ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጋዛን የሚያስተዳድር የባለሙያዎች መንግሥት የሚቋቋምበት ሁለተኛው ምዕራፍ የሰላም ስምምነት ትግበራ ተጀመረ
የጋዛ ጦርነትን ለመቋጨት የተፈረመው የሰላም ስምምነት ግዛቱን የሚያስተዳድር በባለሙያዎች የሚመራ (ቴክኖክራት) መንግሥት ወደሚቋቋምበት ሁለተኛ ምዕራፍ መሸጋገሩን የአሜሪካ መልክዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ አስታወቁ።
ባለፈው ጥቅምት ወር በተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት በምዕራፍ አንድ ትግበራው የታጋቾች እና የእስረኞች ልውውጥ ተፈጽሞበታል። በዚህ ምዕራፍ እስራኤል በከፊል ከጋዛ የወጣች ሲሆን፣ ወደ ግዛቱ የሚገባው እርዳታም ጨምሯል።
ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ መልሶ ለመግንባት እና ጋዛን ሙሉ በሙሉ ከወታደራዊ ኃይል ነጻ ለማድረግ የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደሚተገበሩበት ዊትኮፍ ገልጸዋል።
ሰርጡን ከወታደራዊ ኃይል ነጻ የማድረግ እርምጃ ሐማስ እና ሌሎች የፍልስጤም አማጺ ቡድኖችን ትጥቅ ማስፈታትን እንደሚያካትትም ተናግረዋል።
"አሜሪካ ሐማስ ለግዴታዎቹ ሙሉ በሙሉ ተገዢ እንደሚሆን ትጠብቃለች" ያሉት ዊትኮፍ፤ "ይህንን አለመፈጸም ከፍተኛ የሆነ መዘዝ ያስከትላል" ብለዋል።
ሐማስ ፍልስጤን ነጻ አገር ሆና እስካልተመሠረተች እና እስራኤል ሙሉ በሙሉ ከጋዛ ለመውጣት ቃል እስካልገባች ድረስ ትጥቅ እንደማይፈታ ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል።
ዊትኮፍ ረቡዕ ዕለት የሰላም ስምምነቱ ሁለተኛ ምዕራፍ መጀመሩን ረቡዕ ዕለት ይፋ ሲያደርጉ፤ በዚህኛው ምዕራፍ ጋዛ "ከተኩስ አቁም ወደ ከወታደራዊ ኃይል ነጻ መሆን፣ ቴክኖክራቲክ መንግሥት እና መልሶ ግንባታ እንደምትሻገር" አስታውቀዋል።
"ሁለተኛው ምዕራፍ 'የጋዛ አስተዳደር ብሔራዊ ኮሚቴ' የተባለ ጊዜያዊ የባለሙያዎች (ቴክኖክራቲክ) የፍልስጤም አስተዳደር ጋዛ ውስጥ ያቋቁማል። እንዲሁም የጋዛን ሙሉ በሙሉ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የማድረግ እና የመልሶ ግንባታ ሥራ ይጀምራል፤ [ይህ እርምጃ] በዋነኝነት ማንኛውም ያልተፈቀደለት ግለሰብ ትጥቁን እንዲፈታ ማድረግን ያካትታል" ብለዋል።
በሰላም ሂደቱ አሸማጋይ የነበሩ የቀጣናው አገራት ግብፅ፣ ኳታር እና ቱርክ "የጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድር የፍልስጤም ቴክኖክራቲክ ኮሚቴ" መቋቋሙን በበጎ እንደሚቀበሉት ገልጸዋል። ይህ እርምጃ "መረጋጋትን ለማጠናከር እና ሰብአዊ ሁኔታን ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረት" አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም አክለዋል።
አገራቱ በመግለጫቸው 15 አባላት ያሉት ይህ ቴክኖክራቲክ ኮሚቴ የሚመራው፤ በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ የሚገኙ አካባቢዎችን በሚያስተዳድረው የፍልስጤም ባለሥልጣን ውስጥ የቀድሞ የፕላን ምክትል ሚኒስትር በነበሩት በአሊ ሻዐት እንደሚሆን ይፋ አድርገዋል።
ትራምፕ ከሦስት ወራት በፊት ይፋ ያደረጉት ባለ 20 ነጥብ የሰላም ዕቅድ መሠረት፣ ጋዛ ጊዜያዊ አስተዳደር በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሰብሳቢነት በሚመራ "የሰላም ቦርድ" ቁጥጥር የሚደረግበት ይሆናል።
ሁለተኛው ምዕራፍ ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ ሐማስ እና አጋሩ የሆነው የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ቴክኖክራቲክ የፍልስጤም መንግሥት ለመመሥረት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ መስማማታቸውን ገልጸዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን እንዲጀምር "ተስማሚ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩም" አክለዋል።