ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራን ተቃውሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አረጋገጡ
በኢራን ተቃውሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ አረጋገጡ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን በይፋ የተናገሩት ጠቅላይ መሪው "አንዳንዶቹ የተገደሉት ሰብአዊ ባልሆነ፣ ጭካኔ በተሞላው መንገድ ነው" ብለዋል። ለሰዎቹ ሞት አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል።
መቀመጫውne አሜሪካ ያደረገው የኢራን መብት ተሟጋች ተቋም 'ሂውማን ራይትስ አክቲቪስትስ ኒውስ ኤጀንሲ' እንደገለጸው፤ ኢራን በተቃዋሚዎች ላይ በወሰደችው የኃይል እርምጃ የ3,090 ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።
ሌሎች የመብት ተሟጋቾች የሟቾችን ቁጥር ከፍ ያደርጉታል። ኢንተርኔት ከተቋረጠ ቀናት በማለፋቸው ትክክለኛውን ቁጥር ለማጣራት አዳጋች ሆኗል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራናውያን "በተቃውሞ እንዲቀጥሉ" አበረታትዋል። የኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎች የሚገድል ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚከተልም አስጠንቅቀዋል።
የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ቅዳሜ ባደረጉት ንግግር "ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር ትስስር ያላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል፤ ቀውስም ፈጥረዋል" ብለዋል።
"ለሞቶቹ፣ ለውድመቱ እና የኢራን ስም ለመጥፋቱ ተጠያቂው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ነው ብለን እናምናለን" ሲሉም አክለዋል።
ከምጣኔ ሃብታዊ ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተነሳው ተቃውሞ መሪው ከሥልጣን እንዲወርዱ ወደመጠየቅ ተሻግሯል።
የኢራን መንግሥት ተቃውሞው በአገሪቱ ጠላቶች የተቀነባበረ "ሁከት" እንደሆነ ገልጿል።
ቢቢሲ ፐርዥያን እና ቢቢሲ ቬሪፋይ ያረጋጧቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች የፀጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎች ላይ ሲተኩሱ ያሳያሉ።
የኢንተርኔት ትስስር የሚከታተለው ኔትብሎክስ እንዳለው በአገሪቱ ኢንተርኔት እንደተቋረጠ ሲሆን አጠቃላይ የኢንተርኔት ትስስሩ 2% ይሆናል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት የወጡ ዘገባዎች አለመረጋጋቱ እንደቀነሰ ቢጠቁሙም ሙሉ መረጃ ማግኘት አልተቻለም።
በደቡብ ምዕራብ ኢራን፣ ሺራዝ የምትኖር ኢራናዊት ለቢቢሲ "የፀጥታ ኃይሎች በሞተር ሳይክል ሆነው ሁኔታውን ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነው። አብዛኛው ነገር ግን ወደ መደበኛ እየተመለሰ ነው" ብላለች።
የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ በትናንቱ ንግግራቸው አገራቸው ትራምፕን "ወንጀለኛ" አድርጋ እንደምትወስድ እና በኢራን ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ "ተጠያቂ መሆን" እንዳለባቸው ገልጸዋል።
"የአሜሪካ ግብ ኢራንን መዋጥ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንዳለው ኢራን የአሜሪካ ወታደራዊ መቀመጫዎችን ለመምታት እየተዘጋጀች እንደሆነ መረጃ ደርሶታል።
ኢራን "ከትራምፕ ጋር ጨዋታ ከጀመረች" እና ጥቃት ከፈጸመች "በጣም፣ በጣም ጉልበት ካለው ኃይል ጋር ትላተማለች" ሲልም አክሏል።
ትራምፕ "በኢራን ግድያው ቆሟል" ቢሉም ወታደራዊ እርምጃ የመውሰድ አማራጭ አሁንም እንዳለ ገልጸዋል።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በኳታር የአል-ኡዲድ አየር ኃይል መቀመጫ ያላቸውን ሠራዊት ቁጥር ቀንሰዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣኖች ለቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ እንደተናገሩት አሜሪካ ወታደሮቿን የቀነሰችው "ለቅድመ ጥንቃቄ" ነው።