ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንትን በመያዝ ወደ አሜሪካ ስለወሰደው 'ዴልታ ፎርስ' የምናውቀው
አሜሪካ ለወራት ያቀደችውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን የመያዝ ዘመቻ ተግባራዊ ስታደርግ ካሏት ዘመናዊ አውሮፕላኖች፣ ሄሊኮፕተሮች፣ ድሮኖች እና የጦር ሠራዊት አባላት ምርጦቹን ያሰለፈችው ከፊት ነበር ።
ነዳጅ ባለበት ስሟ የሚነሳው አሜሪካ አሁን በዓለም ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ያላትን ቬንዙዌላን "እመራታለሁ" ብላለች።
ከዚህ ቀደም ወዳጆቿን አስተባብራ በኢራቅ ላይ ወረራ ፈጽማ የፕሬዝዳንቷን ሳዳም ሁሴንን አንገት ለገመድ ዳርጋለች።
በሰሜን አፍሪካዋ የነዳጅ ባለጸጋ አገር ሊቢያ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ውስጣዊ ተቃውሞ ተገን አድርጋ ከአጋሮቿ ጋር የአየር ድብደባ በማድረግ ሞአመር ጋዳፊ በተቃዋሚዎቻቸው እንዲገደሉ አዳክማቸዋለች።
አሁን ደግሞ ለአስርታት ጥርስ ነክሳባት በተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥት ስትፈትናት ቆይታ፣ በግልጽ ወረራ መሪዋን ከመኝታ ክፍላቸው ቀስቅሳ፣ ካቴና እጃቸው ውስጥ አስገብታ ወደ ኒው ዮርክ አግዛቸዋለች። የማዱሮ ዕጣ ፈንታ ከሳዳም እና ከጋዳፊ ይለይ እንደሆነ ወደ ፊት የሚታይ ነው።
አሜሪካ ለወራት ስትጠነስሰው የነበረው የቬንዙዌላው ዘመቻ ከምድር፣ ከአየር፣ ከህዋ እና ከባሕር ላይ ክትትል ሲደረግበት የነበረ ሲሆን፣ ስኬታማ እንዲሆን የሚያስፈልገው ነገር የቀረበለት ተልዕኮ ነበር።
ፕሬዝዳንቱ እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሌሊቱን ቁጭ ብለው በቀጥታ ሲከታተሉት የነበረ ዘመቻ ነው።
የእዚህ ዘመቻ ዋነኛ ግብ አሜሪካ በዕጽ እና በጦር መሳሪያ ወንጀሎች በተደጋጋሚ ስትከሳቸው እና ስትዝትባቸው የነበሩትን የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንትን መያዝ ነበር። የአሜሪካ ሁሉም ኃይል በተልዕኮው ውስጥ ሚና ቢኖራቸውም ዋናውን ሥራ ያከናወነው ግን ዴልታ ፎርስ የሚባለው ልዩ የኮማንዶዎች ቡድን ነው።
ዴልታ ፎርስ ማን ነው?
በአውሮፓውያኑ 1977 የተመሠረተው እና ዋና የጦር ሰፈሩ አሜሪካ ሰሜን ካሮላይና ግዛት፣ ፎርት ብራግ ውስጥ የሆነው ዴልታ ፎርስ ልዩ የኮማንዶ ቡድን፤ በዓለም ላይ ካሉ ኃያል እና ምሥጢራዊ ወታደራዊ ክፍሎች መካከል አንዱ ነው።
ዴልታ ፎርስ በአሜሪካ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ሥር ሆኖ የሚታዘዘው በሠራዊቱ የጋራ ልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ነው። ይህ ቡድን ከዴልታ ፎርስ በተጨማሪ 'ፈርስት ስፔሻል ፎርስስ ኢፕሬሽናል ዲታችመንት-ዴልታ' የሚል ስምም አለው።
ይህ ወታደራዊ ቡድን የተቋቋመው የብሪታኒያ 22ኛው ልዩ የአየር ኃይል አገልግሎት ክፍል አወቃቀርን መሠረት በማድረግ በኮሎኔል ቻርለስ ቤክዊዝ አማካኝነት ነው።
ዴልታ ፎርስ በሚያከናውናቸው ጥብቅ ምሥጢራዊ ዘመቻዎች እና ባለው ተፈላጊነት ምክንያት ቡድኑ እንደየሁኔታው እና ተልዕኮው የተለያዩ ስያሜዎች ሲሰጡት ቆይተዋል።
የዴልታ ፎርስ ዋነኛ ሥራ ምንድን ነው?
ቡድኑ የተለየ ትኩረት የሚደያርገው ከባድ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ በሚባሉ፣ ከፍተኛ ዋጋ በሚሰጣቸው ተልዕኮዎች ላይ ሲሆን፣ ቀዳሚ ኃላፊነቱ ደግሞ የፀረ ሽብር ዘመቻዎች፣ ታጋቾችን ማስለቀቅ፣ ሽብርተኞችን ማስወገድ እና መያዝ እንዲሁም የተለዩ የቅኝት ሥራዎችን ማከናወን ነው።
የዴልታ ፎርስ ቡድን አባላት በተጨማሪም ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ስመ ጥር ሰዎችን ለመጠበቅ፣ መደበኛ ባልሆኑ ውጊያዎች ውስጥ በብቃት እንዲሳተፉ፣ በፈንጂዎች አጠቃቀም፣ በስውር ወደ አንድ ቦታ በመግባት እና በአልሞ ተኳሽነትም ሠልጥነዋል።
ኮማንዶዎቹ በየትኛውም ቦታ እና ሁኔታ ውስጥ ሊሰማሩ ስለሚችሉ ሁሉን አቀፍ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። በዚህም በአውሮፕላን፣ በባቡር፣ በመርከብ እና በመኪናዎች ላይ የሚያጋጥሙ ክስተቶችን ለመቆጣጠር እንዲችሉ የሠለጠኑ መሆናቸው ይነገራል።
የቡድኑ አባላት በተለያየ ኃላፊነት ላይ ተመድበው የመሥራት አቅም አላቸው። በዚህም እንደ ወታደር በቀጥታ በመዋጋት፣ በአነጣጥሮ ተኳሽነት፣ በስለላ ወይም መረጃ በመሰብሰብ እንዲሁም በአንድ ዒላማ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም እና በሌሎችም ይታወቃሉ።
የዴልታ ፎረስ ዋነኛ ዘመቻዎች
ቡድኑ ከተመሠረተ ጀምሮ ያካሄዳቸው አብዛኞቹ ዘመቻዎች እስካሁንም ድረስ በምሥጢር ተይዘዋል። በመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ውስጥ ከተካተቱት የተወሰኑት ብቻ በጊዜ ሂደት ውስጥ ይፋ ሆነዋል። ነገር ግን ስለዘመቻዎቹ ከባለሥልጣናት ከሚሰጡ ጥቅል መረጃዎች ውጪ ሌላው በጥብቅ ምስጢርነት የሚጠበቅ ነው።
የአሜሪካ መንግሥት ለሕዝብ ይፋ ካደረጋቸው የዴልታ ፎርስ ዘመቻዎች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
'ኦፕሬሽን ኤግል ክላው' በኢራን ውስጥ የታገቱ አሜሪካውያንን ለማስለቀቅ የተካሄደ ዘመቻ ነው። ነገር ግን በውጤቱ ስምንት አሜሪካውያን በመገደላቸው የከሸፈ ተልዕኮ ተብሏል።
'ኦፕሬሽን ኧርጀንት ፊዩሪ' በካሪቢያኗ ደሴት ግሪናዳ ውስጥ በሚገኝ ሪችመንድ ሂል በሚባል እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ለማስለቀቅ የተካሄደ ዘመቻ ነው።
'ኦፕሬሽን ጀስት ኮስ' በፓናማ ላይ ወረራ በመፈጸም ፕሬዝዳንቱ ጄነራል ማኑኤል ኑሬጋን በመያዝ የ35 ሺህ አሜሪካውያንን ደኅንነት ማስጠበቅ ተልዕኮው ነበር።
'የባሕረ ሰላጤው ጦርነት' ኢራቅ ኩዌትን በመውረሯ ከአጋሮቿ ጋር የሳዳም ሠራዊትን በማሸነፍ ኩዌትን ነጻ የማውጣት ዘመቻ ነበር።
'ኦፕሬሽን ጎቲክ ሰርፐንት' በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ውስጥ የአሜሪካ ሄሊኮፕተሮች ተመተትው በወደቁበት ጊዜ ተካሄደ ዘመቻ ነው።
'የቶራ ቦራ ጦርነት' ኦሳማ ቢን ላደንን ለመያዝ ወይም ለመግደል አፍጋኒስታን ውስጥ የተካሄደ ዘመቻ ነው።
'ኦፕሬሽን ሬድ ዶውን' ሳዳም ሁሴን የተደበቁበትን ቦታ በመለየት ለመያዝ የተካሄደ ዘመቻ ነበር።
'ኦፕሬሽን ጁፒተር ሺልድ' በሊቢያ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ አሜሪካውያንን ለማዳን የተካሄደ ዘመቻ ነው።
'ኦፕሬሽን ብላክ ስዋን' ኃያሉን የሲናሎዋ የዕጽ ዝውውር ቡድን መሪ ሆነው ዮአኪን 'ኤል ቻፖ' ጉዝማን የተያዘበት ዘመቻ ነበር።
'ኦፕሬሽን ካይላ ሙለር' የአይኤስ ቡድን መሪ ሆነው አቡ ባካር አል ባግዳዲ ሶሪያ ውስጥ የተገደለበት ዘመቻ ነው።
የዴልታ ፎርስ አባል የሚሆኑት እነማን ናቸው?
ለዴልታ ፎርስ አባልነት የሚመለመሉት ብቃት ያላቸው እና በከባድ ፈተና ውስጥ ማለፍ የሚችሉ ብቻ ናቸው። ቡድኑ አባላቱን በአብዛኛው የሚመለምለው ባለአረንጓዴው ቆብ ከሚባሉት የአሜሪካ ሠራዊት ልዩ ኃይል አባላት መካከል እና 75ኛው ሬንጀር ክፍል ከሚባለው ነው።
አንድ የዴልታ ፎርስ አባል ለመሆን የሚፈልግ ወታደር እስከ አራት ሳምንት በሚዘልቀው የምርጫ ሂደት ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል።
የምልመላው ሂደት በጣም ጥልቅ እና ሰፊ ዝርዝር ያለው በመሆኑ ምክንያት ከዕጩዎቹ መካከል በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው አልፈው ወደ ሥልጠና የሚገቡት።
የምልመላ ምርጫው ሂደት የተለያዩ ዘርፎች ያሉት ሲሆን፣ የአካላዊ ብቃት ፈተናው ከ15 ኪሎ በላይ ክብደት ተሸክሞ በሰዓት የተገደበ በምሽት የ60 ኪሎ ሜትር በአስቸጋሪ የመልክዓ ምድር ሁኔታ የሚደረግ የእግር ጉዞን ያካትታል።
ይህንን እና ሌሎችንም ከባድ የምልመላ መስፈርቶችን አሟልተው የሚያልፉ ዕጩዎች ለስድስት ወራት የሚቆይ እጅግ በጣም ከባድ በምድር፣ በአየር፣ በባሕር ላይ እና ውስጥ የሚሰጥ ሥልጠናን በማጠናቀቅ በዓለም ዙሪያ ለሚፈጸሙ እጅግ አደገኛ ተልዕኮዎች ዝግጁ ይሆናሉ።