ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢራን መሪ ተቃዋሚዎች 'ትራምፕን ለማስደሰት እየሞከሩ ያሉ ነውጠኞች ናቸው' አሉ
የኢራን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የፀረ መንግሥት ተቃዋሚዎችን የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ለማስደሰት እየጣሩ ያሉ "ችግር ፈጣሪዎች" ናቸው ብለዋል።
ኢራን ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አሜሪካ "አመፅን በመገፋፋት እና ሰፊ የሆነ ውድመት እንዲደርስ ተቃዋሚዎችን በመጠቀም" የወቅሳ ደብዳቤ አስገብታለች።
ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን "ከባድ ችግር ውስጥ" መግባቷን ተናግረዋል።
በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ተቀስቅሶ ሰፊ የኢራንን ክፍል ያዳረሰው ተቃውሞ 13ተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፤ የእስላሚክ ሪፐብሊክ አገዛዝ አብቅቶ ንጉሳዊው እንዲመለስ ጥሪ ቀርቧል።
በተቃውሞው ቢያንስ 48 ተቃዋሚዎች እና 14 የፀጥታ ኃይል አባላት መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተቋማት አስታውቀዋል።
በአገሪቱ የኢንተርኔታ አገልግሎት ተቋርጧል።
አርብ ዕለት በቴሌቪዥን ቀርበው መልዕክት ያስተላለፉት አያቶላህ ኻሜኒ አሻፈረኝ ባዮችን አስጠንቅቀዋል።
"እስላሚክ ሪፐብሊክ ወደ ሥልጣን የመጣው በበርካታ መቶ ሺህ ሰዎች ደም መሆኑን ሁሉም እንዲያውቅ አድርጉ። እናም [ሪፐብሊኩ] ይህን በሚክዱ ሰዎች ፊት አይወድቅም" ሲሉ የ86 ዓመቱ መሪ ተናግረዋል።
ለተሰባሰቡ ደጋፊዎቻቸው በኋላ ላይ ባደረጉት ንግግር እና በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው በተላለፈ ንግግራቸው ደግሞ ኢራን "ለአጥፊ አካላት መልስ ለመስጠት አትታቀብም" ብለዋል።
የኢራን የመንግሥታቱ ድርጅት አምባሳደር አሜሪካ "በኢራን የውስጥ ጉዳይ በመዛት፣ በማነሳሳት እና ሆን ብላ አለመረጋጋትን እና ግጭትን በማበረታታት ጣልቃ እየገባች ነው" ሲሉ ለተመድ ባስገቡት ደብዳቤ ከሰዋል።
ተቃውሞው ከጀመረ ወዲህ ከ48 ተቃዋሚዎች ግድያ ባለፈ 2,277 ሰዎች መታሰራቸውን መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ ህርና የተባለ የዜና ወኪል ገልጿል።
በኖርዌይ የተመሰረተው የኢራን የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ደግሞ ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 51 ተቃዋሚዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
ቢቢሲ ፐርዢያ ከእነዚህ ውስጥ የ22 ሟቾ ቤተሰቦችን አነጋግሮ ማንነታቸውን ማረጋገጥ ችሏል።
ቢቢሲ እና አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኸን ኢራን ውስጥ ሆነው መዘገብ የተከለከሉ ናቸው።
የዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ መሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ በኢራን አመፅ በአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች እየተወሰደ ያለው እርምጃ እጅግ እንዳሳሰባቸው ገልፀው፤ የተቃዋሚዎችን ግድያ አውግዘዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ ተመድ በጠፋው ሕይወት መጨነቁን ተናግረዋል።
"ሰዎች በየትኛውም የዓለም ክፍል ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ የማሰማት መብት አላቸው። እናም መንግሥታት ይህን መብት የመጠበቅ፤ ይህ መብት መከበሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን የፀጥታ እና የፍትኅ ባለሥልጣናት ተደጋጋሚ እና የተቀናጀ ማስጠንቀቂያዎች ያወጡ ሲሆን፤ የኢራን ዋነኛ የፀጥታ ኃይል ከፍተኛ ብሔራዊ የፀይታ ምክር ቤቱ ተንኮለኞች ያለ ምህረት ይቀጣሉ ብለዋል።
የአገር ውስጥ የፀጥታ አስከባሪዎች "በትጥቅ አመፅ" እና "ሰላም እና ደኅንነትን በመረበሽ" በተቃዋሚዎች ላይ "ወሳኝ እና አስፈላጊ የሕግ እርምጃ ይወሰድባቸዋል" ብለዋል።
ተቃዋሚዎች በመላው አገሪቱ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ሲሆን 'ቢቢሲ ቨርቲፋይ' በ67 አካባቢዎች የተካሄዱ ተቃውሞዎችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ማረጋገጥ ችሏል።