ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢራን መንግሥት በቅርቡ ይወድቅ ይሆን?
ፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት የሚወድቁት እንዴት ነው? ታዋቂው ደራሲ ኧርነስት ሔሚንግዌይ 'መጀመርያ ቀስ ቀበቀስ ይከስራሉ እና ድንገት ትንፋሻቸው ቀጥ ይላል' የሚል ዝነኛ አባባል አለው።
በኢራን የተቃውሞ ሠልፍ የሚያካሄዱ እና ከአገር ውጪ የሚገኙት ደጋፊዎቻቸው በቴህራን የሚገኘው እስላማዊ መንግሥት ድንገት ትንፋሹ ቀጥ እንደሚል ተስፋ ያደርጋሉ።
የኢራን አስተዳደር እየሞተ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች ቢኖሩም ነገር ግን አዝጋሚ ናቸው ይላል የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አርታኢ የሆነው ጀረሚ ቦዌን።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የነበረው አለመረጋጋት ሥርዓቱ ላይ ትልቅ ቀውስ ፈጥሯል።
የኢራናውያን ቁጣና ብስጭት ገንፍሎ ወደ ጎዳናዎች አውጥቷቸዋል።
ይህ የመጣው ባለፉት ሁለት ዓመታት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ካደረሱት ወታደራዊ ጥቃቶች በተጨማሪ ነው።
የአውሮፓ አገራት እና አሜሪካ የጣሏቸው ማዕቀቦች ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ የተቸገሩ ኢራናውያን ላይ የበለጠ ጉልህ የሆነ ተጽዕኖ አስከትለዋል።
በ2015 የኑክሌር ስምምነት ምክንያት የተነሱት የተባበሩት መንግሥታት ማዕቀቦች በሙሉ በመስከረም ወር በእንግሊዝ፣ በጀርመን እና በፈረንሳይ እንደገና ተተክተዋል።
በ2025 የምግብ ዋጋ ግሽበት ከ70 በመቶ በላይ ነበር።
የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ምንዛሬ በታህሳስ ወር ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
የኢራን አገዛዝ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ያለ ቢሆንም፣ ሁኔታዎች ግን ትንፋሹ እየቆመ እንደሆነ አያሳዩም። የጸጥታ ኃይሎች አሁንም ለአገዛዙ ታማኝ ሆነው ቀጥለዋል።
እአአ ከ1979ቱ የእስልምና አብዮት ጀምሮ የኢራን ባለሥልጣናት ጊዜና ገንዘባቸውን በማፍሰስ ሰፊና ከፍተኛ ጫና መፍጠር የሚችል የጭቆና መረብ ዘርግተዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የገዥው አካል የሆኑት የጸጥታ ኃይሎች ዜጎቻቸው ላይ እንዲተኩሱ ታዝዘዋል።
በዚህም ምክንያት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በተካሄዱት ሠልፎች ብቻ ከ2000 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
የተቃውሞውን ጫና በመግታት ግንባር ቀደም የሆነው የኢራን አብዮታዊ ዘብ (አይአርጂሲ) በአገሪቱ ውስጥ በጣም አስፈላጊው ብቸኛ ድርጅት ነው።
በቀጥታ ለበላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ተጠሪ የሆነው ይህ ቡድን የ1979ቱን የእስልምና አብዮት ርዕዮተ ዓለም እና የመንግሥት ስርዓት የመጠበቅ ልዩ ተግባር አለው።
ከኢራን የጦር ኃይል ጋር ትይዩ ሆነው የሚያገለግሉ ወደ 150,000 የሚጠጉ ኃይሎች እንዳሉት ይገመታል።
እንዲሁም በኢራን ኢኮኖሚ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ነው።
የሥልጣን፣ የገንዘብ፣ የሙስና እና የርዕዮተ ዓለም መደበላለቅ ሥርዓቱን ለመከላከል በቂ ምክንያት ይሰጠዋል።
አይአርጂሲ በበጎ ፈቃደኝነት የተመለመሉ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች አባላት የሆኑ የባሲጅ ሚሊሻዎች ድጋፍ አለው።
ይህ የበጎ ፈቃደኞች ቡድን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት እንዳሉት ይናገራል።
አንዳንድ የምዕራባውያን ግምቶች ለሥምሪት በተጠንቀቅ ዝግጁ የሆኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኃይሎች እንዳሉት ይሳያሉ።
ባሲጅ አገዛዙ በተቃዋሚዎች ላይ በሚያደርሰው ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ ተሳትፏል።
እአአ በ2009 በቴህራን አይአርጂሲ እና ባሲጅ አወዛጋቢ የሆነውን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ የተነሱትን ግዙፍ የተቃውሞ ሠልፎች ለማፈን ተንቀሳቅሰዋል።
የባሲጅ በጎ ፈቃደኞች የጎማ እና የእንጨት ዱላቸውን ታጥቀው ጎዳናዎች ላይ ተሰማርተው ነበር።
ከጀርባቸው አውቶማቲክ መሳሪያ የታጠቁ የፀጥታ ኃይሎች ተመድበው ነበር።
በሞተር ሳይክል የሚንቀሰቀቀሱ የፀጥታ አባላት በቴህራን ሰፊ ጎዳናዎች ዙሪያ እየነዱ ተቃውሞ ለማሰማት በሚሞክሩ ቡድኖች ላይ እርምጃ ወስደዋል።
በዚህም የተነሳ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ጎዳናዎቹን አጥለቅልቀው ተቃውሞዎች እያሰሙ እና እሳት እያነደዱ የነበሩ ሠልፈኞች ቁጥራቸው እየተመናመነ ሄደ።
ፀሐይ ስትጠልቅ ተቃዋሚ ሠልፈኖች ልክ ወላጆቻቸው በሻህ አገዛዝ ላይ እነዳደረጉት የቤታቸው በረንዳ ወይንም ጣሪያ ላይ በመውጣት ፈጣሪ ከሁሉ በላይ ነው ብለው ይዘምሩ ነበር።
የአገር ውስጥ የደህንነት ኃይሎች የተቃውሞ ሠልፈኞቹን ዝም ማሰኘት ቻሉ ማለት የበላይ መሪው ወይም የጦር ጄነራሎቻቸው ዘና ማለት ይችላሉ አይደለም።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሁንም እርምጃ ለመውሰድ እያስፈራሩ ነው። የአገዛዙን ውድቀት የሚፈልጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢራናውያን ቂም እና ቁጣ ተሞልተዋል።
በቴህራን መንግሥትና የበላይ መሪው እየገጠማቸው ያለውን ጫና ለማቃለል መንገዶችን እየፈለጉ ይመስላል።
የቤሊኮዝ ይፋዊ ንግግር ከአሜሪካ ጋር ድርድር እንዲጀመር ከቀረበው ሀሳብ ጋር የተቀላቀለ ነው።
ሁለቱ ወገኖች ቀደም ሲል የተደረጉትን ውይይቶች ያላሳኩትን የኢራን የኑክሌር ዕቅዶች እና የባላስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራምን በተመለከተ እንዴት ስምምነት ማድረግ እንደሚችሉ ማየት ከባድ ነው።
ነገር ግን ድርድሩ በተለይም ትራምፕ ስምምነት ማድረግ ባይቻልም እንኳን ንግግር እንዲኖር ከፈቀዱ ለኢራን ጊዜ ሊገዛ ይችላል፤
ትራምፕ ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው አገራት ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተዋል።
ይህ የአሜሪካ እርምጃ እንዴት እንደሚሰራ ለማየት አስቸጋሪ ነው።
ቻይና አብዛኛውን የኢራን ነዳጅ ትገዛለች። ትራምፕ እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ደግሞ የገቡበትን የንግድ ጦርነት ለማስቆም ከስምምነት ላይ የደረሱት በቅርቡ ነው።
በሚያዝያ ወር በቤጂንግ በሚካሄደው የሁለቱ አገራት ጉባዔም እነዚህ የዓለም ልዕለ ኃያላን አገራት የሚጋጫቸውን ጉዳዮች አንስተው ይወያያሉ።
ትራምፕ በኢራን ላይ ጫና ለማሳደር በሚል ብቻ ጉባኤውን አደጋ ላይ ሊጥሉ ወይም ሊያስተጓጉሉ ይፈልጋሉ?
በቴህራን በዕድሜ የገፉት የበላይ መሪ አያቶላህ ካሜኒ ቅድሚያ የሚሰጡት ትልቁ ጉዳይ የእስላማዊ ሪፐብሊክን የአስተዳደር ስርዓት መጠበቅ ነው።
ተጨማሪ የተቃውሞ ሠልፎች ከባድ ምላሽ ሊጠብቃቸው ይችላል።
ለአገዛዙ አንዱ ጥቅም በተቃዋሚዎች መካከል ወጥ የሆነ አመራር የሚሰጥ አካል አለመኖሩ ነው።
ከግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ በፊት በአብዮቱ የተወገደው የሻህ የበኩር ልጅ የተቃውሞ ሠልፉ መሪ ለመሆን ሲሞክሩ ቆይተዋል።
ለተቃዋሚ ሠልፈኞቹ ራሳቸውን ቅርብ ለማድረግ የሞከሩት የቤተሰባቸውን ታሪክ እና ከእስራኤል ጋር ያላቸውን የቅርብ ግንኙነት በማሳየት ብቻ ይመስላል።
በቴህራን ውስጥ ያሉትን የሃይማኖት አባቶችና ወታደራዊ ኃላፊዎች ሊያስጨንቃቸው የሚችል አንድ ትምህርት የመጣው ከቀድሞ አጋራቸው ከሶሪያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ ነው።
ጦርነቱን ያሸነፉ ይመስሉ የነበሩት አላሳድ በሳዑዲ አረቢያ እና በአረብ ሊግ እንዲያገግሙ እየተደገፉ ባለበት ወቅት በሚገባ በተደራጀ ጥቃት እአአ በ2024 ከሥልጣን ተወግደዋል።
ሁለቱ በጣም የቅርብ አጋሮቻቸው ሩሲያም ሆነች ኢራን አላሳድን ለማዳን ፈቃደኛ አልነበሩም ወይም አልቻሉም። በጥቂት ቀናት ውስጥ አሳድ እና ቤተሰቡ ወደ ሞስኮ በመሄድ በጥገኝነት መኖር ጀመሩ።
አምባገነን አገዛዝ ቀስ በቀስ እየበሰበሰ በመሄድ ከዚያም በድንገት ይሞታል።
የአሳድ ሶሪያ ስትወድቅ በጣም በፍጥነት ነበር።
በቴህራን ሊጠና የሚችለው ሌላው ጉዳይ የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት ቤን አሊ በ2011 የገጠማቸው ነው።
የቱኒዚያ ጦር ተቃዋሚዎችን ከአገር ውስጥ የደህንነት ኃይሎች ለመጠበቅ በተንቀሳቀሰበት ወቅት ቤን አሊ ከሥልጣን ተወግደዋል።
የቤን አሊ ውድቀት የግብፁ ሆስኒ ሙባረክን ከሥልጣን እንዲለቁ ምክንያት ሆኗል። በግብጽ የጦር ኃይሉ ራሱን ለማዳን ባይወስን ኖሮ ከከፍተኛ የተቃውሞ ማዕበል መትረፍ ይችሉ ነበር።
ይህ በኢራን ሊከሰት ይችላል? ምናልባት። እስካሁን ያ እየሆነ አይደለም።
የእስልምና አገዛዝ ተቃዋሚዎች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተጨማሪ ጫና እንደሚኖር እና አስተማማኝ አመራር እንደሚመጣ ተስፋ ያደርጋሉ።
በዚህም ምክንያት የሥርዓቱ የመበስበስ ሂደት ተፋጥኖ ከአዝጋሚ ውድቀት ወደ ፈጣን የትንፋሽ መቋረጥ እንዲሄድ ተስፋ ያደርጋሉ።