የአውሮፓ መሪዎች ትራምፕ ግሪንላንድን በታሪፍ ማስፈራራታቸው ተቀባይነት የለውም አሉ
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በግሪንላንድ ምክንያት ስምንት አጋር ሀገራት ላይ ታሪፍ መጣላቸውን የአውሮፓ መሪዎች ተቃወሙ።
የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር የትራምፕ እርምጃ “ፍፁም ስህተት” ነው ሲሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማኽሮን በበኩላቸው “ተቀባይነት የሌለው” ብለውታል።
ትራምፕ ከዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ዩኬ፣ ኔዘርላንድስ እና ፊንላንድ የሚመጡ ምርቶች ላይ 10 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል።
ታሪፍ ከሚመጣው የአውሮፓውያኑ ወር ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን በግሪንላንድ ጉዳይ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ወደ 25 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ተሰምቷል።
ትራምፕ የዴንማርክ ክፍል የሆነችው ራስ ገዟ ግሪንላንድ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አስፈላጊ ናት ይላሉ። ግሪንላንድ ለመቆጣጠር ኃይል ሊጠቀሙ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት የጣሉትን ታሪፍ ተከትሎ የአውሮፓው ኅብረት እሑድ ከሰዓት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።
በተያያዘ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዴንማርክ እና ግሪንላንድ የአሜሪካን እርምጃ ተቃውመው ለሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ ወጥተዋል።
የሕዝብ ቁጥሯ በቅጡ 60 ሺህ የማይሞላው የዓለማችን ግዙፏ ደሴት በማዕድናት የበለፀገች ስትሆን በሰሜን አሜሪካ እና በአርክቲክ መካከል የምትገኝ ስትራቴጂካዊ ስፍራ ናት።