በስደት ላይ የሚገኙት የመጨረሻው የኢራን ንጉሥ ልጅ የዓለም መንግሥታት የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክን ለመጣል ተቃዋሚዎችን እንዲደግፉ ጥሪ አቀረቡ።
ተቃውሞውን አሜሪካ ተቀምጠው የሚመሩት ሬዛ ፓህላቪ ትራምፕ ቃላቸውን የሚጠብቁ መሪ መሆናቸውን እና ከኢራናውያን ጎን እንደሚቆሙ እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
“እስላማዊው ሪፐብሊክ ይወድቃል፤ ሊወድቅ ይችላል የሚለው ሳይሆን መቼ“ የሚለው ነው ጥያቄው ሲሉ ተናግረዋል።
በአሜሪካ የሚኖሩት የተቃዋሚ መሪ የሆኑት ሬዛ ፓህላቪ፣ ዓለም የኢራንን አብዮታዊ ዘብ አመራርን ዒላማ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ይህም "ዓላማችንን ያመቻቻል እንዲሁም ተጨማሪ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ይከላከላል" ብለዋል።
ከሃያ ቀን በፊት በኢራን የኑሮ ውድነትን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመጽ
እስካሁን ድረስ ከ2,600
በላይ ተቃዋሚዎች በኢራን የፀጥታ አካላት መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አስታውቀዋል።
የኢራን መንግሥት ተቃውሞዎቹን በኢራን ጠላቶች የተደገፉ "ረብሻዎች" ሲል ጠርቷቸዋል።
ፓህላቪ በኢራን የሚካሄደው ተቃውሞ መሪ ሆነው ብቅ ያሉ ሲሆን፣ ኢራናውያን ተቃውሟቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
በኢራን የተቀሰቀሰውን መጠነ ሰፊ ተቃውሞ ተከትሎ የኢንተርኔት እና ሌሎች የመገናኛ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ የተቋረጡ ሲሆን፣ የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎችም ጠንካራ እርምጃ መውሰዳቸውን ቀጥለዋል።
ፓህላቪ አርብ ዕለት በዋሽንግተን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢራን የደኅንነት ክፍል በዘመቻው ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆኑን እና የኢራን ባለሥልጣናት ተቃውሞውን ለማብረድ ከውጭ ሚሊሻዎች ማምጣታቸውን ተናግረዋል።
ዓለም የኢራንን አብዮታዊ ዘብ ኃይሎች ዒላማ እንዲያደርግ እና መሠረተ ልማቶችን እንዲቆጣጠር እንዲሁም እንዲያዝ አሳስበው "ወሳኝ የሆነ ጥቃት" እንዲፈጸም
ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ኃያላን አገራት የኢኮኖሚ ጫና እንዲፈጥሩ፣ የኢራን ዲፕሎማቶችን እንዲያባርሩ፣ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እንዲጠይቁ እና በኢራን ውስጥ ግንኙነት እንዲኖር የሳተላይት ኢንተርኔት፣ ስታርሊንክ እና ሌሎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ ግንኙነቶችን እንዲፈቅዱ ጠይቀዋል።
“የኢራን ሕዝብ ወሳኝ እርምጃ እየወሰደ ነው። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሙሉ በሙሉ እንዲቀላቀል ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።
"በዓለም እርዳታ ወይም ያለ ምንም ድጋፍ ሥርዓቱ ይወድቃል። ዓለም ቃሉን ወደ ተግባር ከቀየረ ፈጥኖ ይወድቃል፤ ብዙ ሕይወትም ይድናል።"
ከከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት አድርገዋል ስለሚሉ ዘገባዎች ለመናገር ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ “ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቃላቸውን
የሚያከብሩ ሰው እንደሆኑ እና በመጨረሻም ከኢራናውያን ሕዝብ ጋር እንደሚቆሙ አምናለሁ” ብለዋል።