ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ በሶሪያ በሚገኙ የአይኤስ ዒላማዎች ላይ ጥቃት ፈፀመች
የአሜሪካ እና የአጋር አገራት ኃይሎች በሶሪያ በሚገኙ የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ዒላማዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መፈጸማቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አስታወቀ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ የሰጡበት የቅዳሜ ዕለቱ ጥቃት፤ "ኦፕሬሽን ሆውክአይ ስትራይክ" የተባለው ዘመቻ አካል እንደሆነ ተገልጿል።
ማዕከላዊ ዕዙ በኤክስ ገጹ ላይ ያሰፈረው ጽሁፍ እንደሚያስረዳው፤ ጥቃቱ የተፈጸመው አይኤስ በታህሳስ መጀመሪያ በሶሪያ የሚገኙ ሁለት የአሜሪካ ወታደሮችን ለገደለበት ጥቃት አጸፋ ለመስጠት ነው።
የአሁኑ ጥቃቶች የተፈጸሙት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ እና አጋር ኃይሎችን ለመጠበቅ በማሰብ እንደሆነ ማዕከላዊ ዕዙ ገልጿል።
"መልእክታችን አሁንም ጠንካራ ነው። ተዋጊዎቻችንን ከጎዳችሁ፣ ምንም ያህል ፍትህን ለማምለጥ የትም ብትደበቁ እናገኛችዃለን እናም እንገድላችሏለን" ሲል ማዕከላዊ ዕዙ በኤክስ ገጹ ጽፏል።
ከ20 በላይ ተዋጊ አውሮፕላኖች በተሳተፉበት በዚህ ዘመቻ፤ ከ90 በላይ ትክክለኛ ኢላማቸውን የሚመቱ ተተኳሾች (precision munitions) በ35 ዒላማዎች ላይ መተኮሳቸውን አንድ ባለሥልጣን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
በጥቃቱ ላይ F-15Es፣ A-10s፣ AC-130Js፣ MQ-9s እና የዮርዳኖስ F-16 የተባሉት የጦር አውሮፕላኖች መሳተፋቸውንም አክለዋል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ እነዚህን ጥቃቶች የፈጸሙባቸው ትክክለኛ ስፍራዎች እና ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት፤ ቅዳሜ ዕለት ስለ ወታደራዊው እርምጃ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ "መቼም አንረሳም፣ መቼም አንታክትም" ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር "ኦፕሬሽን ሆውክአይ ስትራይክ" የተባለውን ዘመቻ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረገው ባለፈው ታህሳስ ላይ ነበር። ይህ ዘመቻ የተጀመረው የአይኤስ ታጣቂዎች መካከለኛው የሶሪያ ክፍል በምትገኘው ፓልሚራ ከተማ በፈጸሙት ድንገተኛ ጥቃት ሁለት የአሜሪካ ወታደሮች እና አንድ ሲቪል አስተርጓሚ መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሄግሴት የዚህን ዘመቻ መጀመር ይፋ ባደረጉበት ወቅት "ይህ የጦርነት ጅማሮ ሳይሆን የበቀል አዋጅ ነው" ብለው ነበር።
ማዕከላዊ ዕዝ መረጃ እንደሚያሳየው ከቅዳሜው ጥቃት በፊት፤ የአሜሪካ ኃይሎች ታህሳስ 11 እስከ ታህሳስ 20 ባሉት ቀናት በፈጸሟቸው 11 ጥቃቶች 25 የሚጠጉ የአይኤስ አባላትን ገድለዋል ወይም ማርከዋል።
የዘመቻው የመጀመሪያ ተልዕኮ በተፈጸመት ታህሳስ 10/2018 ዓ.ም. በአይኤስ ቡድን ላይ "ከፍተኛ ጥቃት" የተፈጸመው በአሜሪካ እና ዮርዳኖስ ኃይሎች ነው።
የሁለቱ አገራት ኃይሎች የጦር ጄቶችን፣ ጥቃት አድራሽ ሄሊኮፕተሮችን እና መድፎችን በመጠቀም "በመካከለኛው ሶሪያ በሚገኙ ከ70 በላይ የተለያዩ ዒላማዎች" ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ማዕከላዊ ዕዙ ገልጿል።
በመጀመሪያው ኦፕሬሽን ወቅት፤ በሚታወቁ የአይኤስ መሠረተ ልማቶችን እና የጦር መሣሪያ ማከማቻዎች ላይ "ከ100 በላይ ትክክለኛ ኢላማቸውን የሚመቱ ተተኳሾች" ጥቅም ላይ እንደዋሉ ተነግሯል።
ባለፈው ዓመት ታህሳስ ላይ የፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድ አገዛዝ መውደቅን ተከትሎ ለ13 ዓመታት አገሪቱን ያወደመውን የእርስ በርስ ጦርነት ቢቆምም፤ ሶሪያ ደካማ አገር ሆና ቀጥላለች።
አማፂ ቡድኑ በሽር አል አሳድን ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ አህመድ አል-ሻራ ወይም በውጊያ ስሙ አቡ መሐመድ አል ጆላኒ አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት እየመራ ይገኛል።
ሶሪያ ውስጥ የሚገኘው አይኤስ ቢዳከምም አሁንም ድረስ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል። በዋንኛነትም በሰሜን ምስራቅ በሚገኙ በኩርድ የሚመሩ ኃይሎች ላይ ጥቃቶችን ይፈጽማል።