ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከቬንዙዌላ በኋላ ትራምፕ ዐይናቸውን የጣሉባቸው አገራት የትኞቹ ናቸው?
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፍላጎታቸው የተቀረፀ ሆኗል።
ትራምፕ በአንድ ጀንበር እርምጃ የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት እና ባለቤታቸውን በካራካስ ከባድ ጥበቃ ከሚደረግበት መኖሪያቸው አንጠልጥለው ወደ አሜሪካ በመውሰድ ዛቻቸውን ዕውን አድርገዋል።
ስለ ተልዕኮው ሲጠየቁ ትራምፕ የፕሬዝዳንት ጄምስ ሙንሮን የ1823 የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አዝማሚያን እና የአሜሪካን የበላይነት ለማምጣት የገቡትን ቃል ጠቅሰዋል።
ባለፉት ቀናት በዋሽንግተን ዐይን ውስጥ የገቡ እና ትራምፕ ማስጠንቀቂያ የሰጧቸው አገራት የሚከተሉት ናቸው።
ግሪንላንድ
አሜሪካ በግሪንላንድ ላይ ወታደራዊ ሰፈር አላት ቢሆንም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን መላዋን ደሴት መጠቅለል ይፈልጋሉ።
"ከብሔራዊ ደኅንነት አንጻር ግሪንላንድ እንፈልጋለን" ሲሉ ለጋዜጠኞች በተናገሩበት ጊዜ አካባቢው "በአጠቃላይ በሩሲያ እና በቻይና መርከቦች ወርረውታል" ብለዋል።
የዴንማርክ ግዛት አካል የሆነችው ሰፊዋ የአርክቲክ ደሴት ግሪንላንድ ከአሜሪካ ሰሜን ምሥራቅ በ3,200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።
ግሪንላንድ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና የወታደራዊ መሣሪያዎችን ለመገንባት ወሳኝ በሆኑ ብርቅ ማዕድናት የከበረች ናት።
በአሁኑ ጊዜ ቻይና ውድ ማዕድናትን በማምረት አሜሪካን ትበልጣለች።
ከዚህ ባሻገረም ግሪንላንድ ተፈላጊነቱ የጨመረውን የአርክቲክ ዙሪያ ተደራሽ በማድረግ በሰሜን አትላንቲክ ቀጣና ቁልፍ ስልታዊ ስፍራ ናት። በመጪዎቹ ዓመታት የበረዶ ግግሮች ሲቀልጡ አዲስ የመርከቦች መስመር ይከፈታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬንስ ፍሬድሪሽ ኔልሰን ለትራምፕ ምላሽ ሲሰጡ፤ አሜሪካ ደሴቷን ለመቆጣጠር የያዘችው ፍላጎት "ምናባዊ" ነው ብለዋል።
"ተጨማሪ ጫና አንፈልግም፤ ማስመሰል አያስፈልግም፤ ለመገንጠል መቋመጥ አያስፈልግም። ለንግግር በራችን ክፍት ነው። ነገር ግን መሆን ያለባቸው በትክክለኛ መንገዶች እና ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ ነው" ብለዋል።
ኮሎምቢያ
የቬንዙዌላው እርምጃ በተወሰደ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ትራምፕ የኮሎምቢያውን ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮን "ራስህን ጠብቅ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የቬንዙዌላ የምዕራብ ጎረቤት የሆነችው ኮሎምቢያ ትልቅ የነዳጅ ክምችት ያላት እና ወርቅ፣ ብር፣ ኤመራልድ፣ ፕላቲኒየም እና የድንጋይ ከሰል የመሰሉ ማዕድናትን በሰፊው ታመርታለች።
የቀጣናው የአደገኛ ዕፅ በዋናነት ደግሞ የኮኬንም ቁልፍ አምራች ናት።
አሜሪካ በካሪቢያን እና ፓሲፊክ አካባቢ ያለ ማስረጃ ጀልባዎች አደገኛ ዕፅ ጭነዋል በሚል ካለፈው መስከረም ጀምሮ ጥቃት መፈፀም ከጀመረች ወዲህ ትራምፕ ከአገሪቱ ግራ ዘመም ፕሬዝዳንት ጋር ንትርክ ውስጥ ገብተዋል።
በጥቅምት ወር አሜሪካ ፕሬዝዳንት ፔትሮ አደገኛ ወንበዴዎች እንደልባቸው እንዲሆኑ ፈቅደዋል በሚል ማዕቀብ ጥላለች።
ዕሁድ እለት ኤር ፎርስ ዋን በተባለው አውሮፕላናቸው ውስጥ ትራምፕ ኮሎምቢያ "ኮኬን ማምረት በሚወድ እና ለአሜሪካ በሚሸጥ ሕመምተኛ ሠው እየተመራች ነው" ብለዋል።
"ይህን ለረጅም ጊዜ አያደርገውም" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አሜሪካ ኮሎምቢያ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ትሰነዝር እንደሆነ ሲጠየቁ ትራምፕ "እኔ ደስ ይለኛል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በታሪክ ኮሎምቢያ ለዋሽንግተን የዕፅ ዘመቻ የቅርብ አጋር የነበረች ሲሆን፤ የዕፅ አዘዋዋሪዎችን ለማጥፋት በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ተቀብላለች።
ኢራን
ኢራን በአሁኑ ጊዜ በትልቅ ሕዝባዊ ተቃውሞ እየታመሰች ነው። እናም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዚህ በላይ ተቃዋሚዎች ከሞቱ የኢራን ባለሥልጣናት "በከባዱ ይመታሉ" ብለዋል።
"በቅርብ እየተከታተልነው ነው። እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሰዎችን መግደል ከጀመሩ በአሜሪካ ከባድ ዱላ ይወርድባቸዋል ብዬ አስባለሁ" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ኢራን ትራምፕ ትኩረት ካደረጉበት የምዕራብ ዓለም ጠረፍ ውጪ ብትሆንም ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ካደረሰች ወዲህ ትራምፕ ማስፈራሪያ ሰጥተዋል።
ጥቃቱ እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር የማልማት አቅምን ለማውደም ሰፊ ተልዕኮ ከወሰደች በኋላ የተፈጸመ ነው።
ትራምፕ በግል መኖሪያቸው ማራ ላጎ ባለፈው ሳምንት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጋር ባደረጉት ንግግር ኢራን ዋና አጀንዳ እንደነበረች ተነግሯል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ኔታኒያሁ በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት 2026 አዲስ ጥቃት ኢራን ላይ ሊሰነዘር እንደሚችል መጠቆማቸውን ዘግበዋል።
ሜክሲኮ
የ2016ቱ የትራምፕ ወደ ሥልጣን መውጣት አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር በምትጋራው በደቡባዊ ድንበር "ግንቡን እንገንባ" በሚል የታጀበ ነበር።
በ2025 በመጀመሪያ ቀን ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት እግራቸው ሲረግጥ የሜክሲኮን ባሕረ ሰላጤ "የአሜሪካ ባሕረ ሰላጤ" በሚል መቀየር የሚያስችላቸውን የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
ትራምፕ በተደጋጋሚ የሜክሲኮ ባለሥልጣናት የዕፅ ዝውውርን ወይም በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር በቂ ሥራ አልሰሩም በሚል ይወቅሳሉ።
ዕሁድ እለት በሜክሲኮ በኩል አደገኛ ዕፅ በገፍ እየገባ በመሆኑ "የሆነ ነገር ማድረግ ግድ ይለናል" ያሉት ትራምፕ አደገኛ ወንበዴዎቹ "በጣም ጠንካራ" ናቸው ብለዋል።
የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺምበም በሜክሲኮ ምድር ላይ ምንም ዓይነት የአሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ እንደማይኖር በይፋ አጣጥለዋል።
ኩባ
ደሴት የሆነችው ኩባ ከአሜሪካ 145 ኪሎ ሜትር ብቻ የምትርቅ ሲሆን፤ ከአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በአሜሪካ ማዕቀብ ውስጥ ትገኛለች።
ኩባ ከቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ጋር ቅርብ ግንኙነት አላት።
ትራምፕ በኩባ የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ እንደማያስፈልግ ጠቅሰው ለዚህም ምክንያቱ ኩባ "ለመውደቅ ዝግጁ" በመሆኗ ነው ብለዋል።
"እርምጃ መውሰድ ሚያስፈልገን አይመስለኝም" ያሉት ትራምፕ "ለመውደቅ ያዘመመ ይመስላል" ሲሉ አክለዋል።
"ከዚህ በላይ መቋቋም የሚችሉ አይመስለንም፤ ነገር ግን ኩባ አሁን ገቢ የላትም።"
"ገቢያቸውን ሁሉ የሚያገኙት ከቬንዙዌላ ነው፤ ከቬንዙዌላ ነዳጅ" ሲሉም በቬንዙዌላ ላይ የወሰዱት እርምጃ ጦስ ሀቫና ላይም እንደሚሰማ ጠቁመዋል።
30 በመቶውን የኩባ የነዳጅ ፍላጎት ቬንዙዌላ እንደምታቀርብ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፤ የማዱሮ በቁጥጥር ስር መዋል ይህን አቅርቦት በመበጣጠስ ሀቫና እንድትጋለጥ ያደርጋል።
የኩባዊያን ስደተኞች ልጅ የሆኑት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለረጅም ጊዜ በኩባ የአገዛዝ ለውጥ እንዲደረግ ሲወተውቱ መቆየታቸውን ቅዳሜ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
"ሀቫና ኖሬ ቢሆን ኖሮ እና በመንግሥት ውስጥ ብሆን ሊያሳስበኝ ይገባል፤ ቢያንስ በትንሹ" ብለዋል።
"ፕሬዝዳናቱ [ትራምፕ] ሲናገሩ ከምር ውሰዱት" ሲሉ አክለዋል።