ቀጥታ, በኢራን ተቃውሞ ሁለተኛ ሳምንት ሆስፒታሎች የቁስለኞች ቁጥር ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ተነገረ

ሁለተኛ ሳምንቱን በያዘው የኢራን ተቃውሞ ሆስፒታሎች በቁስለኞች መጨናነቃቸውን የጤና ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናገሩ። በኢራን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ቢያንስ 50 ተቃዋሚዎች እና 15 የጸጥታ አካላት መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አስታውቀዋል። ድርጅቶቹ በተጨማሪ እስካሁን ድረስ 2,311 የተቃውሞ ሠልፈኞች መታሰራቸውን ዘግበዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር 'በየትኛውም ዲሞክራሲ ውስጥ የተቃውሞ ሠልፍ ተፈጥሯዊ ነው' አሉ

    በሊባኖስ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቃቺ “የኢራን ሁኔታ በማዕቀብ እና በተወሰኑ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የተነሳ ችግሮች ቢኖሩም በአጠቃላይ ጥሩ የሚባል ነው” አሉ።

    በመላ አገሪቱ ላላፉት 13 ቀናት እየተካሄደ ያለውን የተቃውሞ ሠልፍም በተመለከተ ሲናገሩ “የተወሰነ የተቃውሞ ሠልፍ ኢራን ውስጥ እየተካሄደ ነው። የትኛውም መንግሥት የተመሰረተው በሕዝብ ሉዓላዊነት እና ዲሞክራሲ ላይ ከሆነ ተፈጥሯዊ ነው። ሕዝቦች በተቃውሞ የሚፈልጉትን ይገልጻሉ፤ እየሆነ ያለው ያ ነው” ብለዋል።

    ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ከመደበኛው ሕዝብ ውጭ ሌሎች ችግር የሚፈጥሩ አሉ፤ የሕዝብ መገልገያዎችን የሚያወድሙ፣ እሳት የሚለኩሱ እና ጉዳዩ በጥንቃቄ መታየት አለበት” ብለዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሌላ ቃለ መጠይቅ ላይ የእስራኤል ባለሥልጣናት የሞሳድ ተሳትፎ እንዳለበት መናገራቸውን ጠቅሰው ወንጅለዋቸዋል።

    በኢራን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ቢያንስ 50 ተቃዋሚዎች እና 15 የጸጥታ አካላት መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አስታውቀዋል።

    ድርጅቶቹ በተጨማሪ እስካሁን ድረስ 2,311 የተቃውሞ ሠልፈኞች መታሰራቸውን ዘግበዋል።

  2. ‘አሜሪካ ጀግና የሆኑ ኢራናውያንን ትደግፋለች’ ማርኮ ሩቢዮ

    በኢራን እየተካሄደ ያለው የተቃውሞ ሠልፍ 13ኛ ቀኑን በያዘበት በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለሠልፈኞቹ ያላቸውን ድጋፍ ገለፁ።

    ሩቢዮ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “ዩናይትድ ስቴትስ ጀግና ኢራናውያንን ትደግፋለች” ብለዋል።

    ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰው የኢራን ሕዝባዊ አመጽ በተለያዩ ከተሞች የተስፋፋ ነው።

    ሠልፈኞቹ እአአ ከ1979 ጀምሮ አገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘው የእስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ እየጠየቁ ነው።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መልዕክት የመጣው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በኢራን ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን ገልፀው ተቃዋሚዎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ከተናገሩ በኋላ ነው።

    ተቃዋሚ ሠልፈኞች የሚገደሉ ከሆነ አሜሪካ ጥቃት እንደምትፈጽምም አስጠንቅቀዋል።

    የኢራን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በበኩላቸው የፀረ መንግሥት ተቃዋሚዎችን የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ለማስደሰት እየጣሩ ያሉ "ችግር ፈጣሪዎች" ናቸው ብለዋል።

    በኢራን የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን እስካሁን ድረስ ቢያንስ 50 ተቃዋሚ ሰልፈኞች ተገድለዋል።

  3. በኢራን ተቃውሞ ሁለተኛ ሳምንት ሆስፒታሎች ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ባለሙያዎች ተናገሩ

    ሁለተኛ ሳምንቱን በያዘው የኢራን ተቃውሞ እና የአገሪቱ ባለሥልጣናት የተቀናጀ ማስጠንቀቂያ ለተቃዋሚዎች እያወጡ ባለበት ሰዓት በሁለት ሆስፒታል የሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎች በቁስለኞች ሆስፒታሎች መጨናነቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    አንድ ሐኪም በቴህራን የሚገኝ የዓይን ሆስፒታል ወደ ቀውስ መግባቱን ሲናገሩ በሌላ ሆስፒታል የሚሰሩ የጤና ባለሙያ ደግሞ ለቢቢሲ በላኩት መልዕክት የታካሚዎችን ፍሰት ለማስተናገድ በቂ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች እንደሌላቸው ገልፀዋል።

    አርብ ዕለት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን “ትልቅ ችግር” ውስጥ እንደገባች እና “ተኩስ መተኮስ እንዳትጀምሩ ምክንያቱም እኛም መተኮስ ስለምንጀምር” በማለት አስጠንቅቀዋል።

    ኢራን ለመንግሥታቱ ድርጅት ባስገባችው ደብዳቤ አሜሪካ ተቃዋሚዎችን ወደ “ኃይለኛ የአመፅ ድርጊት እና ሰፊ ውድመት” በመምራት ወቅሳለች።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓለም አቀፍ መሪዎች በሰለማዊ መንገድ ተቃውሞን የማሰማት መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።

    በኢራን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ በበርካታ ከተሞች የተካሄደ ሲሆን፤ ቢያንስ 50 ተቃዋሚዎች እና 15 የጸጥታ አካላት መገደላቸውን ሁለት የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አስታውቀዋል።

    ድርጅቶቹ በተጨማሪ እስካሁን ድረስ 2,311 የተቃውሞ ሠልፈኞች መታሰራቸውን ዘግበዋል።

    ቢቢሲ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኸን ኢራን ውስጥ መዘገብ የተከለከሉ ሲሆን፤ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ አገሪቱ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ የኢንርኔት ግንኙነትን ዘግታለች። ይህም መረጃ ማግኘትን እና ማረጋገጥን ፈታኝ አድርጎታል።

    በሳተላይት የኢንተርኔት ግንኙነት ከቢቢሲ ጋር የተገናኙ አንድ ሐኪም የቴህራን ዋና የዓይን ልዩ ማዕከል ድንገተኛ አደጋዎች መጨናነቁን ተናግረዋል።

    አስቸኳይ ያልሆኑ እና የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶች የተሰረዙ ሲሆን ባለሙያዎች ድንገተኛ አደጋ ላይ እንዲሰሩ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።

    ቢቢሊ ከሌላ የጤና ባለሙያ ተንቀሳቃሽ ምስል እና የድምፅ መልዕክት የደረሰው ሲሆን፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው ቁስለኞች ወደ ሆስፒታል እየመጡ እና ሆስፒታሉ ለማከም በቂ ባለሙያዎች እንደሌሉት ገልፀዋል።

    የጤና ባለሙያው አብዛኞቹ ታካሚዎች ግንባራቸውን እና ዓይናቸውን በጥይት የተመቱ ናቸው ብለዋል።

  4. በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ያስተናግዳል የተባለው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባት ተጀመረ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን አስጀመሩ።

    ቅዳሜ ጥር 2 2018 ዓ.ም. ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በሆን የመሠረተ ድንጋይ ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "የተለያዩ አውሮፕላን ማረፊያዎችን የመገንባት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የወደፊቷ የአፍሪካ ግንባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት በር የማድረግ ዓላማን ያነገበ " መሆኑን ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ የግንባታውን መጀመር በማስመልከት ባሰፈሩት ጽሑፍ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

    ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዋ ቢሾፍቱ የሚገነባው ይህ አውሮፕላን ማረፊያ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ሲጠናቀቅ በዓመት 60 ሚሊዮን ተጓዦችን የሚያስተናግድ እንደሚሆን ተገልጿል።

    ግንባታው ሲጠናቀቅም አፍሪካን ከዓለም ቀዳሚ የአየር ትራንስፖርት መናኸሪያዎች አንዷ ያደርጋታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ላይ እንደሚደርስ ገልጸዋል።

    የአውሮፕላን ማረፊያው መሰረተ ድንጋይ ሲጣል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፣ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዝዳንት አደም ፋራህ እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።

    በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ የሚገኘው ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ መንገደኞችን በዓመት የማስተናገድ አቅም አለው።

  5. የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር 'ታሪካዊ ይሆናል' የተባለው የሶማሊያ ጉብኝታቸውን ወደሌላ ጊዜ አስተላለፉ

    የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታሪካዊ ይሆናል ተብሎ የተጠበቀውን የሶማሊያ ጉብኝታቸውን አስተላልፈው ወደ ታንዛኒያ አመሩ።

    ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሞቃዲሹ ጉብኝታቸውን ለሌላ ጊዜ ስላለስተላለፉበት ምክንያት የተባለ ነገር የለም።

    የአውሮፓውያኑ 2026 የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በአፍሪካ ያደረጉት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፤ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

    ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቀጣይ መዳረሻቸው ሞቃዲሾ ይሆናል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም በይፋ ባልተገለፀ ምክንያት ለሌላ ጊዜ አስተላልፈውታል።

    የዋንግ ጉብኝት ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ከመግለፅ ውጪ መቼ እንደሚሆንም በይፋ የተባለ ነገር የለም።

    የዋንግ ዪ ጉብኝት እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና በሰጠችበት ወቅት የሚደረግ በመሆኑ ለሞቃዲሹ በዲፕሎማሲው ረገድ ትልቅ አቅም ይፈጥርላታል ተብሎ ተገምቶ ነበር።

    ዋንግ በአዲsእ አበባ በነበራቸው ቆይታ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በጋራ በመሆን እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ዕውቅና ተችተዋል መግለቻ አውጥተዋል።

    ዋንግ በአፍሪካ ጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ባሻገር ታንዛኒያ እና ሌሴቶ ይጓዛሉ።

    የቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ሞቃዲሾን ለመጨረሻ ጊዜ የጎበኘው በ1980ዎቹ ነው።

    የሶማሊያ መንግሥት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ለመቀበል የተለያዩ መንገዶችን በመዝጋት ዝግጅት አድርጎ የነበረ ቢሆንም ጉብኝቱ ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ከተገለጸ ወዲህ ያለው ነገር የለም።

  6. ትራምፕ በናይጄሪያ ክርስቲያኖች መገደላቸውን ከቀጠለ ተጨማሪ ጥቃቶች እንደሚፈጽሙ አስጠነቀቁ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ ክርስቲያኖች መገደላቸው ከቀጠለ ተጨማሪ የአየር ድብደባ ሊያዝዙ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

    ትራምፕ ከኒውዮርክ ታይምስ ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ ምልልስ ላይ በናይጄሪያ ሰሜናዊ ሶኮቶ ግዛት የገና በዓል ዕለት እስላማዊ ታጣቂዎችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች የሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ አካል ናቸው ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

    "አንድ ጊዜ ድብደባ ማድረግ እፈልጋለሁ። ነገር ግን ክርስቲያኖችን መግደላቸውን ከቀጠሉ ብዙ ጊዜ ድብደባ የሚፈጸም ይሆናል" ብለዋል።

    ቀደም ሲል የናይጄሪያ መንግሥት ትራምፕ ክርስቲያኖችን ከጂሃዲስት ጥቃቶች መጠበቅ አልቻለም በማለት የሰነዘሩትን ክስ ውድቅ አድርጓል።

    አክሎም “ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖችም ሆኑ እምነት የሌላቸው” በጥቃቱ ዒላማ ናቸው ብሏል።

    ባለፈው ዓመት በአንዳንድ የቀኝ ክንፍ አሜሪካውያን ዘንድ በናይጄሪያ ክርስቲያኖች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን የሚገልጹ ክሶች መሰማት ጀምረዋል።

    ነገር ግን በናይጄሪያ የፖለቲካ ግጭትን የሚከታተሉ ድርጅቶች እንደሚሉት አብዛኛዎቹ የጂሃዲስት ቡድኖች ሰለባዎች ሙስሊሞች ናቸው።

    ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በወጣው ቃለ ምልልሳቸው ላይ ስለዚህ ጉዳይ ሲጠየቁ "ሙስሊሞችም በናይጄሪያ እየተገደሉ ነው ብዬ አስባለሁ። ግን በአብዛኛው ክርስቲያኖች ናቸው" ሲሉ መልሰዋል።

    የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ተጨማሪ የአየር ድብደባዎች ሊኖሩ ይችላሉ ስለተባለው በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ግን "በጋራ መከባበር፣ በዓለም አቀፍ ሕግ እና በናይጄሪያ ሉዓላዊነት ላይ በመመስረት ገንቢ በሆነ መልኩ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ከአጋሮቻችን ጋር መስራታችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

    "ናይጄሪያ ሁሉንም ዜጎቿን፣ ክርስቲያኖችንም ሆነ ሙስሊሞችን ያለ አድልዎ ለመጠበቅ ቁርጠኛ ሆና ትቀጥላለች" ሲሉ አልካሲም አብዱልቃድር ተናግረዋል።

    ከ230 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የናይጄሪያ ሕዝብ በደቡብ በሚገኙ ክርስቲያኖች እና በአብዛኛው በሰሜን በሚገኙ ሙስሊሞች መካከል በእኩል መጠን የተከፈለ ነው።

  7. የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢራን ሕዝብ ድምፅ መሰማት አለበት አሉ

    የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔ የኢራን መንግሥት ተቃዋሚ ሠልፈኞች ላይ የሚፈጽመውን ግድያ አወገዙ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢራን ባለሥልጣናት በዘፈቀደ የሚፈጽሙትን እስር፣ እንዲሁም የሚወስዱትን የኃይል እርምጃ እና ሕዝባቸው ላይ ፍርሃት ለመንዛት የሚጠቀሟቸውን ስልቶች ኮንነዋል።

    “ከኢራን ሕዝብ ጎን አንቆማለን፤ ነጻነት እና ክብር በሚተይቁበት ወቅት ድምጻቸው መሰማት አለበት” ብለዋል።

    ቀደም ሲል ብሪታኒያ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ በጋራ ባወጡት መግለጫ የኢራን የፀጥታ አካላት በተቃዋሚ ሠልፈኞች ላይ ስለሚፈጽሙት ጥቃት ያላቸውን ስጋት ገልጸው ነበር።

  8. ታይዋን ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያወጣችውን የጋራ መግለጫ ተቃወመች

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ያወጡትን የጋራ መገለጫ ታይዋን ተቃወመች።

    በሶማሊላንድ የሚገኘው የታይዋን ተወካይ ጽህፈት ቤት ኢትዮጵያ "ታይዋን የማትነጠልየቻይና አካል" እንደሆነች እና ለ"አንድ ቻይና" መርኅ ያላትንድጋፍ አረጋግጣለች መባሉ ሐሰተኛ የይገባኛል ሀሳብ የተካተተበት ነው በማለት ተቃውሞ አሰምቷል።

    ጨምሮም “የኢትዮጵያ መንግሥት የተዛባውን በቻይናን ኮሚኒስት ፓርቲ የተቀናበረ ፕሮፓጋንዳን በመቀበል ማስተጋባቱ” በእጅጉ እንዳሳዘነው በመጥቀስ፤ ታይዋን በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሥር ተዳድራ አንደማታውቅ ገልጿል።

    በተባበሩት መንግሥታት እና በሥሩ ባሉ ድርጅቶች ውስጥ ጭምር ታይዋን በቻይና እንደማትወከል በማስታወስ፤ “የትኛውም አገር የታይዋንን ኅልውና የመካድ መብትም ሆነ ሥልጣን የለውም” በማለት ኢትዮጵያ ያንጸባረቀቸውን አቋም ተቃውሟል።

    አክሎም የኢትዮጵያ መንግሥት “በጭፍን ቻይናን መከተል እንዲሁም ቻይና ቀጣናዊ ሰላምን እና መረጋጋትን ለመጉዳት ሆን ብላ የምታሠራጨውን ሃሳብ እና ድርጊትን መቀበልን እንዲያቆም” ጥሪ አቅርቧል።

    ቻይና የታይዋን ደሴትን አንደ አመጸኛ ተገንጣይ የግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥራት ሲሆን፣ ከቀሪው ግዛቷ ጋር መዋሃዷ አይቀሬ መሆነን ታምናለች። ለዚህም ‘የአንድ ቻይና’ መርኅን በመከተል በኃይል ጭምር የማዋሃድ ፍላጎት አላት።

    የራሷ አስተዳደር ያላት ታይዋን ሕገ መንግሥት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎች እና ጦር ሠራዊት አላት። ምንም እንኳን በይፋ ነጻ አገርነቷን ባታውጅም እራሷን እንደ ሉዓላዊ አገር ነው ምትቆጥረው።

    ቻይና የትኛውም የዓለም አገር ለታይዋን የአገርነት ዕውቅናን እንዲሰጥ የማትፈቅድ ሲሆን፣ ከአገራት ጋር በሚኖራት ግንኙነት “የአንድ ቻይና’ መርኅን እንዲቀበሉ ትፈልለጋች።

  9. በአሜሪካ ከተሞች የሚካሄደው ተቃውሞ ቀጥሏል

    የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎች በአንዲት ሴት ላይ የፈጸሙትን ግድያ በመቃወም በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ለሁለተኛ ቀን ተቃውሞ ቀጥለዋል።

    የ37 ዓመቷ ሬኒ ኒኮል ጉድ መኪናዋ ውስጥ ሳለች በጥይት መገዷለን ተከትሎ ከሐሙስ ጀምሮ በሚኒያፖሊስ፣ በሂዩስተን፣ በሲንሲናቲ፣ በዋሽንግተን፣ በፊላደዴልፊያ እና በሌሎችም ከተሞች ዛሬ አርብ ተቃዋሚዎች አደባባይ ወጥተዋል።

    አንዳንዶች የስደተኞች እና ጉምሩክ ተቆጣጣሪው ተቋም እንዲፈርስ የሚጠይቁ ጽሁፎችን ይዘው የታዩ ሲሆን፣ ሌሎች ግድያው በተፈጸመበት ቦታ ላይ አበባ እና ሻማ በመለኮስ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ሲያካሂዱ ታይተዋል።

    የአሁኑ ግድያ የተፈጸመው ከአምስት ዓመት በፊት ፖሊሶች ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊን በጭካኔ ከገደሉበት ስፍ ራአቅራቢያ ነው። በወቅቱ በመላው አሜሪካ ለሳምንታት የዘለቀ የዓለምን ትኩረት የሳበ ከባድ ተቃውሞ መካሄዱ አይዘነጋም።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ኦሪገን ግዛት ፖርትላንድ ውስጥ ሁለት ሰዎች በፌደራል የድበንር ጥበቃ አባላት በጥይት ተመትተው ቆስለዋል።

  10. በኢራን ተቃውሞው ተባብሶ ሲቀጥል፤ ትራምፕ በድጋሚ ዛቱ

    በኢራን የሚካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ሁለት ሳምንትን ባስቆጠረበት በአሁኑ ወቅት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት እንደሚፈጽሙ በድጋሚ ተናገሩ።

    በምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ምክንያት በመንግሥታቸው ላይ ተቃውሞ እያሰሙ ያሉት ኢራናውያን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በምሽት ሳይቀር አደባባይ እየወጡ ነው።

    በተቃውሞው ወቅት የፀጥታ ኃይሎች በሚወስዱት እርምጃ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ ወደ 40 መድረሱን መብት ተቆርቋሪ ቡድኖች እየተናገሩ ነው።

    ትራምፕ ይህ የመንግሥት እርምጃ የሚቀጥል ከሆነ ጣልቃ እንደሚገቡ ባለፈው ሳምንት አሳውቀው የነበረ ሲሆን፣ አሁንም የኢራን ባለሥልጣናት ተቃዋሚዎችን የሚገድሉ ከሆነ "ክፉኛ እንደሚመቱ" ዝተዋል።

    "በተቃውሞዎች ወቅት እንሚያደርጉት ሁሉ ሰዎችን መግደል የሚጀምሩ ከሆነ፣ ክፉኛ እንደምንመታቸው መንገር አለብኝ" ሲሉ በአንድ የአሜሪካ ሬዲዮ ዝግጅት ላይ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም አስተዳደራቸው በኢራን ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን እና "አሁን ከምናገረው በላይ አጽንኦት መስጠት የምፈልገው. . . ተቃዋሚዎችን የሚገድሉ ከሆነ እጅግ የከፋ ቅጣት ይከተላቸዋል" በማለት የአገሪቱን ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል።

  11. "ከአረብ አገራት እና ከቱርክ ጋር ሆነን እስራኤልን እናስወጣለን" የሶማሊያው ፕሬዝዳንት

    የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አገራቸው ከአረብ መንግሥታት እና ከቱርክ ጋር በመሆን እስራኤልን ከአፍሪካ ቀንድ እንደምታስወጣ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው እስራኤል በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ "ወታደራዊ መስፋፋት" እያደረገች ነው ሲሉ ከስሰዋል።

    እስራኤል ሶማሊያ የግዛቷ አካል አድርጋ ለምትቆጥራት ሶማሊላንድ ዕውቅና ከሰጠች በኋላ ይህንን ውሳኔዋን ለመቀልበስ መንግሥታቸው አጋር ከሚላቸው አገራት ጋር በመተባበር እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም ተናግረዋል።

    እስራኤልን በፍልስጤማውያን ላይ ፈጽማዋለች ባሏቸው በተለያዩ ጉዳዮች የከሰሱት ፕሬዝዳንቱ "ሶማሊያ አትወረርም፣ አትከፋፈልም" በማለት ከአረብ አገራት እና የቅርብ ወዳጇ ከሆነችው ቱርክ ጋር በመሆን "ከአፍሪካ ቀንድ" እንደሚያስወጧት ገልጸዋል።

    እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን በመስጠት የመጀመሪያዋ አገር መሆኗን ተከትሎ ሶማሊያ፣ ሌሎች አገራት እና ተቋማት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

    ነገር ግን እስራኤል ዕውንናን የምትሰጠው ወይም ግንኙነት የምታደርገው በራሷ ውሳኔ ብቻ መሆኑን በመግለጽ በዕውቅናዋ እንደምትጸና አሳውቃለች።

    ከቀናት በፊትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ ሶማሊላንድ በመላክ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው የተጀመረው ግንኙነት እንደሚጠናከር አሳውቃለች።

  12. ሩሲያ ብዙም በማትጠቀምበት የኦሬሽኒክ ሚሳኤል ዩክሬን ላይ ጥቃት ፈጸመች

    ሩሲያ ኦሬሽኒክ ባላስቲክ ሚሳኤልን በመጠቀም በዩክሬን ላይ ጥቃት መሰንዘሯ ተነገረ።

    ሐሙስ ምሽት በኪየቭ በተፈጸመው ጥቃት አራት ሰዎች ሲገደሉ 25 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ጥቃቱን ተከትሎ ለሰዓታት ከፍተኛ ድምፅ ይሰማ የነበረ ሲሆን ሰማዩን በፍንዳታ ብርሃን ተጥለቅልቋል።

    ሞስኮ ከዩክሬን ገaር ባላት ጦርነት ኦሬሽኒክን የተጠቀመችው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመችው እአአ ታህሳስ 2024 ማዕከላዊ ዲኒፕሮን ለመምታት ነበር።

    የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱ በታህሳስ ወር መጨረሻ በቭላድሚር ፑቲን መኖሪያ ቤት ላይ ለደረሰው የዩክሬን ድሮን ጥቃት ምላሽ እንደሆነ ገልጿል። ኪየቭ ጥቃቱን አልፈጸምኩም ስትል አስተባብላለች።

    ሚኒስቴሩ የኦሬሽኒክ ጥቃት ዒላማ ምን እንደሆነ ባይገልጽም፣ ከእኩለ ሌሊት በፊት የወጡ የማኅበራዊ ሚዲያ ቪዲዮዎች በምዕራባዊቷ የላይቪቭ ከተማ ዳርቻ ላይ በርካታ ፍንዳታዎች እንደነበሩ አሳይተዋል።

    የዩክሬን ባለሥልጣናት የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ከፖላንድ ድንበር 60 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው በላይቪቭ መሠረተ ልማት ላይ እንደተፈጸመ አረጋግጠዋል።

    ኦሬሽኒክ መካከለኛ ርቀት ያለው፣ ሃይፐርሶኒክ የባለስቲክ ሚሳኤል ሲሆን እስከ 5,500 ኪ.ሜ ሊወነጨፍ ይችላል። ሚሳኤሉ ወደ ዒላማው ሲቃረብ ወደ በርካታ ክፍሎች የሚበታተን ሲሆን የታለመለትን ዒላማ የሚያጠቁ አረሮች እንዳሉት ይገመታል። በዚህም ሚሳኤሉ ልዩ የሆኑ ተደጋጋሚ ፍንዳታዎችን በደቂቃዎች ልዩነት ያስከትላል።

    "እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ከአውሮፓ ኅብረት እና ከኔቶ ድንበር አቅራቢያ መፈጸሙ ለአውሮፓ አህጉር ደህንነት ከባድ ስጋት እና ለትራንስአትላንቲክ ማኅበረሰብ ፈተና ነው" ሲሉ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ ተናግረዋል።

    ጥቃቱ የተሰነዘረው "የፑቲንን ቅዠቶች ለመመለስ" ነው ሲሉ በታህሳስ ወር የፕሬዚዳንቱ ቤትን ዒላማ አድርጓል ስለተባለው የሽብር ጥቃት ጠቅሰዋል።

    የአውሮፓ ኅብረት ጥቃቱ ተፈጽሟል መባሉ ላይ ጥርጣሬ እንዳለው ወዲያውኑ አሳውቋል። ባለፈው ሳምንት ዶናልድ ትራምፕ እንዲህ ዓይነት ጥቃት ተፈጽሟል ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል።

    ላይቪቭ ጨምሮ ሌሎች የምዕራባዊ ክልሎች ሐሙስ ምሽት ዒላማ ተደርገዋል። በኪየቭ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከአስራ ሁለት በላይ ሚሳኤሎች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖች ጥቅም ላይ ውለዋል።

  13. ናይጄሪያ በሕገወጥ መንገድ ያጣቸው 9.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲመለስላት ተደረገ

    በጀርሲ የባንክ ሂሳብ ውስጥ የተያዘ ከ9.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ “ሕገወጥ ገንዘብ” ለናይጄሪያ መንግሥት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክትን ለመደገፍ መመለሱ ታወቀ።

    በጀርሲ የግርማዊነታቸው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ማርክ ቴምፕል ኬሲ በታህሳስ ወር ገንዘቡን ለመመለስ የመግባቢያ ስምምነት ፈርመዋል።

    ስምምነቱ መሠረት ያደረገው ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለናይጄሪያ መመለስን የሚያካትቱ ሁለት ቀደም ሲል በተደረጉ ስምምነቶች ላይ ነው።

    ጥር 2024 ላይ የሮያል ፍርድ ቤት ገንዘቡ የሦስተኛ ወገን ኮንትራክተሮች የመንግሥትን ገንዘብ "ለከፍተኛ የናይጄሪያ ባለሥልጣናት እና ለተባባሪዎቻቸው ጥቅም" ያዛወሩበት የሙስና ዕቅድ አካል የመሆን "የበለጠ ዕድል" እንዳለው አረጋግጧል።

    የናይጄሪያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና የፍትህ ሚኒስትር ላቲፍ ፋግቤሚ የተመለሱት ንብረቶች "ከስምምነቱ ውሎች ጋር በሚስማማ መልኩ" ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ተናግረዋል።

    "የተዘረፉ ንብረቶችን በተሳካ ሁኔታ መልሶ ማግኘት እና ወደ አገር መመለስ መቻሉ ናይጄሪያ ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር በመተባበር በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ሀብት ወይም ወደ ውጭ አገር የሚዛወሩ ንብረቶች እንዳይኖሩ ለማረጋገጥ የምታደርገውን የትብብር ጥረት ውጤታማነት ያሳያል" ሲሉ አክለዋል።

    ገንዘቡ በናይጄሪያ ዋና ከተማ እና በሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ መካከል "ወሳኝ አገናኝ" ሆኖ የሚያገለግል የመንገድ ፕሮጀከትን ለማጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

    ቴምፕል በበኩሉ የገንዘቡ መመለስ "የፍትህ ሕጋችን ጥንካሬ በሙስና ትግል ውስጥ ጠንካራ መሳሪያ መሆኑን” አሳይቷል።

  14. አሜሪካ በኮሎምቢያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ትወስዳለች የሚል 'ተጨባጭ ስጋት' እንዳላቸው ፕሬዝዳንቷ ለቢቢሲ ተናገሩ

    የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ በአገራቸው ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወስደ የሚያመለክት "ተጨባጭ ስጋት" አለ ብlው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ተናገሩ።

    ፔትሮ ይህንን ያሉት ትራምፕ ኮሎምቢያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ከዛቱ በኋላ ሲሆን፣ዩናይትድ ስቴትስ ሌሎች አገራትን እንደ አሜሪካ "ግዛት" አካል አድርጋ ትመለከታለች ብለዋል።

    ፕሬዚዳንቱ አሜሪካ "ዓለም ላይ ተፅዕኖ ከመፍጠር ከዓለም ወደ የመነጠል" አደጋ እያመራች ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር በወንጀል እና በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የገቡ ስደተኞችን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ዘመቻ የሚያስፈጽሙትን የአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ (አይስ) መኮንኖችን እንደ "የናዚ ብርጌዶች" እየሠሩ ነው ሲሉ ከስሰዋል።

    ቢቢሲ በፕሬዚዳንቱ ንግግር ዙሪያ ዋይት ሐውስን አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቬንዙዌላ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት እና የኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር መዋል ተከትሎ ኮሎምቢያን ዒላማ ያደረገ ወታደራዊ ዘመቻ "ጥሩ ይመስላል" ማለታቸው ይታወቃል።

    ትራምፕ በተደጋጋሚ ፕሬዝዳንት ፔትሮ "እንዲጠነቀቅ" ቢናገሩም፣ ፕሬዚዳንቱ ግን ይህንን ዛቻ አዘል አስተያየት አጥብቀው አውግዘዋል።

    ትራምፕ እና ፔትሮ ረቡዕ ምሽት በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ትራምፕ የኮሎምቢያ አቻቸውን በዋይት ሐውስ "በቅርብ ጊዜ ውስጥ" እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

    ትራምፕ ከስልክ ውይይቱ በኋላ ረቡዕ ዕለት በ"ትሩዝ ሶሻል" ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ከፔትሮ ጋር ያደረጉትን ውይይት "ታላቅ ክብር" ሲሉ አሞካሽተውታል። በወቅቱ አንድ የኮሎምቢያ ባለሥልጣን ውይይቱ "ከሁለቱም ወገኖች ዘንድ" የ180 ዲግሪ ለውጥ የታየበት ነው ብለው ነበር።

    ነገር ግን ሐሙስ ዕለት የፔትሮ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የነበራቸው የንግግር ቃና ግንኙነቱ ምንም ያህል እንዳልተሻሻለ ጠቁሟል።

    ፕሬዝዳንት ፔድሮ ከትራምፕ ጋር የነበራቸው የስልክ ውይይት አንድ ሰዓት ያህል እንደፈጀ ለቢቢሲ ተናግረው "አብዛኛውን ጊዜ የወሰደው እኔን የሚመለከት ጉዳይ ነው" ብለዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ "በኮሎምቢያ ስላለ የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር" እና አገሪቱ ስለቬንዙዌላ እና "በላቲን አሜሪካ ዩናይትድ ስቴትስን በሚመለከት ምን እየተካሄደ እንደሆነ" አተኩረው መነጋገራቸውን አብራርተዋል።

  15. ኢትዮጵያ ትሳተፍበታለች የተባለው የብሪክስ አገራት የባሕር ኃይል ልምምድ ዛሬ ይጀመራል

    ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት የብሪክስ አገራት ባሕር ኃይሎች በቻይና መሪነት በደቡብ አፍሪካ የሚያደርጉትን የባሕር ኃይል ወታደራዊ ልምምድ ዛሬ ይጀምራሉ።

    ይህ 'ዊል ፎር ፒስ 2026' በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት የሰላም ፍላጎትን ለማሳየት በሚል የተሰየመው ወታደራዊ ልምምድ የብሪክስ አባል አገራት ባሕር ኃይሎች የሚሳተፉበት ነው።

    በኬፕ ታውን በሚካሄደው የባሕር ኃይል ልምምድ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የብሪክስ አባል አገራት እንደሚሳተፉ እየተነገረ ነው።

    የአስተናጋጇ ደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይል እንዳስታወቀው በቻይና መሪነት የሚደረገው ይህ ወታደራዊ ልምምድ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኢንዶኔዢያ ተሳታፊ ይሆናሉ።

    የባሕር ላይ ልምምዱ ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሳበ ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካ ከአሜሪካ ተቀናቃኝ አገራት ጋር ግንኙነቷን እያጠናከረች መሆኑ ከዋሽንግተን ጋር ያላትን መሻከር የበለጠ ሊያበላሸው ይችላል ተብሏል።

    ለልምምዱ የቻይና እና የኢራን የጦር መርከቦች ወደ ደቡብ አፍሪካ የባሕር ኃይል የጦር ሠፈር የደረሱ ሲሆን፣ የሩሲያ የጦር መርከቦችም እንደሚኖሩ ተነግሯል።

    የባሕር ኃይሎቹ ልምምድ የባሕር ላይ ደኅንነት ላይ ያተኮረ ነው ስትል ደቡብ አፍሪካ አስታውቃለች።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል።

  16. በአሜሪካ ፖርትላንድ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ ሁለት ሰዎች ቆስሉ

    በፖርትላንድ ኦሪገን የአሜሪካ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ተኩስ ከፍተው ሁለት ሰዎች ቆስለዋል ሲሉ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

    የከተማዋ የፖሊስ መምሪያ በሰጠው መግለጫ አንድ ወንድና አንድ ሴት ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ እና ሁኔታቸው እንደማይታወቅ አስታውቋል።

    የአገር ውስጥ ደህንነት መምሪያ (ዲኤችኤስ) ክስተቱ አንድ የቬንዙዌላ ወሮበላ ቡድን አባል በመኪናው የጸጥታ ኃይሎችን “ለመግጨት ሲሞከር” መፈጠሩን ተናግሯል።

    በሚኒያፖሊስ አንድ የፌዴራል የጸጥታ ኃይል አንዲት ሴትን መግደሉን ተከትሎ በአሜሪካ ከተሞች ውስጥ የፌዴራል የሕግ አስከባሪ ተግባራትን በመቃወም ተቃውሞ መከሰቱን ተከትሎ ያጋጠመ ክስተት መሆኑ ታውቋል።

    "የመኪናው ተሳፋሪ እና ዒላማው የተደረገው ግለሰብ ዴ አራጓ ከተሰኘው ቡድን ጋር ግንኙነት ያለው እና በቅርቡ በፖርትላንድ በተፈፀመ የተኩስ ልውውጥ የተሳተፈ ሕገወጥ የቬንዙዌላ ዜጋ ነው" ሲል ዲኤችኤስ በኤክስ ላይ በለጠፈው መግለጫ አስታውቋል።

    “የሕግ አስከባሪዎች ለተሽከርካሪው ተሳፋሪ ማንነታቸውን ሲገልጹ፣ አሽከርካሪው ተሽከርካሪውን እንደጦር መሳሪያ በመጠቀም የሕግ አስከባሪ ወኪሎቹን ለመግደል ሞክሯል።”

    “አንድ የጸጥታ ኃይል ለህይወቱ እና ለደህንነቱ በመስጋት ጥይት ተኩሷል። አሽከርካሪው ከተሳፋሪው ጋር መኪናውን በመጠቀም ከቦታው ሸሽተው ሄደዋል።

    የፖርትላንድ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ፖሊሶቻቸው በጉዳዩ ውስጥ እንዳልተሳተፉ እና የተኩስ ሪፖርቶችን ከተቀበሉ በኋላ መሰማራታቸውን ገልጿል።

    በጥይት የተመቱት ሁለት ሰዎች ማንነት አልታወቀም። ፖሊስም ከተኩሱ ቦታ ርቀው መገኘታቸውን አስታውቋል።

    "ፖሊሶች ወደ ሆስፒታል ከመወሰዳቸው በፊት የአደጋ ጊዜ የሕክምና ባለሙያዎችን ጠርቷል” ሲል መግለጫው አክሎ “ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም" ሲል ገልጿል።

    የአሜሪካ ሚዲያዎች የፖሊስ ምንጮችን ጠቅሰው እንደዘገቡት ከሆነ በጥይት የተመቱት የተጋቡ ጥንዶች ናቸው።

    የፖርትላንድ ዲስትሪክት አቃቤ ሕግ ናታን ቫስኬዝ በተኩሱ ስፈራ የተገኙት "ለመከታተል፣ ለመርዳት እና ጥልቅ እና የተሟላ ምርመራ መኖሩን ለማረጋገጥ ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    "ማስረጃዎች ሙሉ በሙሉ የተጠበቁ መሆኑን እና ስለተከሰተው ነገር ሁሉንም እውነታዎች ማግኘት እንደምንችል አረጋግጣለው” ሲሉ ቃል ገብተዋል።

    ይህ አስተያየት የተሰጠው በሚኒሶታ የሚገኙ ባለሥልጣናት ኤፍቢአይ የአካባቢውን መርማሪዎች እንደማያካትት ካሳወቁ በኋላ ነው። ረቡዕ ዕለት ሬኔ ኒኮል ጉድ ፖሊሶችን ለመግጨት ሞክራለች በሚል በጥይት መገደሏ ይታወቃል።

    “ስለጉዳዩ ለማወቅ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ነን" ሲሉ የፖርትላንድ ፖሊስ አዛዥ ቦብ ዴይ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።

    "በሚኒያፖሊስ በተፈፀመው ተኩስ ምክንያት ብዙዎች የሚሰማቸውን ከፍተኛ ስሜት እና ውጥረት እንረዳለን፣ ነገር ግን የበለጠ ለማወቅ እስክሠራ ማኅበረሰቡ እንዲረጋጋ እጠይቃለሁ።"

    በሃዘልዉድ የተከሰተውን አጋጣሚ የተመለከተው ምርመራ በኤፍቢአይ በበላይነት እየተመራ መሆኑን ተናግረዋል።

    የፖርትላንድ ከንቲባ ኪት ዊልሰን በበኩላቸው የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ አስከባሪ አባላት (አይስ) ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ በከተማው ውስጥ ያላቸውን ሁሉንም ሥራዎች እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

    አክለውም "አስተዳደሩ እኛን ለመከፋፈል፣ ማህበረሰቦችን እርስ በእርስ ለማጋጨት እየሞከረ ነው። ፖርትላንድ፣ ይህ እርስ በርስ ለመተሳሰር የሚያስችለን ጊዜ ነው” ብልዋል።

    ፖርትላንድ ቀደም ሲል ትላልቅ የፀረ-ትራምፕ ተቃውሞዎች የተካሄዱበት ቦታ ነበረች።

    ረቡዕ ምሽት የፖርትላንድ ፖሊስ አንድ ተቃዋሚ በቢላዋ ሌላ ግለሰብን ሲያስፈራራ ካገኙት በኋላ በቁጥጥር ስር አውለውታል።

    ዴሞክራቱ ሴናተር ሉው ፍሬድሪክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የአካባቢው ባለስልጣናት ሐሙስ በተፈጸመው የተኩስ ምርመራ ውስጥ የማይሳተፉ ከሆነ "ማህበረሰቡ ውጤቶች ገለልተኛ አይደሉም በማለት ማመን አይችልም" ብለዋል።

    "ለብዙ ሳምንታት ውጥረቱ እየጨመረ መምጣቱን እና በመንገድ ላይ ውጥረት የነገሰባቸው ሁኔታዎች ግልጽ ሆነዋል" ሲሉ በትራምፕ አስተዳደር ላይ በከተማው ውስጥ እየተካሄዱ ያሉትን ተቃውሞዎች በመጥቀስ ተናግረዋል።

    "የሚያሳዝን ሁኔታ፣ የተከሰተው አሳዛኝ ሁኔታ ቀድሞም የሚታይ ይመስለኛል" ብለዋል።

  17. የቬንዜዌላ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን መልቀቅ ጀመረ

    የቬንዙዌላ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ቡድኖች የፖለቲካ እስረኞች ናቸው የተባሉ ሰዎችን መፍታት ጀመረ።

    የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምስት ዜጎቻቸው እንዲሁም አንድ ጥምር ዜግነት ያለውን ግለሰብን ጨምሮ ከእስር መለቀቃቸውን አስታውቋል።

    ከእነዚህም መካከል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ሮሲዮ ሳን ሚጌል እንደሚገኙበት ይገመታል።

    ይህ እርምጃ የተወሰደው አሜሪካ ቅዳሜ ዕለት በዋና ከተማዋ ካራካስ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን እና ባለቤታቸውን በቁጥጥር ሥር ካዋለች በኋላ ነው።

    ኒኮላስ ማዱሮ ወደ አሜሪካ ተወስደው በኒውዮርክ የአደንዛዥ ዕፅ እና የጦር መሳሪያ ዝውውር ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

    አሜሪካ በቬንዙዌላ በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ነበር።

    የቬንዙዌላ ብሔራዊ ምክር ቤት ኃላፊ እና የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ወንድም የሆኑት ጆርጅ ሮድሪጌዝ በመንግሥት ቴሌቪዥን ቀርበው "ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው" እስረኞች እንደሚፈቱ የተናገሩ ቢሆንም፤ ምን ያህል እና እነማን እንደሆኑ ሳይገልጹ ቀርተዋል።

    በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች በቬንዙዌላ እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ፤ እስካሁን የተፈቱት ጥቂቶች ብቻ ናቸው።

    ጆርጅ ሮድሪጌዝ ጊዜያዊው መንግሥት የፖለቲካ እስረኞቹን "ለብሔራዊ አንድነት እና በሰላም አብሮ ለመኖር" በሚል እንደሚለቅቃቸው አስታውቀዋል።

    በደኅንነት፣ በመከላከያ እና በቬንዙዌላ ወታደራዊ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት ሳን ሚጌል መፈታታቸው የተረጋገጠ የመጀመሪያው እስረኛ ናቸው።

    ግለሰቧ በአውሮፓውያኑ የካቲት 2024 በካራካስ አቅራቢያ በሚገኘው በማይኬቲያ አየር ማረፊያ ተይዘው መታሰራቸው ይታወሰል።

    ማዱሮን በመተቸት የሚታወቁት ሳን ሚጌል ፕሬዚዳንቱን ለመግደል በተቀናበረ ሴራ ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል እና በአገር ክህደት፣ በማሴር እና በሽብርተኝነት ክስ ተመሥርቶባቸው ነበር።

    አንዳንድ አባላቶቹ እና መሥራቾቹ በእስር ላይ የሚገኙት የቬንዙዌላ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በእስረኞቹ መፈታት ዜና የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

  18. ለ12ኛ ቀን በኢራን በቀጠለው የተቃውሞ ሠልፍ የኢንተርኔት አገልገሎት ተቋረጠ

    ሐሙስ ምሽት በተለያዩ የኢራን ከተሞች የተቃውሞ ሠልፎች መካሄዳቸውን ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ኔትብሎክስ ገለፀ።

    በተለያዩ ከተሞች የሚካሄዱ የተቃውሞ ሠልፎችንተከትሎ ከቱርክ ኢስታንቡል ወደ ቴህራን የሚደረጉ በረራዎች ተሰርዘዋል።

    መንገደኞች አውሮፕላናቸው በቴህራን የአውሮፕላን ማረፊያ እንዲያርፍ አንዳልተፈቀደለት ገልፀዋል።

    ወደ ታብሪዝ እና ኢስፋሃን ከተሞችም የሚደረጉ በረራዎች በተመሳሳይ መሰረዛቸው ተሰምቷል።

    በኢራን የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ተከትሎ የተቀሰቀሰውየተቃውሞ ሠልፍ 12ኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን የኢንተርኔት አገልገሎት ፍጥነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ መደረጉ ተሰምቷል።

    ተቃዋሚ ሠልፈኞች በአንዳንድ ከተሞች የፖሊስ መኪና እንዲሁም የመንግሥት ተቋማትን በእሳት መለኮሳቸውን የሚያሳዩ ምስሎች በስፋት ተሰራጭተዋል።

  19. የየመኑ ተገንጣይ ቡድን መሪ 'በሶማሊያ በኩል ወደ አቡዳቢ ሸሽቷል' መባሉን ተከትሎ ሞቃዲሾ ምርመራ ጀመረች

    የሶማሊያ የኢሚግሬሽን ኤጀንሲ የደቡብ የመን ሽግግር ምክር ቤት መሪ አይዳረስ አል ዙባይዲ የአየር ክልሏን ያለፈቃድ ተጠቅሟል መባሉን ተከትሎ ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ።

    የኢሚግሬሽንና የዜግነት ኤጀንሲ (አይሲኤ) ሐሙስ ታሕሳስ 30 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ የአየር ክልልና የአውሮፕላን ማረፊያዎች የአገሪቱን ሕግ ወይም ፈቃድ በመጣስ የ"ተፈላጊ ፖለቲከኛ"ን ጉዞን ለማመቻቸት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ ከሌሎች አገራት ባለሥልጣናት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የተገንጣይ ቡድኑ መሪ በጀልባ ወደ በርበራ ካመራ በኋላ በሞቃዲሹ በኩል ወደ አቡዳቢ መሄዱን ዘግቧል።

    የዜና ወኪሉ በየመን በሳዑዲ አረቢያ የሚመራውን ጥምረት ጠቅሶ እንደዘገበው የደቡብ የመን የሽግግር ምክር ቤት መሪ አይዳረስ አል ዙባይዲ ወደ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በሶማሊላንድ በኩል አድርጎ አምልጧል።

    የአማፂ ቡድኑ መሪ ያመለጠው በሪያድ የሰላም ንግግር ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እያለ ሲሆን ሳዑዲ አረቢያ ዩኤኢ ከአገር እንዲወጣ ረድታዋለች በማለት ወቅሳለች።

    የሶማሊያ መንግሥት ግን አይዳረስ አል ዙባይዲ በጀልባ ወደ ሶማሊላንድ ስለማምራቱ የጠቀሰው ነገር የለም።

    የሶማሊያ የኢሚግሬሽን ኤጀንሲ ዙባይዲ በሞቃዲሾ የአየር ክልል በኩል መውጣቱ ከተረጋገጠ፣ እርምጃዎቹ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የኢሚግሬሽን ሕጎች ላይ ከባድ ጥሰት መፈፀማቸውን እንደሚያመለክቱ ተናግሯል።

    ተፈላጊ ሰዎችን ማዘዋወር ወይም ያለ ፈቃድ በግዛቱ ላይ የሚደረጉ ማናቸውም የተናጠል እንቅስቃሴዎችን ማመቻቸት “ተቀባይነት የሌለው” መሆኑን አፅንዖት ሰጥቷል።

    ሐሙስ ዕለት ሳዑዲ አረቢያ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስን የየመን ተገንጣይ ቡድን መሪ የሆነው እና በአገር ክህደት ወንጀል የሚፈለግ ግለሰብን ከአገር ወጥቶ ወደ አቡዳቢ እንዲሸሽ በማድረግ ወንጅላታለች።

    የሳዑዲ መከላከያ የደቡብ የመን የሽግግር ምክር ቤት መሪ አይዳረስ አል ዙባዲ ከየመን በጀልባ ወደ ሶማሊያ መሸሹን ተናግሮ ነበር።

    ሞቃዲሾ ሳዑዲ አረቢያ በየመን ያለውን ሁኔታ ለመፍታት በሪያድ ለመወያየት ያቀረበችውን ጥሪ “ተገቢ የፖለቲካ ሂደት” እንደሆነ በመግለጽ እንደምትደግፍ አስታውቃለች።

    ኤጀንሲው አል ዙባይዲ “ይህንን ሂደት ለማምለጥ፣ የውጭ ድጋፍ በማግኘት ጭምር፣ የሚያደርገው ማንኛውም ጥረት ቀጣይነት ያለውን የዲፕሎማሲ ጥረት በቀጥታ የሚቃረን ይሆናል” ሲል አክሏል።

    ጥሰት መፈጸሙ ከተረጋገጠ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን እና የዓለም አቀፍ ሕግን መጣስን እንደሚያመለክት ኤጀንሲው ጨምሮ አስጠንቅቋል።

    ኤጀንሲው “በምርመራው ግኝቶች ላይ በመመስረት ጥሰቶች መኖራቸው ከተረጋገጠ ሙሉ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ተገቢ እርምጃዎች ይወሰዳሉ” ብሏል።

  20. በዩክሬን የሩሲያን ጥቃት ተከትሎ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ከማሞቂያ እና ውሃ አቅርቦት ውጭ ሆኑ

    የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ በዲኒፕሮፔትሮቭስክ ክልል ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ከማሞቂያ እና የውሃ አቅርቦት ውጪ መሆናቸውን ተናገሩ።

    ኦሌክሲ ይኩሌባ አክለውም በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል መሠረተ ልማቶችን ያወደመውን ሰፊ ​​ጥቃት ተከትሎ አገልግሎቱን ወደነበረበት ለመመለስ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    በአጎራባች ዛፖሪዝሂያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጪ ሆነዋል፤ ነገር ግን አሁን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደነበረበት ተመልሷል።

    ሩሲያ በቅርቡ በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ የሚሰነዘሩትን ጥቃቶች አጠናክራ ቀጥላለች።

    ይህም በከባድ ክረምት ወቅት የኃይል አቅርቦቱን ለማዳከም ያለመ ነው። ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጥቃቱን "ማላገጥ" ሲሉ ጠርተውት የምዕራባውያንን ድጋፍ ጠይቀዋል።

    በድኒፕሮፔትሮቭስክ የሚገኙ ሆስፒታሎች፣ የውሃ ተቋማት እና ሌሎች ወሳኝ አገልግሎቶች በመጠባበቂያ ስርዓቶች እየሰሩ መሆናቸውን የኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀማቸው ላይ ተጨማሪ ጫና እንዳይፈጠር ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።