ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናሳ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመራማሪው ባጋጠመው "ከባድ የጤና እክል" ተልዕኮውን አቋረጠ
ናሳ በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ (አይኤስኤስ) የሚገኙትን አራት የጠፈር ተመራማሪዎች ወደ አገራቸው እንደሚመልስ አስታወቀ።
ናሳ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከጠፈርተኞቹ አንዱ ላይ በደረሰ "ከባድ የጤና እክል" ምክንያት መሆኑን ገልጿል።
የናሳ የጠፈር ተልዕኮ ሊጠናቀቅ የአንድ ወር ዕድሜ ቀርቶት የነበረ ቢሆንም፤ በተመራማሪው የጤና ሁኔታ የተነሳ ተልዕኮው ቀደም ብሎ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል።
ኤጀንሲው የታመመውን የቡድኑን አባል ስም የግለሰቡን ግላዊ መብት መጋፋት ይሆናል በሚል ከመጥቀስ የተቆጠበ ሲሆን ያለበት የጤና ሁኔታ ግን የተረጋጋ መሆኑን ተናግሯል።
የናሳ ባለሥልጣን "ይህ የአደጋ ጊዜ ማስወጣት አይደለም" ሲሉ ተናግረው "ሁልጊዜ የጠፈር ተመራማሪውን ጤና እናስቀድማለን" ብለዋል።
ናሳ ሐሙስ ዕለት ሁለት የጠፈር ተመራማሪዎች ከጠፈር ምርምር ጣቢያው በመውጣት ጉዞ ለማድረግ ተዘጋጅተው በነበረበት ወቅት "የሕክምና ስጋት" በመጥቀስ በድንገት ተልዕኮውን ሰርዟል።
ሐሙስ ዕለት የቡድኑን አባላት ቀደም ብለው እንዲመለሱ መወሰኑ የተገለጸው የናሳ አስተዳዳሪ ጃሬድ አይዛክማን እና ሌሎች የኤጀንሲው ባለሥልጣናት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።
ስለጉዳዩ ጥቂት ማብራሪያ ብቻ የሰጡት ኃላፊዎቹ የሕክምናው ጉዳይ ከጠፈር ሥራዎች ጋር የተያያዘ እና ባጋጠመ ጉዳት እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የጠፈር ተጓዦቹ በ48 ሰዓታት ውስጥ የደረሱበት እንደሚገለጽ ይጠበቃል ሲሉ አክለዋል።
ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ ተመራማሪዎችን ሲያስተናግድ በነበረው በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ታሪክ አንድ ተልዕኮ ከተያዘለት ጊዜ ቀድም ብሎ ሲያጠናቀቅ ይህ የመጀመሪያው ነው።
አራት ሰዎችን የያዘው ቡድኑ ክሩ-11 ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ የናሳ ጠፈርተኞችን ዚና ካርድማን እና ማይክ ፊንኬን፣ የጃፓን የጠፈር ኤጀንሲ ተመራማሪን ኪሚያ ዩኢን እና የሩሲያ የጠፈር ተመራማሪ ኦሌግ ፕላቶኖቭን ያካተተ ነው።
አንድ አሜሪካዊ የጠፈር ተመራማሪ በአይኤስኤስ ጣቢያ እንደሚቆይ እና ሁለት የሩሲያ የጠፈር ተመራማሪዎች እንደሚቀላቀሉትም ባለሥልጣናቱ ጨምረው ተናግረዋል።
የናሳ የጤና እና የሕክምና ዋና ኃላፊ ዶ/ር ጄምስ ፖልክ ለጋዜጠኞች ይህ በናሳ የ65 ዓመት ታሪክ ውስጥ በሕክምና ችግር ምክንያት ተመራማሪዎቹ ቀደም ብለው የሚመለሱበት የመጀመሪያ ተልዕኮ ነው።
ክሩ-11 ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በስፔስኤክስ ክሩ ድራጎን ወደ ዓለም አቀፉ የጠረፍ ጣቢያ የተደረገ ጉዞ ሲሆን ለስድስት ወራት ያህል በምህዋር ላይ እንደሚቆዩ ተጠብቆ ነበር።
ከጥቂት ቀናት በፊት በሌሎች አራት ሰዎች ከተተኩ በኋላ በሚቀጥለው ወር አካባቢ ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
አይኤስኤስ መሠረታዊ የሕክምና መሣሪያዎች፣ ቁሳቁሶች እና የመገናኛ ሥርዓቶች ያሉት ሲሆን፣ ይህም በምድር ላይ ያሉ ዶክተሮች በጠፈር ውስጥ ካሉ ተመራማሪዎች ጋር በግል እንዲነጋገሩ፣ ሁኔታቸውን እንዲገመግሙ እና የሕክምና ምክር እንዲሰጡ ያስችላቸዋል።
አራት ሰዎችን የያዘው ቡድን ቀደም ብሎ መመለሱ አዲሶቹ ሠራተኞች በሚቀጥለው ወር እስኪመጡ ድረስ አንዳንድ ሙከራዎችን እና የጥገና ሥራዎችን ሊያዘገይ እንደሚችል በኦፕን ዩኒቨርሲቲ የጠፈር ሳይንቲስት የሆኑት ዶክተር ሲሞን ባርበር ተናግረዋል።
"የጠፈር ጣቢያው ትልቅ እና ውስብስብ የምህንድስና ሥራ ነው፤ በተወሰነ ዝቅተኛ ቁጥር ባላቸው ሠራተኞች እንዲንቀሳቀስ የተነደፈ ነው" ብለዋል።
የቀሩት ሠራተኞች "በተወሰኑት የሙከራ ሥራዎች ላይ ተመልሰው እንዲሠሩ እና ሙሉ የሠራተኞቹን ድጋፍ እስኪያገኙ ድረስ በጥገና እና ጣቢያውን ጤናማ ለማድረግ የበለጠ ትኩረት እንዲያደርጉ" እንደሚገደዱ አክለዋል።