቷ ሳይሆን ለብሔራዊ ደህንነታችን።" ብለዋል።
ትራምፕ በተለይ የቻይና እና የሩሲያ መርከቦችን በአቅራቢያው ባሉ ባህሮች ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
57,000 ያህል ሰዎች የሚኖሩባት ግሪንላንድ ምንም እንኳን የመከላከያ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ በዴንማርክ እጅ ውስጥ ቢሆንም እአአ ከ1979 ጀምሮ ሰፊ የራስ ገዝ አስተዳደር አላት።
አብዛኛዎቹ የግሪንላንድ ነዋሪዎች ከዴንማርክ ነፃ መውጣትን ቢደግፉም፣ የአሜሪካ አካል መሆንን እንደሚቃወሙ የሕዝብ አስተያየት መሰብሰቢያዎች ያሳያሉ።
የዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላርስ ሎኬ ራስሙሰን የላንድሪን ሹመትን "በጣም የሚያሳዝን" ሲሉ ገልጸው ዋሽንግተን የዴንማርክን ሉዓላዊነት እንድታከብር አስጠንቅቀዋል።
ቲቪ2 ለተሰኘ ለዴንማርክ የቴሌቪዥን ጣቢያ "የፋሮ ደሴቶችን እና ግሪንላንድን ያቀፈ መንግሥት እስካለን ድረስ የግዛታችንን አንድነት የሚያዳክሙ ድርጊቶችን መቀበል አንችልም" ብለዋል።
የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጄንስ ፍሬደሪክ ኒልሰን በበኩላቸው ደሴቲቱ ከአሜሪካ እና ከሌሎች አገሮች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ብትሆንም ነገር ግን በጋራ መከባበር ላይ ብቻ መሆን አለበት ብለዋል።
"የልዩ መልእክተኛው ሹመት ለእኛ ምንም ለውጥ አያመጣም። የራሳችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንወስናለን። ግሪንላንድ የግሪንላንድ ነዋሪዎች ናት፣ እናም የግዛት አንድነቷ መከበር አለበት።"
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን በኤክስ ገጻቸው ላይ የአውሮፓ ኅብረት "ከዴንማርክ እና ከግሪንላንድ ሕዝብ ጋር አብሮ እንደሚቆም" ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቀደም ብለው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ላንድሪ "ግሪንላንድ ለአገራችን ደህንነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ" እና የአሜሪካን ጥቅም እንደሚያሳድግ ተረድተዋል ብለዋል።
ሰማኒያ በመቶ የሚሆነው ክፍሏ በበረዶ የተሸፈነው ነገር ግን ከፍተኛ ጥቅም ላይ ያልዋለ የማዕድን ሃብት አላት።
ግሪንላንድ በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ መካከል በአርክቲክ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ይህም ለአሜሪካ እና ለኔቶ የደህንነት እቅድ ማዕከላዊ ያደርገዋል።
በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች ዴንማርክን ከተቆጣጠሩ በኋላ አሜሪካ ግሪንላንድን በመውረር የጦር ሰፈርን እና የሬዲዮ ጣቢያዎችን አቋቁማለች።
ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በደሴቲቱ የሚገኙ ወታደራዊ ጦር ሠፈሮችን በጎበኙበት ወቅት የግሪንላንድን ሕዝብ "ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ እንዲደርሱ" ጠይቀዋል።
አሜሪካ እአአ በ1953 የነበራትን የቆንስላ ቢሮ ከዘጋች ወዲህ በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን በ2020 በግሪንላንድ ዋና ከተማ በሆነችው ኑክ የሚገኘውን ቆንስላ ዳግም ከፍታለች።
በርካታ የአውሮፓ አገራት እንዲሁም ካናዳ በግሪንላንድ የቆንስላ ቢሮዎች አሏቸው።