ሕዋ፡ ቀጣዩ የኃያላን ወታደራዊ ፉክክር መድረክ እና አሜሪካ እየገነባችው ያለው የጠፈር ኃይል

በዴንቨር፣ ኮሎራዶ ከተማ ዳርቻ ላይ ከሚገኘው ተቋም ውስጥ ከኮምፒውተራቸው ፊት ለፊት ተቀምጠው ከየትኛውም የዓለም ክፍል የሚተኮስ ሚሳዔልን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይታያሉ።

መከታተል ብቻ ሳይሆን ሚሳዔሉ ከተወነጨፈበት ቦታ ጀምሮ ዒላማውን እስኪመታ ድረስ በመከታተል መረጃዎችን ይሰበስባሉ።

ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱት እነዚህ ሰዎች በአሜሪካ የጠፈር ኃይል ውስጥ ወታደር ሳይሆን ጠባቂዎች ተብለው ነው የሚጠሩት።

ቢቢሲ በበክሌይ የጠፈር ኃይል ጣቢያ በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የጠፈር ኃይል የሚሳዔል ማስጠንቀቂያ እና ክትትል ኦፕሬሽን ክፍል ውስጥ እንዲገቡ ከተፈቀደላቸው የመጀመሪያዎቹ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች መካከል ነው።

በዚህ ጣቢያ ያሉት ጠባቂዎች ሳምንቱን በሙሉ 24 ሰዓት በንቃት የሚሠሩ ሲሆን፣ ይህም የተቋሙ የነርቭ ማዕከል ነው።

የጦር ኃይሉ አባላት በሕዋ ውስጥ ካሉ የጦር ሳተላይቶች የተላኩ ካርታዎችን እና መረጃዎችን በሚያቀርቡ ግዙፍ መቆጣጠሪያዎች ተከብበዋል።

እነዚህ ጠባቂዎች ሚሳዔል ሲወነጨፍ የጨረር ሙቀት አሻራን ለመለየት የመጀመሪያዎቹ ናቸው።

ባለፈው ሰኔ ኢራን አሜሪካ እና እስራኤል ለፈፀሙት ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በኳታር አል ኡዴይድ ወደሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ሚሳዔል ስታስወነጭፍ ቀድመው ለይተውታል።

ኮሎኔል አን ሂዩስ በዚያ ቀን የነበረውን ስሜት "ከባድ" ነበር ስትል ትገልጸዋለች።

ከአብዛኞቹ ማስወንጨፍያዎች በተለየ፣ ስለዚያ ጥቃት አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

ስለዚህም እነዚያን የኢራን ሚሳዔሎች መከታተል እና ያንን መረጃ በመሬት ላይ ላሉት የአየር መቃወሚያዎች ማሳወቅ ችለዋል።

"በመጨረሻም መላውን ተቋም እና እዚያ የነበሩትን ሠራተኞች አድነናል" ትላለች እፎይታዋን በሚገልጽ ድምጽ።

ኮሎኔል ሂዩዝ እንደምትለው ከሆነ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአውሮፓ ጦርነቶች በመቀስቀሳቸው ሥራ በዝቶባቸዋል።

ለዩክሬን ማስጠንቀቂያ ይሰጡ እንደሆነ የተጠየቀችው ሂዩዝ "ለሁሉም የአሜሪካ እና አጋር ኃይሎች ስልታዊ እና ወሳኝ የሚሳዔል ማስጠንቀቂያ እንሰጣለን" ብላለች።

አሜሪካ በይፋ ባታረጋግጥም ምናልባት ኪየቭ በሩሲያ ጥቃት ሊፈጸምባት ሲል አስቀድማ መረጃ ሳታደርሳት አትቀርም።

በክሌይ የጠፈር ኃይል ማዘዣ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ሚሳዔል መከላከያ 'ጎልደን ዶም' ተብሎ የሚጠራው ዕቅድ ቁልፍ አካል ነው።

ይህ በእስራኤሉ የአየር መቃወሚያ፣ 'አይረን ዶም' መነሻነት የተጀመረው ግዙፍ ፕሮግራም 175 ቢሊዮን ዶላር ተመድቦለታል። ብዙዎች ግን ከዚህም በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ ያምናሉ።

ለዚህም መሠረት የሚሆኑት ነገሮች በበክሌይ ይገኛሉ። ዙሪያው ከፍተኛ አቅም ያላቸው ግዙፍ የሳተላይት መቀበያ ሳህኖችን ለመከለል በሚያስችሉ የእንቁላል ቅርጽ ባላቸው ጉልላት መሳይ መሸፈኛዎች ተከቧል።

ከርቀት ሲታዩ ግዙፍ የጎልፍ ኳሶች ይመስላሉ። እነዚህ ሳተላይቶች በ11,000 የብርሃን ዓመታት ርቀት ላይ ካለው ሱፐርኖቫ የራዲዮ ፍሪኩዌንሲ ሞገዶችን ይቀበላሉ።

የዩናይትድ ስቴትስ የጠፈር ኦፕሬሽን ኮማንድ አዛዥ ሌተናንት ጄነራል ዴቪድ ሚለር ገና ሥራው ያልተጀመረው ጎልደን ዶም አሜሪካ የተጋፈጠችውን ስጋት መሠረት አድርጎ መታቀዱን ተናግረዋል።

ለዚህም በተለየ ሁኔታ ቻይናን እና ሩሲያን ይጠቅሳሉ።

ሁለቱም ከድምጽ ፍጥነት አምስት እጥፍ በላይ ሊጓዙ የሚችሉ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች ሠርተዋል።

ሁለቱም ለመከታተል አስቸጋሪ የሆኑትን ፍራክሽናል ኦርቢታል ቦምባርድመንት ሲስተምን የተባለውን ሥርዓት ሞክረዋል።

ፍራክሽናት ቦምባርድመንት ሲስተም (FOBS) የኒውክሌር መሳሪያ ወደ ዝቅተኛ የምድር ምህዋር ለማስወንጨፍ የተነደፈ የስትራቴጂክ የጦር መሳሪያ ዓይነት ሲሆን፣ ከየትኛውም አቅጣጫ ወደ ዒላማው መምዘግዘግ ይችላል። ይህም ሚሳዔሉን ለመለየት ወይም ለመከላከል በጣም ከባድ ያደርገዋል።

ጄነራል ሚለር "እነዚያን ሚሳዔሎች ከመጥለፍ ጋር የተገናኙት ፍጥነት እና ፊዚክስ ጠፈር ላይ የሚገኙ ማክሸፊያዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል" ብለዋል።

በሕዋ ላይ ካሉ የጦር መሳሪያዎች ይልቅ የአሜሪካን ጥቅም ለማስጠበቅ ስለ "አቅም" ማውራት ይመርጣሉ።

የዩናይትድ ስቴትስ የጠፈር ኃይል ከአምስት ዓመት በፊት መመሥረቱ ሕዋ አሁን የጦርነት ጎራ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህንን ኃይል ያስጀመሩት በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ሲሆን፣ ሕዋ "በዓለም ላይ አዲስ ጦርነት የሚካሄድበት ስፍራ" ሲሉ ገልጸውት ነበር።

ቻይና እና ሩሲያ ፀረ ሳተላይት ሚሳዔሎችን እንዲሁም ግንኙነታቸውን የሚያጨናግፉበትን መንገዶች ሞክረዋል።

ጄነራል ሚለር እንዳሉት ሩሲያ ሕዋ ላይ "ኒውክሌር ለማስቀመጥ የሚያስችል አቅም አሳይታለች" ብለዋል።

ሕዋ ቀድሞውንም "በጣም የሚያከራክር አካባቢ ነው" ሲሉ አክለው፤ "በሕዋ ላይ ለሚፈጠር ግጭትም መዘጋጀት አለብን" ብለዋል።

ኮሎኔል ፊኒክስ ሃውዘር ዴልታ 7 በመባል የሚታወቀውን የጠፈር ኃይሎች ደኅንነት፣ ክትትል እና መረጃ ክፍል ትመራለች። የዚህ ክፍል ሥራ በሕዋ ላይ ምን እየተከሰተ እንዳለ ማወቅ ነው።

በኮሎራዶ ስፕሪንግ አቅራቢያ ባለው ጣቢያቸው፣ በዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ትናንሽ ነጠብጣቦችን የሚያሳዩ የኮምፒውተር ስክሪኖች ላይ አፍጥጠዋል።

በጠፈር ውስጥ ቀድሞውኑ ወደ 12 ሺህ የሚጠጉ ሳተላይቶች አሉ። ከአስር ዓመት በኋላ ይህ ቁጥር ወደ 60 ሺህ ሊያድግ ይችላል።

ኮሎኔል ሃውዘር ቀዳሚ ትኩረታችን ቻይና ላይ ነው ብላለች።

"ያለውን ስጋት እየተከታተልን ነው።"

ቻይና ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሳተላይቶች አሏት፤ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ግማሾቹ ወታደራዊ ናቸው። በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ፣ ኮሎኔል ሃውዘር በዝቅተኛ የምድር ምኅዋር ውስጥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሳተላይቶች ይኖሯታል ብላለች።

ሕዋ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጨናነቀ እና እያጨቃጨቀ ነው።

"በጠፈር ላይ እየተፎካከርን ነው" ትላለች። "ከጠላቶቻችን ሙያዊ ያልሆኑ እና ደኅንነታቸው ያልተጠበቀ እንቅስቃሴዎች እናያለን።"

ይህም ግንኙነቶችን ለማፈን የሚያስችል መሳሪያ የተገጠመላቸው ሳተላይቶች፣ጨረር አመንጪዎች እና አልፎ ተርፎም መረብ ያላቸው እና ለግጭት የሚያጋልጡ ቅጥያዎች ያሏቸውን ያጠቃልላል።

አንዳንዶች በጠፈር ውስጥ ቀድሞውኑ "የአየር ላይ ውጊያ" እየተካሄዱ እንዳሉ ጠቁመዋል።

ኮሎኔል ሃውዘር "ቶፕ ገን ላይ እንዳለው ከስር ከስር እየተከተልን ውጊያ እያካሄድን መሆኑን አላውቅም" ብላለች። "ግን በእርግጠኝነት ዝግጁ መሆን ያለብን ነገር ነው" ስትል አክላለች።

የአሜሪካ የጠፈር ኃይል በሕዋ ላይ ግጭት ቢፈጠር በሚል እየተዘጋጀ ነው።

ኮሎኔል ሃውዘር ከዓመት በፊት "በሕዋ ላይ ማጥቃት ስለሚያስችለን አቅም ማውራት የምንችልበት ደረጃ ላይ አልነበርንም" ብላለች።

አሁን ትኩረታቸው "ለፕሬዝዳንቱ አማራጮችን በማፍለቅ፣ በማጥቃት እና በመከላከል የሕዋ የበላይነትን ለማግኘት እና ለማስቀጠል ነው" ትላለች።

ጄነራል ሚለር ግጭትን ለመከላከል ብቸኛው መንገድ "ጥንካሬ ነው፤ እናም የእኛ የሆነውን ለመከላከል የራሳችን አቅም ሊኖረን ይገባል" ብለዋል።

ይህ ግን በትክክል ምን ማለት እንደሆነ በዝርዝር አልገለፁም።

ነገር ግን በቅርቡ አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ የፈጸመችው ጥቃት፣ ኦፕሬሽን ሚድ ናይት ሀመር፣ የአሜሪካ የጠፈር ኃይል ምን ማድረግ እንደሚችል ፍንጭ ይሰጣል።

እነዚያ በቢ-2 ቦምቦ ጣይ አውሮፕላኖች የተፈጸሙት ጥቃቶች ለአሜሪካ መከላከያ ኃይል የሕዋ የበላይነትን ማስቀጠል ወሳኝ የሆነው ለምን እንደሆነ ያሳያል ብለዋል።

ጄነራል ሚለር "የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከጠፈር የምናገኘውን የበላይነት ምን ያህል እንደሚጠቀም መረዳት አለብህ።"

ይህም በአድማስ ላይ ያለውን የግንኙነት መረብ ከማሰስ ጀምሮ፣ ጂፒኤስን በመጠቀም ትክክለኛ ቦታን እስከ መምታት የሚያስችል ብቃትን ያካትታል።

ቢቢሲ የዩናይትድ ስቴትስ የጠፈር ኃይል ጠባቂዎች በዘመቻው ውስጥ እንዴት እንደተሳተፉ የሚያሳይ ዝርዝር መረጃ ተሰጥቶታል።

ጄነራል ሚለር "ከሠራናቸው ነገሮች አንዱ የኤሌክትሮማግኔቲክ ጦር መሳሪያ አቅማችንን በመጠቀም በዘመቻው ሁሉ የበላይነታችንን ማረጋገጥ ነው።"

የኤሌክትሮማግኔቲክ ስፔክትረም የሬዲዮ ሞገዶች፣ማይክሮዌቮች፣ኢንፍራ-ሬድ እና የሚታይ ብርሃንን ያካትታል።

"አካባቢው እንደሚጠለፍ እናውቅ ነበር" ይላሉ።

የአሜሪካ የጠፈር ኃይል የአሜሪካ ቢ-2 ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ዒላማቸው ላይ እንዲደርሱ እና በአቅጣጫ ጠቋሚ መሳሪያ (ጂፒኤስ) የሚመሩ ግዙፍ ቦምቦችን በትክክል ዒላማቸው ላይ መጣል እንዲችሉ እና እንዳይከሽፉ ተከላክሏል።

ቀደም ሲል ከአሜሪካ የጠፈር ኃይል ዴልታ 3 የኤሌክትሮኒክ ጦርነት ስፔሻሊስቶች የተወጣጡ አባላት በቀጠናው ውስጥ እየሠሩ ነበር።

አዛዣቸው ኮሎኔል አንጀሎ ፈርናንዴዝ የሳተላይት ዲሽ እና የትዕዛዝ መስጫ ቁሶች በዓለም ላይ ወደ የትኛውም ቦታ መብረር እንደሚችሉ ለቢቢሲ አሳይቷል።

ዲሾቹ የጠላት ኃይሎችን ግንኙነት መጥለፍ ከዚያም "ከፍተኛ ድምጽ በመልቀቅ" ማጨናገፍ የሚችሉ መሆናቸውን ይናገራል።

"ሁለቱም የአሜሪካ ንብረቶችን ለመጠበቅ እና በተመሳሳይ ጊዜ የበረራ መስመሮችን ለመክፈት ይችላሉ" ይላል።

ከተልዕኮው በፊት፣ በተልዕኮው ወቅት እና በኋላ፣ የዴልታ 7 የአሜሪካ የጠፈር ኃይል ጠባቂዎች ክትትል እያደረጉ ነበር።

ኮሎኔል ፊኒክስ ሃውዘር የኤሌክትሮማግኔቲክ ስፔክትረምን በመከታተል "ኢራን ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ታውቃለች? ጥቃቶቹ ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ስልታዊ ማስጠንቀቂያ አላት?" የሚለውን ሲከታተሉ እንደነበር ትናገራለች።

ሳይታሰብ በድንገት ጥቃት መፈፀም እንዲቻል በማድረግ፣ አብራሪዎቹ ሳይነቃባቸው ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ ማድረግ ችለዋል።

የአሜሪካ የጠፈር ኃይል ከተመሠረተ ገና ዕድሜው ለጋ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ለአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል ወሳኝ ነው።

ጄነራል ሚለር የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሠራዊት በሙሉ "በሕዋ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ነው" ብለዋል።

ይህ ጉዳይ መቀጠል አለበት። ለማንኛውም ጠላት ማስጠንቀቂያው ደርሶታል ሲሉም አክለዋል።

"የአሜሪካ ጦር በአንድ ነገር ላይ ሲያተኩር ግቡን ሳያሳካ ዓይኑን አይነቅልም፤ ፈጣሪ ይርዳችሁ!" ብለዋል።