አሜሪካ በቬንዙዌላ የሚኖራት ተሳትፎ ለዓመታት ሊቀጥል እንደሚችል ትራምፕ ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው በቬንዙዌላ ውስጥ ያላት ተሳትፎ ለዓመታት ሊቆይ እንደሚችል ተናገሩ።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የአሜሪካ ወታደሮች በቬንዙዌላ የፈጸሙትን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ የአገሪቱ መሪን ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ኒው ዮርክ ታይምስ አሜሪካ የአገሪቱን አስተዳደር ለምን ያህል ጊዜ በበላይነት እንደምትቆጣጠረው ሲጠይቃቸው እርሱን "ጊዜ ብቻ ነው የሚነግረን" ብለው ነበር።

ትራምፕ በተጨማሪም የማዱሮ የቅርብ ሰው የሆኑት ዴልሲ ሮድሪጌዝ የሚመሩት ጊዜያዊ መንግሥትን ለመተካት በቬንዙዌላ ምርጫ ይካሄድ እንደሆነ ወይም መቼ እንደሚካሄድ አልገለጹም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቬንዙዌላ ተቃዋሚ መሪ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ የማዱሮ ከሥልጣን መነሳት አገሪቱ "ነፃ እንድትሆን" የሚያደርጋትን "የማይቀለበስ ሂደት" ፈጥሯል ብለዋል።

ኒውዮርክ ታይምስ ትራምፕን በነዳጅ የበለፀገችውን አገር እንደሚያስተዳድሩ ከተናገሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ስለ ቬንዙዌላ የወደፊት እቅዳቸው ጠይቋል።

ረቡዕ ዕለት ቀደም ብሎ፣ ዋይት ሐውስ አሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበትን የነዳጅ ዘይት ሽያጭን "ለማይታወቅ ጊዜ" እንደምትቆጣጠር ተናግሮ ነበር።

የአሜሪካ የኢነርጂ ሚኒስትር ክሪስ ራይት በካራካስ ውስጥ ያለውን ጊዜያዊ መንግሥት ለመቆጣጠር አሜሪካ የቬንዙዌላ የነዳጅ ሽያጭን መቆጣጠር ያስፈልጋታል ሲሉ ተከራክረዋል።

ትራምፕ አስተዳደራቸው በዓለም ላይ ትልቁ የተረጋገጠ ክምችት ካላት ቬንዙዌላ "ነዳጅ እንደሚወስድ" ቢናገሩም፣ የአገሪቱን የነዳጅ ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት "ጊዜ እንደሚወስድ" አምነዋል።

የቬንዙዌላ የነዳጅ ምርት የማዱሮ መንግሥትና የቀድሞው አስተዳደር በፈጸሙት የአስተዳደር ብልሽት እንዲሁም ለዓመታት ተጥሎ በቆየው የአሜሪካ ማዕቀብ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

ትራምፕ ለኒውዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከሮድሪጌዝ ጋር "በቋሚነት ይገናኛሉ"።

ሮድሪጌዝ የቬንዙዌላ ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ ሆነው በፕሬዝዳንቱ ማዱሮ ታማኝ ደጋፊዎች በተሞላው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ፊት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

ሮድሪጌዝ "አስፈላጊ ነው ብለን የምናስበውን ሁሉ እየሰጠችን ነው" ሲሉ አክለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቀደም ብለው እንደተናገሩት ጊዜያዊው መንግሥት ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ በአሜሪካ የሚመረቱ ዕቃዎችን ብቻ ለመግዛት ይጠቀሙበታል።

እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ዘጋቢዎች ገለጻ፣ ትራምፕ ሮድሪጌዝን የቬንዙዌላ አዲሱ መሪ አድርገው ለምን እንደተቀበሉ ለቀረቡላቸው ጥያቄ መልስ አልሰጡም።

ብዙ የቬንዙዌላ ፖለቲካ ተንታኞች የማዱሮ ከሥልጣን መባረር በኋላ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ እና ማሪያ ኮሪና ማቻዶ በፍጥነት ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ጠብቀው ነበር።

ነገር ግን ትራምፕ የአሜሪካን ጥቃትን ተከትሎ በሰጡት የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የማቻዶን መመለስ አጣጥለውታል። ቬንዙዌላን ለመምራት በቂ "አክብሮት" እና ድጋፍ እንደሌላት ተናግረዋል።

"መሪ መሆን በጣም ከባድ እንደሚሆንባት አስባለሁ" ነበር ያሉት።

ማቻዶ እአአ ከ2024ቱ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት ከኋላዋ ያሉትን የተቃዋሚ ቡድኖች አንድ ማድረግ ችላ የነበረ ቢሆንም የማዱሮ መንግሥት ግን ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዳትወዳደር አግደዋታል።

ከዚያም ድጋፏን ለቀድሞዋ ዲፕሎማት ጎንዛሌዝ ሰጥታለች።

በመንግሥት ታማኝ ደጋፊዎች የሚመራው የምርጫ ምክር ቤት ማዱሮ እንደገና መመረጣቸውን አስታወቁ።

ሆኖም ግን፣ በተቃዋሚዎች የተሰበሰቡት የድምጽ ቆጠራዎች፣ እና በነጻነት የተረጋገጡት፣ ጎንዛሌዝ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፉን ይጠቁማሉ።

ጎንዛሌዝ ምርጫውን ተከትሎ ከነበረው የመንግሥት ጭቆና ለማምለጥ ስደት የሄዱ ሲሆን ማቻዶም በቬንዙዌላ ውስጥ ተደብቃ ቆይታለች።

በቬንዙዌላ "ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በማራመድ ያላሰለሰ ጥረት" የተሸለመችበትን የኖቤል የሰላም ሽልማት ለመቀበል በታህሳስ ወር ወደ ኦስሎ ለመጓዙ በመሬት፣ በባህር እና በአየር አደገኛ ጉዞ አድርጋለች።

ማቻዶ አሁን የት እንዳለች የማይታወቅ ቢሆንም ነገር ግን በቅርቡ ወደ ቬንዙዌላ ለመመለስ ዕቅድ እንዳላት ተናግራለች።