ወደ ደብረማርቆስ ሲጓዙ የነበሩ አራት መንገደኞች በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ታገቱ

ከአዲስ አበባ ወደ ደብረማርቆስ እየሄደ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን "አሊዶሮ" በተባለ አካባቢ በታጣቂዎች ጥቃት ተከፍቶበት አራት መንገደኞች መታገታቸውን የአውቶብሱ ባለንብረት የሆነው ኤፍኤም ባስ ትራንስፖርት ለቢቢሲ ተናገረ።

ታግተው ከተወሰዱት መንገደኞች መካከል አንዱ የድርጅቱ ተቆጣጣሪ መሆኑን የኤፍኤም ባስ ትራንስፖርት ሥራ አስኪያጅ አቶ አይክፋው ምናዬ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሰኞ ታሕሳስ 27/2018 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ የተነሳው የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ፤ የደብረ ማርቆስ ጉዞውን የጀመረው 51 መንገደኞችን አሳፍሮ እንደነበር ተገልጿል።

አውቶቡሱ ከአዲስ አበባ ጉዞውን የሚጀምረው ከለሊቱ 10፡30 መሆኑን የገለፁት አቶ አይክፋው፣ በየቦታው ኬላዎች በመኖራቸው እና ከ12 ሰዓት በፊት ለጉዞ ክፍት ስለማይሆኑ አውቶቡሱ አሊዶሮ አካባቢ የደረሰው ጠዋት 3፡00 አካባቢ እንደሚሆን ተናግረዋል።

አውቶቡሱ አካባቢው ላይ ሲደርስ ታጣቂዎቹ በከፈቱት ተኩስ ጎማው እና መስኮቱ ላይ መመታቱን ገልጸዋል።

የተወሰኑ መንገደኞችም ጉዳት እንደደረሰባቸው የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ በጥይት ተመትተው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች "ሦስት እና አራት" እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

አቶ አይክፋው፤ ታጣቂዎቹ አግተዋቸው ከነበሩ ተሳፋሪዎች መካከል ሴቶቹን በመመለስ "አራት ወንዶችን ለይተው" መውሰዳቸውን ይናገራሉ።

ታጣቂዎቹ መኪናው ላይ ተኩስ በከፈቱበት ወቅት ተደናግጠው "የሮጡ እና ያመለጡ" እንዳሉ የሚገልፁት አቶ አይክፋው፣ መኪናው ጥቃት ሲፈጸምበት ሌሎች ተከታትለው ሲሄዱ የነበሩ አውቶቡሶቹም ወደ ፍቼ ተመልሰው እንደነበር አስረድተዋል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የጸጥታ አካላት በቦታው በመድረሳቸው እና ሁኔታዎች በመረጋጋታቸው ተስተጓጉሎ የነበረው ጉዞ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ጥቃት ከደረሰበት አውቶቡስ አምልጠው የነበሩ እና ከእገታው የተለቀቁ ሰዎችን በሌላ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ወደ ደብረ ማርቆስ ማጓጓዝ መቻሉንም ጨምረው ገልፀዋል።

ሥራ አስኪያጁ፤ መንገደኞቹን በሌላ አውቶቡስ ወደ መዳረሻቸው ሲያጓጉዙ አራት ሰዎች መጉደላቸውን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

መንገደኞቹን ወደ ደብረማርቆስ የወሰደው ሌላ የኤፍኤም ባስ ትራንስፖርት ተሽከርካሪ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አይክፋው "የእኛ የራሳችን መኪና ቀይሮ የወሰዳቸው አለ። ስለዚህ የቀሩትም፣ የጎደሉትም አራት ሰዎች ናቸው" ብለዋል።

አራቱ ሰዎች በእገታ ስር መሆናቸውን እንዴት እንደተረጋገጠ የተጠየቁት ኃላፊው፤ "ወደ ቤተሰቦቻቸው ተደውሏል፤ በትክክለኛ የት ናቸው የሚለውን ግን አናውቅም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

መኪናው ላይ ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው አራት መንገደኞች እጃቸው እና እግራቸው ላይ ቀላል የሚባል ጉዳት እንዳጋጠማቸው ተናግረው "ከኋላ በነበረው መኪና ወደ ደብረማርቆስ ሄደዋል" ብለዋል።

እገታው የተፈጸመው በማን አንደሆነ ምንም መረጃ እንደሌላቸው የሚናገሩት አቶ አይክፋው፤ "ባልታወቁ ኃይሎች መፈጸሙን ነው የምናውቀው" ብለዋል።

ከሁለት ወር በፊት በዚህ መንገድ ላይ ለሚንቀሳቀሱ መኪናዎች የፀጥታ ኃይሎች እጀባ ያደርጉ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን 'ሁኔታዎች ተረጋግተዋል' ተብሎ በመታሰቡ መቅረቱን ገልፀዋል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በዚሁ ስፍራ ወደ ደብረማርቆስ የሚሄድ የድርጅቱ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ተሳፋሪዎች ላይ እገታ ተፈጽሞ እንደነበር አቶ አይክፋው ያስታውሳሉ።

"አደጋው በተፈጠረበት አካባቢ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል "እጀባ ማድረግ ይጀምር እና መንገዱ ፀድቷል ተብሎ ሲታሰብ እጀባው ይቋረጣል" ብለዋል።

በመንገደኞቹ እገታ ዙሪያ የፀጥታ አካላት እስካሁን ድረስ ምንም ያሉት ነገር የለም።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን "አሊዶሮ" ተብሎ በሚጠራው ልዩ ቦታ በአገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈጸም ሲሆን ከዚህ ቀደምም መንገደኞች መታገታቸው ይታወሳል።