ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ በሶሪያ ለወታደሮቿ ሞት ተጠያቂ የሆነ የአል-ቃይዳ መሪ መግደሏን ገለፀች
አሜሪካ በሶሪያ ባደረሰቸው ጥቃት ለወታደሮቿ ግድያ ተጠያቂ የሆነ የአል-ቃይዳ መሪን መግደሏ ተገለጸ።
ሦስት አሜሪካውያን ወታደሮች በሶሪያ እንዲገደሉ አድርጓል የተባለው የአል-ቃይዳ መሪ ከአይኤስ ጋር "ቀጥተኛ ግንኙነት" እንዳለው ተገልጿል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንዳለው ቢላል ሐሰን አል-ጃሲም የተባለው የአል-ቃይዳ መሪ ባለፈው ሳምንት አርብ በተፈጸመ ጥቃት ተገድሏል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ነው።
በሶሪያ የአሜሪካ ወታደሮችን እና ሶሪያውያንን ከገደለው እና ካቆሰለው የአይኤስ ቡድን ጋር "ቀጥተኛ ግንኙነት" ነበረው ተብሏል።
ቢቢሲ ጉዳዩን በገለልተኛ አካል ማጣራት አልቻለም።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ኮማንደር አድሚራል ብራድ ኩፐር "ለሦስት አሜሪካውያን ግድያ ተጠያቂ የሆነውን አሸባሪ መግደል ኃይላችን ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ምን እንደሚጠብቃቸው ማሳያ ነው" ብለዋል።
"አሜሪካውያን እና ወታደሮቻችን ላይ ጥቃት የሚያቀነባብሩ ወይም የሚፈጽሙ ሰዎች የትም አይደበቁም። እናገኛችኋለን" ሲሉም አክለዋል።
አሜሪካ አይኤስ ላይ በማነጣጠር በሶሪያ ጥቃት እየፈጸመች ነው። 'ኦፕሬሽን አዋክዬ ስትራይክ' የሚል ስም ተሰጥቶታል።
እአአ በ2025 ሦስት አሜሪካውያን ወታደሮች በማዕከላዊ ሶሪያ፣ ፓልማያራ ከተገደሉ በኋላ ነው ኦፕሬሽኑ የተጀመረው።
እስካሁን ድረስ አሜሪካ 200 መሣሪያዎችን በመጠቀም "100 መሠረተ ልማት እና የመሣሪያ ማከማቻ ዒላማዎችን" መምታቷን ወታደራዊ ዕዙ አስታውቋል።
በ11 ወታደራዊ ስምሪቶች አማካኝነት 25 የሚጠጉ የአይአየስ አባላትን መያዙን ባለፈው ወር አስታውቋል።
ከፕሬዝዳንት ባሽር አል-አሳድ ከሥልጣን መወገድ በኋላ አሕመድ አል-ሻራ (ወይም አቡ መሐመድ አል-ጆላኒ) አገሪቱን እየመሩ ነው።
አይኤስ በሶሪያ ቢዳከምም አሁንም እንቅስቃሴው አልተገታም። በተለይም በአገሪቱ ደቡብ ምሥራቅ አካባቢ የሚገኙ የኩርድ ይዞታዎች ጥቃት ይፈጽማል።