ትራምፕ ከኖቤል አሸናፊዋ ይልቅ የማዱሮ ምክትል የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ለምን መረጡ?

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ አሜሪካ የወሰደችውን እርምጃ ያህል የአሜሪካ ባለሥልጣናት "ጊዜያው አስተዳደር" እያሉ የሚጠሩትን የቬንዙዌላ መንግሥትን እየመሩ ያሉት ሴት ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኗል።

ትራምፕ በከባድ ወንጀሎች እንዲከሰሱ ከሥልጣናቸው አፈናቅለው ወደ የወሰዷቸውን የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት በመተካት ሥልጣን የያዙትን ዴልሲ ሮድሪጌዝ መሪነት የተቀበሉት ይመስላሉ። ለምን?

የቀድሞው የማርክሲስት ሸማቂ ልጅ የሆኑት እና የአብዮተኛው ኒኮላስ ማዱሮ ምክትል የነበሩት ዴልሲ ሮድሪጌዝ፤ በነዳጅ ሀብት የታደለችውን የደቡብ አሜሪካዋን አገር እንዲመሩ በትራምፕ አስተዳደር ዐይን ውስጥ እንዴት ሊገቡ ቻሉ?

ዋሽንግተን የ2024ቱን ምርጫ አሸንፈዋል ተብሎ ከሚታመኑት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዋ ማሪያ ኮሬና ማቻዶ ይልቅ የሁጎ ቻቬዝ ቀንደኛ አቢዮተኛ የሆኑትን ሴት የመረጠችው ለምን ይሆን?

እንደ የቀድሞ በቬንዙዌላ የአሜሪካ አምባሳደር ከሆነ የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ቀላል ነው።

በፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ዘመን ከአውሮፓውያኑ 2002 እስከ 2004 በቬንዙዌላ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ቻርለስ ሸፒሮ ትራምፕ በአሁኑ ጊዜ በቬንዙዌላ "ከዲሞክራሲ ይልቅ ማረጋጋትን መርጠዋል" ይላሉ።

"ከአምባገነኑ መሪ ማዱሮ ውጭ አምባገነኑ አገዛዝ በቦታው እንዲቆይ አድርገዋል። የሥርዓቱ ቀኝ እጆቹ በሙሉ አሁንም በቦታቸው ናቸው።"

"እንደማስበው ከሆነ ይህ አደገኛ አደጋ ነው" ይላሉ።

ይሁን እንጂ አጠቃላል የአገዛዝ ለውጥ ማድረግ እና የማቻዶን ተቃዋሚ እንቅስቃሴ መደገፍ ከተቃዋሚዎች ጋር ግጭትን እና ቬንዙዌላዊያንን ማግለልን ጨምሮ አደጋ የደቀነ ውሳኔ ነው።

ባለፈው ቅዳሜ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋን ማቻዶን በቬንዙዌላ ውስጥ "የማይከበሩ" ሲሉ አጣጥለው፤ የማዱሮን ምክትል ሮድሪጌዝን ደግሞ "ቸር" ሲሉ መጥራታቸው አብኞቹን ታዛቢዎች አስደንግጧል።

በካራከስ የአሜሪካ ኤምባሲ የቀድሞ ምክትል የተልዕኮ አዛዥ ኬቨን ዊታካር "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማሪያ ኮሬና ማቻዶ ብቁ አለመሆናቸውን ሲናገሩ ስሰማ በጣም ነው የደነገጥኩት" ይላሉ።

ማዱሮ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ሮድሪጌዝ ወዲያው እንዲመሩ መደረጉ ታዛቢዎች የቀድሞዋ ምክትል ፕሬዝዳንት ዕቅዱ ሲጠነሰስ እንደሚያውቁ ያሳያል የሚል ግምታን እንዲያስቀምጡ አድርጓል።

የአሜሪካ ስለላ ተቋም ሲአይኤ የቀድሞ ባልደረባ የሆኑት ሌንሲ ሞራን "ማዱሮን ይዘን ምክትል ፕሬዝዳንቷ ምንም አለመሆናቸው ብዙ ይነግረናል ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።

"ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያሉ ምንጮች እንደነበሩ ግልጽ ነው። ወዲያው የነበረኝ ግምታ እነዚህ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ምንጮች ራሷ ምክትል ፕሬዝዳንቷ ባትሆን እንኳ በቢሮዋ ውስጥ የነበሩት እንደሆኑ ነው።"

ካራከስ የሚኖሩት የዓለም አቀፉ የቀውስ ተከታታይ ቡድን (አይሲጂ) ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ፊል ገንሰን የሴራ ትንተናው የማዱሮ ታማኝ አጋር የሆኑት የቬንዙዌላ መከላከያ ሚኒስትር ጄነራል ቭላድሚር ፓድሪኖ ሎፔዝ እና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኦዳዶ ካቤሎ ያላቸውን ግዙፍ ሥልጣን የዘነጋ ነው ይላሉ።

"ራሷን ለጥቃት አጋልጣ ማድሮን ለምን አሳልፋ ትሰጣለች? ለዚያውም የጠመንጃውን ቃታ የሚቆታጠሩ ሰዎች እያሉ?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

ይልቁንም ሮድሪጌዝን መሪ ለማድረግ የተደረሰው ውሳኔ ማቻዶን መሾም ለአገሪቱ አደገኛ አለመራጋጋት ያስከትላል በሚል ማስጠንቀቂያ የታጀበ ነው።

ባለፈው ጥቅም ቡድኑ "ዋሽንግተን የአገዛዝ ለውጥ ማድረጓን ታጢነው" ብሏል።

"ከድኅረ ማዱሮ መውደቅ በኋላ ሊከሰት የሚችለው ሁኔታ አነስተኛ ተደርጎ የሚታይ አይደለም" ሲል የሚያሳስበው ሪፖርቱ፤ የፀጥታ ኃይሉ ክፍል በአዲሱ አስተዳደር ላይ የሽምቅ ውጊያ ሊጀምር እንደሚችል ጠቁሟል።

ዎል ስትሪት ጆርናል ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ የደረሰ እና ሮድሪጌዝን ጨምሮ ጊዜያዊ መንግሥቱን የማዱሮ አስተዳደር አባላት ቢመሩት የተሻለ እንደሚሆን የሚያሳይ ምሥጢራዊ የደኅንነት ሰነድ መኖሩን ዘግቧል።

በሪፖርቱ ዙሪያ ዋይት ሐውስ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም በቀጣይ ከሮድሪጌዝ ጋር ለመሥራት ያለውን ዕቅድ ግን በግልጽ ተናግሯል።

በዋሽንግተን የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል ተባባሪ የሆኑት ሄነሪ ዚመር ፈተናው አሁን እንደሚጀምር ይናገራሉ።

"ማዱሮን መያዙ ቀላሉ ክፍል ነው። በሰፊው ቬንዙዌላን መገንባት፣ ነዳጁ፣ አደገኛ ዕፁ እና የዲሞክራሲ ግቦች. . . ፍሬ ለማፍራት ረጅም ጊዜ ይወስዳል" ይላሉ።

ለአሁኑ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ከሮድሪጌዝ ጋር ለመሥራት የሚችል ይመስላል።

ገንሰን "[ሮድሪጌዝ] የኢኮኖሚ በሩን መክፈት አስፈላጊ መሆኑን ታውቃለች እና የውጭ መዋዕለ ነዋይን ወደ አገር ውስጥ መመለስን የምትቃወም አይደለችም" ይላሉ።

ሄነሪ ዚመርም ፕሬዝዳናቷ የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎችን በመቀበል፣ የፀረ አደገኛ ዕፅ ትብብርን በማሳደግ እና ቀስ በቀስ የአሜሪካ ማዕቀብ እንዲነሳላት ከቻይና፣ ከኩባ እና ከሩሲያ ጋር ቬንዙዌላ ያላትን ግንኙነት በመቀነስ የዋሽንግተንን ምኞት ለመፈጸም የሚቸግራቸው ላይሆኑ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።

"ይህን ይፈፅማሉ ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።

"ይሁን እንጂ አሜሪካ ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር እውነተኛ እርምጃ ከጠየቀች ነገሮች ከባድ ይሆናሉ።"

አሁን ላይ በዋሽንግተን ቅድሚያ ከሚሰጣቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች መካከል ያለ አይመስልም።

ረቡዕ እለት መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለቬንዙዌላ አገሪቱን ማረጋጋት እና በአሜሪካ ክትትል ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን በርሚል ነዳጅ በመሸጥ የሚጀምር ሦስት ደረጃዎች ያሉት ዕቅድ መንደፋቸውን አሳውቀዋል።

ዕቅዱ ለተቃዋሚዎች ምህረት መስጠት፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ምኅዳርን መገንባትን ጨምሮ ሩቢዮ "የእርቅ ሂደት" ብለው ወደገለጹት መንገድ የሚወስድ ነው ተብሏል።

"ሦስተኛው ምዕራፍ ሽግግር ነው የሚሆነው" ሲሉ ሳያብራሩ ተናግረዋል።

የቬንዙዌላ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 233 ፕሬዝዳንቱ "ለማገልገል በቋሚነት በቦታቸው የማይኖሩ" ከሆነ በ30 ቀናት ውስጥ ምርጫ መደረግ አለበት ይላል።

ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሰኞ እለት ከኤንቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ምርጫ እንደማይደረግ እና "አገሪቱን መጀመሪያ ማስተካከል አለብን" ሲሉ ጠቁመዋል።

ገንሰን ዋሽንግተን የአገዛዝ ለውጥ ላለማድረግ ያሳለፈችው ውሳኔ ለአጭር ጊዜ ትርጉም ቢኖረውም፤ የመካከለኛ ወይም የረጅም ጊዜ ዕቅድ አለመኖር ግን አሳዛኝ እንደሚሆን ተናግረዋል።

"ትራምፕ ሊያተርፉበት ይችላሉ፤ ነገር ግን ቬንዙዌላዊያን አያተርፉም" በማለት "እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ተራ ተርታ ቬንዙዌላዊያን ይቸገራሉ" ብለዋል።